>

የሁለቱ መንግስታት የደህነንት ኃላፊዎች ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴና ጌታቸው አሰፋ...?!? (ዘ -  አዲስ)

የሁለቱ መንግስታት የደህነንት ኃላፊዎች
ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴና ጌታቸው አሰፋ…?!?
ዘ –  አዲስ

የህወሀት የደህንነት ሀላፊ የነበረው ጌታቸው አሰፋ መሞቱን ኢሳት ገልጿል፡፡ የሱ ሞት በመሰማቱ፣ ብዙዎች ደስታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ ጭካኔውና ክፋቱ ሲታሰብ ሞቱ ሊያስደስት ይችላል፡፡ ግን ኪሳራው ወዲህ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ( ኢሕድሪ) መንግስት( ተለምዶ ደርግ) የደህነት ኃላፊ እንጀምር፡፡
ኮሎኔል መንግስቱ ስልጣን በያዙ በጥቂት ግዜያት ውስጥ ( ያኔ ኮሎኔል አልነበሩም) ፣ የሀገሪቱ የደህንነት ሀላፊ የነበሩት ተካ ቱሉ ነበሩ፡፡ ያኔ የሀገሪቱ ውጥንቅጥ ብዙ ነበር፡፡ሀገሪቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ወራሪዎች፣ ህልውናዋ አደጋ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ሶማሌ ኦጋዴን ድረስ የኔ ነው ብላ ጦርነት ጀምራለች፡፡ ህወሀት፣ ኦነግ፣ ሻብያና ኢህአፓም ይሄንን ደግፈው ፣ ከፍተኛ ክህደት ሀገር ላይ ፈጸሙ፡፡ ስለዚህም ውለታቸው፣ እነ መለስ ዜናዊ ሶማልያ ቢሮ ተሰጣቸው፡፡ ውጭ ሀገር የሚጓዙትም በሶማሊያ ፓስፖርት ነበር፡፡ ታሪኩ ተድበስብሶ ይነገራል እንጂ፣ ጀግናው ያየር ኃይል ፓይለት ጀነራል ለገሰ ተፈራ ተመቶ ሲወድቅ አሳልፈው የሰጡት የኦነግ ሰዎችም ነበሩ፡፡ ያኔ ኦነግ ፣በተለይ በባሌ በኩል ከሶማሌ ወግኖ ኢትዮጵያን በግልጽ ይወጋ ነበር፡፡ ሻብያና ወያኔም በሰሜን በያቅጣጫው ውጊያ እንዲጀምሩና የኢትዮጵያን መንግስት እንዲያፍረከርኩ፣ የአረብ ጌቶቻቸው በሰጧቸው ትዛዝ መሰረት፣ ሁለቱም በያቅጣጫው ውጊያ ጀመሩ፡፡ ከተማዎች በነጭ ሽብር ታምሰዋል፡፡ በሰሜን ፣ በምስራቅ ፣በምዕራብ ጦርነት ተጀምሯል፡፡አሜሪካና አጋሮቿ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ከፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጀምሮ እስከ ማዕቀብ መጣል ደረሱ፡፡
አልፎ ተርፎ፣ ኢትዮጵያ ከፍላ የገዛችውን መሳርያ ከለከሉ፡፡ በዓለም መንግስታት፣ ኢትዮጵያን ያብጠለጥሏት ገቡ፡፡ ከላይ እሳት፣ ከታች እሳት ውስጥ ገባች _ ኢትዮጵያ! በነገራችን ላይ ፣ ያ ግዜ አሁን ያለንበትን ግዜ ይመስላል፡፡ የነገሩ ክብደትና የተካ ቱሉ ጉዳይ ያልተዋጠላቸው መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ቀጭኑን የስለላ ባለሙያ ተስፋዬ ወልደሥላሴን ደህንነት ሀላፊ አድርገው ሾሙ፡፡
 ተስፋዬ እስራኤል ድረስ ሄደው ስለላ የተማሩ፣ አደገኛ ሰው ነበሩ፡፡ ወላይታ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ አብሯቸው ያደጉት አብሮ አደጎቻቸው እንደሚናገሩት፣ ሰውየው ከልጅነታቸው ጀምሮ አስፈሪና አደገኛ ነበሩ፡፡ የምስጢር ስራው ግን ተመቻቸው፡፡ ምስጢር እየዋጡ አበጡ!
በስለላው የሚመራው ጦርነት ተፋፋመ፡፡ ሶማሌን እንዳትነሳ አድርገው ሰበሯት፡፡ ምነው በቀረብኝ ብላ ኦጋዴንን ለቀቀች፡ የኦነግን ሴል፣ ለወሬ ነጋሪ አስተርፈው ለበለቡት፡፡ ኢህአፓን ዳግም እንዳይነሳ አድርገው ቀነጠሱት፡፡ ወረራ የፈጸመውችውን ሶማሌንና ወያኔና ሻብያን ቤዝ ሰጥታ ኢትዮጵያን የምታስወጋውን ሱዳንን የማፍረስ እቅድ ዘርግተው፣ ሱዳንም ሶማሌም ላይ እሳት ለኮሱ፡፡ የደቡብ ሱዳንን ተዋጊዎች በማሰልጠን ፣ የትጥቅና የስንቅ ድጋፍ በማድረግ፣ ሱዳንን ገዘግገዟት፡፡ እንዳሰቡትም ፣ ሱዳን ለሁለት ተቆረሰች፡፡ ሶማሌም ላይ ፣ የሶማሌ ተቃዋሚዎች በማስታጠቅ፣ ሶማሌን አመሷት፡፡ እንደ እቅዳቸውም፣ ሶማሌን በተኗት፡፡ ከሶስት ሀገራትና ከአራት የሀገር ውስጥ ታጣቂ ቡድኖች ጋር ሲፋለም የነበረው የኮሎኔሉ መንግስት ግን ፣ ግን ቦት 20/ 1983 በሻብያና ወያኔ ጥምር ጦር ወደቀ፡፡
የሻብያ ሚሊሻ፣ የህወሀት ሚሊሻ፣ የኦነግ ሚሊሻ፣ የሱዳን ና የአረብ ሀገሮች መሳርያና ስለላ፣ ያሜሪካና አጋሮቿ ያልተቆጠብነ የገንዘብና የዲፕሎማቲክ ድጋፍ ታክሎበት፣ አስራ ሰባት ዓመት ከዚህ ከዛም ሲዋጋ የነበረው ጦር ተፈታ፡፡
የኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ አስደናቂ ነገር የሚቀጥለው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ኮሎኔሉ፣ የሻብያና የህወሀት ሰራዊት ሲገባ አልሸሹም፡፡ ቢራቸው ቁጭ ብለው ህወህትን ጠበቋት፡፡ በሚደንቅ ሁኔታ “ ይሄ የሀገሪቱ የስለላ ሚስጥር ነው፡፡ “ ሀገራችሁን ጠብቁበት በማለት ቆጥረው ለወያኔ አስረክቧት፡፡ ወያኔም ፣ አዲስ አበባ ከገባች በኋላ፣ ተስፋዬ ወልደሥላሴን ያስቀመጠችው እስር ቤት አልነበረም፡፡ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ ከዛም የተለየ ቦታ ወስዳ፣ ብዙ የሀገር ጉዳዮችን ትጠይቃቸው ነበር፡፡ በኋላም፣ ተከሰው፣ የእድሜአቸውን አንድ ሶስተኛ ያህል በስር አሳልፈው ሊፈቱ አንድ ቀን ሲቀራቸው፣ ግንቦት 26/ 2003 ዓ.ም ፣ ወያኔ መድሃኒት ሰጥታ ገድላቸዋለች፡፡
የዶክተር ዓብይ አህመድ ለውጥ ሲመጣ፣ የደህነንት ሀላፊ የነበረው ጌታቸው አሰፋ የሰራው ነገር ግን የሚደንቅ ነው፡፡የሀገሪቱን የስለላ ሰነዶች በሙሉ ዲጂታይዝ በማስደረግ፣ ዲጂታል ኮፒውንም ሆነ ዋናዎቹን ፋይል በሙሉና የስለላ መሳርያ ህርድዌሮችን ነቅሎና አውጥቶ ባዶ ቢሮ ነበር ያስረከባቸው፡፡
ለዘመናት የተከማቹት ፣ የኢትዮጵያ የደህነት መስሪያ ቤት ሰነዶችና ፋይሎች፣ እስካሁን የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡ “ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አስተሳሰብ የታወሩት የህወሀት ጀሌዎች የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ይሄ ነው፡፡ እነሱ ስልጣን ላይ ከሌሉ፣ ሀገር ብትፈርስ፣ ብትወድም ፣ ብትዋረድ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ለነሱ የሚያሳስባቸው፣ ስልጣን ላይ ሆነው ፣ አላግባብ ከሕዝብ የሚዘርፉት ብርና ሀብት ብቻ ነው፡፡ ምናልባትም፣ እነዚህን ፋይሎች የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለሚጻረሩ ሀገሮች ሸጠውት ሊሆን ይችላል፡፡ ቢያንስ ኮፒው እንኳን የኢትዮጵይ መንግስት የለውም፡፡ የሀገር ምስጢር በትንንሾች ሲያዝ ውጤቱ ይሄ ነው፡፡
የጌታቸው አሰፋ ሞት የሚያሳስበው እዚህ ላይ ነው፡፡ የሀገሪቱ የደህንነት ፋይሎች ሚስጥር የሚያውቀው ጌታቸው አሰፋ ነው፡፡ ከዛም ባሻገር፣ ብዙ የሀገር ሚስጥሮች በሱ ዙርያ ብቻ ያሉ ነበሩ፣ ይኖራሉ፡፡ ይሄን ሁሉ ይዞ ግን ሞተ፡፡
ጨካኙ፣ ዘማዊው፣ ነፍሰገዳዩ፣ ርኩሱ ጌታቸው መሞቱ ርግጥ ከሆነ ኪሳራም ውለታም ነው፡፡ እንደሱ አይነት ጨካኝ መወገዱ አንድ ደስታ ቢሆንም፣ ሰርቆት የተሰወረው የህገር ምስጢር ሳይገኝ መሞቱ ደግሞ ኪሳራ ነው፡፡
Filed in: Amharic