>

ተናጋሪዎችን የጎዱ መስሏቸው መስሚያቸውን የደፈኑ ትህነጎችና ኦህዲድ/ኦነጎች! (አምባቸው ደጀኔ - ከወልዲያ)

ተናጋሪዎችን የጎዱ መስሏቸው መስሚያቸውን የደፈኑ ትህነጎችና ኦህዲድ/ኦነጎች

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)


በጣም ከመዘውተሯ የተነሣ ተሰልችታ እንዳይሆን ፈርቼ ተውኳት እንጂ ርዕስ ማድረግ የነበረብኝ እንኳን የሞኝቱን ሚስት አድራጎት ነበር፡፡ ወራቱም ፆም ነውና ግዴለም ትቅርብኝ፡፡ እንግዲያማ ‹ጨዋነቴ›ም ተጨምሮበት ሁኔታዎች ባይገድቡኝ ኖሮ “ባሏን የጎዳች መስሏት እንትኗን በጋሬጣ ወጋች” ማለት ተስኖኝ አልነበረም:: 

ስለሁለት ነገር አሁን ተከሰትኩ ለማንኛውም፡፡ 

 

1 – መጋቤ ሀዲስ እሸቱ  ዓለማየሁ Feb. 13, 2021 በአርትስ ቲቪ ሲናገር ከሰማሁት አንድ ነገር ላይ አስተያየት መስጠት ፈለግሁ፡፡

2 –  አንድ ሀገር ምርጥ (Qualitative) መሪዎችን የሚያገኘው ሕዝቡም ምርጥ ሲሆን እንደሆነ የሚሰማኝን ለመጠቆም ወደድኩ፡፡

ኢትዮጵያን ፈጣሪ ጥሎ አልጣላትም፤ አይጥላትምም፡፡ በመሆኑም በጭንቋ ጊዜ ሁሉ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም የተወሰኑ የቁርጥ ቀን ልጆችን ይሰጣታል፡፡ አሁን ካሉን የጭንቅ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች አንደኛው መጋቤ ሀዲስ እሸቱ ዓለማየሁ እንደሆነ ለመረዳት በየሚገኝበት ዐውደ ምሕረትና በየሚጋበዝበት መድረክ ሁሉ የሚናገራቸውን ጥልቅ አስተምህሮዎችና የሀገር ፍቅር የሚንጸባረቁባቸውን ንግግሮች ማዳመጥ በቂ ነው፡፡ ስንቶቻችን ፈርተንና በሚስቴ ድስቴ የማቄን ጨርቄን የሽፋን ምክንያቶች ተጋርደን በየማጀት ሣሎናችን ተደብቀን ሳለ እነዚህን መሰል ጀግኖች የሀገራችንን ችግር በድፍረት በማፍረጥረጥ ነውረኞችን እየገሰጸና እኛንም እያስተማረ ይገኛል፡፡

ዛሬ ጧት የተመለከትኩት ዝግጅት ከነዚህ የመጋቤ ሀዲስ ምርጥ የመድረክ ንግግሮች አንደኛው ነው፡፡ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ እንደመሆኑ ግን በአንደኛዋ ሃሳቡ ላይ የተሰማኝን ቅሬታ መናገር ወደድኩ፡፡ እርግጥ ነው እርሱም ቢሆን ያቺን ነገር የተናገረው ለመናጆነት እንጂ ሙሉ በሙሉ አምኖበት ስለመሆኑ ብቻችንን ብንገናኝ የምንጠያየቅበትና የምንተማመንበት ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ “አማራ ከ50 እና 60 ዓመታት በፊት እኔን ብቻ ስሙኝ አለ – ግን አልተሳካለትም፡፡ ትግሬ ከ1983 ጀምሮ እኔን ብቻ ስሙኝ አለ – ግን አልተሳካለትም፡፡ አሁን ደግሞ ኦሮሞ እኔን ብቻ ስሙኝ ‹የማለት አዝማሚያ› ያሳያል – ይህም አይሳካም፡፡ የሚጠቅመው ሁላችንም የሚሰማንን ስንናገር ሁላችንም ማዳመጥና መደማመጥ ነው…” ይላል መጋቤ ሀዲስ (በትክክል እንዳልጠቀስኩ አውቃለሁና ይቅርታ)፡፡ በጣም ትልቅ እውነት ነው፡፡ ለገባንበት የችግር አዘቅት መፍትሔውም ይሄው ብቻ ነው፡፡ 

ቅሬታየ – ከ50 እና 60 ዓመታት በፊት በርግጥም አማራ የሚባል ዘር በአማራነቱ እየተኮፈሰና እየተንቀባረረ በሌሎች ላይ መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ያካሂድ ነበር ወይ? “እኔ የይፋቴዋ ልጅ!”፣ “እኔ መሬው!”፣ “የቋሪቷ ልጅ!” ከማለት በዘለለ አማራ በአማራነቱ በግልጽ ይሁን በኅቡዕ ተደራጅቶ ሌሎችን ያጠቃበት፣ በፖለቲካ ፕሮግራምም ይሁን በዘረኛ ታልሙዳዊ ሰነድ ለምሣሌ “ኦሮሞን ከነገዳ ሥርዓቱ ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ” ወይም “ትግሬዎችን ከነቋንቋቸው ለማጥፋት መቼም የማይበርድ ማኅበራዊ ዕረፍት እነሳቸዋለሁ” ብሎ ተነስቶ ነበር ወይ? … ብለን ስንጠይቅ – እንዳንኮነን – መልስ አናገኝም፡፡ ብዙ ነገሮች በአማራ ጠላቶች የተፈበረኩና በምልምል የሀገር ውስጥ ተላላኪዎቻቸው የተሰራጩ የሀሰት ትርክቶች እንጂ በእውነቱ መንገድ ከተራመድን አማራ የሚወራበት ሁሉ ሀሰት ነው፡፡

ይህን ስል ግን አማራን የማይወክሉ፣ ምሥኪን የጎጃምንም በለው የጎንደርን ገበሬ የማያውቁ ግን በጥጋብና በዕብሪት ተነሳስተው አማራን ጨምሮ ሌሎችንም የሚጨቁኑ ዜጎች (የትውልድ ሀረጋቸው ከየትኛውም ብሔርና ነገድ የሚመዘዝ) አልነበሩም ማለት አንችልም፡፡ ማንም ያጥፋ ጥፋቱ የሚላከከው ግን በፈረደበት አማራ ሆነና ጦስ ጥምቡሱ እንደጥላ እየተከተለ በተለይ አሁን በመንግሥት በሚደገፍ የዘር ፍጂት መርሐ ግብር አማራ በተገኘበት ቦታ ሁሉ እንደዐይጥ የሚጨፈጨፍ ነገድ ሆነ፡፡ መተከልና ወለጋ ኅያው የሽመልስ አብዲሣ ቅዠት መገለጫዎች መሆናቸው ለዚህ የሀሰት ትርክት አንዱ መገለጫ ናቸው፡፡ እንጂ በዚያን አማራ ነገሠ ወይ ገነነ በሚባልበት ዘመን የነበሩ ባለሥልጣናትንና በጨቋኝነት የተፈረጁ ዜጎችን ማንነት ብናጤን እንደዛሬ ሁሉ ያኔም ሰው ሲወለድ “ከማንኛው ዘርና በየትኛው ሀገር መወለድ ትፈልጋለህ?” ተብሎ የሚጠየቅ ባለመሆኑ “አማራ ነው” ወይም “ትግሬና ኦሮሞ ነው” ሊባል የሚችል አልነበረም፡፡ ለዚህ ደግሞ ከኦሮሞና አማራ ቅይጦቹ ከአፄ ምኒልክ፣ አፄ ኃ/ሥላሤ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ፣ አቶ መለስና አፄ አቢይ አህመድ የተሻለ ማስረጃ  ልናቀርብ አንችልም፡፡ ሴትዮዋ “ዕድሌ ሆኖ ፈሴ ይሸታል” እንዳለችው አማራ ዕድሉ ሆኖ ነገር ይገንበታል እንጂ የየጎሣው መኳንንትና መሣፍንት የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨቁነዋል፡፡ የጨቋኞችን አኃዛዊ የዘር ስብጥርና ኮታ ጉዳይ ለፀጉር ሰንጣቂ ሥራ ፈቶች መተው ነው፡፡  

ስለሆነም ያ ዘመን ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ለመናጆነት የአማራ ዘመን እንደነበረ ይጠቀስ እንጂ እንደውነቱ ከሆነ ግን የሁሉም ዘመን ነበር ማለት እንችላለን፡፡ ከራሴው ገጠመኝ ምሣሌ እንድጠቅስ ቢፈቀድልኝ – ሥራ ስቀጠር በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከተቀጠርን በርካታ ምሩቃን መካከል አብዛኛዎቹ በአሁኑ አገላለጽ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ያኔ ሰው በዜግነቱ እንጂ “አንተ እንዲህ”፣ “አንቺ እንዲያ” የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ከችሎታና ብቃት ውጪ አማራነት ሥፍራ ቢኖረው ኖሮ አሁን መላ አዲስ አበባ በኦሮሞ ሥራ ተቀጣሪዎች ተጥለቅልቃ እንደምናያት ታንጉትና ጉዝጉዝ፣ አደፍርስና ጓንጉል ከወሎና ከጎንደር ወይም ከሸዋና ከጎጃም በመኪና እየተጫኑ መጥተው መሥሪያ ቤቱን ሁሉ ካለምንም ትምህርትና የሥራ ልምድ ባጨናነቁት ነበር (እንዴ! አሁን እኮ በጣም እያፈርን ነው፡፡ እኔ በበኩሌ በምሰማውና በማየው ሁሉ ስለነሱ በሀፍረት ተሸማቅቄ መሞቴ ነው፤ አዲስ አበባንና አካባቢዋን ባወጡ እየቸበቸቡ በአንድ አዳር የናጠጡ ቱጃሮችም እየሆኑ ነው፡፡ መሸታ ቤቱ ሁሉ፣ ሴተኛ አዳሪዎች ሁሉ ሥራ በዝቶባቸዋል አሉ)፡፡  ስለዚህ ይህን ምሥኪን ሕዝብ ባልዋለበት አንውቀሰው፡፡ ጥቂት ግለሰቦች ባጠፉ በጅምላ አንፈርጀው፡፡ ሁለተኛውን ርዕሴን ለሌላ ጊዜ ላስተላልፈው መሰለኝ … ቻው፡፡

Filed in: Amharic