>

ሁሉም ምልክቶች . . . ወደ ኦዳ ዛፍ ያመራሉ! (አሰፋ ሀይሉ)

ሁሉም ምልክቶች . . . ወደ ኦዳ ዛፍ ያመራሉ!

አሰፋ ሀይሉ
 
The Oromuma is getting interesting!

 

ዶ/ር አሰፋ ጃለታ ባቀረበው የጥናት ጽሑፍ እንዲህ ይናገራል ስለ ኦዳ ዛፍ፡- ‹‹የኦዳ ዛፍ የኦሮሞ ሐይማኖት እምብርት ነው፡፡›› (”‘Odaa’ or Sycamore tree is the center of religion for Oromo society.”)፡፡ በተጨማሪም የኦዳን ዛፍ በጊዜ ብዛት የማይደበዝዝ ህያው የቃልኪዳን ሰነዳችን ነው ይለዋል፡- ‹‹ኦዳ ዛፍ ያለፈውን ዘመን የኦሮሞ ትውልድ የፖለቲካና ማህበራዊ ስሪት በአንድ ላይ አሰባስቦ የሚከስት የማይደበዝዝ ታሪካዊ ሰነዳችንም ነው››፡፡
 
ከ7 ዓመታት በፊት ደግሞ ገመቹ ከድር ‹‹ለኦሮሞ ማህበረሰብ ከኦዳ ዛፍ በስተጀርባ ያለው ድብቅ ትርጉም›› በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ለንባብ ባበቃው ጽሑፉ ስለዚሁ የኦዳ ዛፍ እንዲህ ይለናል፡- 
 
‹‹አንድ ማኅበረሰብ የጋራ የሆኑ መለያ ጠባዮቹን የሚገልጽበት አንድ የጋራ የሆነ ምልክት እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው፡፡ አንድ ብሔር የራሱን የተለየ ባህል የሚገልጽበት የራሱ የተለየ ዓለማዊና መንፈሳዊ እይታም ይኖረዋል፡፡ የእኛን (የኦሮሞን) ማህበረሰብ ስናነሳ ደግሞ የኦዳን ዛፍ እንደዚያ አድርገን መውሰድ እንችላለን፡፡ የኦሮሞ ብሔርና የኦዳ ዛፍ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም መንታ ገጾች ናቸው፡፡ በየትኛውም ቦታ፣ እና በየትኛውም ጊዜ፣ ኦዳ ዛፍ የኦሮሞን ማህበረሰብ የሚወክል መለያችን ነው፡፡›› 
 
በማለት ይቀጥላል ትንተናውን እንዲህ ሲል፡- 
 
‹‹የሰው ልጅ የመጀመሪያውን ምልክት ቀርጾ መጠቀም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ኦዳ የኦሮሞን ማህበረሰብ ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለ፣ የዝንተ ዓለም የኦሮሞ ምልክት ነው፡፡ ይህን እውነታ ለመረዳት የፈለገ ቢኖር በአሁኑ ሰዓት በኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ላይ፣ እና በገዳ መሪዎች አዳራሽ (ማለትም በ«ገልመ አባ ገዳ») ላይ እንዲሰፍር የተደረገውን የኦዳ ዛፍ መመልከት ይበቃዋል፡፡›› 
 
በመጨረሻም የኦዳ ዛፍንና የኦጎሞን የገዳ ሥርዓት ጥንታዊ ትስስርና ግንኙነት ሲያስረዳ ገመቹ ከድር እንዲህ ይላል፡-
 
‹‹የገዳ ሥርዓት በትክክል መቼ እንደተጀመረ ጥንታዊ የጽሑፍ ማስረጃዎች ባይኖሩም፣ በኦሮሞ ማህበረሰብ በቃል ከትውልድ ትውልድ ሲዋረድ በመጣው ታሪካችን መሠረት ግን፣ የኦዳ ዛፍ፣ በዘመናት ውስጥ ሁሉ፣ የአባ ገዳ ሥርዓት የፀነሳቸውን የኦሮሞ ባህላዊ ተቋማት ሁሉ ሲወክል የኖረ፣ ብቸኛው ሁሉን-አቀፍ የኦሮሞ ህዝብ ዘመን ተሻጋሪ ምልክት ነው፡፡››
 
እንግዲህ ስለ ኦዳ ዛፍ በተለያዩ የኦሮሞ ምሁራን የሚገረንን ከሰማን.. የኦዳ ዛፍ የኦሮሞን ባህል (ኦሮሞ አንድ ባህል ብቻ ያለው ከሆነ)፣ የኦሮሞን ሐይማኖት (ኦሮሞ ሁሉ አንድ ሐይማኖት ካለው)፣ የኦሮሞን ማህበራዊና ፖለቲካዊ አስተሳሰብና (ኦሮሞ ሁሉ አንድ ወጥ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አሰተሳሰብ ካለው)፣ እና የኦሮሞን ዓለማዊና መንፈሳዊ ማንነት የሚወክል (ይህን የመሰለ የኦሮሞ ህዝብ ሁሉ የሚጋራው መንፈሳዊና ዓለማዊ የጋራ እይታ ካለ) – ሆኖ ነው የሚቀርበው፡፡ በርካታ ጥናት ያጠኑ የኦሮሞ ምሁራንም የሚነግሩን ይህንኑ ነው፡፡ ኦዳ የኦሮሞ አባቶች – ስለማህረበሰባቸው እርቅና ውይይት የሚያደርጉበት የጨፌን ምልክት የያዘ – የአባ ገዳ ሥርዓት መወከያ ምልክትም ተደርጎ ሲቀርብ እናገኛለን፡፡ 
 
ይህን ስናይ – እና በፖለቲካ ጠቀሜታው ካሰብነው – የኦሮሞ የፖለቲካ ኤሊቶች የኦዳን ዛፍ – ከቋንቋ ምስስሎሽ ባለፈ – እጅግ የተለያየ ዓይነት ባህልና ወግ፣ ሐይማኖታዊና ዓለማዊ እምነት፣ አስተሳሰብና አኗኗር ሥርዓት ያለውን የተሰበጣጠረና የተበታተነውን የኦሮሞ ማህበረሰብ – አንድ አድርጎ እንደ ጥላ እንዲያሰባስብላቸው፣ ወደ አንድ የጋራ ግንባር አምጥቶ እንዲያያይዛቸው የፈጠሩት ወይም የተጠቀሙበት መሆኑን አለማየት አይቻልም፡፡ በልሂቃኑ አስተምህሮት መሠረት የኦዳ ዛፍ የጋራ ምልክት ሆኖ የኦሮሞ የተለያየ ማህበረሰብ ሁሉ በባህላዊው የገዳ ሥርዓታቸው ሥር አንድ አድርጎ የሚያገናኝ የጋራ መሰባሰቢያ ጥላ፣ አንድ የጋራ የኦሮሞ ህልውና ምልክት ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ተቆጥሯል፡፡ ምናልባትም ነው፡፡ 
 
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በኢትዮጵያችን እየተስተዋለ የመጣው ጉዳይ – ይህ የኦሮሞ ባህልና ሐይማኖት፣ የኦሮሞ መንፈሳዊና ዓለማዊ እይታ፣ እና የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ምልክት ሆኖ የተወሰደው የኦዳ ዛፍ – ድፍን ኢትዮጵያን እንዲወክል – የኦሮሙማው ኦሮማይዜሽን ፕሮጀክት አካል ሆኖ በየነገሮች ሁሉ ውስጥ እየገባና እየተስፋፋ ያለ ምልክት እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ 
 
በቅርብ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የተቆፈረ የውሃ ገንዳ ያለው ፓርክ (እና ዘንድሮ የኢሬቻ በዓል ከደብረዘይት ወይም ቢሾፍቱ ወደ አዲስ አበባ ተዛውሮ በተከበረበት ወቅት የኢሬቻ ሐይማኖታዊ በዓል ማክበሪያ ሆኖ የዋለው የውሃ መዝናኛ ሥፍራ) – የታከለ ኡማና የአብይ አስተዳደር ስለ ቅርጹና አጠቃላይ ሥራው የተናገረው ነገር ባይኖርም – በመጨረሻ ሲታይ ግን – የውሃው ገንዳ ቅርጽ በትልቅ የኦዳ ዛፍ አምሳል የተቀረጸ ሆኖ መገኘቱ መነጋገሪያ ሆኖ እንደሰነበተ እናስታውሳለን፡፡
 
አሁን ግን የአዲስ አበባ (ወይም የኦሮሞ ልሂቃን ፊንፊኔ ብለው የሚጠሯት የመዲናችን አዲስ አበባ) የህዝብ መዝናኛ ፓርክ ቅርጽ ብቻ አይደለም በኦዳ አምሳል ተቀርጾ የምናገኘው፡፡ የኦዳን ዛፍ በኦነግ ባንዲራ ላይ ብቻ አይደለም የምናገኘው፡፡ የኦዳን ዛፍ በኦሮሚያ ክልላዊ ባንዲራ ላይ ብቻ አይደለም የምናገኘው፡፡ የኦዳን ዛፍ ጨፌ ኦሮሚያ ላይ ወይም በገልመ አባ ገዳ ላይ ብቻ አይደለም የምናገኘው፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ምሁር – የኦዳን ዛፍ ‹‹ቦታ የማይወስነው፣ ጊዜ የማይገድበው›› ብሎ እንደጠራው – እውነትም – ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ – የኦዳ ዛፍ በሁሉም ነገር ላይ፣ በሁሉም ሥፍራ፣ ጊዜና ቦታ ሳይወስነው ጉብ ብሎ እየተገኘ ያስገርመን ጀምሯል፡፡ 
 
ለምሳሌ የብልጽግና ፓርቲን አርማ ልብ ብሎ ላየው – በትክክል አጠቃላይ ቅርጹ የኦዳን ዛፍ እንዲመስል ተደርጎ የተሠራ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህን ስመለከት የሽመልስ አብዲሳ ተቀርጾ የወጣ ንግግር ይመጣብኛል፡፡ የብልጽግና ፓርቲን የመሠረትነው እኛ ኦህዴዶች ነን፡፡ ኦሮሞን እንዲመስል አድርገን ነው የመሠረትነው፡፡ በብልጽግና ኦሮሞ ያላለው ነገር አይከናወንም፡፡ እኛ እንድናዝበት አድርገን ነው ያቋቋምነው፡፡ ያለው አባባል ትዝ አለኝ፡፡ መጀመሪያ ላይ ይሄን የብልጽግና አርማ የኤስ ኦ ኤስ ህጻናት ማሳደጊያን አርማ ይመስላል እያልን የተሳለቅን ሁሉ – የኦዳው ዛፍ ከአርማው መሀል – እያደር እየጎላ ሲወጣ ስንመለከት – ጉድ ነው ያልነው! እስከዚህ ድረስ የዘለቀ ረቂቅነትና ምጥቀትን ተላብሰው በማግኘቴ በግሌ ኦሮሙማዎቹን አድንቄያቸዋለሁ፡፡  
 
የዘንድሮውን የኢህአዴግ ብልጽግና ፓርቲ የመወዳደሪያ ምልክት ነው ተብሎ በስፋት እየተዋወቀ ያለውን የድሮ አምፑል ምልክትም መውሰድ እንችላለን፡፡ አምፑሉ እየተዋወቀ ያለው ብርጭቆው ወደ ላይ ተገልብጦ ነው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ግራ ሲገባን ነበር፡፡ ይሄ አምፑል በኢትዮጵያውያን ሁሉ ቤት ውስጥ ብርጭቆው ወደ ታች ሆኖ ተንጠልጥሎ የሚበራ አምፖል ነው፡፡ እና ለምን ወደ ላይ መገልበጥ አስፈለገ? እያልኩ ስመራመር ነበር፡፡ ለካ ይሄም አምፑል – የኦዳ ዛፍ መሆኑ ነው!! የምር ግን አድናቆቴ እጅግ እጅግ ከፍ ብሏል ለእነዚህ ሰዎች፡፡ 
 
ማንም ስለ ቅርጽ ሥራ የሚያውቅ (የማያውቅም) ሰው በቀላሉ የብልጥግናን አምፑል አይቶ ማረጋገጥ የሚችለውን ጉዳይ ነው እያወራሁ ያለሁት፡፡ የብልጽግናው አምፑል አዲስ ምልክት አይደለም፡፡ ያው ራሱ በኦነግ ባንዲራ ላይ ያለው፣ በኦሮሚያ ባንዲራ ላይ ያለው፣ በኢሬቻ ፓርክ የውሃ ገንዳ ላይ ያለው፣ ያው ራሱ በብልጽግና አርማው ላይ ያለው – ያው ራሱ የአባ ገዳው የኦዳ ዛፍ ነው፡፡ የብልጽግና የምርጫ መወዳደሪያ አምፑል – በኦዳ ዛፍ አምሳል የተሠራ – የኦሮሙማው ቅርጸ ሥራ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ 
 
የኦሮሙማዎቹ ድርጊት በቀላሉ የሚታይ አይመስለኝም፡፡ ከፋሺስታዊ አመለካከት የመነጨ ነው፡፡ ሌላውን በራሳቸው አምሳል፣ እና በራሳቸው ቁጥጥር ሥር የማዋል ያልተገራ ፍላጎታቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ ዶሚናንስ፣ እና ሬስ፡፡ ያ ነው ህልማቸውም ቅዠታቸውም፡፡ ናዚዎችን ያስታውሱኛል፡፡ 
 
ልክ አሁን ኦሮሙማዎቹ እየቃዡ እንዳሉት – የጀርመን አርዓያን ዘር ፣ የዘሮች ሁሉ የበላይ ነው፣ ሁሉንም የሰው ዘሮች በቁጥጥሩ ስር ማዋል አለበት – በሚል ቅዠት የተነሳሱት የናዚ ፓርቲ መስራቾች  – እነ ሂትለር፣ ጎብልስ፣ ጎሪንግ፣ ወዘተ ይመጡብኛል፡፡ እነሱም – ልክ እንደ ኦሮሙማዎቹ – ለፓርቲያቸው ምልክትነት ይሁነን ብለው ያስሱ የነበሩት ጥንታዊ ምልክቶችን ነበር፡፡ ካልጠፋ የመስቀል ቅርጽ – በጥንታዊ ገድሎችና ቅርጾች ውስጥ የሚገኘውን የተቆለመመ የመስቀል ቅርጽ – ለናዚ (ማለትም ለብሔራዊ ሶሻሊስት) ፓርቲያቸው ምልክትነት እንዲውል ያደረጉት በዚህ ዝንባሌያቸው ነበር፡፡ 
 
እና ናዚዎቹ እንደሚታወቀው – ሀገራቸውን ብቻ ሳይሆን ዓለሙን ሁሉ የናዚን ቅርጽ አጥለቅልቀውት ጠፉ፡፡ ሌላ ቀርቶ ከጥቂት ዓመታት በፊት በራይንላንድ የሚገኝ አንድ ጥቅጥቅ ደን ከሄሊኮተር ላይ (ከሰማይ) በድንገት ሲታይ በዛፎቹ ከለር በሥነሥርዓት ተተክሎ የበቀለውን የናዚን አርማ አገኙት፡፡ ትልቅ ደን ነው፡፡ ደኑን ምን እንደሚያደርጉት በቡንደስታግ (በፓርላማቸው) ሲጨቃጨቁ ነበር፡፡ 
 
እኛም የኦሮሙማውን መጨረሻ ለማየት የቱንም ያህል ብንጓጓ፣ እና የቱንም ያህል ኦሮሙማው ኃይል ከቅዠቱ ተመልሶ ለሁሉም የምትሆን፣ እና ሁሉንም የምትወክልን ኢትዮጵያን ይዞ ለመጓዝ የሚነሳበት ቀን ቢናፍቀንም፣ እስከዚያው ግን እነዚህን የመሠሉ በሚገርም መርቀቅና አካሄድ (ኮንቪንስም ኮንፊዩዝም አድርጎ) እየሠራቸው ያሉ ኦሮሙማዊ ሸፍጦች ግን – በግሌ ሳያስደምሙኝ አላለፉም፡፡ 
 
እንዲህ በየነገሮች ውስጥ ምልክቱን እየተወ የመሄዱን ምኞትና ትጋት ስመለከት – እነዚህ ሰዎች እኮ ኢሉሚናቲዎቹን ራሱ ሊያስከነዱ የቀራቸው ጥቂት ጊዜ ብቻ ነው እላለሁ በአድናቆት፡፡ እና በበዛ አግራሞት፡፡ ግዜ ከሰጠናቸው በእርግጥም ኢሉሚናቲዎችን የሚያከነዱ ባለ ምልክት ምሥጢራዊ ሶሳየቲዎች የመሆን ዕድላቸው ከፍ ያለ መሰለኝ፡፡ ሁሉም ነገሮች ወደ ኦሮሙማው እየወሰዱን ነው፡፡ እስቲ ጊዜ እንስጣቸው፡፡ እና በጥበባቸው ይራቀቁ፡፡ ብዬ ተሰናበትኩ፡፡ 
 
The Oromuma is getting interesting!
 
ከኦዳ ዛፍ ጋር ወደፊት!            
   
__________________________________
Image: The secret behind the symbolic representation of ‘Odaa’ (Sycamore) tree for the Oromo society. Source: Internet.
Filed in: Amharic