>

`እነርሱ ሊዘምቱብን ዝግጅታቸዉን አጠናቀዋል፤ እኛስ ምን ላይ ነን....??? መንግስት ቁርጣችንን ይንገረን!!! (አህመድ ሱሌይማን)

`እነርሱ ሊዘምቱብን ዝግጅታቸዉን አጠናቀዋል፤ እኛስ ምን ላይ ነን….??? መንግስት ቁርጣችንን ይንገረን!!!
አህመድ ሱሌይማን

ግብፅ እና ሱዳን በኤምሬት እና በሳዑዲ አረቢያ ፔትሮ ዶላር ድጋፍና ከትራምፕ እስከ ባይደን በተንሰራፋ ግልፅ ሴራ ታግዘዉ በአሜሪካ አስታጣቂነት በህልዉናችን ላይ ለመዝመት ዝግጅታቸዉን እያጠናቀቁ ነዉ። እኛ ኢትዮጲያዊያንስ ምን እያደረግን ነዉ? ብቻችንን ነን?። በአገራችን ላይ ያንዣበበዉ ይህ አደጋ ለህዝባችን በግልፅ ቀርቦ ይፋዊ በሆነ መልኩ በምንችለዉ ሁሉ በህዝባዊ ንቅናቄ እንድንዘጋጅ መንግስት ሊነግረን ይገባል እንላለን። አገራችንን የሚደግፉ አገራት ወይም ወገኖች ስለመኖራቸዉ እየተነገረን አይደለም…… መንግስት ቁርጣችንን ይንገረን!…´´ በማለት ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ይጠይቃል በዛሬዉ የዘሀበሻ ሪፓርቱ።
*****
የግብፅ ጦር አዛዥ ካርቱም ፤ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካይሮ ናቸው።
በመጪዉ ቅዳሜ ደግሞ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ሱዳንን ይጎበኛሉ።
ካርቱም ላይ ፦
ሰኞ ወደ ካርቱም ያመሩት የግብፅ ጦር አዛዥ ሌ/ጀ ሙሀመድ ፋሪድ ከሱዳን አቻቸው ሌ/ጀ ሙሀመድ አል ሁሴን ጋር የተለያዩ ወታደራዊ ስምምነቶችን ፈፅመዋል።
የግብፁ ጦር አዛዥ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ግብፅ እና ሱዳን #ተመሳሳይ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት (ኢትዮጲያ) ተደቅኖባቸዋል፤ በጋራ መስራት የሚገባን ጊዜ አሁን ነው ብለዋል። እንዲሁም “ሱዳን ለምታቀርብልን ወታደራዊ ነክ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ለመስጠት ግብፅ ዝግጁ ናት” ሲሉ ተናግረዋል (ሱዳን በወረረችዉ ድንበሮች ግብፅ ወታደሮቿን ለማሰማራት አስባ ይሆን)
የሱዳኑ አቻቸው እንዳሉት ደግሞ ሃገራቱ #የጋራ አደጋ (ኢትዮጲያ) የተደቀነባቸው በመሆኑ በወታደራዊ መስክ ትብብራቸው ጠንክሯል ብለዋል።
ካይሮ ላይ ፦
የሱዳን ው/ጉ/ሚኒስትር ማርየም አል ሳዲቅ ግብፅ በማቅናት በዋናነት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከግብፅ መንግስት ሃላፊዎች ጋር ሲመክሩ ዉለዋል።
የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን እንዳይካሄድ ለማድረግ ያስችላል ያሉትን ምክክር አድርገዋል (የዉሀ ሙሌቱን የሚያስቆመዉ የህዳሴ ግድብ አካባቢ ከተወረረ ብቻ ነዉ፣ ምክክሩ በዛ ዙሪያ ይሆን?)።
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርየም አል ሳዲቅ፥ ኢትዮጵያ ለብቻዋ (በገዛ ዉሀ፣ አገራችን እና  ግድባችን) የምታደርገውን ነገር እንድታቆም እንነግራታለን ፥ አካሄዷ ወደአላስፈላጊ አቅጣጫ (ወደ ጦርነት) ይዞን ሊሄድ ይችላልም ሲሉ ማስፈራሪያ አዘል ንግግር ሲያደርጉ ተደምጠዋል።
ሰላም ሙሉጌታ እና ኡስታዝ ጀማል በሽር እንደዘገቡት
****
በዚህ በኩል ግብፅና የአረብ ግመሏ ሱዳን በሌላ በኩል አሜሪካ ኖርዌይ ስዊድንና የመሳሰሉት አዉሮፓዊያን ኢትዮጲያን በጫና ብዛት ሊያፈርጧት የፈለጉ ይመስላል። በመጪዉ ሐሙስ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ም/ቤት ስለ ኢትዮጲያ ለመወያየት ይሰበሰባል። የዛሬ ወር በነበረዉ የፀጥታዉ ም/ቤት ስብሰባ፣ ኢትዮጲያን ለማዉገዝ ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም የፀጥታዉ ም/ቤት ቋሚ አባል በሆኑት ሩሲያና ቻይና እንዲሁም ጊዚያዊ ተሳታፊ በነበረችዉ ኬኒያ ተቃዉሞ ምክኒያት ሳይሳካ ቀርቶ ነበር። በመጪዉ ሐሙስ ስብሰባም በሩሲያና ቻይና የድምፅ ተአቅቦ፣ ኢትዮጲያን ለማዉገዝ ሊደረግ የሚችለዉ ሙከራ እንደሚከሽፍ ይጠበቃል። በወታደራዊም ሆነ በዲፕሎማሲያዊ ዘርፉ፣ ኢትዮጲያ ላይ ከምንግዜዉም በላይ ከባድ አደጋ የተደቀነባት ወቅት ላይ እንገኛለን። አደጋዉ እየመጣ ባለበት ፍጥነትና ግዝፈት ግን መንግስታችን እየተንቀሳቀሰ አይመስልም።
Filed in: Amharic