ከተረኝነት ወደ ወራሪነት…!!!
ጌጥዬ ያለው
አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይተካል ያሉትን የ ‹መደመር› እሳቤ ከገዳ ሥርዓት እንደቀዱት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ተናግረዋል፡፡ በርግጥ ገዳ አንድ የኦሮሞ ወራራ ቡድን እንጂ ሥርዓት ነው ብሎ ለመቀበል አስቸጋሪ ነው። ለአቅመ ሥርዓትነት ደርሶ አያውቅም። ቡድንም እንበው ሥርዓት ገዳ የአቃፊነት እና የዴሞክራሲያዊነት ተምሳሌት ተደርጎ ሲቀርብም ይታያል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ በየስምንት አመቱ መሪዎቹን መቀየሩ ዴሞክራሲያዊ ቢያስመስለውም የኢ-ሰብዓዊነት ጥግ የሚታይበት አሠራር ነው፡፡ ገዳ እና በስሩ ያለው የሞጋሳ ወይም ገበሮ እንቅስቃሴ ሌሎችን የመውረሪያ መሳሪያ ነው፡፡ ግድያን የጀግንነት፣ ሥልጣን ላይ የመውጫ እና የጋብቻ መስፈርት ያደረገ አደረጃጀት ነው፡፡ በገዳ ውስጥ አባላቱ በየተራቸው ይሾማሉ፡፡ ሹመኛው ሉባ ይባላል፡፡ ሉባ እስከሚሆን ድረስ አይገረዝም፡፡ ሳይገረዝ ከወለደ ደግሞ ልጁን ሜዳ ላይ ጥሎ እንዲገድል ይገደዳል፡፡ ከአርባ አመት በታች ያሉ ወንዶች ሉባ አይሆኑም፡፡ በተመሳሳይ እስከዚህኛው እድሜያቸው ድረስ አይገረዙም ማለት ነው፡፡ ሥለዚህ ከአርባ አመታት በታች ከሆኑ አባቶች የሚወለዱ ጨቅላዎች ሁሉ ሜዳ ላይ እንዲጣሉ የገዳ ማሕበር ይመክራል፡፡ የማሕበሩ አባላትንም ያስገድዳል፡፡ ይህ መመሪያው ነው፡፡ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ያጠናክራል የተባለው ‹መደመር› ግብሩ መከፋፈልና መገዳደል የሆነው ከዚህ ማሕበር ስለተኮረጀ ይሆን?
በገዳ ቡድን ውስጥ በየስምንት ዓመቱ ማለትም ሥልጣን ከአንደኛው ገዥ ወደ ሌላኛው ገዥ ከመዘዋወሩ በፊት የሚደረግ ዘመቻ አለ፡፡ ይህ ዘመቻ በእነርሱ አጠራር ‹መስፋፋት› ይባላል፡፡ ግብሩ ግን ወረራ ነው፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ ገዥዎች የሚመሰገኑትም በሞጋሳ ወይም ገበሮነት የሌላውን ማንነት እየቀየሩ ኦሮሟዊነትን እያላበሱት ወይም ሙሉ በሙሉ እያጠፉት ሌላውን መውረር ሲችሉ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሥርዓቱ ከ28 በላይ ነባር የኢትዮጵያ ነገዶችን ማጥፋቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጠቅሰው ኒዋርክ በሚገኘው ረትገርስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ አስተማሪና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሀብታሙ መንግሥቴ ‹በራራ-ቀዳሚት አዲስ አበባ› በሚል አብይ ርዕስ ባቀረቡት መፅሐፍ አብራርተዋል፡፡
በወረራ የጠፉ ነገዶች!
በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጥናት መሰረት በሰዮ ወለጋ አካባቢ ብቻ ሞጋሳ ከአሥር በላይ ነባር የኢትዮጵያ ነገዶችን አጥፍቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ካንቺ፣ ኮንቺ፣ ሙጩኮ፣ ጋንቃ፣ ወራጎ፣ ዳምታ፣ ካዛ፣ አጋዲ፣ ገበቶ፣ መጀንግ፣ ክወራ፣ ክዋማ እና ቡሳሴ ተጠቅሰዋል፡፡ ከ28ቱ መካከል ጋፋት፣ ማያ፣ አንፊሎና ወርጅህ ይገኙበታል፡፡ እነኝህ ነገዶች ከነቋንቋቸውና ሌሎች ማንነቶቻቸው ቁጥራቸው ቀስ በቀስ እንዲቀንስና ፈፅሞ እንዲጠፉ የተደረጉት የገዳ ሥርዓት ባመጣው ወረራ እንደሆነ ዶክተር ሀብታሙ ከላይ በተጠቀሰው መፅሀፋቸው አስረግጠዋል፡፡ የሺናሻ፣ የዘይ፣ የአርጎባ እና የማኦ ማሕበረሰቦችም በመጥፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ የሞት አፋፍ ላይ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ ወቅት በተለይም ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ ኦሮሞ ያልሆኑትን ሁሉ በመግደል፣ ንብረታቸውን በመዝረፍና በማቃጠል እየተፈፀመ ያለው የማግለል እንቅስቃሴም ተቋርጦ የነበረውን የወረራ ዘመቻ ለማስቀጠል ያለመ ይመስላል፡፡ ‹በአዲስ አበባ ተቋርጦ የነበረው የኢሬቻ በዓል ከ150 ዓመታት በኋላ ዳግም መከበር ጀመረ› እንደተባለው ሁሉ ‹ተቋርጦ የነበረው የገዳ የመስፋፋት ዘመቻ ተጀመረ፡፡ ቀዳሚ ዘመቻውንም ወደ አዲስ አበባና ደቡብ ኢትዮጵያ አድርጓል› የሚል ዜና በቅርቡ እንሰማ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ማሕበር በኦሮሞ ፖለቲከኞችና ብሔርተኞች ሁሉ ተደግፎ እየተሠራበት ነው፡፡ እነኝህ ሃይሎች መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉ መሆናቸው ደግሞ ነገሩን ቀላል ያደርገዋል፡፡ የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ በሌላ ምክንያት ለጊዜው በምርጫ ቦርድ ከፓርቲነት ቢሰረዝም ማህተሙን እንጂ አጀንዳውን አልተቀማም፡፡ ምስጋና ለአዲሱ ኢሕአዴግ/ብልፅግና¡ የገዳ ማሕበር የገዥው ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ሊሆን የ ‹መደመር› እሳቤ ምንጭ ተደርጓል፡
የመጭው ወረራ ኢላማዎች!
የኦሮሞ ፖለቲካ አዲስ አበባን የትግል ማዕከሉ ማድረጉን ከሚታየውም በላይ አቶ ታከለ ኡማ በአንድ ወቅት አስረግጠው ነግረውናል፡፡ የአዲስ አበባን ፖለቲካ ከሕወሓት እስከ ኦሕዴድ ገዥ ብሔርተኛ የፖለቲካ ሃይሎች አጥብቀው ይፈሩታል፡፡ ኦሕዴድ መራሹ ብልፅግናም ቅርሶችን ከማውደም፣ ዜጎችን እስከ ማፈናቀል በዘለቀ እንቅስቃሴው ከተማዋ ላይ የጥላቻ ጡንቻውን እያሳረፈባት ነው፡፡ ከተማዋ መከላከል የምትችልበት አደረጃጀት እንኳን ሳይኖራት ነው ይህ ጡንቻ ሲደልቃት የቆየው፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከተቋቋመ በኋላ በመጠኑም ቢሆን መከላከል ወደ ምትችልበት አደረጃጀት መጥታለች ማለት ይቻላል፡፡ ከአንድ አመት ገደማ በፊት አቶ ለማ መገርሳ መልሰው ቢያስተባብሉም የአዲስ አበባን የሕዝብ ስብጥር እንደሚቀይሩ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሽመልስ አብዲሳም ኦሮሞ ከተማዋን እንደተቆጣጠረ ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ ንግግሮች አዲሱ የገዳ የወረራ ዘመቻ አዲስ አበባ ላይ መጀመሩን በግልፅ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹የምኒልክ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጥረን የታደሰ ብሩን ሃውልት እንገነባለን›› የሚለው የመረራ ጉዲና ንግግር ሲጨመርበት የወረራ አዋጁን ያስጀመረው ነጋሪት ከተጎሰመ ቆይቷል ወደ ሚል ድምዳሜ ይወስደናል፡፡ የወረራው የመጀመሪያ ምዕራፍ ኦሮሞ በስፋት በሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ሌሎች ዜጎችን በግድያም ሆነ በማሰደድ ማስወገድ ነው፡፡ ይህ በተደጋጋሚ ያለማቋረጥ ተፈፃሚ እየተደረገ ነው፡፡ ከተለያዩ የኦሮሚያ ‹ክልል› አካባቢዎች ዜጎች በግፍ ተፈናቅለዋል፡፡ ከኢሉባቡር የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ከብቶቻውን እንኳን ሽጠው እንዲወጡ አልተፈቀደላቸውም፡፡ ከእንስሳት እስከ አዝመራ፣ ከቤት እስከ መሬት ሀብት ንብረቶቻቸውን ሁሉ ለተደራጁ ወጣቶች አውርሰው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ከእነርሱ እንስሳትን ለመግዛት የሞከሩ ሰዎችም ‹የመጤ ደጋፊ› ተብለው ታስረው ተፈተዋል፡፡ የተደራጁ ወጣቶች ነባር ነዋሪዎችን አስወጥተው ውርሱን የሚከፋፈሉበት ስነ ስርዓት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የተዘጋጀው በአካባቢው የመንግሥት አመራሮች መሪነት እንደሆነም ከተፈናቃዮች የሰማነው ሀቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዝግጅቱ ላይ የሙዚቃ ፕሮግራሙን እንዲያቀርብ የተጋበዘው የሙዚቀኞች ቡድን ወደ ስነ ስርዓቱ እያመራ ሳለ ተፈናቃዮች ሜዳ ላይ ወድቀው በማየቱ ‹‹አልዘፍንም›› ብሎ መመለሱ ሰብዓዊነት የታየበት ነው፡፡
አቶ ለማ መገርሳ የአዲስ አበባን የሕዝብ ስብጥር ስለመቀየር የተናገሩትን ቢያስተባብሉም ከሶማሌ ‹ክልል› የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን በአዲስ አበባ አንድ የመኖሪያ መንደር ውስጥ እንዲሰፍሩ የማድረጉ እንቅስቃሴ የወረራው አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ይህ የሰፈራ ቅኝ ግዛት (Settler Colonialism) ጭምር ነው፡፡ በአንፃሩ ጥቂት የማይባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሁለት መንገድ ማንነታቸው እየተለየ ተፈናቅለዋል፡፡ አንደኛው በማንነታቸው እየተለዩ በሕገ ወጥ ሰፋሪነት ተፈርጀው የተፈናቀሉ ናቸው፡፡ እነኝህ ተፈናቃዮች በአመዛኙ የአማራና የጉራጌ ተወላጆች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከኦሮሞ ተወላጆች ውጭ ያሉ ነዋሪዎች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን አልፎ አልፎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ኦሮሞዎችንም ያካተተ ነው፡፡ ለዚህ የቦሌ ወረገኑ ተፈናቃዮች ምስክሮች ናቸው፡፡ ሁለተኛው በልማት ተነሽነት ሰበብ የሚደረግ ማፈናቀል ነው፡፡ ይህኛው ማፈናቀል ምትክ የሚሰጥ በመሆኑ ፈፅሞ ከከተማ የሚያስወጣ አይደለም፡፡ ነገር ግን ተመሳሳይ ማንነት እና ስነ ልቦና ያላቸው ዜጎች በአንድ መንደር እንዳይኖሩ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ በመበታተን ማንነታቸውን ለማጥፋትና ሌላ ስነ ልቦና እንዲላመዱ የሚያደርግ ነው፡፡ ከእነኝህ ምክንያቶች በተጨማሪም በኮሮና ተህዋሲ ወረርሽኝ በማሳበብ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው ከከተማዋ እንዲወጡም ተደርጓል፡፡ ከሁለት መቶ በላይ የጉልበት ሰራተኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ከአዲስ አበባ በአምስት ተሸከርካሪዎች ተጭነው በሌሊት ወደ ባሕር ዳር ተወስደዋል፡፡ ከአዲስ አበባ በማናለብኝነት የወሰዳቸው ከተማ አስተዳድሩ ባሕር ዳር ላይ በግድ የለሽነት በትኗቸው ተመልሷል፡፡
በታከለ ኡማ የሚመራው አስተዳድር ዜጎችን ሰበብ ፈጥሮም ይሁን ያለ ሰበብ እያፈናቀለ በምትኩ ደግሞ የኦሮሞ ተወላጆችን በመምረጥ ወደ ከተማዋ ያስገባል፡፡ ከሶማሌ የተፈናቀሉት ኦሮሞዎች ብቻ አልነበሩም፡፡ የመኖሪያ መንደር ተገንብቶ የተሰጠው ግን ለእነርሱ ነው፡፡ በአንፃሩ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ለጋራ መኖሪያ ቤት ሲቆጥብ የኖረው የአዲስ አበባ ነዋሪ የቤት ባለቤትነቱን ተነጥቋል፡፡ 2 ሺህ 4 መቶ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መጥፋታቸውም በሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን በደል ድርብርብ አድርጎታል፡፡ መገናኛ ገቢዎች ባለሥጣን አካባቢ ያለ የጋራ መኖሪያ መንደር ለመንግሥት ባለሥልጣናት ተላልፎ መሰጠቱም የአዲስ አበባን ሕዝብ ከኗሪነት ወደ አኗኗሪነት የቀየረ ይመስላል፡፡
አዲሱ የገዳ ወረራ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚፈፀምባቸው መንገዶች መካከል የከተማ ግብርና የሚሉት ፕሮጀክትም ይገኝበታል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ስም ‹የልማት ተነሽ አርሶ አደር ልጅ› በሚል ሰበብ ከአዲስ አበባ ውጭ ይኖሩ የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ከተማዋ እንዲገቡና መሬት እንዲታደሉ ተደርጓል፡፡ ወረራው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም ለመስፋፋት እያኮበኮበ ይመስላል፡፡
የሆነው ሆኖ በኦሮሚያ የሚኖረው አማራ ከፍተኛ ቢሆንም የኦሮሚያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ውክልና የለውም፡፡ በአንፃሩ በአማራ ‹ክልል› የሚኖሩ ኦሮሞዎች በራሳቸው ልዩ ዞን ይመራሉ፡፡
መንግሥት ይፋ ያደረገው አሃዝ የጉራጌ ሕዝብ ቁጥር ከ1.9 ሚሊዮን እንደማይበልጥ ይገልፃል፡፡ የጌራጌ ሕዝባዊ ንቅናቄ (ጉሕን) አጠናሁት ባለው መሰረት ደግሞ ቁጥሩ ወደ 15 ሚሊዮን ያሻቅባል፡፡ ለአሀዙ ማሽቆልቆል በምክንያትነት የሚጠቀሰውም ‹በኦሮሚያ የሚኖሩ ጉራጌዎች በኦሮሞነት ተቆጥረዋል› የሚል ነው፡፡ ቁጥራቸው እያሽቆለቆለ ከመጡ ነገዶች መካከል አንዱ የሆነው አርጎባ ባለፈው አመት ጥቃት ተከፍቶበት ነበር፡፡ በወቅቱ ግጭቱ የተፈጠረው በአርጎባዎችና በከረዩዎች መካከል ቢሆንም በአካባቢው የሠፈሩት የኦነግ ሸኔ አባላት ለከረዩዎች የትጥቅ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
በአጠቃላይ ወረራው በሁለት መንገዶች እየተደረገ ነው፡፡ አንደኛው በግልፅ በመግደል እና በማፈናቀል እየተፈፀመ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ነባር ማንነትን በማጥፋት እየተፈፀመ ያለ ነው፡፡ ለአብነትም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመስቀል እና የጥምቀት በዓላት ማክበሪያ የሆኑትን መስቀል አደባባይን እና ጃን ሜዳን በልማት ሰበብ እየተፈፀመ ያለው ማራከስ ይጠቀሳል፡፡ በአንፃሩ ለኢሬቻ ማክበሪያ ሰው ሰራሽ ሀይቅ አዲስ አበባ ላይ እንደሚሠራም ቃል ተገብቷል፡፡ ይህ እንደ ስውር የዘር ፍጅት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከዚህ በፊት በቤተ ክርስቲያኗ የመሬት ይዞታዎች ላይ ተነስቶ የነበረው ሰጣገባ የሚታወስ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንን በማራከስ፣ ቅርሶችን በማውደም እየተገረገ ያለው ታሪክን ሰርዞ ልብ ወለድ የመፃፍ እንቅስቃሴ ከግራኝ አሕመድ ወረራ ጋር ይመሳሰላል፡፡