>

«ዘርና ሃይማኖት ሳይለያየን ለሀገራችን የምንቆምበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን...!!!» - ፕሮፌሰር አደም ካሚል

«ዘርና ሃይማኖት ሳይለያየን ለሀገራችን የምንቆምበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን…!!!»
ፕሮፌሰር አደም ካሚል
 (ኢ ፕ ድ) 
ኢትዮጵያ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ የውጭም የውስጥም ኃይሎች በጋራ ሀገሪቱን ለመበታተን ቆርጠው የተነሱበት በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመገንዘብ አደጋውን በጋራ ክንድ ሊመክተው እንደሚገባ ፕሮፌሰር አደም ካሚል አመለከቱ ።
ፕሮፌሰር አደም ካሚል በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፣ ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ ከመከፋፈል ይልቅ ወደ አንድነት መምጣቷ ያሳሰባቸውና የሀገሪቱ መረጋጋት የቀጠናውን መረጋጋት እንደሚያመጣ የተረዱ ሀገራት እየተፈጠረ ያለውን ህብረትና አንድነት ለመበተን ቀን ከሌት እየሰሩ ነው
የሀገሪቱ መጠናከር እንደፈለጉ እጃቸውን ለመስደድ ለሚፈልጉ ወገኖች አመቺ አለመሆኑ የተረዱ ወገኖች ላለፉት 30 ዓመታት ስንከተለው የነበረው የልዩነት ፖለቲካ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፤ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፤ አብሮ ከማደግ ይልቅ አብሮ መውደቅን የመረጠ እንደነበር ያመለከቱት ፕሮፌሰር አደም ፣ ይህ የፖለቲካ አካሄድ ሀገሪቱን ከውስጥ አልፎ ለውጭ ጠላቶች አሳልፎ እንደሰጣት አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን መጠንከር የማይሹና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ድክመቷን ለሚመኙ አካላት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸው የቆየ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር አደም፣ እነዚህ ሃይሎች እንደገና ይህንን ከፋፋይ ሥርዓት ለመመለስ የሞት ሽረት ትግል እያካሄዱ ነው ብለዋል።
‹‹ቀደም ሲል ሊደፍሩን ወኔ የሌላቸው ሀገራት ጭምር ድንበራችንን በኃይል ለመውረር ችለዋል፤ አንዳንዶቹም ጭራሽ ሀገሪቱን ለማፈራረስ ቆርጠው ተነስተዋል።ሄደው ሄደውም የህዳሴ ግድብ ያረፈበት የቤኒሻንጉል ክልል የእኛ ነው የሚሉ ወገኖች ብቅ ብለዋል›› ያሉት ፕሮፌሰር አደም ካሚል፣ በርካታ የውጭ ተቋማትና ሚዲያዎቻቸውም ኢትዮጵያን ለማዳከምና የተጀመረውን የአንድነት መንፈስ ለመበረዝ ሌት ተቀን እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
Filed in: Amharic