>

 የቃሊቲን ውሎዬን በጨረፍታ...?!? (ኤልያስ ገብሩ)

 የቃሊቲን ውሎዬን በጨረፍታ…?!?

ኤልያስ ገብሩ

– እነ እስክንድር እና አቦይ ስብሓት የታሰሩበት ክፍል ተለያይቷል።
—-
ዛሬ ከሰዓት በኋላ እነ እስክንድርን ለመጠየቅ እኔ፣ Abel Alemayehu A  እና Habtamu Menale  ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት አምርተን ነበር። ከሌሎች ጠያቂ ወዳጆቻችን ጋራም በዚያው ተገናኘን።
መጠየቂያው ስፍራ ስንደርስ፣ በጥሩ ስሜት እና ኹኔታ ላይ የሚገኘው እስክንድር፣ በሕዝብ ስልክ እየተነጋገረ አገኘነው። እኛም እሱም በመገናኘታችን ደስ ብሎን ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርበት ሰላምታ ተሰጣጠን። እስኬው፣ ህጻናት ልጆች ከልባቸው ፍልቅልቅ ብለው እንደሚስቁት ከልቡ እየሳቀ ደስ በሚል ፈገግታ ኹላችንም ሰላም አለን። እስኬው፣ ከብርታቱ፣ ከሞራሉ፣ ከድፍረቱ፣ ከጀግንነቱ፣ ከቅንነቱ፣ ደስ ከሚለው ልባዊ ሳቁ ጋራ ነው። ስንታየሁም ከባለቤቱ ጋራ እያወጉ ነበር። ስንቴም በጥሩ መንፈስ እና አካላዊ ኹኔታ ላይ ነበር። ተቀላልደን ሰላም ተባባልን። እስክንድርም ስንታየሁም፣ “መጽሐፍት (የአገዛዞች ቀይ መስመር) መውጣቱን ሰምተናል። እንኳን ደስ ያለህ። እዚህ መግባት ቢችልና ብናነበውም ደስ ይለናል።” በማለት ሐሳባቸውን በየተራ አጋሩኝ። በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ደጀኔ ጣፋንም  አግኝቻቸው ሰላምታ አቀረብኩላቸው። እሳቸውም በትህትና እና በፈገግታ ሰላምታ  ሰጡኝ። አቶ ደጀኔም በዛ ያሉ ጠያቂዎች ነበሯቸው።
ከስንታየሁ ጋራ፣ በጨዋታ መሐል፣ ከእነ አቦይ ስብሐት ጋራ በአንድ ክፍል ውስጥ ስለመገኘታቸው ሐሳብ ተነሳ።
 “ካልጠፋ ክፍል እኛ ጋራ አምጥተዋቸው ነበር። ከዚህ ቀደም ብዙ ካሰቃዩን ከእነ አቦይ ጋራ አብረን አንድ ክፍል ውስጥ እንታሰራለን ብዬ በጭራሽ አስቤ አላውቅም ነበር፣  ወደክፍሉ ሲያመጧቸው ግን፣ እንደሰው ክፍሉ ውስጥ የነበረ ፍራሽ ሰጥተናቸዋል። በተለያየ አስተሳሰብ ላይ የምንገኝ ቢኾንም፣ በጣም ጥቂት ንግግሮችን ተለዋውጠናል። ካልጠፋ ክፍል እኛ ጋራ ለምን እንዳመጧቸው አልገባንም ነበር፣ እኔ አስቤው ጨንቆኝም ነበር። የ86 ዓመት አዛውንትን ደበደቧቸው ብለው በሐሰት ሊወንጅሉን ፈልገው ይኾን? ብዬም አስቤ ነበር (እዚህ ጋራ ሳቅ አለ)። ዶ/ር አብረሃም ተከስተ የተረጋጋ እና ዝምተኛ ናቸው። አቦይን ከአንድ ቀን አዳር በኃላ፣ እነ አብዲ ኤሊ እና ክንፈ ዳኘው ወዳሉበት ክፍል ቀይረዋቸዋል። ዶ/ር አብርሃም ግን በእኛ ክፍል ውስጥ ናቸው ።”
በማለት ስንታየሁ አውግቶናል።
እስክንድርንም ኾነ ስንታየሁን የምንጠይቅ ሰዎች ብዛት ስለነበረን፣ ከእስክንድር ጋራ ብዙም ሐሳብ መቀያየር አልቻልንም። በመጨረሻም፣ ጠባቂዎች፣ “ሰዓት ሞልቷል፣ በቃችኹ” በማለት እንድንወጣ አደረጉ።
ይኸው ነው።
Filed in: Amharic