>
5:13 pm - Sunday April 18, 6258

ኬርያ ኢብራሒምን ከእስር እየፈቱ የወንጀል ባልደረቦቿን  እነ ጌታቸው ረዳን፣ ጌታቸው አሰፋንና ደ/ጺዮን ገ/ሚካሄልን ለምን ይፈልጓቸዋል?  (አቻምየለህ ታምሩ)

ኬርያ ኢብራሒምን ከእስር እየፈቱ የወንጀል ባልደረቦቿን  እነ ጌታቸው ረዳን፣ ጌታቸው አሰፋንና ደ/ጺዮን ገ/ሚካሄልን ለምን ይፈልጓቸዋል? 
አቻምየለህ ታምሩ

በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሕወሓት ማዕካላዊ ኮሚቴ፣ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚና ምክር ቤቱ በወሰነው መሰረት የተካሄደ ጥቃት እንደነበር አገዛዙ እስካሁን ሲነግረን የቆዬው ብቻ ሳይሆን  በሕወሓት ሰዎች ላይ እየተካሄደ ያለውን ምርመራ እያካሄደው ያለው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግሥቴም አረጋግጦልን ነበር።
ምን ይኼ ብቻ! በማይካድራ የተፈጸመው የንጹሐን የአማራ ተወላጆች ፍጅት፤ ጎንደር፣ ባሕር ዳር እና አስመራ ከተሞች ላይ የተደረገው የሮኬት ድብደባ፤ በቴሌኮሙኒከሽንና መብራት ኃይል ማሰራጫዎች ላይ የተፈጸሙት ጥቃት ሁሉ የተካሄዱት የሕወሓት ማዕካላዊ ኮሚቴ፣ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚና ምክር ቤቱ በወሰነው መሰረት ነው።
ይህ ከሆነ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም፣ በማይካድራ የንጹሐን የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ፍትጅ እንዲያሄድ፤  ጎንደር፣ ባሕርዳርና አስመራ ከተሞች በሮኬት እንዲደበደቡ፤ በቴሌኮሙኒከሽንና መብራት ኃይል ማሰራጫዎች እንዲወድሙ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነችው ኬርያ ኢብራሒምም ልክ እንደ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ጌታቸው ረዳ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ወዘተ አብራ ወስናለች ማለት ነው።
ይህ ማለት እንደ አንድ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሥራ አስፈጻሚ አባልነቷ ኬርያ ኢብራሒም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም፣ በማይካድራ የንጹሐን የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ፍትጅ እንዲያሄድ፤  ጎንደር፣ ባሕርዳርና አስመራ ከተሞች በሮኬት እንዲደበደቡ፤ በቴሌኮሙኒከሽንና መብራት ኃይል ማሰራጫዎች እንዲወድሙ በወሰነችው ውሳኔ ልክ እንደ ጌታቸው አሰፋ፣ እንደ ደብረ ጺዮን ገብረ ሚካኤል፣ ጌታቸው ረዳ፣ ወዘተ ሁሉ ከነሱ እኩል ተጠያቂ ናት ማለት ነው።
ዛሬ እንደሰማነው ግን የዚያ ሁሉ ድርብርብ ወንጀል ፈጻሚ ኬርያ ኢብራሒም ከእስር ተለቃለች። ይህ ማለት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም፣ በማይካድራ የንጹሐን የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ፍትጅ እንዲያሄድ፤ ጎንደር፣ ባሕርዳርና አስመራ ከተሞች በሮኬት እንዲደበደቡ፤ በቴሌኮሙኒከሽንና መብራት ኃይል ማሰራጫዎች እንዲወድሙ ያደረገው ሕወሓት አይደለም ለማለት ነው? ያንን  ሁሉ ወንጀል የፈጸመው ሕወሓት ከሆነ ያ ሁሉ ወንጀል እንዲፈጸመ የወሰነው ድርጅት የማዕከላዊና የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነችው፤ አገዛዙ እስካሁን ሲነግረን እንደቆየው ያ ሁሉ ወንጀል የተፈጸመው የሕወሓት ማዕካላዊ ኮሚቴ፣ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚና ምክር ቤቱ በወሰነው መሰረት ከሆነ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ጥቃቱን አብራ ያዘዘቸው ኬርያ ኢብራሒም ከእስር ተለቅቃ እነ ጌታቸው ረዳ፣ ጌታቸው አሰፋና ደብረ ጺዮንን ለምን ይፋልጓቸዋል?
ወያኔ ደርግን የከሰሰው «የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ» በሚል ስም ደርግ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ባስነረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በአዋጁ ስም መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ያደራጀው መቺ ኃይል በተፈጸመ ግፍና ግድያ ነው። እንደሚታወቀው ደርግ የ120 አካባቢ የበታች መኮንኖች ኮሚተ ነው። መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ጊዜያዊ ወታደራዊ «መንግሥት» የሆነው ደርግ 120 የደርግና አባላትን ይዞ በደርግ ስም በመሰየም ነው። መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር 3 የሚሆኑ የደርጉ የዕቅድ ኮሚቴ አባላት [ሻለቃ ብርሀኑ ባይህ፣ ሻምባል ሲሳይ ኃብቴና  ሻምበል ሚካኤል ገብረ ንጉሥ]  መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ያወጡትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገጉት «የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አዋጅ» ብለው የ120ው የደርግ አባላት አዋጅ አድርገው ነበር። ይህንን ያወቀው ወያኔም በአዋጁ ምክንያት በተፈጸመ ወንጀል  በደርግ ላይ ክስ ሲመሰርት  ተጠያቂ ያደረገው መንግሥቱ ኃይለ ማርያምንና አዋጁን ያዘጋጁትን ሶስት ደርጎች  ብቻ ሳይሆን ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ብለው «መንግሥት» የሆኑትን 120ውን የደርግ አባላት ሁሉ በእኩል ወንጀል ነው።
መንግሥቱ ኃይለማርያምና ሶስቱ የደርግ መኮንኖች  በ120ዎቹ የደርግ አባላት ስም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ያወጡት  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ሕወሓት በሰሜን ዕዝና በማይካድራ የዘር ማጥፋት ለማካሄድና ጦርነት ለመክፈት በድርጅቱ አባላቶችና በፓርላማ እንዲጸድቅ ካደረገው የጦርነት አዋጅ ጋር አንድ አይነት ነው። መንግሥቱ ኃይለ ማርይም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ባወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አዋጁን ተከትሎ በተፈጸመው ግፍና ግድያ ተጠያቂ የሆነው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ብቻ ሳይሆን  አዋጁ በስማቸው የመጣው 120ዎቹም የደርግ አባላት ሁሉ ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም እኩል አዋጁ ተከትሎ በተካሄደው ግፍና ግድያ ተጠያቂ እንደተደረጉ ሁሉ ወያኔም በማይካድራና በሰሜን ዕዝ ጭፍጨፋ እንዲያደርግና ጦርነት እንዲከፍት የፈቀዱ የድርጅቱና የክልሉ የፓርላማ አባላት ሁሉ  ወያኔ  በፈጸመው ጭፍጨፋ፣ ግፍና ግድያ  ሁሉ ተጠያቂ የማይደረጉበት ምክንያት ያለም።
መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ሶስት የደርግ አባላት በደርግ ስም ባወጡት አዋጅ በተከተለው  ግድያና ግፍ የግድያና ግፍ ተሳታፊ ያልነበሩት የደርግ አባላት ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደረጉ ወያኔዎች ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም፣ በማይካድራ የንጹሐን የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ፍትጅ እንዲያሄድ፤  ጎንደር፣ ባሕርዳርና አስመራ ከተሞች በሮኬት እንዲደበደቡ፤ በቴሌኮሙኒከሽንና መብራት ኃይል ማሰራጫዎች እንዲወድሙ ሲወስኑናና ሕዝብ ለመጨፍጨፍና ጦርነት ሲያውጁ  በሚደርሰው ጥፋት እያንዳንዱ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የምክር ቤት አባላቱ፣ ወዘተ  በጭፍጨፋው፣  በግፉና ግድያው  ተጠያቂ እንደሚሆኑ ያውቃሉ። በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የምክር ቤት አባል፣ ወዘተ በማይካድራና በሰሜን ዕዝ በተካሄደው ጭፍጨፋ እጁን ያስገባው እያወቀ “ትግራይ የአሐዳውያን መቀበርያ እንጂ የአሐዳውያን መፈንጫ አይደለችም!” የሚል መፈክር እያሰማ ነው።
ባጭሩ እያንዳንዱ በሰሜን ዕዝ፣ በማይካድራ፣ ወዘተ በተካሄደው  ጭፍጨፋ እና የዘር ማጥፋት ተጠያቂው “ጁንታ” የሚሉት ብቻ ወያኔ ነጹሐንን ያለ ምህረት ለመጨፍጨፍ ያወጣው የግድያና የዘር ማጥፋት ጦርነት የደገፉ  እና “ትግራይ የአሀዳውያን መቀበርያ እንጂ የአሐዳውያን መፈንጫ አይደለችም!” እያሉ በወንጀል የሚጠየቅበትን መዝገብ የፈረሙት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮምቴ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የምክር ቤት አባላት፣ ወዘተ  በሙሉ ናቸው። ከተሸነፉ በኋላ እነሱ በሰጡት ድጋፍ በግፍ የወደቁ ሰማዕታት ፍትሕ እንዲያገኙ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ ሲባል «ሳላምንበት ነው ድጋፍ  የሰጠሁት» ፤ «ተገድጄ ነው የደገፍሁት» የሚለው የብልጣብልጦች ፖለቲካ  አይሰራም። ይህ ሰበብ ለ120ው የደርግ አባላትም አልሰራም። መንግሥቱና በቅርቡ በነበሩ ሶስት ደርጎች በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንኳን በሕይወት የነበሩቱ የሞቱት የደርግ አባላትም ከመከሰስ አልዳኑም። እያንዳንዱ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ሥራ አስፈጻሚ፣ የምክር ቤት አባል፣ ወዘተ. .  በወገኖቻችን ላይ የተካሄደውን ጭፍጨፋና ፍጅት ““ትግራይ የአሀዳውያን መቀበርያ እንጂ የአሀዳውያን መፈንጫ አይደለችም!” እያለ የደገፈው ወያኔ የሚሸነፍ ስላልመሰለውና በወንጀል ልጠየቅ አልችልም በሚል ትዕቢት ተወጥሮ ነው።
በመሆኑም በሰሜን ዕዝ፣  በማይካድራ፣ ወዘተ በተካሄደው ጭፍጨፋና ጦርነት በግፍ ክብረ ወሰን እንደተቀዳጀው ጁንታ ተብዮው ሁሉ የሕወሓት አባላት ሁሉ በንጹሐን ደም ተጨማልቀዋልና  እጃቸው የኋሊት በመጫኛ ታስሮ ለፍርድ  መቅረብ አለባቸው። እያንዳንዱ የደርግ አባል ያውም ባላጸደቀበት ሁኔታ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ግብረ በላዎቹ በደርግ ስም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ባወጡት አዋጅ ከነመንግሥቱ ኃይለ ማርያም እኩል ተጠያቂ ሆኖ ወያኔን በፓርላማ ግደል ብሎ እጅ በማውጣት የጦርነት አዋጅ  እንዲጸድቅ ርዳታ የሰጠ ማንኛውም የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባልና የሕወሓት አላባት በሙሉ ጁንታ ተብዮው ባካሄደው ጭፍጨፋ ተጠያቂ የማይሆንበት አንዳች አመክንዮ የለም።
የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የምክር ቤት አባል የሆነችው ኬርያ ኢብራሒም ሕወሓት በፈጸማቸው አለማቀፍ ወንጀሎች የለችበትም ተብሎ ከእስር የምትለቀው ከሆነ ግን  የወንጀል ባልደረቦቿ የሆኑትን እነ ጌታቸው ረዳን፣ ጌታቸው አሰፋንና ደ/ጺዮን ገ/ሚካሄል፣ ወዘተ … ከኬርያ ኢብራሒም የተለየ የሰሩት ነገር የለምና እንደ ኬርያ  ኢብራሒም ሁሉ ሊፈለጉ አይገባም!
Filed in: Amharic