>

የምክር ቤቱ አሠራር በሴራ ፖለቲካ ተጥሷል!  (ሙሉአለም ገ.መድህን)

የምክር ቤቱ አሠራር በሴራ ፖለቲካ ተጥሷል! 

ሙሉአለም ገ.መድህን

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአባላት ሥነ-ምግባርና ደንብ አሰራሩ መሰረት፣ በፓርላማ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ስብሰባው ከመካሄዱ ከ5-3 ቀን ድረስ በጽሁፍ ገቢ መሆን አለባቸው።
ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በየአጀንዳው ለይቶና አደራጅቶ ወደ ጠ/ሚ/ጽ/ቤት የሚልከው አፈ-ጉባዔ ጽ/ቤት ቢሆንም፣ የጥያቄዎቹን ይዘት ከፖለቲካ፣ ከሕግ፣ ከሞራል፣ ወዘተ አኳያ የሚገመግመው “አስተባባሪ ኮሚቴ” የሚባለው ቡድን ነው።
እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር፥  የኢትዮጵያ ፓርላማ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አሰራርን ዛሬም ድረስ የሚከተል መሆኑን ነው። አስተባባሪ ኮሚቴ የሚባለው ስብስብ በቀድሞው ኢህአዴግ የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች የመሰረታዊ ድርጅት ተጠሪዎች የሚገኙበት ሲሆን፤ ሰብሳቢያቸው በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ተብሎ የሚመደበው አካል ነው። በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ብልጽግና ወኪል የሆነው አቶ ጫላ ለሚ የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነው። በቀደመው አሰራር የአስተባባሪ ኮሚቴው ዋና ተልዕኮ ከፓርቲው ፍላጎትና አቋም ውጭ አባላቱ እንዳያፈነግጡ ጠርንፎ መያዝ ነው።
ከመጋቢት 2010ሩ የአመራር ለውጥ ወዲህ ይህ አሰራር እንዳልተለወጠ፣ ከብልጽግና ፓርቲ ምስረታ በኋላ የክልል ተጠሪ በሚል አስተባባሪ ኮሚቴውን በተለመደ ተልዕኮው እንዳስቀጠሉት መረጃው አለኝ። አሁንም ቢሆን አስተባባሪ ኮማቴውን የሚመራው በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ተብሎ የተመደበው አቶ ጫላ ለሚ ነው።
አስተባባሪ ኮሚቴው ከፓርላማው አመራር ጋር ሆኖ ጥያቄዎቹን ፈትሾና ገምግሞ ከስብሰባው ሦስት ቀናት በፊት  ወደ ጠ/ሚ/ጽ/ቤት የሚልክ ቢሆንም በዛሬው የምክር ቤቱ ውሎ ግን በትላንትናው ምሽት የኦሮሞ ብልጽግና ካወጣው መግለጫ ጋር የሚናበብና ከሃያ አራት ሰዓት ወዲህ የተከሰቱ ክስተቶች ጨምሮ በተዛባና አደገኛ በሆነ የፖለቲካ አተያይ ከሁለት የም/ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ሲቀርቡ ተመልክተናል።
ምክር ቤቱ ጠ/ሩ በተገኙበት በመደበኛም ሆነ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሲመክር ጥያቄዎቹ ቀድመው የገቡ ቢሆን እንኳ፣ ማሻሻያ ለማድረግ ወይንም አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚንስትሩ ማቅረብ ቢያስፈልግ ለአስተባባሪ ኮሚቴው ድጋሚ ማቅረብ የግድ ይላል።  ይህ የሚሆነው ከፖለቲካ ጥርነፋው ባሻገር በሃይማኖትም ይሁን በብሔር ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሱ፣ ጥላቻንና ግጭትን የሚያባብሱ፣ የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ወዘተ ጥያቄዎች በድንገት እንዳይቀርቡና ችግሮች እንዳይፈጠሩ በሚል ነው። ዛሬ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው!
በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል የከሚሴ ልዩ ዞን የምርጫ ወረዳዎች የፓርላማ ተመራጭ የሆኑ ሁለት የምክር ቤት አባላት ያቀረቡት ጥያቄ በይዘት ደረጃ የምክር ቤቱን የአባላት ሥነ-ምግባርና ደንብ የሚቃረን፣ በክልሉ ውስጥ ሃይማኖታዊ መካረሮችን የሚያባብስ፣ የሥልጠናና ሎጀስቲክስ ድጋፍ ያለውን አሸባሪ ታጣቂ ኃይልን ውድመት የሚክድ፣ የአማራ ክልልን መንግሥት፣ የፖለቲካ አመራሩንና የክልሉን ልዩ ኃይል ገጽታና እውነተኛ ማንነት የማይገለጽ ስም ማጥፋትና ጥላቻ የታየበት በምክር ቤት አባል ደረጃ የማይጠበቅ ነበር።
በተለይም የክልሉን ልዩ ኃይል “የጦር ወንጀል ፈጽሟል” በሚል ከአንደኛው የምክር ቤት አባል የቀረበው ስም ማጥፋት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ስም አጥፊውን ብቻ ሳይሆን የምክር ቤቱን አስተባባሪና የፓርላማ አመራሩን በአሰራር ደረጃ ያስጠይቃል። እንደ ተቋም በ FDRE Defense Force – የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት  እና በከፍተኛ  የጦር መኮንኖች ደረጃ ሕዝባዊነቱና ሀገር ወዳድነቱ የተመሰከረለትን የአማራ ልዩ ኃይል በምክር ቤት ደረጃ ከነባር እሴቶቹ በሚጣረስ መልኩ “የጦር ወንጀል ፈጽሟል” በሚል በድፍረት የሃሰት ክስ ያቀረበው ሰው የተማመነው ነገር የምክር ቤቱን አሰራር ሳይሆን ከጀርባው የሚገፉትን የኦሮሞ ብልጽግና ሴረኛ ኃይሎችን ነው።
የምክር ቤት አባላት ለህሊናቸው፣ ለመረጣቸው ሕዝብና ለሕገ-መንግሥቱ ታማኝ ሊሆኑ እንደሚገባ አያከራክርም፤ ይህም ሲባል ለመረጣቸው ሕዝብ ድምጽ ሲሆኑ፣ ከህሊናቸው ጋር ተጣልተው መሆን የለበትም፤ ሊሆንም አይገባም! በምርመራ ያልተረጋገጠን ነገር የአንድን ግዙፍ ክልል የፖለቲካና የጸጥታ አመራር “የጦር ወንጀል ፈጽሟል” ማለት ለህሊናቸውም ሆነ ቁመንለታል ለሚሉት ህገ-መንግሥት አለመታመን ነው። ከዚህም አልፎ በምክር ቤቱ የአባላት ሥነ-ምግባርና ደንብ መሰረት ተጠያቂነትን የሚያስከትል ጥፋት ነው።
በጥቅሉ የሁለቱ የምክር ቤት አባላት የዛሬ ንግግር ፥ ፓርላማው በምን አይነት ሸፍጥ እንደተሞላና የሴራ ፖለቲካው ትድግና የት እንደደረሰ ማሳያ ነው። የአስፈጻሚው አካል ፍጹም ጥገኛ የሆነው ምክር ቤቱ በታሪኩ ውስጥ  በርካታ ቅሌቶች የታዩበት ቢሆንም ይህኛው ግን እጅግ የተለየ ነው። አማራን መጥላትና ውድቀቱን መመኘት ያለና የነበረ ቢሆንም በምክር ቤት ደረጃ ያውም ከዛው ከክልሉ በወጡ ሰዎች የጠላት ቢላ ሆነው እንዲህ ሲወጉት የታየበት አጋጣሚ ግን አልነበረም!!!
ለጊዜው በአቶ አብርሃም አለኸኝ ጥሩነህ/Abrham Alehegn Tiruneh የሚመራው የአማራ ብልጽግና ጽ/ቤት የአማራ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተጠሪ የሆኑትን አቶ አሰፋ ጫቅሉን በጽ/ቤቱ ጠርቶ ማብራሪያ መጠየቅ አለበት።
በክልሉ የተፈጸመውን ግልጽ ወረራና ጥቃት በመካድ ጩኸት የቀሙ፣ የክልሉን መንግሥት አመራርና ሕዝባዊነት መለያው የሆነውን የክልሉን ልዩ ኃይል ስም ያጠፉትን አካላት በምክር ቤቱ የአባላት ሥነ-ምግባርና ደንብ መሰረት እንዲጠየቁ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በተመሳሳይ እንደዚህ አይነት ሕዝብና ሕዝብን በሃይማኖትና በብሔር የሚያፋጅ፣ ቅራኔን የሚያባብስ፣ ሕጋዊ እውቅናና ሥልጣን ያለውን የክልሉን መንግሥት ስም የሚያጠፋና በሃሰት የሚወነጅል ክስ በምክርቤቱ እንዲቀርብ ያደረጉ አካላት ሊጠየቁ ይገባል።
ምክር ቤቱም ያለስሙ ስም ሲሰጠው ለዋለው የአማራ ክልል መንግሥትና የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል።
መዘንጋት የሌለበት ነገር የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የትህነግን ጥቃት ባይመክትና ከበባ ውስጥ ለገባው የሀገር መከላከያ  ሠራዊት ባይደርስለት ኑሮ ይህ ፓርላማ ዛሬ ላይ ተበትኖ ነበር!
ሀገረ-መንግሥቱን የታደገው የአማራ ልዩ ብሔራዊ ኃይል ሽልማት እንጅ ስም ማጥፋት ፈጽሞ አይገባውም !
Filed in: Amharic