>
5:33 pm - Friday December 5, 4110

ወደ 13 የሚደርሱት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት የጋራ መግለጫ አወጡ...!!! ቪ.ኦ.ኤ

ወደ 13 የሚደርሱት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት የጋራ መግለጫ አወጡ…!!!
ቪ.ኦ.ኤ

ዋሽንግተን ዲሲ


በተባበሩት መንግሥታት ሥር ያሉትን ጨምሮ፣ ወደ 13 የሚደርሱት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት መሪዎች፣ በትናንትናው እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በኢትዮጵያው ትግራይ ክልል ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው፣ በተለይም ሴቶችና ህጻናትን እየደረሰባቸው ካለው ጥቃት መታደግ የሚቻለው፣ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶችና ድንጋጌዎችን ሙሉ ለሙሉ መሠረት ባደረገው የተቀናጀ ጥረት ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሌላም በኩል የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ በዛሬ እለት በሰጡት መግለጫ፣ በምዕራብና ማዕከላዊ ትግራይ ባንዳንድ አካባቢዎች ያለውን ግጭት በመሸሽ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ሽሬ አክሱም እና አድዋ መምጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በምግብ እጥረት ለተጎዱ ተፈናቃዮችም መንግሥት ይፋ ባደረገው የጭነት ማጓጓዣ የስምሪት ሥርዓት መሰረት፣ ወደ ስፍራው በመሄድ፣ የሰብአዊ እርዳታዎችን የሰብአዊ እርዳታ ሰጭዎች በቦታው ደርሰው የተሻለ እርዳታ እንዲሰጡ እያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሰብአዊ ቀውሱ አሁንም በከፋ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

በኒው ዮርክ፣ ጄንቭ እና ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙት 13ቱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በትናንትናው እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ

“የሰብአዊ ቀውሱ እየተባባሰበት ባለው የኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ፣ አስገድዶ መድፈርና ሌሎች አሰቃቂ መልክ ያላቸው የወሲብ ጥቃቶች፣ በሁሉም ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደረጉ በደሎች፣ ከፍተኛው ደረጃ መድረሳቸውን አስመልክቶ የሚወጡ ሪፖርቶች አሁንም እንደቀጠሉ” መሆኑን ገልጸው፡፡ “ይህ መቆም አለበት፡፡” ብለዋል፡፡

ድርጅቶቹ በመግለጫቸው “በግጭቱ ውስጥ የሚገኙ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ወገኖች በሙሉ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህጎች መሠረት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡” በማለት

“እነዚህ ኃይሎች የሰላማዊ ዜጎችን በተለይም ሴቶችና ህጻናትን ከሁሉም የሰብአዊ ጥቃቶች እንዲጠብቋቸው፣ በተለይም ሁሉንም ወሲብ ነክ ጥቃቶች በግልጽ ማውገዝና ጥቃቶች በተፈጸሙባቸው አካባቢዎችም ወንጀለኞቹን ለህግ የማቅረብ እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን “ ብለዋል፡፡

የጥቃቱ ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ህጻናት ጤንነታቸውና ማህበራዊ ደህንነታቸው፣ የፍትህ አገልግሎታቸው ከፍተኛ ችግር እየገጠመው መሆኑን ሪፖርቶች እያመላከቱ ነው፡፡ መሆኑን ገልጸው “በትግራይ ክልል በተለይም ለሴቶችና ህጻናት የሚደረገው እርዳታ የተሟላ የሚሆነው ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶችና ህጎችን ሙሉ ለሙሉ መሠረት ባደረገው የተቀናጀ ጥረት ብቻ መሆኑን” አስታውቀዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

https://amharic.voanews.com/a/gender-based-violence-in-Tigray-ethiopia/5825732.html

Filed in: Amharic