>

የእኛ የሰማያዊ አምባሻ ፎቢያ፣ እና የኢህአዴግ የንፁኅ ባንዲራ ፎቢያ - ምንና ምን...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የእኛ የሰማያዊ አምባሻ ፎቢያ፣ እና የኢህአዴግ የንፁኅ ባንዲራ ፎቢያ – ምንና ምን…!!!

አሰፋ ሀይሉ

ልጅ ሆኜ ነው፡፡ አዲሳባ ልደታ ሰፈር፡፡ 1980 ዓመተ ምህረት፡፡ ክረምት ላይ፡፡ ጥሎብኝ የማልወደውን ነገር ጎረቤታችን አቡሽ ከሳማው ላይ በባህርዛፍ ቅጠል አንስቶ፣ በቲሸርቴ ውስጥ አስርጎ፣ ጀርባዬ ላይ ጨመረብኝ፡፡ የሚዝለገለግ የቀንድ አውጣ፡፡ እጅግ የምጠላው ነገር ነው ብዬአለሁ፡፡ በጣም ከመረበሼ በቀር፣ ምን እንደተሰማኝ አላውቀውም፡፡ ግን ለ2 ሣምንት ያህል የጀርባዬ ቆዳ እንደ አለርጂክ ተንደብድቦ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል መወሰድ ነበረብኝ፡፡ በስንት መከራ ዳነልኝ፡፡ ሳስበው እንደ ቀንድ አውጣ አጥንት አልባና ሰስ ፍጡር አይገኝም፡፡ ግን እንዲህ ሰውነትህን አስቆጥቶ ተገኘ፡፡ የስነልቦና ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ሳይንሱ ‹‹ፎቢያ›› ይለዋል፡፡ ገና ስታስበው ሰውነትህን፣ አዕምሮህን፣ ሁለመናህን የሚኮሰኩስብህ ነገር፡፡ ፎቢያ የሚባለው ያ ነው፡፡ በልጅነቴ አንድ ፎቢያ ነበረኝ፡፡ እሱም ቀንድ አውጣ ነው፡፡
አሁን ያን ቀንድ አውጣ ለምን አስታውሰዋለሁ? ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ቀንድ አውጣውን የማስታውሰው የልጅነት ፎቢያዬ ስለነበረ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ የልጅነት ፎቢያዬ ቀጥሎ የገጠመኝ ሌላ የህይወት ዘመን ፎቢያዬንም ስለሚያስታውሰኝ ነው፡፡ ከቀንድ አውጣው ቀጥሎ የገጠመኝ ፎቢያስ ምንድነው? ባንዲራው ላይ የተሰነቀረው የወያኔ አምባሻ፡፡ የወያኔ-ኢህአዴግ የሠይጣን ኮከብ፡፡ ያ ነው ሁለተኛው የዕድሜ-ዘመን ፎቢያዬ፡፡
ወያኔ-ኢህአዴግ 1983 ላይ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የተጋደሉትን የኢትዮጵያችንን ጀግኖችና አባት አርበኞች ጭምር ቀብሮ – ከሻዕቢያ ጋር የኢትዮጵያን ግዛተ መንግሥት ሥልጣን ሲቆጣጠር ለኢትዮጵያ ባንዲራ ያደረበትን ንቀትና ጥላቻ በመሪዎቹ አንደበት ጭምር ነበር ይገልጽ የነበረው፡፡ መለስ ዜናዊ በ1984 ላይ ባንዲራውን እንዲህ ነበር ያለው፡-
‹‹ይሄ ባንዲራ ደርግ እያውለበለበ ወገኖቻችንን በሃውዜን  በግፍ የጨፈጨፈበት ባንዲራ ነው፣ ይሄ ባንዲራ ንጉሡ  ለውሾቻቸው ከእንግሊዝ ምግብ እያስመጡ እያበሉ
ህዝባችንን ያስራቡበት ባንዲራ ነው፣ ይሄ ባንዲራ ታጋይ ጓዶቻችንን የነጠቀን የደርግ ባንዲራ ነው፣ ይሄ ባንዲራ ለእኛ ጨርቅ ነው፣ እና የክፉ አገዛዝ ምልክት ነው፣
በትግል ላይ እያለን በአህያ ላይ የምንጭነውን ጨውና ስንቅ ነበር የምንቋጥርበት፣ ይሄ ባንዲራ ለእኛ ምንም የተለየ ትርጉም የለውም!›
የወቅቱ ባለጊዜ መለስ ዜናዊና ግብረአበሮቹ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት ባንዲራ እንዲያ ሲያረክሱና ሲያዋርዱ – ብዙ ኢትዮጵያውያን ተቃውመዋል፡፡ ብዙ የዕድሜና የልምድ ባለፀጋዎችም ወደ ወያኔ ጎንበስ ብለው መክረዋል፡፡ ወያኔ-ኢህአዴግ ራሱ ባዘጋጃቸው ድራማዊ የህገመንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ተብዬ ስብሰባዎች መሐል ራሱ ስለ ባንዲራችን ክብር ለወያኔ በልበሙሉነት የመሰከሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በቪዲዮ ሳይቀር ታሪካዊ ቃላቸው ተመዝግቦ ይገኛል ለታሪክ፡፡ እና ወያኔዎች እንደ ሻዕቢያ አዲስ ባንዲራ ሊሰቅሉ የተመኙትን ያህል፣ ነገና ከነገ ወዲያ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከወደቀበት አንስቶ ሕዝብን ከጎኑ የሚያሰልፍባቸው ትውልድ እንደሚፈጠር ስለተረዱ፣ ሳይወዱ በግዳቸው የሚጠሉትን ባንዲራ ለመቀበል ተገደዱ፡፡
በዓለም ታሪክ ፎቢያ የሆነበትን ባንዲራ እያውለበለበ የገዛ ብቸኛ ገዢ ወያኔ-ኢህአዴግ ይመስለኛል፡፡ ቅኝ ገዢዎች እንኳ አንድን ሀገርና ህዝብ ሲቆጣጠሩ የህዝቡን ባንዲራ መሬት ጥለው የእነርሱን ሰቅለው ይገዙ ነበር እንጂ – በህዝቡ ባንዲራ ህዝቡን ለመግዛት የተገደደ ቅኝ ገዢ ከወያኔ-ኢህአዴግ በቀር ማንንም አላውቅም!!
ወያኔ-ኢህአዴጎች ያን ፎቢያ የሆነባቸውን ለዘመናት የኖረ የኢትዮጵያ ባንዲራ ለመቀበል ሲገደዱ ግን ዝም ብለው አልነበረም፡፡ ለባንዲራው ያላቸውን ንቀትና ጥላቻ የሚያሳይ አንድ ነገር አደርገው ነው፡፡ ያም የድፍረትና የንቀት አምባሻቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት አክብሮት በኖረው ንጹሁ የኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ መደንቀር ነበር፡፡ ያን ያደረጉት ለሌላ ለምንም ዓላማ ሳይሆን ለዘመናት በደማችን ተከብራ የኖረችውን አንዲት የኢትዮጵያን ንፅህት ታሪካዊ ባንዲራችንን ለማርከስ ነው፡፡ ያ መሐሉ ላይ ጉብ ያለው የጥላቻ አምባሻ ነው የልጅነት የቀንድ አውጣ ፎቢያዬን ያስታወሰኝ፡፡ ለኢህአዴጋውያኑ ንፅሂት የኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራችን ፎቢያቸውን ትቀሰቅስባቸዋለች፡፡ ንፁኋን ባንዲራ ሲያዩዋት ይታመማሉ፡፡
የባንዲራችንን ክብር ለማጉደፍ በወያኔ ፀረ-ታሪኮች መሐሉ ላይ በድፍረት ስለተሰነቀረው ቀንዳውጣ ስለሚመስለኝ ሰማያዊ አምባሻ በተመለከተ – እንደ ብዙው አሁን ወያኔ ሲወድቅ ተረኛውን ከቦ እንደሚያጫፍረው ሰው ሳይሆን – ወያኔ በሙሉ ሥልጣኗ ላይ እያለች ከ7 ዓመት በፊት በፌስቡክ ገጼ ‹‹በባንዲራውና በብራችን ላይ የተገጠገጠው ሰማያዊው ኮከብ የባፎሜት የሰይጣን ኮከብ›› መሆኑን በመግለጽ በአደባባይ ጽፌ ነበር፡፡ በምሠራበት ቦታ ሳይቀር ብዙ ቁጣን ቀስቅሶብኛል፡፡ ጉዳዬ አልነበረም፡፡ በዚያም ብቻ ሳላቆም ከዚያም ወዲህ ደጋግሜ የኮከቡን እውነተኛ ምንነት ከምስሎች ጋር እያስደገፍኩ አቅርቤያለሁ፡፡ እውነቱ ያ ስለሆነ፡፡ አሁንም ወደፊትም፡፡
በጣም የሚገርመው ያንን በጥላቻ የተገመደ ያደባባይ ሸፍጥ ለመሸፋፈን ሲባል፣ የተደረተውን የአምባሻውን ቅዱስ ተምሳሌትነት የሚያስዳ የቃላት ጋጋታ ማየት ነው፡፡ አሌክሳንደር ፖፕ የተባለውን ዘመን አይሽሬ ገጣሚ ስንኞች ያስታውሰኛል፡-
‹‹The Devil cites a scripture for his purpose
An evil soul producing a Holy witness.››
(‹‹ዲያብሎስም ለዓላማው ቅዱስ መጽሐፍን ያጣቅሳል እርኩስ ነፍስ ቅዱስን ምስክር ያቀርባል፡፡››)
ለክፋት፣ ለንቀትና ለድፍረት ዓላማው ሲል ይሄን የሰይጣን ኮከብ ለገንዘብና ለስም የቋመጡ አርቲስቶችን አወዳድሮ በባንዲራችን ላይ የሰነቀረውን ወያኔ-ኢህአዴግ ሳስብ የሚመጣብኝ ይህ ለዘመናት የኖረ የአሌክሳንደር ፖፕ ግጥም ነው፡፡ ወያኔ-ኢህአዴግ ንጹህ ባንዲራችን ላይ በጥላቻ ብዛትና ለእኩይ ዓላማው የሰነቀረውን ሰማያዊውን አምባሻ በተመለከተ በህገመንግሥት ተብዬው፣ እና በባንዲራ አዋጁ ላይ የደረደራቸውን የተቀደሱ የአምባሻውን ትርጉሞች ለማንበብ ዕድሉን ያገኘ ሰው መቼም በወያኔ ብጽዕና መደነቁ አይቀርም፡፡ አሁንም አምባሻው የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተገለጸበት የሰማይ ምልክታችን ነው የሚሉ ኢህአዴጋውያን ያንኑ ወያኔ የጻፈላቸውን ውዳሴ አምባሻ እያነበነቡ ጨፍኑ ላሞኛችሁ ሲሉን ስመለከት – እኔ ለእነርሱ አፍራለሁ፡፡ ሰው እንዴት በጊዜ ሂደት ከድንዛዜው አይነቃም? ጤነኛ ሰው እንዴት 100 ሚሊየን ህዝብን ሁልጊዜ ጨፍኖ ለማሞኘት ይከጅላል? በምን ዓይነት ደናቁርት ነው የምንመራው?
በንጹኋ የኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ እጆቼን ጭኜ ቃልኪዳን የፈጸምኩ የታላቋ ኢትዮጵያ ልጅ ነኝ፡፡ ንጹኋን ያልተበተዘች ያልተከለሰች ያላደፈች የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ አድርጌ በክብር እየሰቀልኩ፣ ዝቅ አድርጌ በክብር አጣጥፌ እየተቀበልኩ ያደግኩ የሀገር ፍቅር እንደ እሳት በልቡ የሚነድ ትውልድ አካል ነኝ፡፡ ያ አስተዳደጌ፣ እና ያ ማንነቴ እጅግ ያኮራኛል፡፡ ከሁሉም በላይ እጅግ የሚያኮራኝ ግን በስህተት እንኳ – በስህተት ይሄን የሰይጣን አምባሻ የተጋገረበትን ባንዲራ በህይወቴ ሙሉ ለአንድ ሰከንድ እንኳ በእጄ ነክቼው አለማወቄ ነው፡፡ ይሄን ንፅህናዬን ከልቤ እወደዋለሁ፡፡
ምክንያቴ ግልጽ ነው፡፡ ይሄ የወያኔ-ኢህአዴግ የጥላቻ አምባሻ የተጋገረበት ባንዲራ የእኔ ባንዲራ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ባንዲራም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው ብዬ ለሰከንድ ሚሊዮንኛ ሽራፊ ተቀብዬው አላውቅም፡፡ አንድ ቀን ይሄን የወያኔ-ኢህአዴግ አምባሻ በድፍረት ከሰቀሉበት ባንዲራችን ላይ መንቀረን አውጥተን የሚወዱት እንዲበሉት እንደምናሻማቸው እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የታገሱት የኢትዮጵያ ልጆች፣ አንበሶቹ ትውልዶች ሲነሱ፣ ያ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንዲህ እያልን እንዘምርላት ነበር ለንጽሒቱ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንራችን፡፡ ወደፊትም ከፍ አድርገን እንዲሁ እንዘምርላታለን፡፡
«ባንዲራችን የነጻነት
 አርማችን ነሽ የአንድነት
ተውለብለቢ አለኝታችን
ለዘልዓለም ኑሪልን ባንዲራችን
ባንዲራችን ኑሪ
በጀግኖችሽ ተከበሪ
ቃል ገብተናል ልጆችሽ
መስዋዕት ልንሆንልሽ
ለዘላለም አለንልሽ አለንልሽ!»
ታሪኬን የምቋጨው ከዚህ ጽሑፍ ጋር ስላኖርኩት ፎቶ ጥቂት ብዬ ነው፡፡ ፎቶው በ1999 ዓም ላይ (በጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር 2007 ላይ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሶማሊያ ሞቃዲሾ ግዳጁን ጨርሶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ በተደረገለት የሽኝት ስነሥርዓት ላይ የተነሳው የመታሰቢያ ፎቶ ነው፡፡ በወቅቱ የፈረንሣዩ የዜና ወኪል (አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ – ኤኤፍፒ) ከሞቃዲሾ በሽኝቱ ላይ ተገኝቶ ይህን ፎቶ በማንሳት ዜናውን ለዓለም ለቀቀው፡፡ የተለያዩ የዓለም ዜና ማሰራጫዎችም ምስሉን ተቀባብለው በአየር ላይ አናኙት፡፡ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም (የተቃዋሚ ሚዲያዎችን ጨምሮ) በዚህ ፎቶ ላይ የመከላከያ ሠራዊታችን ከፍ አድርጎ ያውለበለባትን እውነተኛዋን ንጹህ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ወደው ፎቶውን አዳረሱት፡፡ የወያኔ ሽማግሌዎች ዓይናቸው ቀላ፡፡ እና የወያኔ-ኢህአዴግ መንግሥት የፕሮፓጋንዳ ማሽን በአንዲት ባንዲራ መውለብለብ ከባድ ድንጋጤ ላይ ወደቀ፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ በሙሉ ይሄንን የሞቃዲሾ ጀግኖች ያሳዩትን አርዓያ ቢከተል በወያኔ በህገመንግሥት በተደገፈችው የአምባሻዋ ትርክት ላይ የሚደርሰውን መኮላሸት ማሰብ አያዳግትም፡፡ በጊዜው የዚህችን ባንዲራ ምስል ከዓለም ዓይኖች ላይ ለመቀልበስ – ወያኔ-ኢህአዴግ በድጋሚ በሌላ ሚሽን ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ ሠራዊቶችን አካልቦ ባለ አምባሻውን ባንዲራ አስይዞ ደግሞ ደጋግሞ በተቆጣጠራቸው ችኮ ሚዲያዎች እየለቀቀ ሲያደርቀን ሰነበተ፡፡ እና ሽኝቱ ስነሥርዓት ላይ በእጃችን ባንዲራ ስላልነበረን እዚያው ያገኘነውን ባንዲራ ነው ያውለበለብነው የሚል ማስተባበያ ሁሉ ከሠራዊቱ አባላት አፍ እስከማስነገር ደረሰ፡፡
ወያኔ የሠይጣኑ ሉሲፈር ዓለምን እወርሳለሁ ብሎ የሚፎክርበት ምልክት፣ ሠይጣኑ ባፎሜት በግንባሩ ላይ ተነቅሶት በትልልቅ የጥበብ አምዶች ላይ የምናየው፣ ይሄንን የሰይጣን ኮከብ፣ ይሄንን ሰማያዊ የወያኔ አምባሻ – የኢትዮጵያን ታሪክ ለማንቋሸሽ ከመጠቀም አልፈው – ማምለክ ጀምረዋል ኢህአዴጋውያኑ፡፡ ያ ኮከብ ከባንዲራችን ላይ ሲርቅ ሥርዓቱ አምልኳቸው ይስተጓጎልባቸዋል፡፡ እና የሚይዙትን የሚጨብጡትን ያጣሉ፡፡ ከትናንት ወዲያ የአድዋ በዓልን ሊያከብሩ የመጡ የ5 እና የ6 ዓመት ህጻናትን ሳይቀር ከግንባራቸው ላይ የጠመጠሙትን ንጹሁን የኢትዮጵያ ባንዲራ ሲያስፈቱ ነበር የአብይ አህመድ ወታደሮች፡፡ የሰይጣን ልክፍት ከያዘ አይለቅም!
የሚገርመው ያ የወያኔ አምባሻ ለዓመታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ አንድነቷን፣ ዳር ድንበሯን አላስደፍርም ብሎ ለእናት ሀገሩ የተዋጋውንና አምርረው የሚጠሉትን እውነተኛ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያን የዘመናት ታሪክና፣ የጀግንነት ተጋድሏችንን  ለማንኳሰስ ከማዋል አልፈው፣ በሠይጣን ቅርፅ ያሰሩትን ኮከብ ማምለካቸው ብቻ አይደለም፡፡ እጅግ የሚገርመን ያንን የባንዲራውን አምባሻ እንደ ታማኝነት ቃልኪዳንም ሲጠቀሙበት ስናይ ነው፡፡
የወያኔ አምባሻ በኢህአዴግ ቤት በተለከፉ ሰዎች ሁሉ ዘንድ እንደ ታማኝነት ቁርባን የሚቆጠር ‹‹ወገን ነን›› የማለቻ ቋንቋቸው ነው፡፡ ወገንና ጠላትን የሚለዩበት ነው፡፡ ባለፈው ላፍቶ ላይ አንድ ከወያኔ ካምፕ ተጎራብቶ የሚኖር – ግን ከወያኔ-ኢህአዴግ ንክኪ ነጻ መሆኑን የማውቀው – በላቡ-አደር ወዳጄ፣ ግሮሰሪው በር ላይ ባለ አምባሻውን ባንዲራ በትልቁ ሰቅሎ አገኘሁት፡፡ እና ልገባ የነበርኩት ሰውዬ ፎቢያዬ ተቀሰቀሰና ኮሰኮሰኝ፡፡ አምባሻው ስለዘጋኝ ሃሳቤን ቀይሬ የምገዛውን ነገር በቴክ-ኧዌይ አስጠቅልዬ ወደቤቴ ልወስድ ተነሳሁ፡፡ ከባለቤቱ ላይ እየተቀበልኩት እንደ ዘበት አንድ ጥያቄ ግን ወርወር አደረግኩለት፡- ‹‹ይሄ ባንዲራ ደሞ ምንድነው? ምን ያደርጋል እዚህ?›› አልኩት በጣቴ ወደ ውጪው በረንዳ እያመለከትኩት፡፡ ቀና ብሎም አላየውም፡፡ ሳይገረም በሳቅ እየደከመ እንዲህ አለኝ፡-
‹‹ሰሞኑን እኮ ግርግር ነው፣ አልሰማሽም እንዴ፣ ክፈት ዝጋ እያሉ መከራዬን ሲያበሉኝ፣ ለመብረቅ መከላከያ ብዬ አምባሻውን ሰቀልኩላቸው፣ ይኸው እርግፍ አርገው ከተዉኝ ሶስተኛ ቀኔ! ምን አጨቃጨቀኝ ሥራዬን ሠርቼ ባድርስ?አይሻልም?… በነገራችን ላይ፣ በፊት በሩ ላይ ተሰቅሎ የነበውን ባንዲራም እኮ እኔ አልነበርኩም የሰቀልኩት፣ የሰፈሩ ልጆች ናቸው…!››
አብሬው ፈገግ ብዬ፣ እየገረመኝ ያስጠቀለልኩትን ይዤ ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡ ከዚህ ባለ አምባሻውን ባንዲራ እንዲሰቅል ከተገደደው ወዳጄ ምላሽ ግን እስካሁንም ያልረሳኋት አንዲት ቃል አለች፡፡ ያቺን ‹‹ለመብረቅ መከላከያ ብዬ…›› የምትለውን አባባሉን፡፡ ብዙው ሰው – በተለይ አዲሳባ ውስጥ – ከወያኔ-ኢህአዴግ ጋር የተነካካውም ያልተነካካውም ሰው – በግሉ ስትጠይቀው የወያኔ ሰማያዊ አምባሻ – ከእኔም ከራሴ በላይ – ለማየት ራሱ የሚያቅለሸልሸው ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ ግን በየሱቁና በየቢሮው ሰቅሎት ታገኘዋለህ፡፡ ለምን? ምክንያቱም ሥርዓቱ አዞ ነው፡፡ የሥርዓቱ ወገን መሆንህን ካላሳወቅክ አዞው ቀልድ አያውቅም፡፡ ወገኔ ነህ፣ አሊያ ግን ጠላቴ ነህ ነው መመሪያው፡፡ የሚያውቀው ቋንቋ ሁለቱን ብቻ ነው፡፡ ሌላ መንገድ የለም፡፡ ወይ ጠላቱ ነህ፡፡ ቀረጣጥፎ የሚበላህ፡፡ ወይ ወገኑ ነህ፡፡ አብረኸው የምትኖር፡፡ ከዚህ ውጪ ምርጫ የለም፡፡
እና ብዙው ሰው አዞው ኢህአዴግ ላለመበላት፣ በወያኔው የአምባሻ መብረቅ ላለመመታት ሲል አምባሻውን ያውለበልባል፡፡  የወያኔ-ኢህአዴግን ህገመንግሥት እንደ ግል አዳኝህ አድርገህ የተቀበልክ መሆንህ የሚረጋገጠው በያዝከው የባንዲራ አይነት ነው፡፡ በኢህአዴጋውያኑ የዓለም አተያይ ህገመንግሥቱን ለመናድ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በቀር አምባሻው ያልተጋገረበትን ንጹሁን የኢትዮጵያ ባንዲራ ይዞ የሚገኝ ማንም የለም! አንዳንዶች ከአዞው ፍራቻ ብዛት በመኝታ ቤታቸው ራሱ ይሰቅሉታል፡፡ አምባሻውን፡፡ ይሄን ሰላቢ መንግሥት በመኝታ ቤትህ ውስጥስ ራሱ ላለማግኘትህ ምን መተማመኛ አለ? ይመስላል የሰዉ ነገር፡፡ ወያኔ-ኢህአዴግን አታምነውም፡፡ እንዴት ብሎ እንደሚመጣብህ አታውቀውም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ አምባሻውን እያውለበለበ፣ አምባሻውን ሲጋግር ይውላል፡፡ ያለው የኑሮ አማራጭ ነው፡፡ እውነታው ይህ ነው፡፡
አንዴ የማልረሳው ከጥቂት ዓመታት በፊት በፌስቡክ ገጼ ላይ የኢትዮጵያ ንጹህ ባንዲራ መሐል ላይ ፎቶዬን ሚክስ አድርጌበት የፌስቡክ ፕሮፋይል ፒክቸር አደረግኩ፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት አንድ መቀሌ ከከተመ የድሮ ኢህአዴጋዊ ወዳጄ አንድ ጥያቄ መጣልኝ፡፡ ለማሳጣት ይሁን ለመፈተን አልገባኝም፡፡ እንዲህ አለኝ፡- ‹‹አሳፍ ኮከቡስ የታለ? የት አድርገኸው ነው?››፡፡ ገረመኝ በጣም፡፡ እና ምናልባትም ጥቂት ንዴት ጎበኘኝ፡፡ እና እንዲህ ብዬ መለስኩለት፡- ‹‹ወዳጄ! ይሄ የእኔ የፌስቡክ ሾው ነው፣ ኮከቡ ደግሞ እኔ ነኝ!›› ብዬ፡፡ ክፉም በጎም ሳይል አለፈኝ፡፡ እያሰብኩት ይገርመኝ ነበር፡፡ ከሱቆችና ከቢሮዎች ደጃፍ አልፈው – የህገመንግሥቱ ታማኞች – በፌስቡክ ላይ ሁሉ የአምባሻውን መውለብለብና አለመውለብለብ ለመቆጣጠር መፈለጋቸው፡፡ ጤነኝነት አይመስለኝም፡፡ ልክፍት ነው፡፡ የሠይጣን ሥራም ነው፡፡ እንዲህ ነው ማለት ነው የሚያደርገው? እላለሁ – ንፁሁን ባንዲራችንን ሲያዩ የሚያክለፈልፋቸውን ነገር እያየሁ፡፡
አንድ ቀን – አንድ ቀን ግን – የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ከሸበበው የፍርሃት ቆፈን ወጥቶ – በነጸነት መንፈስ ተሞልቶ – ፊት ለፊት በአደባባይ ንጹሁን፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን ለነጻነታችንና ለአንድነታችን የተጋደሉበትን፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዪን ባንዲራችንን በኩራትና በነጻነት ይዞ – አምባሻውን ለወያኔ-ኢህአዴጋውያኑ አዞዎች ሻሞ ብሎ እንደሚወረውርላቸው አልጠራጠርም!
የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻም አይደለም፡፡ ከ1983 ጀምሮ እስከዛሬዋም ዕለት ድረስ – ወገንተኝነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን እስኪዘነጋ ድረስ – ከላይ ታች በካድሬ ሰንሰለት ታስሮ፣ አፍንጫውን ተሰንጎ የተያዘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት – አንድ ቀን – ራሱን ከወያኔ-ኢህአዴግ የሥልጣን አስጠባቂ ቅጥረኛ ካድሬዎች መዳፍ ነጻ አውጥቶ – አምባሻውን ለካድሬዎቹ ሰጥቶ – እንዲህ በሶማሊያ ሞቃዲሾ ግዳጁን ከሚገባው በላይ እንደተወጣው የመከላከያ ሠራዊት – እውነተኛዋን የኢትዮጵያ ባንዲራ በክብር ከፍ አድርጎ የሚያውለበልብበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
የእኛ ነገር እንዲህ ሆኖ መቅረቱ ያስቆጫል፡፡ ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ ‹‹ሀገሬ እውር ናት፣ ማየት የናፈቃት፤ አለሁልሽ ብሎ፣ ዓይን እየዳበሰ፣ ዓይኗን የሚሰርቃት›› ነው ያለችው መሰለኝ በአንድ ግጥሟ፡፡ የአሁኖቹ ከቀድሞዎቹ ቢብሱ እንጂ አያንሱም፡፡ በምኒልክ ኃውልት ፊት፣ ነጻነታችንን በተቀዳጀንበት አምድ ሥር፣ ግራዚያኒ አፍርሶት መልሰን በገነባነው የምኒልክ ሀውልት ሥር – ከህጻናት ላይ ሳይቀር ወራሪውን ጣሊያንን ድል ስናደርግ ያውለበለብናትን ንጹኋን ባንዲራችንን ሲያዩ ደማቸው በሚፈላ የወያኔ-ኢህአዴግ ቀማኛዎች ሥር መኖር ምርር የሚለን ቀን እንደሚመጣ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ አንድ ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ – ልክ እንደ አቡነ ጴጥሮስ – እውነተኛ ጀግኖቹን፣ እውነተኛ ሀገሩን፣ እና እውነተኛ ባንዲራውን ይዞ ለሀቅ በሀቅ እንደሚነሳ አልጠራጠርም፡፡ በዚያን ቀን የእኛ የምንለው መከላከያ ሠራዊትም በኢትዮጵያ የዘመናት ተጋድሎ ውጤት በሆነው በንጹሁ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራችን አጊጦ እናያለን፡፡ የሚል ጽኑ ተስፋ አለኝ፡፡ ይህ በቅርቡ እውን ሆኖ እንደማይ ጽኑ ምኞቴ ነው፡፡
ፈጣሪ ንፁሁን ትውልዳችንን፣ ንፁኋን ባንዲራችንን፣ ንፅሂት እናት ሀገራችንን ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክልን፡፡ አይምሬው ይሉኝታ ቢሱ አዞ በላያችን የነዛብንን የፍርሃትና የጥርጣሬ ቆፈን ከላያችን አውልቆ ይጣልልን! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በነጻነት በፍቅር ትኑር!
Filed in: Amharic