>
5:33 pm - Saturday December 5, 1868

ስለትግራይ ሲነሳ ብዙ ብዙ ይወሳል...!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ስለትግራይ ሲነሳ ብዙ ብዙ ይወሳል…!!!

በእውቀቱ ስዩም

እኔ ጭሮ አዳሪ ስለሆንኩ መጀመርያ የማስታውሰው የፅሁፍ ሰዎችን ነው፤   አለቃ ተወልደ መድህን ፤ ደብተራ ፍስሀ ወልደጊዮርጊስ ፥      ገብረህይወት ባይከዳኝ ፤   ስብሀትለአብ ገብረእግዚአብሄር ፥  ከትግራይ ምድር የተሰጡኝ  የኢትዮጵያ ገፀበረከቶች ናቸው፤
ከ ሶስት መቶ አመት በፊት  የተፃፈ የታሪክ ድርሳን አግኝተህ ብታነብ  ትግራይ በእርሻ በቀንድ ከብት እና በሌላው ምርት  የበለፀገች እንደነበረች  ትረዳለህ ፤ ከዚያ   ያ ሁሉ አዱኛ  ምን ሆነ ?  ፤ ጂኦግራፊ  እና ታሪክ ከእኛ ምርጫ በላይ የሆኑ ነገሮች ናቸው ፤   የትግራይ ምድር የኢትዮጵያ ዋናው በር ነው፤ የውጭ ውራሪ የወረወረው ሁሉ ቀድሞ እዚህ በር ላይ ይወድቃል ፤በውስጥም፤የሃያላን መደባደቢያ መድረክ ሆኖ ቆይቱዋል፤
 በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ያለውን ብቻ ማየት ይበቃል   ፤በቴዎድሮስ ዘመን አገው ንጉሴ የሚባል ሸፈተና ወደ  አክሱም  አፈገፈገ ፤ (1861) ንጉሱ   ከሸዋ ወደ አክሱም ገስግሰው  ገጠሙት  ፤   ከቴዎድሮስ  ህልፈት በሁዋላ ፤ የላስታው ጎበዜ  ተክለጊዮርጊስ ተብለው  ነገሱ፤ካሳ ምርጫ የተባለ ወደረኛቸው  አልገዛም አለ  ፤ አድዋ ላይ ተቀጣጥረው  ተፈሳፈሱ ፤ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰው አልቆ  ተክለጊዮርጊስ ቆስለው ተማረኩ፤ካሳ ምርጫ ዮሀንስ አራተኛ ሆነው  ነገሱ ፤ ከዚያ ባፄ ምኒልክ   ወደ ስልጣን ሲወጡ  እነ መንጌ  አሻፈረኝ አሉ፤ደሞ ባዚያ ዘመን መንጌ ምን ይሰራል ለሚለኝ አንባቢ  መንጌ ያልኩት ራስ መንገሻን ነው፤     አጤ ምኒልክ ትግራይ ወጡና ውጊያ ገጠሙ ፤ ከአመታት በሁዋላ ደሞ ጣልያን “ በጀልባ ተሻግሮ “  መጣና በራሳችሁ ሜዳ ይዋጣልን  አለ፤በአምባላጄ በአድዋ በመቀሌ ጥይት ዘነበ!  ከቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘመን የነበረውን ጀምሮ የነበረውን የጦርነት ታሪክ ብዙ ሰው ስለሚያውቀው ልግደፈው፤
 እና በዚህ ሁሉ  በአረር ሲለበለብ በመድፍ ሲታረስ  የኖረ መሬት ሳር ማብቀሉም  ይደንቃል  ፤   ባጠቃላይ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ  በህይወት መቆየት፥  ወልዶ መሳም  በራሱ ቶምቦላ ነው ፤
ለማንኛውም :-
አጥቂዎችን የእጃቸውን ይስጣቸው!  ጌቶችም  ስራቸው ያውጣቸው፤ አርሶ ነግዶ ከሞላ ጎደል ከጎረቤቱ ጋር ቡና እየተጠራራ መከራና ተድላ እየተጋራ  የሚኖር  ህዝብ ፤ግፍ ሊፈፀምበት አይገባም፤
    ሰንበት ነውና፥  በቁምነገር  የጀመርኩትን  ፅሁፍ በቁጭ-ነገር እንድዘጋው ይፈቀድልኝ    ፤ከ “አሜን ባሻገርን “ ለመፃፍ በከተሞች ስዞር  አድዋን አዲግራትን አክሱምን እና መቀለን ጎበኘሁ፤( በነገራችን ላይ መቀለ የሚለው ቃል ለመፃፍያ የሚያገለግለው  “ ባለ ባርኔጣው ቀ “  ኪቦርዴ ላይ የለም)   አንድ ቀን     ወዳጄ መሀመድ ሳልማን  መቀለ  ዩንቨርሲቲ ጋብዞኝ  ውየ ሳበቃ ወደ ሆቴል የሚመልሰኝ  ባጃጅ ተሳፈርሁ፤   አብርሃ ካስል ስደርስ  ወረድኩና
“ስንት ነው?” አልኩት ባለ ባጃጁን
“  ዙብለህ  ደስ ያለህን ስጠኝ ”  ብሎ መለሰልኝ ፤
  ከዚያ በፊት ሌላ ባጃጅ ያስከፈለኝ አስር ብር ነው ፤ ግን የዚህኛው ልጅ  ትህትናው  ልቤን ስለነካው፥ መልኩም ኪሮስ አለማየሁን ስለሚመስል፤     ገና ከባንክ የወጣ ትኩስ አምሳ ብር አውጥቼ   ሰጠሁት  ፤
 ልጁ  እሳት ለብሶ ፤ እሳት  ተንተርሶ እንዲህ አለኝ፤
“ ዋይ!   ከሌለህ  የለኝም  አትልም እንዴ? “
Filed in: Amharic