>

የሌባ ዐይነ ደረቅ. . .  !!!

የሌባ ዐይነ ደረቅ. . .  !!!

ባለፉት 30 ዓመታት ወያኔ በአማራ ላይ ሲያካሂድ የኖረው የዘር ማጥፋት ከትግራይ ክልል በስተቀር  ያልተሰማው ኢትዮጵያዊ አልነበረም። ከ30 ዓመታት በፊት የአማራ ሕዝብ የሚከላከልለት ኃይል ባጣ ጊዜ ትግሬን ነጻ ለማውጣት የተቋቋመው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግሬ በወረራ በያዛቸው የጎንደርና የወሎ ወረዳዎች ነባር የአማራ ተወላጆች ላይ ሲፈጽመው የነበረውን የዘር ማጥፋት እንዲያቆምና በወረራ የያዛቸውን የጎንደርና የወሎ ወረዳዎች ለቅቆ እንዲወጣ ጥሪ ያላቀረበና ኢትዮጵያዊ ዜግነታዊ ሚናውን ያልተወጣ ቢኖር ትግራይ ክልል ብቻ ነው።
ወያኔ የዘረፈው ሁሉ ይገባኛል የሚለው አብርሀ ደስታ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ ፍዳውን ሲያይ ቢከርምም እሱ እንደሚገምተው ማሰብ የማይችል ደንቆሮ አለመሆኑን የተገነዘበ አይመስል። ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ፍዳና መከራ ሲያደርስ የኖረው የጭካኔ ስርዓት ቁንጮ የሆነውን ጌታቸው አሰፋን አሳልፈን  አልሰጥም እያለ ሲፎክር የነበረው አብርሀ ደስታ በምን ሞራሉ ነው ጌታቸው አሰፋ ሲመትረው ለኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዜግነታዊ ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ የሚያቀርበው? አብርሀ ደስታ ከሶስት ወራት በፊት  ከሕወሓት ጋር ወግኖ  ምን ሲያደርግ እንደነበር የኢትዮጵያ ሕዝብ የማያውቅ ይመስለዋል ይሆን?
አንድ ሰው መሬቴ ያለአግባብ ተወስዶብኛል ብሎ ካመነ ወይም ቅሬታ ካለው ማስረጃ በማቅረብ ያላግባብ ተወሰደብኝ የሚለው የራሱ ስለመሆኑ ማስመስከር አለበት።  ሆኖም ግን  አብርሀ ደስታን ጨምሮ አንድም የትግሬ ብሔርተኛ ወልቃይትና ራያ ላለፉት 30 ዓመታት በወያኔ ተወረው ወይም occupied territories ሆነው ወደ ትግራይ በኃይል ከመወሰዳቸው በፊት የትግሬ እንደነበሩ ሲያስመሰክርና ማስረጃ አቅርቦ ሲከራከር አላየሁም። ሁሉም የትግሬ ብሔርተኞች እየጠየቁ ያሉት ወያኔ የዘረፈው ሁሉ ለኛ ይገባናል የሚል ጥያቄ ነው።
እኛ ግን ባለፉት 30 ዓመታት በወረራ የተያዙት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ ቢያንስ ላለፉት 1660 ዓመታት በአንድም የታሪክ ወቅት የትግሬ ሆነው እንደማያውቁ ፤ ይልቁንም ነበሩ ባለርስት አማራ እንደሆነ ከ700 በላይ ማጣቀሻ (መጠቆሚያ) ተጠቅመን ውሸታውን ያረከሰ መጽሐፍ በማሰናዳት ለገበያ አቅርበናል። በመጽሐፉ የቀረበውን የታሪክ ሙግት አለኝ የሚለውን ማስረጃ አቅርቦ የተቸ አንድም የትግሬ ብሔርተኛ የለም።
መጽሐፍ ከመጻፍም አልፈን እነ አብርሀ ደስታን  አለን የምትሉትን ማስረጃ ይዛችሁ በፈለጋችሁት መድረክም እንገናኝና በኢትዮጵያ ሕዝብ ዳኝነት እንከራከር ብለን በአደባባይ ብለን ጠይቀናቸው ነበር፤ እነሱ ግን የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል። አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ  እንጠይቃለን! ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ የሚያቀርበው አብርሀ  የትግሬ መሬቴ ያለአግባብ ተወስዷል ብሎ የሚያምን ከሆነ ማስረጃውን ይያዝና ጥሪ ባቀረበለት በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ቀርበን እንከራከርና እንዳኝ። ከዚህ ውጭ በድርቅና ወያኔ የዘረፈው ሁሉ ይገባኛል ማለት ሊሰርቅ ገብቶ ባለቤቱ ሲደርስበት ምን አገባህ? ብሎ ግግም ብሎ እንደተከራከረው የሌባ ዐይነ ደረቅ ብጤ መሆን ነው:: (አቻምየለህ ታምሩ)
Filed in: Amharic