>
5:26 pm - Saturday September 15, 0429

ይድረስ ለሀዋሪያ ዘላለም ጌታቸው (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

ይድረስ ለሀዋሪያ ዘላለም ጌታቸው

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ


በአንድ የመንፈሳዊ ፕሮግራም ላይ ሀዋሪያ ዘላለም ጌታቸው እንዲህ ሲል ሰማሁ፡ ‘’በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የሚያምን ሰው ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሆናል ብሎ ያሰበ አለ? ገና ስድባችን ሳይደርቅ  እግዚአብሄር ቤተ መንግስቱን ይዞታል እኮ፤ አንተ ያሳደግኸው ልጅ ወደ ዙፋኑ ሲመጣ ከተቃወምህ ፀረ ክርስቶስ ሰው ነህ’’ ሀዋርያ ዘላለም ከተናገረው የተወሰደ፡፡ 

ወዳጀ ልቤ፡ እግዚአብሄር  ቤተ መንግስቱን ቢይዘው ንሮ ምድራችን የዘር ፍጅት፤ የለቅሶና የእርግማን ማእከል ባልሆነች ነበር፡፡ ለጨፍጫፊው  ለጉምዝ፣ እና ለኦነግ ሸኔ ሽፋንና እገዛ መንግስት እንደሚሰጣቸው የተለያዩ መረጃዎች እያሳዩን እና  ከአራስ ጨቅላ እስከ ደካማ አረጋውያን ድረስ የሰው ልጅ በግፍ፣ በጭካኔ እንደ በግ እየታረደ የዕለት ዜና በሆነበት ሀገር መሪው ወንጌልን ያውቃል ብለህ ምስክርነት ስትሰጥ አየሁና በአንተ ሀዋርያነት አፈርሁ፡፡  

አብይ አህመድ በሚመራት ሀገር የአማራ ህዝብ በጅምላ ተጨፍጭፎ በግሪደር ሲቀበር፣ ሻሸመኔ፣ጅማ እና ዝዋይ ከተሞች በፅንፈኞች ሲነዱ እያየን፣ ነፍሰ – ጡር እናት ስትታረድ እያየን፣ ከአንድ ቤተሰብ ከአምስት ሰዎች በላይ በግፍ በማንነታቸው የጥቃት ሰለባ እየሆኑ እያየን፤ በማይካድራ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ በኮንሶ፣ በሰገን፣ በቡራዬ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቁማርና ሸፍጥ በሞላበት ፖለቲካችን ዜጎች ደመ-ከልብ ሁነው ቀርተዋል፡፡  በኢትዩጲያ ላይ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በተለይ ደግሞ ላለፉት ሶስት ዓመታት በታሪካችን ሰምተነው፣አይተነው የማናውቀው ዘግናኝ ታሪክ ነው እያሳለፍን ያለነው፡፡ ይህንን ማስቆም ያልቻለ መሪ አብይ አህመድ ክርስቲያን ነው ብትለኝ፤ አንተው ወንጌል አልገባህምና ወንጌል ዳግም ለአንተው ሊሰበክልህ ይገባል እልሀለሁ፡፡ 

ክርስቶስ አላዘርን እንደሚያስነሳው እያወቀ ወደ አላዘር መቃብር ሲጠጋ ክርስቶስ እንዳለቀሰ ወንጌል ያስተምረናል፡፡ ወንጌልን ያውቃሉ የምትላቸው መሪ ግን ይህ ሁሉ እልቂት ሲፈፀም ምንም ስሜት አልተሰማቸውም፡፡ በኃጥያት ምክንያት በመጣው ቋንቋ ተቧድነን ሳይጣንን በሚያስንቅ አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ ተዘፍቀን መሪ አጥተን እየባዘንን ባለንበት ጊዜ  እግዚአብሄር ቤተ መንግስቱን ይዞታል ማለት ቧልት ነው የሚሆነው፡፡  ይህ በእንዲህ እንዳለ ጆሮ-ዳባ-ልበስ ብለው የተቀመጡትን መሪ ክርስቶስን ያውቃሉ ካልህ አንተም ክርስቶስን ስለማወቅህ እጠራጠራለሁ፡፡

ለእኔ ክርስትና በህይወት የሚገለፅ፣ የሚነበነበ ሳይሆን ክርስቶስ በድርጊት እና ፍቅር በተሞላበት ህይወት የምናሳይበት የህይወት ሂደት ነው፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሰው ለእውነት ይቆማል፤ እውነት ክርስቶስ ነውና፤ ክርስቲያን የሆነ ዜጋ ዘረኝነትን አያራግብም፣አድሎዓዊነትን ይፀየፋል፣ አይሸነግልም፣ለሰው ልጅ ህይወት ክብር ይሰጣል፡፡ ክርስትና በልባችን ማህተም የምናምነው፤ በህይወት የምንተገብረው፣ ከስጋዊ ተፈጥሮ ማንነታችን በላይ በሰብዕና ታላቅነት እና በፍቅር የሚገለፅ፣ በጥበብና በሚዛናዊነት የተሞላ፣ በግብረ-ገብ ልዕልና የታሸ፣ ከሁሉም በላይ ለሰው ልጅ ህይወት ዋጋ የሚሰጥ በከፊል የተረዳነው  የህይወት መርህ ነው፡፡ 

ወንድሜ ዘላለም ጌታቸው ሆይ ፖለቲካ ንፁህ ሳይንስ መሆኑ ቀርቶ በባለጌ መዳፍ እጅ ገብቶ ቁማር ሁኖዓል፡፡ ስለዚህ ስለማታውቀው ቁማር አታውራ፣ ምስክርነትም አትስጥ፣ እውነተኛ የወንጌል ጥሪ አለብኝ ካለህ ወንጌልን ብቻ ስበክ፤ በማታውቀው ነገር እየገባህ ህዝቡን አታደነጋግር፡፡ ሀዋሪያ ነኝ ካልህ እንደ ሀዋርያነትህ የተሳሳተን ምዕመን ልትገስፅ ሲገባ ምዕመኑ በስህተቱ እንዲቀጥል/እንዲገፋበት ማድረግ አንተንም ያስጠይቅሀል እና ተጠንቀቅ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነትና ሰላም አዕምሮህን ይጎበኘው ዘንድ አመኝልሀለሁ፡፡

Filed in: Amharic