>

ዐድዋ፡- የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ብሩሕ ፋና!! (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

ዐድዋ፡- የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ብሩሕ ፋና!!

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


ደቡብ አፍሪካዊው የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ፣ የነጻነት አርበኛና የዓለም ሰላም ኖቤል ተሸላሚው፣ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ- የዐድዋ ድልን ፋይዳና ትሩፉት በተመለከተ፣ በአንድ ወቅት አፍሪካውያን መሪዎች በተገኙበት አንድ ትልቅ የስብሰባ መድረክ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፡-

‘‘The Adowa Victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self-reliance, race pride, spirituality, and freedom from colonialism.’’

ዐድዋ- በሺህ ዘመናት ታሪኳና ቅርስዋ፣ ገናና ሥልጣኔዋና አኩሪ ባህሏ ለምትታወቀው፣ በነጻነቷና በሉዓላዊነቷ ጸንታ የኖረችውን ሀገራችንን ኢትዮጵያን ዳግመኛ በዓለም መድረክ ከፍ ያደረገ ነው። ዐድዋ የአፍሪካውያን፣ የአፍሪካ አሜሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አለኝታ፣ የወኔና ስንቅ የሆነ፤ ሰው የመሆን ከፈጣሪ ዘንድ የተቸረ መለኮታዊ ፍቅርንና ክብርን ያላቀ ነው፡፡

በርግጥም ኔልሰን ማንዴላ በንግግራቸው ለመጥቀስ እንደሞከሩት ዐድዋ- ለኢትዮጵያዊነት ዝርግፍ ጌጥ፣ የተደነቀ ውበት፣ ሰው የመሆን ክብርንና የመንፈስ ልእልናን ያጎናጸፈ፣ ከዘረኝነት እኩይ እሳቤን የናደ፤ የቅኝ ግዛት ቀምበር እንዲሰበር ያደረገ አንፀባራቂ ድል ነው፡፡

ታሪክ እንደሚነግረን ጥቁር ሕዝቦች ለአፍሪካዊ ማንነታቸው፣ ታሪካቸው፣ ቅርሳቸው፣ ነጻነታቸውና ሉዓላዊነታቸው መከበርና ዕውን መኾን የአኅጉሪቷ እልፍ ልጆቿ ደም እንደ ጅረት ፈሷል፣ አጥንታቸውም ተከስክሷል፡፡ አፍሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝብ በሰስትና በናፍቆት የሚያስቡትና የሚያዩት አረንጓዴው፣ ቢጫውና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማችን፣ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ክቡር ደም መሥዋዕትነትና አጥንታቸው መከስከስ ያሸበረቀና ያንጸባረቀ ነው፡፡ ተወዳጇ ከያኒ እጅጋየሁ ሽባባው/ጂጂ ‹‹ዓድዋ›› በሚለው ተወዳጅ ዜማዋ ዜማዋ እንዲህ ብላ እንዳጎራጎረችው፡-

“… የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፡፡

ስንት ወገን ወደቀ፣ በነጻነት ምድር፣

ትናገር ዓድዋ፣ ትናገር አገሬ፣

እንዴት እንደቆምኩኝ በፊታችሁ ዛሬ …፤”

ይህ ዛሬ በነጻነት የቆምንባት ምድር በብዙዎች፣ በእልፎች ክቡር ደም መሥዋዕትነት የጸና መኾኑን ለአፍታ እንኳን ልንዘነጋው አይገባም፡፡ በእነዛ ጥቁር መኾን እንደ ወንጀልና ክህደት በተቆጠረበት አስከፊ ዘመን፣ ለጥቁር ሕዝቦች ከእንሰሳ ያነሰ ክብር እንኳን በተነፈገበት የአፍሪካችን የጨለማና እንደ መርግ የከበደ የመከራ ዘመኗ፣ አፍሪካውያን የሰው ልጅ ሕሊና ሊሸከመው የማይችል ውርደትና መከራን አሳልፈዋል፡፡

ለዘመናት በእንዲህ ዓይነት ውርደትና መከራ ጀርባዋ ለጎበጠው አፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ- እማማ ኢትዮጵያ አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ በናፍቆትና በሰቀቀን የሚያስቧት፣ በዘላለም ቃል ኪዳን በልባቸው ጽላት የተጻፈች፣ የታተመች ከሩቅ  አሻግረው የሚያይዋት አፍሪካዊት የነጻነት ቀንዲል፣ የነጻነታቸውና የሉዓላዊነታቸው የተስፋቸው፣ ምድር ነበረች፡፡

አገራችን ኢትዮጵያን በብዙዎች አፍሪካውያንና በመላው የጥቁር ሕዝብ ዘንድ የነጻነታቸው ተስፋና ብርሃን ተምሳሌት ሆና ከፍ ብላ እንደትታይ ያደረጓት በርካታ ታሪካዊ ሐቆች አሉ፡፡ በሺሕ ዘመናት የሚለካው ታሪኳ፣ ጥንታዊና ገናና የኾነ ሥልጣኔዋ፣ ነጻነታቸውን አፍቃሪ ለኾኑ የዓለም ሕዝቦች ተምሳሌት የኾነው የልጆቿ የአይበገሬነት ጽኑ የነጻነት መንፈስ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሣው አንጸባራቂው የዓድዋው ድል በግንባር ቀደምትነትና በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው፡፡

ይህ መላው አፍሪካ በባርነት ቀንበር ስር ወድቆ በሚማቅቅበት ዘመን፣ ከምሥራቅ አፍሪካዊቷ፣ ጥንታዊት አገር የተሰማው የድል ብስራት፣ ለአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሊሰሙትና ሊቀበሉት የተናነቃቸው ታላቅ መርዶ ነበር፡፡ በ1888 ዓ.ም. ከሮማ ገሥግሦ፣ ቀይ ባሕርን አቋርጦ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጣው ኃይል በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ብርቱ ክንድ ተመቶ በታላቅ እፍረት ወደመጣበት ተመለሰ፡፡ ያ አንፀባራቂ የዓድዋ ድልም በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍን ከፈተ፡፡

የዚህ ድል ዜማም በዓለም ዙሪያ ሁሉ ከፍ ብሎ ተሰማ፡፡ በአውሮፓ የሚታተሙ ጋዜጦችም ድሉን አስመልክተው በፊት ገጾቻቸው ዘገቡ፡፡ ቪቫ ምኒልክ! ቪቫ ጣይቱ! የሚሉ የድል ብስራቶችና ዜናዎች በመላው ዓለም ናኙ፡፡ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በካረቢያንና በጃሜይካ በዓድዋው የድል ስሜትና፣ በኢትዮጵያዊነት የነጻነት ተጋድሎ ሰሜት የተረገዙ ንቅናቄዎችም ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ዓድዋ የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል ኾኖ ደምቆ፣ ፈክቶ አበራ፡፡ በባርነትና በቅኝ ግዛት ስር ኾነው የሚማቅቁ አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦችም ከዓድዋው ድል በኋላ  ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት ጀመሩ፡፡

ሁጊንስና ጃክሰን የተባሉ አውሮፓውያን ምሁራን፣ An Introduction to African Civilizations with Main Currents in Ethiopian History, በሚል ርእስ ባስነበቡት መጽሐፋቸው እንደገለጹትም፣

‘‘አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ ሰራዊት በኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ኃይሎች ላይ የተጎነጸፉት ድል፣ ጥንታውያኑን ኢትዮጵያውያንን ዘመናት ያስቆጠረ ነጻነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ዳግም በተግባር ያረጋገጠ ድል ነው፡፡’’ በማለት ምስክርነታቸውን ሲሰጡ፤ እንግሊዛዊው ጸሐፊ ጆርጅ በርኬሌይ ደግሞ፣ ‘‘የዓድዋ ድል ቅኝ ገዢ ተስፋፊ የኾኑ አውሮፓውያን ቆም ብለው እንዲያሰቡ ያደረጋቸው አንጸባራቂ ድል ነው፡፡’’ በማለት ነበር የገለጸው፡፡

ዐድዋ በቅኝ ግዛት ስር ወድቀው ሲማቅቁ ለነበሩ ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተስፋ ጮራን የፈነጠቀ፣ ለነጻነት ታጋዮች ትልቅ ወኔንና መነቃቃት የፈጠረ ድል ነው፡፡ ዐድዋ ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦች ብቻ ሣይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ- ሰው የመሆን ከፈጣሪ ዘንድ የተቸረን መለኮታዊ ፍቅርና ክብርን ከፍ ከፍ ያደረገ የድል፣ የነጻት ታላቅ ዓርማ ነው፡፡ ይህ የነጻት ድል በአፍሪካና በመላው ዓለም ሲሰማ፣ ዳግመኛ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዓለም መድረክ አብቦ፣ ፈክቶና ደምቆ፣ ከፍ ከፍ ብሎ ታየ፡፡

ለመውጫ ያህል፤

ይህን የዐድዋን አንጻባራቂ ድል በተመለከተ፣ ታሪካዊ እሴቱን፣ ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ቅርስና ውርስ መሆኑን በሚመጥን መልኩ የሚገባውን ያህል ዋጋና ክብር ሰጥተነዋል ብሎ ለመናገር የምንደፍር አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆነኝ ዘንድ አንድ ሁለት አብነቶችን ለማንሳት ልሞክር፤

አፍሪካውያን የነጻት ታጋዮች፣ አርበኞች እንደ ፓን አፍሪካኒስቶቹ- የጋናው የነጻት አባት ዶ/ር ክዋሜ ንኩርማ፣ የኬንያው የነጻት አባት ጆሞ ኬንያታ፣ የደቡብ አፍሪካው የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ፣ የካረቢያኑ እነ ማርከስ ጋርቬይ፣ ዶ/ር ዊልያም ዱ ቦይስ… እና ሌሎችም አፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን የነጻነት አርበኞች-  የዐድዋው ድልና የኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ነጻነት ክብርና ኩራት፣ ወኔና ስንቅ ሆናቸው ነው ለነጻነታቸው የበቁት፡፡

ዐድዋ ድል የትናትናውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬውን የአፍሪካ ኅብረት ዕውን እዲሆን ያስቻለ ነው፡፡ ግና በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ ለጋናው ፓን አፍሪካኒስትና የነጻነት ታጋይ የመታሰቢያ ሀውልት በቆመለት ግቢ ውስጥ፣ ለዚህ አፍሪካዊ የነጻነት ታጋይ፣ ለመላው አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች የወኔ ስንቅ ኾኖ ያገለገለው ዓድዋ ምንም መታሰቢያም ኾነ ማስታወሻ አለመቆሙ የሚያስቆጭም፣ የሚያስተዛዝብም ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ‘የታሪክ ምፀት’ ራሱ ዶ/ር ንኩርማ ከመቃብር ቀና ብሎ ቢመለከት እኛንም ኾነ አፍሪካውያኑን ወገኖቹን ከልቡ እንደሚታዘበን ነው የምገምተው፡፡

በኅብረቱ ግቢ መታሰቢያ የቆመለት ፓን አፍሪካኒስቱ ዶ/ር ንኩርማ በሕይወት ዘመኑ ለእርሱና ለሕዝቦቹ የነጻነት ቀንዲል የኾነች ኢትዮጵያ ሁሌም የነጻነት ብርሃን ኾና በልቡ ለዘላለም ታትማ እንደምትኖር ነበር ሲገልጽ የኖረው፡፡ እንዲሁም የኬንያው የነፃነት ታጋይና ዐርበኛ ጆሞ ኬንያታም ለትምህርት እንግሊዝ አገር በነበሩበት ወቅት በዩኒቨርስቲያቸው ቤተ መጻሕፍት መደርደሪያ ላይ ‘የኢትዮጵያን ታሪክ’ በሚተርከው መጽሐፍ ውስጥ ያገኙትን የዳግማዊ ዐጤ ምኒልክን ፎቶ ወደ ደረታቸው አስጠግተው በማቀፍ፣ ዓይኖቻቸው በደስታና በሲቃ እንባ ተሞልቶ እንዲህ ብለው ነበር፤

ኦ! ምኒልክ የአፍሪካና ጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ ኦ! ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድል ብስራት፣ የነጻነታችን ተስፋ መሬት፣ የልባችን ኩራት… ታላቁ ንጉሥ ምኒልክ ሁሌም አከብርዎታለሁ!!

ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻት ችቦን ለለኮሰው ዐድዋ ድል መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የዓድዋ ድል በአፍሪካ ደረጃ እንዲከበር የኅብረቱ መቀመጫ በኾነችው አገር በኢትዮጵያ ሰፊ የኾነ እንቅስቃሴና ቅስቀሳ ሊደረግ ይገባል፡፡ በእርግጥም ደግሞ ዐድዋ በኅብረቱ አዳራሽ ቋሚ መዘክርም ሊደረግለት ይገባል፡፡ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጃማይካና ካረቢያ ብዙዎችን ለነጻነታቸውና ለሰብአዊ መብታቸውና ክብራቸው ያንቀሳቀሰ ይህ ታላቅ ድል፣ በኢትዮጵያውያንም ኾነ በአፍሪካውያኑ ልብ ውስጥ መዘንጋቱ በጣሙን፣ በጣሙን የሚያስቆጭ ነው፡፡

በእነ ጆሞ ኬንያታ፣ በንኩርማ፣ በእነ ሴዳር ሴንጎር፣ በሮበርት ሙጋቤ፣ በእነ ኔልሰን ማንዴላና በእልፎች አፍሪካውያን የነጻነት ዐርበኞችና ታጋዮች ልብ ውስጥ የነጻነትን ብርሃን ጎህ የቀደደ የዓድዋ ድል በኢትዮጵያም ኾነ በአፍሪካ በታላቅ ድምቀትና ስሜት ሊከበር፣ ሊዘከር ይገባዋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ መንግሥት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር፣ የታሪክና የቅርስ ባለሙያዎች ዓድዋ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይገባል፡፡

በውጭ አገራት ያሉ፣ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶችም የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን፣ የመላው ጥቁር ሕዝብና በአጠቃላይም ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ የሰው ልጆች ሁሉ የሚጋሩት ድል መኾኑን በማስመልከት በስፋት ሊንቀሳቀሱና ሊሠሩ ይገባቸዋል፡፡

ሰላም!!

ፍቅር እና ክብር የነጻነትን ክቡድ እና ክቡር መንፈስ ከዐድዋ ተራሮች እስከ አፍሪካና ዓለም ጫፍ ድረስ በክብር ለናኙት የዐድዋ ጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን ሁሉ!!

ፍቅር እና ክብር የነጻነትን ሕያውና ክቡድ መንፈስ በደማችን ላሰረፁብን፣ ኢትዮጵውያን ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ሁሉ!!

Filed in: Amharic