>

አገሬ?! (ጌታቸው አበራ)

 አገሬ?!

ጌታቸው አበራ


አገሬም አድጋለች¡ እንደሌሎች ሁላ፣

ሰማይ-ጠቀስ ፎቆች ሕንጻዋን ቆልላ፤

ገበሬዋን ገላ፣ በዘር-ዘር በሽታ፣

ድንግል መሬት ታቅፋ፣ ስንዴዋን ሸምታ፣

የዕድገት ምልክቷን ባዶ ቁጥር ጠርታ፣

ከዓለም ኢኮኖሚ ካንደኞቹ ተርታ፣

አገሬም አድጋለች¡ ቆማ ተንጠራርታ።

 

    አድጋለች አገሬም ጎዳና ዘርግታ፣

    ሽመል ባነገቡ ቄሮዎች ቱማታ፣

      ማንም ላያልፍበት በቋጥኝ ዘግታ፤

መጥቃለች አገሬ፣ በባህሉም ጎራ፣

በዩ-ቲዩብ፣ ፌስ ቡክ… ስሟ እስከሚጠራ፤

በግብረ-ገብ ትምህርት አንጻ ገንብታ¡

ያፈራችው ትውልድ፣ ትኩሱ ወጣቷ፣

ይኸው ደረሰላት ሜንጫውን አንግቦ፣

የደረሰውን ሰብል ሊከምር ሰብስቦ…¡

ለፍቶ-አዳሪውን፣ እርሻ ያስተማረውን…

ምስኪኑን ገበሬ፣ ቆራርጦ ከታትፎ፣

የነፍሰ-ጡር ሚስቱን ሆድ-ዕቃ ዘርግፎ፣

ሃረገ-ሕይወት ሽሏን በጡቷ አስታቅፎ…

አረጋዊ አባቱን፣ እናቱን…ቀርጥፎ…፣

ባንዲት ክብሪት አንጨት፣ ጎጆውን አንድዶ፣

አገሩን ዳረጋት፣ ለሃዘን ፣ ለመርዶ…!

 

   ይኸው ተመንድጋ ከስልጣኔ ጠርዝ ደረሰች አገሬ¡

   ወልዳ፣ አሳድጋ – የወገኑን ስጋ እሚበላ አውሬ!

በዘር-ፍጅት መዝገብ ስሟን አሳትማ፣

አገሬ ቂብ አለች ከዕድገት ምጸት ማማ!

 

አገሬስ ማቅ ለብሳ እንዳዘቀዘቀች፣ 

ከቶ ትቀር ይሆን?! ለዜጎች ሳትመች?!

 

ጌታቸው አበራ

መጋቢት 2013 ዓ/ም

(ማርች 2021) 

 

Filed in: Amharic