
የቋንቋ ነገር…!!!

(በእውቀቱ ስዩም)
ለአዲሳባ ከንቲባነት ልወዳደር ወይስ ለክቡር ገና ልተውለት? ምን ያንሰኛል? ሌላው ቢቀር ሁለት ቋንቋ እችላለሁ – የአራዳና የገጠር አማርኛ አቀላጥፌ እናገራለሁ፤
የዛሬ አመት ገደማ ይመስለኛል: በካፒታል ሆቴል ጀርባ ባለው አቋራጭ መንገድ ሳልፍ ሁለት ጎረምሶች ይተናነቃሉ፤ ገባሁና ገላገልኩ፤ ሳጣራ አንዱ በቅርቡ ከታክሲ ረዳትነት የተቀነሰ ከተሜ ሲሆን ሁለተኛው ከገጠር የመጣ መፅሀፍ አዙዋሪ ነው፤ ምን እንዳጣላቸው ጠየኳቸው ፤
ከተሜው:-” መፅሀፍ ልገዛው በሰላም ቀረብኩት ፤ ጀለስ ለካ የመጨረሻ ፋራ! በቅርቡ በኮንትሮባንድ የገባች እንደሆነ አላወቅሁም የሾዳየን መጣመም አለባበሴን ከልማ ሃንግ እምሰራት መሰላት፤ የሌለ ተከመረችብኝ! ጭራሽ እንደ ቴርሞሜትር ቤቢቶውስ ከቶ አልጨመቀኝም! በዚያ ላይ ፤ ጣራው የተነሳለት ቤተመፀሀፍት ተሸክሞ የሚውለው ክንዱ የሌለ ፌሮ ነው! የቤቢቶው ኬሚካል ሳይደፋኝ ደርሰህ ስለገላገልከኝ አመሰግናለሁ “
ወደ መፅሀፍ አዙዋሪው ዙሬ ” አንተስ ምን ትላለህ?”
-“አየ ጌታው! የመፀሀፍቱን ነዶ አውርጀ የጫማየን ሲባጎ ላጠባብቅ ጎንበስ ስል ይሄ ግንጭላም የግንጭላም ልጅ ተሁዋላየ መጥቶ ተዘበበ ! አልፎሃጅ ይሆናል ብየ ዝም አልኩት! አድብቶ ዳናውን እንደ መብራት አጥፍቶ ተጠጋኝ፤ ተጠጋኝና በጃኬቱ ኪስ ስር ባለ ብረት ጠቆም አድርጎኝ ! “ አባ ያለሽን ከቻሳ አድርጊው “ አለኝ፤ ውጥንቅጡ የወጣ አማርኛው ባይገባኝም ቀናለቀን ስዘርፍህ ተባበረኝ ማለት መሆኑን ግብኔ ነገረኝ ! ወይ አለመተዋወቅ ብየ በልቤ ስቄ ዝም አልሁ! “ አባው! ብቻየን እንዳልመስልሽ ለጀለሶች ምልክት ብሰጣቸው ከቻሳ ብለው አጉዋጉል ያደርጉሻል እያለ ቀባጠረ ፤ እኔ በወገን ልመካ ብል አባይ ማዶ በጥይት ወፍ የሚያረግፉ ዘመዶች አሉኝ፤ ግን ላንተ እኔ አላንስም! እግዜርን ታልፈራሁ እንደ አደፈ ጨርቅ ጨፍጭፌ አሰጣሀለሁ ! ለነፍስህ ካዘንክለት ተዚህ ወግድ ብየ ቁርጡን ነገርኩት! እንዲህ አንድ አንድ ስንመላለስ ፤ጉርምቦየን ሊያንቀኝ ተንጠራራ፤ አልሞት ባይ ተጋዳይ ተጋፈጥሁት ! ብቻ ሁለት ደቂቃ ሳይሞላ ብን ብሎ ጠፋብኝ ! የት ገባ ብየ ወድያ ወዲህ ሳጣብር ክርክርየ (ብብቴ) ስር ተሰንቅሮ አገኘሁት! መጣህ ማርያም ታምጣህ ብየ ፤ ባለ በሌለ ሃይሌ እንደ ተልባ ሳሸው ፤ምላሱ እንደ ማግ ተጎለጎለ ! እርስዎ እንደ ሊቀ መላኩ ደርሰው ባያስጥሉት ኑሮ በእጄ ላይ ጠፍቶብኝ ነበር! “
እኒህን አማርኞች አቻችላ የምትኖረውን አዲሳባን ለመምራት ከኔ በላይ ማን ይኖራል?
2
የሆነ ጊዜ ላይ አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ አንድ ከተማ ጎበኘሁ፤ የተቀበለኝ ልጅ ጥሩ ልጅ ነው፤ አብረን ከሰነበትን በሁዋላ ግን እንዲህ አለኝ “ በውቄ! to be honest with you እንግሊዝኛ ስትናገር እንደ ግእዝ ነው፤ስለዚህ የምትፈልገውን ነገር ለኔ ንገረኝና አስተረጉምልህለሁ”
እየመረረኝ እሺ ብየ ተስማማሁ ፤
የሆነ ቦታ ስንደርስ ካፌ ውስጥ ይዞኝ ገባና
“ምን ልዘዝልህ አለኝ?
“ በጅንጅብል የፈላ ሻይ “ አልኩት፤
ራሱን እያከከ ለረጅም ደቂቃ ቆየ ፤
ተግባብተናል፤
በመጨረሻ እንዲህ አለ፤
“ እዚህ አገር ጅንጅብል አያውቁም፤ ሌላ ነገር እዘዝ”