>

የሩዋንዳን ጠባሳ ያየ በጎሣ ፖለቲካ አይቆምርም!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የሩዋንዳን ጠባሳ ያየ በጎሣ ፖለቲካ አይቆምርም!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ሩዋንዳ በዘር ፍጅት ያጣቻቸውን በመቶ ሺዎችን እያሰበች የአበባ ጉንጉን ከመታሰቢያቸው ሀውልት ስር በምታስቀምጥበት በዚህ ወቅት ከሩዋንዳዊያን እልቂት መማር ያቃተን እኛ፤ ኢትዮጽያዊያን አንዳችን የሌላችንን ጉድጓድ እንቆፍራለን። ልብ ያለው፤ ልብ ይበል!!
አብረው እና አከባብረው ሊያኖሩን የሚችሉ ብዙ የጋራ ነገሮች ያሉን። እጅግ የተጋመድንና የተዋሃድን ሕዝብ ነን። ውብ አገር እና የማይጠገቡ ብዙ እሴቶች ያሉን።  በልዩነታችን ውስጥም ውበቶቻችን ፈክተው የሚታዩ፤ አብረን ብንቆም ለማንም የሚያስፈራ ግርማ ሞገስ መፍጠር የምንችል፣ ረዥም የታሪክ መሰረት ያለንም ነን። እየወረድን ካለንበት የመቃብር ጉዞ በግዜ እንመለስ።
የሩዋንዳን ጠባሳ ያየ በጎሣ ፖለቲካ አይቆምርም። ዘር ላይ ያተኮሩ ብሽሽቆች፣  መወነጃጀሎች፣ ጠአት መጠነቋቆል፣ የእርስ በርስ ዛቻና ይዋጣልን መባባሉን አቁመን ከገባንበት ቅርቃር በጋራ እንዴት መውጣት እንደምንችል፣ ከወረድንበት አዘቅት በምን መንገድ መመለስ እንደምንችል እና ያንጃበቡብንን አስፈሪ አደጋዎች እንዴት በጋራ መጋፈጥ እንደምንችል ሳይረፍድ ብንመካከር፣ ብናሰላስል እና ብንሰራ ይበጀናል። በተንኮል ፖለቲካ የቀነጨሩ ልሂቃንን ተከትለን አብረን ገደል እንዳንገባ አይናችንን እንግለጥ።
Filed in: Amharic