>

"የአማራና የኦሮሞ ህዝብ አንድ ነው!!!"  የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ 

“የአማራና የኦሮሞ ህዝብ አንድ ነው!!!”

 የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ 

 

በክልላችን ሰሜን ሽዋ ዞንና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በወንድማማቾች መካከል የተለኮሰው እሳት ሳይጠፋ ፣ የወደቁ የንጹሃን አስከሬኖች ሳይነሱ፣ የወደመው ንብረት፣ የተቃጠሉ ቤተ እምነቶችና መኖርያ ጎጆዎች፣ በጥፋት መልዕክተኞች የተቀጣጠለው ሰደድ እሳት የለበለባቸው የእህል ክምሮችና የእንስሳት መኖዎች በውል ሳይለዩ፣ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈትቤት እራሱ ከሳሽና ፈራጅ የሆነበትን መግለጫ ለተመለከተ ሰው ፖለቲካችን ገና በአዝጋሚ የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚገኝ፣ የምንመራውን ህዝብ የማይመጥን፣ ከሀገርና ከህዝብ ክብር በእጅጉ ወርዶ ጫማችን ስር የሚገኝ መሆኑን ያረጋግጣል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አካባቢው በችግር የታመቀ፣ ውስብስብ አደጋ ያለበትና የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ የሚጫነው መሆኑን ከብሔረሰብ ዞኑ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ጋር በተደጋጋሚ የገመገመው የአደረ አጀንዳ መሆኑን ያስታውሳል።
ይህ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ በተወሰዱ ስምሪቶች እርምጃ የተወሰደባቸው፣ በቁጥጥር ስር የሚገኙና በጥብቅ የሚፈለጉ የኦነግ ሸኔ አባላት መኖራቸው አዲስ መረጃ አይደለም።
ችግሩ በተፈጠረባቸው ሁሉም አካባቢዎች ክልሉን ጨምሮ የሁለቱም ዞኖች  አመራሮች ለተከታታይ ቀናት ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል አካባቢው ሰላማዊ መሆኑና የእርስ በእርስ መተማመን የተፈጠረበት ምህዳር መኖሩን ፓርቲያችን ይገነዘባል።
ይሁን እንጂ ኦነግ ሸኔና መሰል ፅንፈኛ ኃይሎች በተደጋጋሚ በሚለኩሱት እሳት በአካባቢው ነዋሪዎችና ከአጎራባች የአፋር  ክልል ነዋሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች እንደነበሩ ያልተቋረጠ ክስተት ነው።
በተመሳሳይ በአካባቢው ስውር ስልጠናዎችና አደረጃጀቶች እንዳሉ፣ በሂደትም ለንጹሃን አመራሮች ሳይቀር አደጋ ሊሆን እንደሚችል ከዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በግልም  በጋራም ሳይነሳ ያለፈበት ጊዜ አልነበረም።
አልፎ አልፎም በጥቂት የዞኑ አመራሮች ላይ የሚስተዋለውን የሁለት ክልል አመራር የመምሰል ዝንባሌን ለማስተካከል ትግል ተደርጓል።
ይህ ሁሉ ጥሬ ሀቅ ባለበት ነባራዊ ሁኔታ የአማራ ልዩ ኃይል ከአካባቢው መንቀሳቀሱንና ፓርቲያችን ስልጠና መጀመሩን ከህቡዕ አደረጃጀታቸው የተረዱ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ለተነሱለት የጥፋት ዓላማ ስኬት ያግዘናል ያሉትን ዘዴ ተጠቅመው  የሃይማኖት መሪና የሀገር ሽማግሌ በመግደል ግጭት መጀመራቸው የማይካድ ሀቅ ነው።
የአካባቢው ጉምቱ ሽማግሌዎች ችግሩን በጥንቃቄ ተመልክተው በእርቅ ለመፍታት የተስማሙ ቢሆንም “ሰዶ ማሳደድ ቢያምርህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ” እንዲሉ ከባድ መሳርያና ተወርዋሪ ቦንብ እስከአፍንጫው የታጠቀ የኦነግ ሸኔ ሰራዊት አካባቢውን ከልክ በላይ በመውረር ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ፈጽሟል።
ይህንን ኃይል መመከት ተፈጥሯዊ መብት ቢሆንም ቅሉ በአካባቢው የተሸረበው ሴራ ለጠላት የሚመች ስለሆነ ችግሩን በጋራ ከመታገል ይልቅ ፅንፈኛ ሚዲያዎችንና የረዥም ዕይታ ችግር ተጠቂ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመጠቀም መፈራረጅን ያስቀደመ የአመራር ብልሽት አጋጥሟል።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ያወጣው መግለጫም ከችግር ፈቺነቱ ይልቅ የአእምሮን ሚዛን ያልጠበቀ ችኩልነት የሚጫነው፣ ተራ ውግንና ያጠላበት ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ ሆኖ አግኝተነዋል። ስለሆነም የሚከተለውን ባለአምስት ነጥብ መግለጫ አውጥተናል።
1. በሰሜን ሽዋ ዞንና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ወንድማማቾች መካከል ኦነግ ሸኔና የተልዕኮው ምርኮ የሆኑ ግለሰቦች የፈጠሩትን ድንገተኛ ጥቃት እያወገዝን ጥቃቱን ተከትሎ  በህይወታቸው፣ በአካላቸውና በንብረታቸው ጉዳት ለደረሰባቸው የፌዴራልና የክልላችን የጸጥታ አካላት እና  ወንድማማቾች ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን።
ፓርቲያችን የአማራ ብልጽግና ጽሕፈት ቤትም ጉዳት የደረሰባቸው የክልላችን ነዋሪዎችን ለማቋቋም እንደወትሮው ሁሉ በጽናት ይታገላል።
2. የአማራና የኦሮሞ ህዝብ የበርካታ ክፍለ ዘመናት ትስስርና ውህደት ያላቸው፣ ክፉና ደግ የሆነውን የታሪክ አቀበት አብረው የወጡ፣ ረዥሙን የህይወት መንገድ ተጉዘው ሀገር ያቀኑ፣ ማንም ባለጊዜ ሊነጣጥላቸው ከቶ የማይችል ውሁድ ህዝብ ናቸው።
ስለሆነም ህዝብን መያዣ በማድረግ የግጭት ነጋሪት መጎሰም ለማናችንም ስለማይጠቅም የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንታገል ለሁሉም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጥሪ እናቀርባለን።
3. የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ሁሉም የዴሞክራሲ ኃይሎች ለችግሩ ተደማሪ ችግር  ከመሆን ይልቅ መፍትሄው ላይ በመተባበርና በመረባረብ ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ መታገል ይኖርብናል። በተፈጠረው ችግር የደረሰ ያልተገባ ጉዳት አለ ከተባለ የሚመለከተው አካል ገብቶ ጉዳዩን እንዲያጣራና በኃላፊነት ስሜት ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ  የፓርቲያችን ተልዕኮ ነው። ከዚህ ውጪ በተመሳሳይ የሀገር ሉዓላዊነትን በመጠበቅ ህዝብና መንግስት የሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት በበርካታ ግንባሮች ተሰልፎ ለህይወቱ ሳይሳሳ አኩሪ ተጋድሎና የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ያለን የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ መውቀስና ተጠያቂ ማድረግ ፍጹም ነውር ከመሆኑም በላይ የልዩ ኃይላችንንም ሆነ የሚሊሻችንን ክብር የማይመጥን ፍረጃ እንደሆነ ልናሰምርበት እንፈልጋለን።
በተመሳሳይ በአካባቢው ኦነግ ሸኔ የለም ብሎ መበየን ለብዙ ትርጉም ስለሚያጋልጥ ከእርባና ቢስ ሙግት ወጥተን በታሪክ አጋጣሚ እጃችን ላይ የወደቀውን የህዝብ አደራ በማስተዋልና በብልሀት እየተወጣን ሀገራችንንና ህዝባችንን እንደመዥገር ተጣብቆ እየተፈታተናት ከሚገኝ ፅንፈኝነት አንጻራዊ ነጻነታችንን መጠበቅ ይኖርብናል ብለን እናምናለን።
4. በክልላችን የተፈጠረው ይህ ችግር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተፈታተነን የቆየው ተረፈ ትህነግ ሰንኮፍ እንጂ አዲስ ጉዳይ አይደለም። ችግር በተፈጠረ ቁጥር የአማራንና የኦሮሞን ህዝብ በማጣላት ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው እንቅስቃሴ እንኳንስ የምርጫ ድባብ ተጭኖት ይቅርና ወትሮም ቢሆን የስልጣን ጥም ለሚፈታተናቸው ሱሰኞች ሰርግና ምላሽ ነው። ህዝብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎት በላይ ነው።
የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ከብልጽግና ፓርቲም በላይ ነው። ህዝቡ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችን ፈጠራቸው እንጂ በፓርቲዎችና በፖለቲከኞች የተፈጠረ ህዝብ የለም። ስለሆነም ከህዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የሚደረግን ማንኛውም እንቅስቃሴ ፓርቲያችን በጽኑ ያወግዛል።
5. ህዝብን በመያዣነት የሚጠቀም የፖለቲካ ፍልስፍናና መንግስታዊ እንቅስቃሴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም በአጽንኦት  እናሳስባለን። ኢትዮጵያ የመላ ኢትዮጵያውያን ናት። የፌዴራል መንግስትና ፓርቲያችን ብልጽግና የሚያደርጉትን ያልተቋረጠ ትግል በውል እንረዳለን። የሁሉም ክልሎች  ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤቶችም ሆኑ የየብሄራዊ ክልሎች መንግስታት በየቦታው የሚፈነዳውን ችግር ለመቆጣጠር እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ እንዳሉም ፓርቲያችን ይገነዘባል። ይሁን እንጂ ችግር በተፈጠረ ቁጥር በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ዛቻና ማስፈራርያ፣ ራሱን እንኳ ከቅርብ አደጋ እንዳይከላከል የሚፈጸምበት መድሎና ወከባ፣ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስና በፓርቲ ማዕቀፍ ተካቶ ትግል እንዳያደርግ የሚፈጸምበት ግፍና መድሎ ከእስከአሁኑ ይልቅ የወደፊቱ ያሳስበናል። ስለሆነም እርስ በእርስ መተራረማችንን ባንጠላውም ፓርቲያችን ትክክለኛ የህዝብ ፓርቲ ሆኖ ነጥሮ እንዲወጣ ለሁሉም ዜጎች የተመቸ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር አለበት ብለን እናምናለን። በጽናት የምንታገለውም ለዚህ ነው። ከዚህ ውጭ ያሉ ሁሉም አማራጮች ለማናችንም የማይጠቅሙ፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር  ሁላችንንም የሚጎዱና ወደተጠያቂነት አደባባይ የሚያደርሱ ስሁት መንገዶች ናቸው።
በመጨረሻም የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የብልጽግና ፓርቲ አካል እንጂ የተነጠለ ቅርጽም ሆነ ይዘት የሌለው በሀገር አቀፍ ትግል ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወት የለውጥ ኃይሎች ስብስብ መሆኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን።
በየጊዜው በሚፈጠሩ ቀውሶች ላይ ተንተርሰን የምናወጣቸው መግለጫዎች የተነጣይነት ወይም የተገንጣይነት ልክፍት ስላለብን ሳይሆን በገፊ ምክንያቶች ስለምንታጠርና ስለምንወጠር ብቻ ነው። የኢትዮጵያንና የሁሉንም ክልሎች ጥቅም የሚጎዳ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ በፍጹም አንዘፈቅም። የሚዘፈቅም ካለ ከብልሁ ህዝባችን ጋር ሆነን እናጠራዋለን እንጂ የትህነግንም ሆነ  የኦነግ ሸኔን እርካሽ መንገድ አንከተልም። ስለሆነም በማንኛውም ሁኔታ ህዝብንና አገርን እናስቀድማለን። ከቃላት ድርደራ በላይ ለተግባር እርብርብ ቅድሚያ እንሰጣለን። መንገዳችንም ሆነ ትልማችን ይኸው ነው።
ቅድሚያ ለአገርና ለህዝብ !!! 
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ  ጽሕፈት ቤት 
Filed in: Amharic