>

ምኒልክ - ከቅኝ ግዛት ባርነት ያዳነን ተዓምረኛ! (አሰፋ ሀይሉ)

ምኒልክ – ከቅኝ ግዛት ባርነት ያዳነን ተዓምረኛ!

አሰፋ ሀይሉ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና፣ የባህል ተቋም (UNESCO) የዓለም ሕዝብ እውነታውን አውቆ እንዲማርበት በማለት “Africa Under Colonial Domination 1880-1935” በሚል ርዕስ 765 ገጾች ያሉት የዳጎሰ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ በመጽሐፉ የወቅቱ የአውሮፓ ቅኝ-ገዢ ኃያላን ሀገሮች፣ አፍሪካውያንን እንዴት አድርገው እንደ ተቀራመቷቸው የሚያሳዩ የያንዳንዱ ሀገር ታሪኮች ከሰነድና ምስል ማስረጃዎቻቸው  ጋር ተካተዋል፡፡
ቅኝ ግዛት የሰውን ልጅ ሰውነት አልቀበልም ብለው ጥቁሮችን ባርያችን እናደርጋለን ብለው ያን ሃሳባቸውን በተግባር የተረጎሙ እኩያን ኃያላን ታሪክ ነው፡፡ ዓለም አንገቱን የሚደፋበት ታሪክ፡፡ በዚያ አሳፋሪ ታሪክ ውስጥ ነው የአጼ ምኒልክ ተጋድሎ የሚገዝፍብን፡፡ ቅኝ ገዢዎቹ አውሮፓውያን ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫዎች ከብበው ጦራቸውን አከማችተዋል፡፡ በዚያ ላይ ከየተቆጣጠሯቸው ግዛቶች – ምንዳ እየቆረጡ ከጎናቸው ያሰለፏቸው በሺህ የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ‹‹አስካሪዎችም›› አሏቸው፡፡ እነዚህ ባንዳዎች ከነጮቹ ባርነት በመጠኑ ለመላቀቅና ለመኖር የሚፍጨረጨሩባትን የአገልግሎት ዋጋ (ምንዳ) ለማግኘት ሲሉ ለነጮቹ አድረው በአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው ላይ ይዘምታሉ፡፡ ከታዘዙ ነጮቹን የሚዋጉትን ይወጋሉ፣ ይገርፋሉ፣ ይሰቅላሉ፡፡
አንድ የኬንያ አስካሪ ባንዳ ስለዚያ አሳፋሪ ታሪኩ በጻፈው መጽሐፍ ሲናገር፡- ‹‹በሠላሙ ጊዜ ድንጋይ እያስፈለጡና አሸዋ እያስጋዙ መንገድ ያሰሩናል፣ እኛ ለቁራጭ ምንዳ ብለን ወገባችን እስኪጎብጥ ስንሠራ ነጮቹ ገዢዎቻችን ከፊታችን እየተንጎማለሉ ያዩን ነበር፣ የሚያሳዝነው ነገር ጦርነት ሲያደርጉ ግን እነዚያ በሠላሙ ቀን ከፊት ሆነው የሚንጎማለሉ ገዢዎች እኛ ለጥይት እራት እንድንሆን ከፊት አሰልፈው እነሱ ከኋላ ከኋላችን ይከተሉን ነበር›› በማለት አፍሪካውያን ባንዳዎች በሠላሙም በጦርነቱም በቅኝ ገዢዎቹ እጅ ያሳለፉትን ግፍ ይናገራል፡፡ እንግዲህ አፍሪካዊ ወገኖቻቸውን መካዳቸውና በባንዳነት ለነጮቹ መሰለፋቸው የሚያደርስባቸው ውስጣዊ የህሊና ወቀሳ ሳይጨመርበት ነው ይሄ፡፡
ምኒልክ ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢዎቹ ጥርስ ውስጥ እንደገባቸው የገባው ገና ወደ ንግሥናው ሳይመጣ ነበር፡፡ ረዥም ዓመታት በፈጀ የዲፕሎማሲ መንገድ – አጼ ዮሐንስን ይወጋልናል ብለው ከጎመዡት ነጮች በርካታ የጦር መሣሪያና ትጥቅ ሲያከማች ነው የኖረው ምኒልክ፡፡ ጉልበት ባገኘና ህዝቡን ባስታጠቀ ቁጥር – በቻለው ሁሉ በምስራቅ ኢትዮጵያና በምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል እየዘመተ የግብጾችንና የኦቶማን ወራሪዎችን ብዙ ጊዜ ድል እያረገ ከድንበር አባሯል፡፡
በእርስ በእርስ የሥልጣን ሽኩቻ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ገዢዎች ጋር ጦርነት ለመግባት በሚገደድባቸው ጊዜ ሁሉ – ምኒልክ – የተዋጋቸውን በማጥፋትና በመጠፋፋት የሚያምን ሰው ሳይሆን – በእርቅና በይቅርታ – እና ገና የውጊያው ደም ሳይደርቅ መልሶ ያሸነፋቸውን ሰዎች እዚያው በሀገሩ ወግና ልማድ ህዝባቸውን እንዲያስተዳድሩ መልሶ የሚሾማቸው – እና ታማኙ የሚያደርጋቸው መሪ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲታይ ምኒልክ – ዋናው ዓላማውና ጭንቀቱ ከራሱ የሀገሩ ሰዎች ጋር መጫረስ ሳይሆን – ሀገሩን ኢትዮጵያን ከከበቧት ጉልበተኛ የአውሮፓ ኃያላን ወራሪዎች እጅ እንዴት አድርጎ እንደሚያስጥላት – ገና በጊዜ ያሰበ፣ ያለመና የገባው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ምኒልክ ወደ ንግሥና መንበር ሲወጣ – በካርታው ላይ ባለው መልኩ አውሮፓውያን፣ የሶማሊ ጂሃዲስቶች፣ ግብጾችና ኦቶማን ቱርኮች ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫዎች እንዴት አድርገው እንደሚወርሯት፣ ማን የቱን የኢትዮጵያ ክፍል እንደሚደርሰው ተስማምተው ያበቁት ጉዳይ ነበር፡፡ በፈረንሣይ፣ እንግሊዝና ጣልያን (ጀርመንም ጭምር) መሐል የተደረገው ‹‹ትራይፓርታይት ኮሎኒያል ፓርቲሽን አግሪመንት›› የተሰኘው የሶስትዮሽ ስምምነት – እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ – ፈዲስን አንተ ውሰድ፣ ሸዋን አንቺ ውሰጂ፣ ጎጃምና ወለጋን እገሌ ይውሰድ፣ እገሌ በዚህ በኩል አድርጎ እንዲያቋርጥ የባቡር መስመር እንዲዘረጋ እንፍቀድለት፣ ወዘተ የሚሉ ስምምነቶችን ያቀፈ የወረራ ስምምነት ነበር፡፡ የሰው ሀገርን ወርረው የሚደርሳቸውን ቅርጫ እኮ ነው የሚስማሙት አስቀድመው፡፡ በእነዚህ ጅቦች ዙሪያውን ተከብቦ ነው ምኒልክ የቆመው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሣይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ባሳተመው መጽሐፍ ይሄ ሁሉ የአውሮፓውያኑ ሸርና ከበባ በግልጽ ተመላክቷል፡፡ ያውም በካርታዎች ተደግፎ፡፡ በሰሜን ግብጾች ተሰናድተዋል፡፡ በሰሜን ምስራቅ ግብጾችና ኦቶማኖች በወደብ በኩል ተከማችተው ለወረራ ዝግጁ ናቸው፡፡ በሰሜን ምዕራብ በኦቶማን የሚደገፉ እስላማዊ ቡድኖች (‹‹ሎካል ካሊፋቶች››) መሣሪያ ታጥቀው በኢትዮጵያ ላይ ለመዝመትና የምርኮ ድርሻቸውን ለማግኘት ተማምለው ተቀምጠዋል፡፡ በሰሜን ምዕራብ በኩል የእንግሊዞችና ግብጾች ጥምር ወራሪ ኃይል አካባቢውን እስከ ሱዳን ተቆጣጥሮት ኢትዮጵያ ላይ ለመዝመት ሱዳን እስክትሰክንለት እየተጠባበቀ ነው፡፡ በምዕራብ በኩል ፈረንሳዮች አመጽ ለማክሸፍ ነው በሚል ጦራቸውን ልከው እዚያው አስፍረው እየተጠባበቁ ነው፡፡ በምስራቅ በኦቦክ (በጂቡቲ) በኩልም ፈረንሳዮቹ ጦራቸውን አስፍረዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ የግብጽና እንግሊዝ ጥምር ጦር እስከ ከፋ ድረስ ዘልቆ ገብቶ ይዞታውን እያጠናከረ ነው፡፡ በደቡብ በርካታ የቡጋንዳ አስካሪ ባንዳዎችን ያሰለፈ የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ እስከ ዩጋንዳና ሱዳን ኢትዮጵያን ከቦ የሚወርበትን ቀን እየተጠባበቀ ነው፡፡ በደቡብ በኩል ጣልያኖች ሶማሊያን ከእንግሊዝ ጋር ተሻርከው በቁጥጥራቸው ሥር አውለው የኦጋዴንን ጠረፋማ ቦታዎች ሁሉ ከብበው እየተቁነጠነጡ ነው፡፡ በደቡብ ምስራቅ በኪስማዩ በኩል፣ እንዲሁም በምስራቅ በሰሜን ሱማሌ (በብሪቲሽ ሱማሊላንድ) በኩል እንግሊዞች ኢትዮጵያን ሊወርሩ በዓይነ ቁራኛ እየተጠባበቁ ነው፡፡
በሠሜን ምስራቅ በኩል እስከ ምጽዋና አሰብ የተዘረጋውን ረዥም የኢትዮጵያ የባህር መገናኛ ድንበር ሁሉ ኢጣልያኖች ከእንግሊዞች ላይ ተረክበው ብዛት ያለው የራሳቸውን ጦርና ከሶማሊና ከኤርትራ የሚመለምሉትን ጦር አስታጥቀው ለወረራ እያከማቹበት ነው፡፡ ጣልያኖቹ ከሶማሊያና ከኤርትራ በኩል ቀስ በቀስ – ምኒልክ ‹‹እንደ ፍልፈል መሬት እየቆፈሩ›› ብለው እንደጠሯቸው መሬት እየቆፈሩ – ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ እየዘለቁ አዳዲስ ምሽጎችን ያጠናክሩ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ ላይቤሪያን የዶሮ ሳንባ የምታህል አገር እስክትቀራቸው ድረስ ከአራቱም አቅጣጫ ከበው እየቦጫጨቁ እንደተጫወቱባት – ኢትዮጵያም ላይ ሊጫወቱባትና ሊቀራመቷት አሰፍስፈዋል፡፡ ቢያንስ ላይቤሪያ የተረፈላትን ሙዳ ግዛት ያተረፈችው – አሜሪካ ከጎኗ አለሁሽ ብላ ስለቆመችላት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ግን አለሁሽ ብሎ ከጎኗ የሚቆምላት ኃያል ሀገር አልነበራትም፡፡ ራሺያኖቹ ቀናነቱ ቢኖራቸውም ገና ድሮ ከግዛታቸው ውጪ ርቀው ሄደው ጦርነት ገጥመው አውሮፓውያኑን እንደማያሸንፉ አውቀው – ለአሜሪካ የአላስካ ግዛታቸውን ሸጠው ወደ ሀገራቸው የገቡ ናቸው፡፡ ጀርመኖቹ፣ ስፓኞቹና፣ በግራኝ ወረራ ወቅት ሀገራችንን መጥተው የረዱት ፖርቹጋሎቹ ራሳቸው በየክፍላተ ዓለሙ ከእንግሊዝና ፈረንሳዮች ጋር እየተስማሙ የራሳቸውን ነባርና አዳዲስ ቅኝ ግዛቶች እያደላደሉ ነበር፡፡
የእኛ አድዋ ጦርነት አካባቢ የነጻነት አርበኛ ነን የሚሉት አሜሪካኖች የቅኝ ግዛቱ ቅርጫ አጓጉቷቸው ፊሊፒኖዎችን ከስፔኖች ላይ በ200 ሚሊዮን ፔሴታ ሊገዙ ድርድር ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ እና ኢትዮጵያ ወደ የምትጠጋበትም፣ ድረስልኝ ብላ የምትጮህለትም የቅርብም የሩቅም ወደጅ አልነበራትም፡፡ ይህን የአውሮፓ ጸሐፊዎች – ኢትዮጵያ ላለፉት 300 ዓመታት ለውጪው ዓለም በርና መስኮቷን ዘግታ መቆየቷ ያመጣባት ዕዳ ነው ሲሉ ይሄሱታል፡፡ እምዬ ምኒልክ ደግሞ እንዲህ በማለት የተናገሩትን የዩኒስኮው መጽሐፍ ለታሪክ ቀርጾ አስቀምጦት እናገኛለን፡- “Ethiopia has need of no one; she stretches out her hands unto God!” (‹‹ኢትዮጵያ በማንም አትመካም፣ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!››)፡፡
የዩኔስኮ ጥናትና ምርምር መጽሐፍ ይሄን ሀቅ አስቀምጦ እውነት ነው የሚል ማረጋገጫውን ይሰጣል፡፡ ከፈጣሪ በቀር ኢትዮጵያ የምትመካበት ማንም አልነበራትም፡፡ ደግሞም በኢትዮጵያውያንም፣ በላይቤርያውያንም ዘንድ የምናገኘው በፈጣሪ አምላካቸው ላይ ያላቸው ጥልቅ እምነት – የፈለገ ኃያል ቢመጣባቸው እግዚአብሔር ከጎናችን ነው ብለው ለነጻነታቸው በልበ ሙሉነት እንዲቆሙና እንዲዋጉ ያስቻላቸው ትልቁ ምክንያት ነው – በማለት ያስቀምጣል ይህ የአፍሪካችንን ታሪክ ለዓለም የሰነደ የዩኔስኮ ህትመት፡፡
ምኒልክ ቀዳማዊ ከጠቢቡ የብሉይ ዘመን የእስራኤል ንጉሥ ዘር ይወለድ አይወለድ – እውነትም ይሁን አፈታሪክ – ጥበብ በዘር ይተላለፍም አይተላለፍም – በትክክል በዚህች የአፍሪካችን ቀንድ – በኢትዮጵያ – ተፈጽሞ የታየው ግን – የምኒልክን ልክ እንደ ብሉይ ዘመኑ ንጉሥ እንደ ጠቢቡ ሠሎሞን ጥበብንና የፈጣሪ ኃይልን – ሁለቱንም ተላብሶ የተገኘ አፍሪካዊ ንጉሥ ሆኖ መገኘቱ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዙሪያዋን ሊበሏት ባሰፈሰፉ ጅቦች የተከበበችውን ኢትዮጵያን የሚታደግለት – ከራሱ፣ ከገዛ ህዝቡና ከፈጣሪ አምላኩ በቀር አንድም ኃያል አጋር አልነበረውም፡፡
ምኒልክ ከአድዋ ጦርነት ጥቂት ወራት አስቀድሞ ለእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶሪያ በላከላት ደብዳቤ ‹‹ኃይላችን እግዚአብሔር ነው፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪዋ ትዘረጋለች!›› ብሎ ነበር የጻፈላት! ወቅቱን ያየ፣ የከበቡንን ኃያላን ያየ፣ ምስኪኒቱን ኢትዮጵያን ያየ ሁሉ፣ ይህን የምኒልክን ቃል አጉል ፈጣሪን እንደ መፈታተን ቆጥሮት ነበር፡፡ ‹‹እኛ ምድራዊ ተዓምራችንን ልናሳይ ዝግጅታችንን ጨርሰናል፣ ምኒልክ ደግሞ የፈጣሪውን ሰማያዊ ተዓምር እየጠበቀ ነው፣ ፈጣሪን ከኛ በላይ የሚቀርበው ይመስላል…›› – ሲል የኢጣልያ የእንግሊዝ ቆንሲል በምኒልክ መልዕክት ላይ ተሳልቆበት ነበር፡፡
‹‹ምኒልክ ተስፋው እግዚአብሔር ነው›› ይል ነበር ከጦርነቱ መልስ ለምኒልክ ከፈረንሣዩ ንጉሥ በሥጦታ የተላከለት ሰይፍ፡፡ ምኒልክ በአድዋ ዘመቻ ታጥቆ የወጣውን ሠይፍ – ሩሲያዊው የጦር መኮንን አሌክሳንደር ቡላቶቪች በፎቶ ጭምር አስደግፎ አሳትሞታል፡፡ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት የታጠቀው ሰይፍ – ከአያቱ ከሸዋው ንጉሥ ሣህለሥላሴ በውርስ የተላለፈለትን ኢትዮጵያዊ ቅርሱን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ አላሳፈረውም! ብዙዎች የዓለም ምሁራን – ምኒልክ በአድዋ ላይ – ኢትዮጵያን ለከበቡ ቅኝ ገዢዎች ሁሉ የማያወላዳ መልዕክትን ያስተላለፈ አንጸባራቂ ድል ሲገናፀፍ – ዓለም ሁሉ በመደመም ነበር የተቀበለው ዜናውን፡፡ ባለማመን ጭምር፡፡ ብዙዎች ያን የምኒልክን የአድዋ ድል ‹‹ከተዓምር የማይተናነስ!›› ብለው ሲገልጹት ነው የምንመለከተው፡፡
በአሜሪካኖች የነጻነት ትግል እንቅስቃሴ ጅማሮው በዓለም የሚታወቀው የሀርቫርዱ ጥቁር አሜሪካዊ ዶክተር ዱ ቧስ በአንደኛው መጽሐፉ ስለ አድዋ ድል ሲናገር፡- ‹‹አድዋ – በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ – ከዚህ በኋላ – መቼም – እና የትም – ነጮች ጥቁሮችን በባርነት የመግዛታቸው ታሪክ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማብቃቱን ለሰው ልጆች ሁሉ በሚሰማ ግልጽ ቋንቋ ያበሠረ ተዓምራዊ ዜና!›› ሲል ነበር የገለጸው፡፡ ኢጣልያኖች ዳግም በ1928 ዓም ኢትዮጵያን ሊወርሩ ሲመጡ፣ የዱ ቧስን ንግግር እንደ ትልቅ ቂም አስታውሰው እየጠቀሱ – እኛ ደግሞ ጥቁሮች የሁልጊዜም ባሪያዎች መሆናቸውን ልናረጋግጥ ነው የምንዘምተው – እያሉ ይሳለቁና የብዙ ነጮችን ድጋፍ ያሰባስቡ ነበር፡፡
የአድዋው ተዓምረኛ ድላችን – ከእኛ አልፎ – በሱማሊያ ውስጥ በእንግሊዝና በኢጣልያ ቅኝ ገዢዎች ሥር ይማቅቁ ለነበሩት ሶማሊዎች ትልቅ የነጻነት ብሥራት ሆኗቸው በሱማሊያ አቋርጦ ቀይ ባህር ጠረፍ እስኪደርስ ድረስ የሚያገኛቸው ሶማሊዎች ሁሉ በደስታ እየፈነደቁ የሚያወሩት ሁሉ – ስለ ኢትዮጵያውያኑ የአድዋ ድል እንደነበረ – በአድዋ ጦርነት ወቅት፣ እና ከጦርነቱ ማግሥት በሥፍራው የነበረው ፖላንዳዊ ተጓዥ ካውንት ጄ. ፖቶኪ ስለ ሶማሊያ ጉዞው ‹‹Sport in Somaliland:…›› ብሎ ከአድዋ ድል 4 ዓመት በኋላ ባሳተመው መጽሐፉ አስፍሮት እናገኛለን፡፡
የፓን አፍሪካኒዝም ቀደምት አቀንቃኝ በመሆን በታሪክ ስሙ ገንኖ የሚጠራው የሄይቲው ምሁርና ጸሐፊ ቤኒቶ ሲልቪያን በበኩሉ ከአድዋ ድል በፊትም በምኒልክ መንግሥትና ሀገር አስተዳደር፣ በምኒልክ ኃያል የጥቁር ህዝቦች ግዛት እጅጉኑ የተማረከና ደጋግሞ ወደ ኢትዮጵያ የተመላለሰ ተጓዥ ነው፡፡ እና እሱ ከአድዋ ማግስት የሄይቲውን ፕሬዚደንት አሌክሲስ ልዩ የአድናቆት መልዕክት ለምኒልክ ይዞ መምጣት ብቻ ሳይሆን፣ ከአድዋ በኋላ ራሱን የፓን አፍሪካኒዝም ሃዋርያ አድርጎ በማሰማራት፣ በዓለም በባርነት ያላችሁ ጥቁር ህዝቦች ሆይ፣ ወደ ተስፋይቱ የነጻነት ምድር ወደ ኢትዮጵያ ተነሱ!›› እያለ እስከ መስበክና መጸሕፍትን እስከማሳተም ደርሶ እናገኘዋለን፡፡
ወደ ኢትዮጵያ በመምጣትና ንጉሠ ነገሥት ምኒልክን በአካል በማግኘት የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ነው በሚል በህይወት ታሪኩ ውስጥ ሰፍሮ የምናገኘው የኩባ ተወላጁ የቴክሳስ ታዋቂ ጥቁር አሜሪካዊው ዊልያም ኤች ኤሊስ በበኩሉ ከፓን አፍሪካኒዝምም አልፎ የወጣለት የኢትዮጵያኒዝም አቀንቃኝ በመሆን በመላው አሜሪካ እየዞረ የኢትዮጵያን የነጻነት ተጋድሎ በወቅቱ በአሜሪካ መብታቸውን ተነፍገው በባርነት ይኖሩ ለነበሩ ጥቁር አሜሪካውያን ማህበረሰቦች ይሰብክ ነበር፡፡ ይህን የዊልያም ኤሊስ ታሪክ ከዩኔስኮው ህትመት በተጨማሪ The Ethiopianism Online Revival በተሰኘ የፌስቡክ አካውንት የዛሬ 6 ዓመት ላይ፡- «Remembering William Henry Ellis – The first African-American to meet Emperor Menelik» በሚል ርዕስ ዝርዝር ታሪኩን አስፍሮለት እናገኘዋለን፡፡
የምኒልክ ድል ምን ያህል ታላቅ የነጻነት መንፈስ መነቃቃትን በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ዘንድ እንደፈጠረ በማሰመልከት ጂ. ሸፐርሰን በ1960 ዓም ባሳተሙት «Ethiopianism: Past and Present» በሚል ታዋቂ መጽሐፋቸው፡- ‹‹እስራኤሎችን ከፈርኦኖች ባርነት ነጻ እንዳወጣው እንደ ሙሴ ስም ባለ ታላቅ ክብር፣ ከአድዋ ድል በኋላ ባሉት ዓመታት የምኒልክ ስም በየጥቁሮቹ ቤተክርስትያናት እየተጠራ ዝናውና ገድሉ ይወደስ ነበር›› በማለት ይገልጹና፣ በዚህም የተነሳ በነጮች ቅኝ ግዛት በተያዘችው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ቤተክርስትያን በ1892 ዓም (በጎርጎሮሳውያን ካሌንደር በ1900) ላይ እስከ መቋቋም እንደደረሰ ያወሳሉ፡፡
ይህን የአድዋ ድል በደቡብ አፍሪካውያን የነጻነት ታሪክ ውስጥ የፈጠረውን ‹‹ነጮችን በጦርነት ገጥሞ ማሸነፍ ይቻላል ማለት ነው?›› የሚለውን የመጀመሪያውን ‹‹አሃ!›› የፈጠረ ታላቅ የደቡብ አፍሪካውያን ባሮች ተስፋ እንደነበር – ኔልሰን ማንዴላ በ”Long Walk to Freedom” መጽሐፉ አስፍሮት እናገኛለን፡፡
የደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ ስቲቭ ቢኮ ‹‹ታዝማኒያ›› የተሰኘች ከነጮች ቅኝ ግዛት የተላቀቀች፣ በጥቁሮች በራሳቸው የምትተዳደር ፍጹም የነጻነት ደሴትን ለደቡብ አፍሪካውያን እንደ ‹‹አይዲያል ኢየሩሳሌማቸው እንዲያስቧት›› ሲሰብክ የነበረው – በአድዋ ድል ዝናዋን የሰማውንና እኛም ነጻ ወጥተን እንደ ምኒልክ ያለች ነጻ የአፍሪካውያን ደሴት እንመሰርታለን በሚል ተስፋ በጽኑ አምኖ መሆኑን – የስቲቭ ቢኮ የህይወት ታሪክ ያወሳል፡፡
ስቲቭ ቢኮ ሲሞት መቃብሩ ላይ እንዲጻፍለት ተናዝዞ የተጻፈችለት ጽሑፍ ያቺ በኢትዮጵያ አምሳል ያሰባት፡- ‹‹አንድ ታዝማኒያ፣ አንድ ሕዝብ›› የምትል የህልም የነጻነት ደሴቱ ነበረች፡፡ እስካሁንም ተጠብቃ አለች፡፡ በብዙዎች ትጎበኛለች፡፡ ከዚያም አልፎ ኔልሰን ማንዴላ ስለ አድዋ ሲመሰክሩ ለመላው አፍሪካውያንና የዓለም ቅኝ ተገዢ ህዝቦች በነጻነት መኖር እንደሚቻል ተዓምሩን ያሳየ ድል ነው የሚሉት፡፡ የእምነት ተጓዦች ወደ ኢየሩሳሌም ወይ ወደ መካ እንደሚሄዱት ነው የሆነችው ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ከእምዬ ምኒልክ የአድዋ አንጸባራቂ ተዓምራዊ ድል በኋላ፡፡ ማንዴላም ወደዚህችው ነጻዋ የነጻነት ደሴቱ ኢትዮጵያ ነበር የነጻነትን መንፈስ ለመላበስ የመጣው፡፡
በጋና ብንሄድ የምናገኘው ደግሞ የጋናውን ቀዳሚ ምሁር ጄ. ኢ. ኬስሊ ነው፡፡ ኬስሊ ምኒልክን የመሰላቸው ልክ እንደ በግሪክ አፈታሪክ ለሰው ልጆች ነጻነትን በልባቸው ለማምጣት ሲል – አማልክቱን ክዶ – እና ከአማልክቱ ጋር ብርቱ ፍልሚያ አድርጎ – የሰው ልጆችን ከእንስሳት ከፍ እንዳደረጋቸው የግሪኮች ምናባዊ ጀግና እንደ ፕሮሜቲየስ ነው፡፡ ፔርሲ ቢሽ ሼሊ በ1820 የጻፈችው እና አብዛኛው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ዓለም ያነበበው ‹‹Prometheus Unbound›› የተሰኘ የፕሮሜቲየስን ለሰው ልጅ ውለታና፣ ያን በማድረጉ በመጨረሻ ነጻ እስኪወጣ በአማልክቱ እጅ የተቀበላቸውን ስቃዮች የሚያሳይ መጽሐፍ ነው፡፡
እና የጋናው ጄ ኬስሊ የአድዋውን ጀግና ምኒልክንና ኢትዮጵያን ልክ እንደ ፕሮሜቲየስ ለአፍሪካውያንና ለመላው በባርነት ሥር ላሉ የሰው ልጆች የነጻነትን ጮራ በልቡ ውስጥ የፈነጠቁ የዘለዓለም ባለውለታዎቻችን ሲል ይገልጻቸዋል ‹‹Ethiopia Unbound›› በተሰኘውና መታሰቢያነቱን ‹‹በዓለም ሁሉ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ልጆች ይሁንልኝ›› በማለት ባሳተመው – በዓለም እንደ ብርቅና እንደ ጉድ በተነበበ ታዋቂ መጽሐፉ፡፡
ብናወራው፣ ብንዘረዝረው፣ ብንዘክረው ብንከርም አያልቅም የምኒልክ ተዓምር፡፡ በምን ያለ ተዓምር ከዚህ ሁሉ ከከበቧቸው አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች – ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ማትረፍ እንደቻሉ – የሚያውቁት እራሳቸው ተዓምረኛው እምዬ ምኒልክ ብቻ ናቸው፡፡ እና የእርሳቸውን ተዓምር ዘልቀን ለመረዳት ለፈቀድን፣ ታሪካችንን ለማክበርና ለመረዳት ለፈቀድን፣ ለእኛ የኢትዮጵያ ልጆች የተሰጠ ነጻነትንና ጥበቡን የመረዳት ውርስ ነው ይሄ!!
የምኒልክን እኛን ህዝቦቻቸውን ከባርነት የማዳን ተዓምር ጽፌ ጽፌ አልጨርሰውም፡፡ ተገድጄ ማብቃት ብቻ ነው የምችለው፡፡ እና ተገድጄ ላብቃ፡፡ የበዛ ክብር ለእምዬ ምኒልክና ኢትዮጵያን ብለው ለተዋደቁ የአድዋ አርበኞች ጀግኖች አያት ቅድመ አያቶቻችን ይሁንልን፡፡ ኢትዮጵያን ከከበቧት ጅቦች የሚጠብቅ አምላካችን ለዘለዓለሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በነጻነት ትኑር!
Filed in: Amharic