>

ወራሪውን ተወራሪ ጨፍጫፊውን ተጨፍጫፊ ያደረገው አሳፋሪው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ መግለጫ...!!! (ሙሉአለም ገብረመድህን)

ወራሪውን ተወራሪ ጨፍጫፊውን ተጨፍጫፊ ያደረገው አሳፋሪው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ መግለጫ…!!!
ሙሉአለም ገብረመድህን

 

*….በትላንትናው ምሽት ከኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ ቤት በኦሮምኛ ቋንቋ ያወጣው መግለጫ በይዘትም ሆነ በአቀራረብ ደረጃ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚጋጭ፣ የተወረረውን የአማራ መንግሥት  “ወራሪ” ፣ ጥቃት የተከፈተበትን ልዩ ኃይላችንን “ጨፍጫፊ” አድርጎ ያቀረበ በሕግና በሞራል የሚያስጠይቅ መግለጫ ነው..  !!
ራሱን “የኦሮሞ ብልጽግና” ብሎ የሚጠራው ጸረ-ሕዝብ ኃይል ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ በአማራ መንግሥት እና የሀገረ-መንግሥቱ ዘብ የሆነው መከላከያ ሠራዊት ከጀርባ ሲወጋ የታደገውንና በህልውና ዘመቻው ግዙፍ አበርክቶ የተወጣውን ልዩ ኃይላችን ላይ በታሪክ ፊት ሲጠቀስ የሚኖር ክህደት ፈጽሞበታል! 
 
በመግለጫው ላይ በ Non-State Actors ወረራና ጥቃት የተፈጸመበትን የአማራ ክልል መንግሥትና ልዩ ኃይላችንን፦
 
“ለስልጣን ጥም ተብሎ ሰላማዊ ኦሮሞ ህዝብ በአማራ የጸጥታ ኃይል ተጨፍጭፏል። እናወግዛለን። የንጹሃን ገበሬዎች ንብረትና ህይወት ከባድ ጉዳት ደርሶበታል። ኦነግ ሸኔ ኦሮሞ ልዩ ዞን እንደማይንቀሳቀስ እየታወቀ የአማራ ክልል ‘ኦነግ ሸኔ ነው’ ያለው ቅጥፈት ነው። ይህን ብልጽግና አጥብቆ ያወግዛል።”
 
ሲል በኦሮምኛ ቋንቋ የበሬ ወለደ መግለጫ  አውጥቷል። እውነታው ግን መጋቢት 09/2013 በአጣየ በኩል የጀመረው የኦነግ ሸኔ ጥቃት በሥልጠናና በሎጀስቲክስ የሚደገፈው ይሄ ጸረ-ሕዝብ የሆነ ኃይል ነው። አጣየና ሸዋ ሮቢትን ያዳረሰው ወረራና ጥቃት ወደ ከሚሴ በመዛመት መጋቢት 12-13/2013 አማራውን ነጥሎ የማጥቃት ቤት ንብረቱን የማውደም ውንጀል ተፈጽሟል። በተለይም በትላንትናው ዕለት በከሚሴ ከተማ ለተፈጸመው ጥቃት የልዩ ዞኑ አስተዳደሮች  ከኦሮሞ ብልጽጌና ጋር የጋራ ፖለቲካ አይዲዮሎጅ፣ ግብና ዓላማ ካላቸው Non-State Actors ጋር ሲተባበር ውሏል። ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን ወደ ከተማው ተንቀሳቅሰው የነበሩ የልዩ ኃይላችን አባላት ላይ ጥቃት ተከፍቶባቸው የተሰው ጓዶች አስከሬን እንዳይነሳ እስከማድረግ የደረሰ ደባ ፈጽመዋል። 
 
የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር፣ ንጹሃንን ለመጠበቅ የግዳጅ ስምሪት ላይ ለዋለው የአማራ ልዩ ኃይል ስንቅና ትጥቅ እንዳይደርሰው መንገድ እስከማዘጋት ደርሰዋል። ከፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር ለማጋጨት ሴራዎች ተወጥነው ነበር፣ አልተሳኩም እንጅ! ሌሎች እዚህ ላይ ሊጠቀሱ የማይችሉ በጣም አሳፋሪ ደባዎችና ክህደቶች በልዩ ኃይላችን ላይ  ተፈጽመዋል። 
 
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ጸረ-ሕዝብ የሆነው የኦሮሞ ብልጽግና በመግለጫው ላይ፦
 
“የአማራ ጸጥታ ኃይል የፈጸመው የንጹሃን ኦሮሞዎች ፍጅት ዋና አላማ  ኦሮሚያ ውስጥ አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት ታስቦ ” ነው ይለናል። 
 
ይህ ሆን ተብሎ ታስቦና ታቅዶ በቀጣይ በአማራው ላይ ሊያካሂዱት ላሰቡት ፍጅት ተጠያቂ ላለመሆን የሚደረግ ጥረት ነው።  በጥቅሉ በትላንትናው ምሽት ከኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ ቤት በኦሮምኛ ቋንቋ ያወጣው መግለጫ በይዘትም ሆነ በአቀራረብ ደረጃ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚጋጭ፣ የተወረረውን የአማራ መንግሥት  “ወራሪ” ፣ ጥቃት የተከፈተበትን ልዩ ኃይላችንን “ጨፍጫፊ” አድርጎ ያቀረበ በሕግና በሞራል የሚያስጠይቅ መግለጫ ነው ያወጣው። 
 
ከምንም በላይ ትህነግን የመደምሰሱና ሀገረ-መንግሥቱን የመታደግ የግዳጅ ተልዕኮው ባልተጠናቀቀበት በዚህ ወቅት፣ በህልውና ትግሉ ውድ ዋጋ የከፈለውን የአማራ ልዩ ኃይልና የክልሉን መንግሥት በNon-State Actors በውረርና ማጥቃት፣ ይህን ተግባር በሀሰት ውንጀላ ገልብጦ ለሕዝብና ለሚዲያ ማቅረብ የሀገር ክህደት ነው! የተፈለገው ነገር የአማራና የኢትዮጵያ መከታ ሆኖ በደማቅ መስዋዕትነቱ ሀገርና ሕዝብን እየታደገ ያለውን የአማራ ልዩ ኃይልና የክልሉን አመራር ገጽታ በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ፊት ማጠልሸትና ወንጀለኛ አድርጎ ማቅረብ ነው። ይህ ለአማራ ሕዝብ የተዘጋጀ ወጥመድ ነው። 
***
አቅጣጫዎች
~~
=> ክህደት የተፈጸመበት የአማራ ክልል መንግሥት ስለወረራውና ጥቃቱ፣ ከሚሴ ውስጥ ስለተፈጸሙ ሴራዎች ለመላ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች፣ ማብራሪያና መግለጫ ሊሰጥ ይገባል፤ የውስጥ ጉዳያችን ቢሆንም ቅሉ እንደለአስፈላጊነቱ ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን ማሳወቅ ተገቢ ነው፤ 
 
=>የሕዝብ ግንኙነት ሥራው ኃይል የሚያሰባስብ እንጅ የሚበትን እንዳይሆን የቀውስ ጊዜ መመሪያ መሆን በሚችል የሕዝብ ግንኙነት ፕሮቶኮል መመራት ይኖርበታል፤ እንደአልፈላጊነቱ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የሚለጡ የዞንና የወረዳ ኮምዩኒኬተሮችኖ ሁኔዎችን ሲያስረዱ በጥንቃቄ መሆን ይኖርበታል፤  
 
=> በየትኞቹም ዞን፣ ከተማና ወረዳዎች የአስተዳደርና ፀጥታ መዋቅሩ የፀጥታ ኃይሉን አቀናጅቶ የመምራት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ባይገባም ከርዕሰ- መስተዳድሩ የሚጀምረውን ተዋረዳዊ የዕዝ ሰንሰለቱን ማስጠበቅ የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፤ 
 
=> የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዮ ዞን በመባል የሚጠራው አስተዳደራዊ መዋቅር ጤናማ ያልሆነ የአመራር ስምሪት ያለበት ቦታ እንደሆነ ይታወቃል። ወቅቱ የጸጥታ ጉዳይን ቁልፍ ተግባር አድርጎ መውሰድን የሚጠይቅ በመሆኑ፣
ይህ የቀውስ ጊዜ እስከሚያልፍ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ከማዕከል/ከክልል በልዩ ሁኔታ ሊያዙ ይገባል፤ 
 
የኦሮሞ ብሄረሰብ በመባል የሚጠራው ይህ ልዮ ዞን ብዝሃነትን ከማስተናገድ ይልቅ ቀድሞውንም አማራን በመስታውት ቤት ውስጥ የማስቀመጥ ዓላማ ይዞ የተመሰረተ መሆኑ ይታወቃልና የጽንፈኛውን ኃይል የሽብር መረብ ጊዜ ሰጥቶ ማጽዳት ይገባል። 
 
=> ጉዳዮን የሃይማኖታዊ ግጭት መልክ ለመስጠት የሚጥሩአክራሪና ጽንፈኛ ኃይሎች በማያቋርጠው የሚዲያ ፕሮፖጋንዳቸው ላይ ግጭቱን ለማስፋፋት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በተለይም የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ ኃይሎችን ወደ ኮምበልቻ አስርጎ የማስገባት ሙከራዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ኮምበልቻ ልዩ ጥበቃ ያስፈልጋታል፤ 
 
=>የአማራ ክልል የኃይማኖት ተቋማት የጋራ ጉባዔ ክልሉን በሃይማኖት ግጭት ለማተራመስ የሚፈልጉ አክራሪና ጽንፈኛ ኃይሎችን በጋራ መግለጫ እንዲያወግዝ መድረክ ማመቻቸት ይገባል፤ 
***
 
የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ አንቂዎች በጥቅሉ የአማራ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ ልንቆም ይገባል። ውድቀታችንም ሆነ ስኬታችን በእኛው ጥንካሬ ልክ ይወሰናል። አማራ ከወንድም ሕዝቦች ጋር በጋራ በገነባት ሀገር በተደጋጋሚ ጭፍጨፋዎች ፍጹም ባይተዋርነት እንዲሰማው ለማድረግ እየጣሩ ያሉ እኩያን ኃይሎች በቆፈሩት ጉድጓድ መቀበራቸው አይቀርም። እውነት ይዘናልና የአማራ ወዳጆች ብቻ ሳይሆኑ የፍትህ ጉዳይ ግድ የሚላቸው የሰው ልጆች ሁሉ ከእኛ ጎን እንዲሰለፉ በርትተን እንስራ!!
Filed in: Amharic