(ይህ በአያሌው ፈንቴ ከተጻፈው ጥልቅ የምርምር ሥራ የተወሰደ ጽሑፍ ነው)
ጋሎች (ኦሮሞዎች) ከ10ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ጀምረው ዛሬ የሶማሌ ግዛት በሆነው በበርበራ አካባቢ ይኖሩ እንደነበር በአርኪዎሎጂስቶች የሰው ዘር አመጣጥ ጥናቶች ተረጋግጧል። በዚህ ሥፍራ መቼና ከየት እንደመጡ ግን በማስረጃ የተረጋገጠ ነገር የለም።
በ10ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ (ከ937 ዓ.ም ወዲህ) የሱማሌ ነገድ ከታጁራ ባሕረ ሰላጤ ተነስቶ ጋሎችን (ኦሮሞዎች) ስለወጋቸውና ስላሸነፋቸው፣ ከሚኖሩበት ከሰሜን ሶማሌ (ከእንግሊዝ ሶማሌ) ከጋርዳይፋ ሠፈር ለቀው በሽሽት ወደ ደቡብ ምዕራብ ተሰደው በዋቢ ሸበሌና በጁባ ወንዞች መካከል በቤናድር ሰፈሩ።
ይህ ሥፍራ ሞቃዲሾ የሚገኝበትን የቤናድር አውራጃ ይዞ እስከ ደቡባዊ የባሌ የቆላ አውራጃዎች ይደርሳል። በዚህ ሥፍራ ሲኖሩ ከውጭ ሕዝብ የሃይማኖትም ሆነ የንግድ ግንኙነት የሌላቸው ዘላኖች ነበሩ። ስለዚህ ክርስቲያኖችም እሥላሞችም አልነበሩም።
ከጊዜ በኋላ ባንቱ የተባለ ኃያል ነገድ ከቤናድር አሥወጣቸው።
ስለሆነም ጋሎች (ኦሮሞዎች) ሰላምና የግጦሽ መሬት ፍለጋ ጉዟቸውን ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በመቀጠል በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ውስጥ ቦረና ነገሌና አባያ ሐይቅ አካባቢ ከሚገኘው ራሳቸው “ወላቡ” ብለው ከጠሩት ሥፍራ ሰፈሩ።
ቦረና (ወላቡ) ለከብቶቻቸው ግጦሽና ውሀ እንደልብ የሚገኝበትና ከቤናድር ምድር ሲወዳደርም ለምለምና ነፋሻ ሥፍራ በመሆኑ ብዙ የሙገሳና የምሥጋና ዘፈን ዘፍነውለታል። ለረጅም ዘመን ያለጦርነት በሰላም ኖሩበት። (ቦረና በሁሉም ቀደምት የአፍሪካ ካርታዎች ላይ ‹የጋላ ምድር› በሚል የሚጠራ ብቸኛው የኦሮሞ መኖሪያ ሆኖ ለመታወቅም በቃ፡፡)
ኦሮሞዎች በአንድ ሥፍራ ረግተው ሲኖሩ በከፍተኛ ቁጥር በመራባታቸው የግጦሽ መሬት እየጠበባቸው መጣ። በግጦሽ መሬት ምክንያት የሚነሱ የእርስ በእርስ ግጭቶችም እየበረከቱ ስለመጡ የነገዱን ችግር ለመፍታት “ገዳ” የተባለውን አስተዳደርን፣ አምልኮንና ጦርነትን የሚመራ ሥርአት አቋቋሙ። (ስለ ገዳ ሥርዓት በይበልጥ ለመረዳት አቶ ይልማ ደሬሳ በ1956 ዓ.ም. ያሳተሙትን “የ16ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ” መፅሐፍ ይመልከቱ)።
የኦሮሞ ወረራ
በ1500 ዓ.ም. አካባቢ (1ኛ) ወላቡ በመጥበቡ፣ እና (2ኛ) የድሮ ጠላታቸው የሶማሌ ነገድ በባሌ ቆላዎች በኩል እየመጣ ጥቃት ስለሚያደርስባቸው፣ ከወላቡ ተነስተው መሃል ኢትዮጵያን ለመውረር አሰቡ።
በዚህም መሠረት በ1506 ዓ.ም. ከወላቡ ወደ ሰሜን ጥቂት በመግፋት “ኦዳ ነቤ” ብለው እስከሰየሙት ቦታ ድረስ መጥተው ቆሙ። ሆኖም በ1508 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንጉሥ በአዳል ወራሪዎች ላይ ያገኘውን ድል ሲሰሙ በመፍራት ከወረራው ተቆጥበው በነበሩበት አካባቢ በትዕግሥት ቆዩ።
ከ1517-1535 ዓ.ም. አማራዎችና ግራኝ በጦርነት ሲጨራረሱ ኦሮሞዎች የጦርነቱን ውጤት ይጠብቁ ነበር። ግራኝም አሸነፈ፣ ንጉሱም አሸነፉ ኦሮሞዎች ግዛታቸውን ለማስፋፋት ከተዳከመ ጦር ጋር ቢጋጠሙ እንደሚሻላቸው ተገንዝበዋል።
ኦሮሞዎች ወላቡ በነበሩ ጊዜ በአራት ዋና ዋና ነገድ የተከፈሉ ነበሩ። እነሱም ከረዩ፣ መጫ፣ ቱለማና ወሎ ናቸው። እያንዳንዱም ነገድ በስሩ ብዙ ጎሣዎችን ያቀፈ ነው። ግራኝም ሆነ ንጉሡ የኦሮሞዎችን አባያ አካባቢ መሥፈር የሚያውቁ አይመስልም። ቢያውቁም ይህን ያህል ለጦርነት የሚዘጋጅና የሚደራጅ ኃይል አልመሰላቸውም።
ኦሮሞዎች ወላቡና ኦዳ ነቤ በነበሩ ጊዜ የነበራቸው “ለፎ” የሚባል እግረኛ ጦር ብቻ ነበር። ወረራቸውን በስፋትና በብዛት እንዲሆን ሲያቅዱ የፈረሰኛ ጦር መመልመልና ማሰልጠን ጀመሩ።
ግራኝ ሲሸነፍ ገላውዲዎስ በየአውራጃው አስተዳደሩን ለማረጋገት ቢሞክርም የንጉሡ ጦርም ሆነ አስተዳደር በየአቅጣጫው የተዳከመ ነበር። ቀደም ሲል እንደተገለጸው በግራኝ ወረራ ሳቢያ በተከሰተው ጦርነት የደቀቀችው ኢትዮጵያ ‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል› እንዲሉ፣ ለጋሎች (ለኦሮሞዎች) ብርቱ ተቀናቃኝ በሌለበት ወረራ በአጭር ጊዜ ብዙ ግዛቶችን ለመያዝ የተመቸ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
በ1535 ዓ.ም. መጨረሻ የከረዩ ነገድ የሆነው በሜልባ ገዳ አስተዳደር የሚመራው የጃዊ ጎሳ የዊብን ወንዝ ተሻግሮ ደቡብ ባሌን ወረረ። የወረራው ዋና ዓላማ በደቡብ ኢትዮጵያ አውራጃዎች ላይ ሠፊ የመስፈሪያ ቦታ ለማግኘት ነበር።
ባሌን ለመከላከል ሀመልማል የተባለ የንጉሡ ሹም “በትረ አሞራ” የተባለውን ጦር ይዞ ከጃዊዎች ጋር ሲዋጋ ሞተ፣ ጦሩም ወደ ሰሜን ባሌ ሸሸ። ጃዊዎችም ጦርነቱ ቢቀናቸውም የዘረፉትን ይዘው ወደ ወላቡ ተመለሱ እንጅ ሰፍረው አልቀሩም። ሆኖም ለወደፊቱ በወረራ ብዙ ቦታ መያዝ እንደሚቻል ግንዛቤ ሰጥቷቸዋል።
በ1536 ዓ.ም. ሁለተኛው የባሊ(ባሌ) ወረራ በሙደና ገዳ አስተዳደር በሚመራው በበርቱማ ጎሣዎች ተደረገ። ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ይህን ወረራ የሚከላከል አንዳችም ጦር በቦታው ስላልነበረ፣ ኦሮሞዎች እያንዳንዱ ወረዳ ውስጥ ኗሪ የነበረውን ሕዝብ እየፈጁ ሰፊ መሬት ያዙ። በእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ በአብዛኛው ኗሪ የነበሩት አማራዎችና ሀዲያዎች ነበሩ። በግራኝ ጦርነት የደቀቁ ስለነበር ምንም ዓይነት መከላከል አላደረጉም።
በ1538 ዓ.ም ባሊ (ባሌ) ሙሉ በሙሉ ተወርሮ አብቅቶ፣ የኦሮሞ ጦር ደዋሮ (ሐረር) እና ፈጠጋር (አርሲ) ሠፈረ። የከረዩ ነገድ በአብዛኛው ከወላቡ ተንቀሳቅሶ በሥሩ ያሉት በሜልባ ገዳ አስተዳደር የተመራው የጃዊ፣ እና በሙደና ገዳ አስተዳደር የተመራው የባርቱማ ጎሣዎች ወግተው በያዙት በባሊ(ባሌ) ላይ ሠፈሩ።
በ1543 ዓ.ም ደዋሮ (ሐረር) ድንበር ላይ የሰፈረው የኦሮሞ ጦር ወደፊት በመግፋት ከፊል ፈጠጋርን (አርሲን) ሲወር ሠለባ የሆኑት የአገሩ ነባር ነዋሪዎች የሀድያ፣ የከንባታና የአማራ ሕዝብ ናቸው።
አፄ ገላውዲዎስ ፈጠጋር (አርሲ) ውስጥ የመደበው “ቆለታ” የተባለው ጦር በከረዩ ነገድ ጦር ወደመ። እንደገና “አዳል መብረቅ” የተባለውን የተጠናከረ ጦር ቢልክም አዳል መብረቅም ተሸነፈ። አፄ ገላውዲዎስ ከዚህ በኋላ ነው ዳግመኛ ከግራኝ ቀጥሎ ጠንካራ ወራሪ እንደመጣበት የተረዳው።
ስለሆነም ንጉሡ አፄ ገላውዲዎስ የራሱን ጦር እየመራ “አሣ ዘነብ” ከተባለ ቦታ ከከረዩዎች ጋር ተዋግቶ አሸነፋቸው። ብዙ የኦሮሞ ሠራዊትም አለቀ። ይሁን እንጅ አፄ ገላውዲዎስ ግራኝ ያፈረሳቸውን አብያተ ክርስቲያናት ለማሠራት ወደ ሰሜን ተቻኩሎ ስለተመለሰ የተሸነፉት ኦሮሞዎች ብዙም ወደኋላ ሳይመለሱ በነበሩበት ቆሙ።
በዚህ ዘመን የነበረው የኦሮሞዎች አስተዳደር የኪሎሌ ገዳ ነበር። የደዋሮ ጦርነት ሲደረግ ቱለማ፣ ሜጫና ወሎ የተባሉት ታላላቅ ነገዶች ገና ከወላቡና ከኦዳ ነቤ አልተንቀሳቀሱም። ሆኖም ሥንቅና ፈረስ ለቀደሙት የከረዩ ጦረኞች ያቀብሉ ነበር።
በ1551 ዓ.ም በሚችሌ ገዳ የሚመራው ጦር የቀሩትን የደዋሮንና የፈጠጋርን ወረዳዎች ለመውረር እንደገና ተንቀሳቀሰ። የንጉሡ የአፄ ገላውዲዎስ ጦርና የሜያ ቀስተኞች ከኦሮሞዎች ጋር “ደጎ” ከሚባል ቦታ ላይ ተዋግተው ኦሮሞዎች አሸነፉ። የሜያዎችን መርዘኛ ቀስት የሚከላከል ከበሬ ቆዳ የተሠራ ጋሻ ኦሮሞዎች አዘጋጅተው ስለነበር የሜያ ቀስተኞች የተጠበቀውን ውጤት አላስገኙም። በዚህ ጦርነት ደዋሮና ፈጠጋር ሙሉ በሙሉ በከረዩ ኦሮሞዎች እጅ ወደቁ።
ስለዚህ ጦርነት በጊዜው የነበሩት አባ ባሕርይ የተባሉ መነኩሴ ስለ ኦሮሞ ጦረኞች የጭካኔ ግድያ በግዕዝ በፃፉት ማስታወሻቸው “ከበግና ከፍዬል በቀር ሰውን ወንዱንም ሴቱንም ከብቱንም ገደሉ” ብለዋል። ቤርሙዴዝም በተወው ማስታወሻው ላይ ስለ ጦርነቱ የጭካኔ አገዳደል ተመሳሳይ ቃል ትቶልናል።
መጋቢት 27 ቀን 1551 ዓ.ም ገዋኔ ወንዝ አጠገብ ሀዘሎ ከተባለ ቦታ አፄ ገላውዲዎስ እና ተጠናክሮ የመጣ የግራኝ ዘመድ ዐሊ ኑር ታላቅ ጦርነት አድርገው አፄ ገላውዲዎስ በጦርነቱ ተሸንፈው ሞቱ። ማንም ቢያሸንፍ አሸናፊው ጦር የተዳከመ ስለሚሆን ኦሮሞዎች ሊገጥሙ አድፍጠው ይጠብቁ ነበር።
የዐሊ ኑር ሰዎች በድል ሰክረው ወደ ሐረር ሲመለሱ ዐሊ ኑርና ጥቂት ሰዎች ሲተርፉ፣ ብዙዎቹ ባላሰቡት ቦታና ጊዜ በኦሮሞ ጦር ተወግተው ረገፉ። ከረዩዎችም ጦሩን ተከታትለው ሐረርን ወጉ። ሕዝቡንም ወጉ። ለምና ደጋውን የሐረር አውራጃዎች ሠፈሩበት።
የሠፈሩባቸውን ወረዳዎችና አውራጃዎች ሥም የጎሳዎቻቸውንና የሰዎቻቸውን ስም ሰጡ (አቦራ-ወበራ አውራጃ፣ ጨርጨር፣ ድሬዳዋ፣ ጋራ ሙለታ፣ ጉርሱም፣ ወዘተ)። እነዚህ ሁሉ ቦታዎች ከዚህ ወረራ በፊት በሌላ ስሞች ይታወቁ ነበር።
ዐሊ ኑርም ሐረር ከተማን ከኦሮሞ ጦረኞች ለመከላከል ሲል በሐረር ከተማ ዙሪያ እስከዛሬ የሚታየውን የጀጎል ግንብ አጥር አሣጠረ። ከረዩዎችን ግን አላቆማቸውም።
ከላይ እንደተገለፀው እሥካሁን ያለውን ወረራ ያካሄደው የከረዩ ነገድ ነበር። ቀሪዎቹ ሦስቱ ነገዶች ወላቡና ኦዳ ነቤ እየጠበባቸው ስለሄደ እርስ በርሳቸው በማይጣሉበት ሁኔታ የሚወሩትን አካባቢ በዕጣ ለመከፋፈል ተስማሙ።
ከረዩዎች የወረሩትን ባሌን፣ ደዋሮን፣ ፈጠጋርን እንደያዙ እንዲቆዩ ሥምምነት ተደርጎ ለቀሪዎቹ ሦስቱ ነገዶች በወጣው ዕጣ መሠረት፦
1ኛ) ከአዋሽ በስተምዕራብና በስተደቡብ የሚገኘውን አገር የመጫ ነገድ እንዲወር፣
2ኛ) በስተሰሜን ምሥራቅ ያለውን አገር የወሎ ነገድ እንዲወር፣ እና
3ኛ) ከአዋሽ ወንዝ በስተሰሜን ያለውን የቱለማ ነገድ እንዲወር ወሰኑ።
በተደረገው ክፍፍል መሠረት እያንዳንዱ ነገድ ያደረገውን ጉዞና ነባር የኢትዮጵያ ሕዝብ እያስለቀቀ የያዛቸውን ግዛቶች እንመልከት።
አንደኛ/ የመጫ ነገድ ጉዞ
መጫዎች ጉዟቸውን ከመጀመራቸው በፊት አዋሽ ወንዝ ላይ ከቱለማ ነገድ ጋር ብዙ ከብቶች አርደው በልተው ጠጥተው ተላቅሰው ተለያዩ። መጫዎች ከወረራው በፊት ፈረሰኛ ሰላዮችን አስቀድመው እየላኩ የሚሰፍሩበትን ቦታ አዘጋጁ። ጊቤ ወንዝ አካባቢ “ጡጤ ብስል” ከምትባል ጉብታ ሥፍራ ላይ ሠፈሩ።
ጡጤ ብስል ለከብቶቻቸው ሣርና ውሃ እንደልብ የሚገኝባት አካባቢ ነበረች። ከዚች ሥፍራ በመነሳት የመጫ ፈረሰኞች የጋፋቶችንና የእናርያዎችን አገር ዳሞትን እና ቢዛምን ወጉ። የእናርያ ነገዶች ብርቱ መከላከል ቢያደርጉም ስለተሸነፉ ብዙዎቹ ዐባይን ተሻግረው ዛሬ ጎጃም ክፍለ ሀገር ውስጥ ከሚገኘው ዳሞት አውራጃ ውስጥ ተሰደው ሠፈሩ።
በዚያን ጊዜ ዳሞት ከጊቤ ወንዝ አንሥቶ የዛሬውን ጎጃምን የሚያጠቃልል ሠፊ ግዛት ነበር። ቢዛም ደግሞ መጫዎች ከሠፈሩበት በኋላ ወለጋ ብለው የቀየሩት ክፍለ ሀገር ነው። ዳሞትና ቢዛም ለንጉሡ የሚገብሩ በዛሬው አጠራር ክፍላተ-ሀገራት ነበሩ።
ጡጤ ብስል በሰውና በከብት ብዛት በመጥበቧ በመጫዎች መካከል ጠብ ተጀመረ። ጠቡን ለመፍታት ግዛት ማስፋፋት ነበረባቸው። ባደረጉት ስምምነት መሠረት በመጫ ነገድ ሥር የተሰባሰቡት ጎሣዎች የሚከተለውን የአገር ክፍፍል አደረጉ፦
(ሀ) የጨሊያና የሊበን ጎሣዎች ከጡጤ ብስል እስከ ግንደ በረት ያለውን ያዙ፣
(ለ)ሌቃ የተባለው ጎሳ ከጊቤ ‹ቱሉ ወለል› ብለው እስከሰየሙት ተራራ ድረስ ያለውን ለምና ሀብታም አገር ያዘ። ይህም ቢዛምንና በከፊል ከፋን (ከፋ ጥንትም ስሙ ከፋ ነበር) እና “ላሎ ቅሌን”(በኋላ ኢሉ አባ ቦር እና ኢሉባቡር የተባለውን) አካባቢ ያጠቃልላል።
ሌቃዎች ቱሉ ወለልን የጭዳ ማረጃና የአምልኮ ቦታቸው አደረጉ። ስለ ቱሉ ወለል ግጥምና ዘፈኖችም አወጡ። ከፋና ላሎ ቅሌ ውስጥ የያዙት መሬትም በአብዛኛው የነባሮቹ የአንፊሎዎች ነው። አንፊሎዎች ብዙ ቢከላከሉም ስለተሸነፉ ሌቃዎች “ገባሮ” የሚል ሥም ሠጥተዋቸው አብረው ኖረው ተዋህደዋል። የአንፊሎዎች ቋንቋ እየሟሸሸ ቢሆንም ከቄለም በስተምዕራብ በሚገኙ አካባቢዎች እስከዛሬ ይነገራል።
(ሐ) ሁሌ የተባለው ጎሳ ደግሞ ከዴዴሳ ወንዝ እስከ ጎጀብ ወንዝ ያለውን ያዘ፣
(መ) ጂማጉማ፣ ጌራና ሊሙ የተባሉት ጎሣዎች ተሰባስበው የጊቤን መንግሥት አቋቋሙ። ይህም የእነጅማ አባጅፋር አገር መንግሥት መሆኑ ነው።
ከቄለም በስተምዕራብ ያለው አካባቢ የበረሀ ወባ ያለበት በመሆኑ ለመጫዎች አመች ቦታ አልሆነላቸውም። ስለዚህ የአካባቢው ነባር ሕዝብ ጋምቤላዎች ከወረራ ተረፉ።
ሁለተኛ/ የወሎ ነገድ ጉዞ
የወሎ ነገድ ከዝቋላ እስከ ይፋት ድረስ ከሜያዎች ጋር እየተዋጋ በስተምዕራብ አድርጎ ወደ ሰሜን በመጓዝ እንደገና ወደግራ ተቀልብሶ አንጎት (ራያ) የተባለውን አማርኛና የአማራ ባሕል የዳበረባትን የጥንት የአማራ አገር ወረረ።
አንጎት ከመድረሳቸው አስቀድሞ “ጊዮርጊስ ኃይሌ” የተሰኘ የንጉሡ ጦር ገጥሟቸው አሸንፈውት ተጓዙ። የተጓዙትም በአዳልና በአማራ መካከል ሲሆን የግራኝ ጦር ለዘመናት ያዳከመው በመሆኑ ከባድ ጦርነት አልገጠማቸውም።
ወደ ሰሜን በማቅናት የአንጎት አካባቢንና ዛሬ የጁ (ቤተ አማራ)፣ ራያና አዘቦ ተብለው የሚታወቁትን አካባቢዎች፣ ቀጥሎም ጋንዘንንና ሳይንትን ወረው ሰፈሩበት። የሰፈሩባቸውንም ቦታዎች እንደተለመደው የመሪዎቻቸውን በአጠቃላይ የጎሳዎቻቸውን እና የጥንት ቦታዎቻቸውን ሥም ሰጡ።
ለምሳሌ የጥንት ሥሙ ላኮ መልዛ የነበረውን በጎሳቸው ሥም ወሎ አሉት፣ ዋስልን ወረሂመኖ አሉት፣ መጀመሪያ ኢትዮጵያ ሲገቡ በነበሩበት አካባቢ በሚገኘው “ገላን” ወንዝ ሥም “ገላና” የሚባል ወንዝ የጁ ውስጥ ሰይመዋል። መቻሬ፣ ጉባላፍቶ* [*አሁን በአዲስ አበባ ውስጥ ያቋቋሙትን አዲስ ክፍለ ከተማ ጉባላፍቶ ብለው እንደሰየሙት ልብ ይሏል]፣ መርሳ፣ ውርጌሳ፣ ወረኢሉ፣ ወረባቦ፣ ወሎ ቦረና፣ ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው።
ከሳይንት ወረራውን በመቀጠል ባርቱማ የተባለው የወሎ ነገድ አማሮች የሚኖሩበትን በጌምድርን ለመውረር ሞክሮ ብርቱ ጥቃት ስለደረሰበት ወደኋላ ተመለሰ።
ሶስተኛ/ የቱለማ ነገድ ጉዞ
ሦስቱ ነገዶች ወረራዎችን ሲያከናውኑ የቱለማ ነገድ በዕጣ የደረሰውን አካባቢ ለመውረር ከኦዳ ነቤ አልተነሳም ነበር።
በ1562 ዓ.ም ከአዋሽ በስተሰሜን ያለውን ሸዋን ለመውረር ተንቀሳቀሱ። በወቅቱ የነበረው ንጉሥ አፄ ሚናስ አዝማች ዘረ ዮሐንስ የተባለ ሠው የሚመራውን ጦር ቢልክም፣ ቱለማዎች አዝማቹንም ገደሉ፣ ጦሩንም በታተኑት። ወደፊትም በመግፋት ዛሬ የሸዋ ኦሮሞ ያለበትን ምድር ሠፈሩበት።
ሸዋ የመንግሥት እምብርት የነበረች በመሆኗ ከሌሎች አካባቢዎች መወረር የበለጠ መንግሥትን አሳስቦታል። ይሁን እንጅ የአፄ ሚናስ መንግሥት ከአፄ ገላውዲዎስ ዘመን የባሰ የተዳከመ መንግሥት ስለነበር ወረራውን ለመከላከል ያደረገው ሙከራ ሁሉ ፍሬ አልባ ነበር።
የአማራ ሕዝብ ለም ከሆነው አገሩ ከባሊ (ባሌ)፣ ከደዋሮ (ሐረር)፣ ከፈጠጋር (አርሲ፣ ሲዳሞና ጎምጎፋ) እና ከመሃል ሸዋ በወረራው ተፈናቅሎ ወደ ሰሜን ሸዋ ተሰደደ።
አፄ ሚናስ ሞቶ አፄ ሠርፀ ድንግል ሥልጣን ሲይዝ ወረራውን ሊያቆም ባይችልም ከሁሉም ነገሥታት የበለጠ ተዋግቶ ብዙ ድሎችን በወራሪዎች ላይ ተጎናፅፏል።
በ1567 ዓ.ም የሠርፀ ድንግል ጦር ዝዋይ ሐይቅ አጠገብ ደርሶ በአካባቢው የሰፈሩትን “የአባቲ” ጎሳዎችን ወግቶ አሸነፋቸው። በአባ ባሕርይ ማስታወሻም መሠረት በዚህ ጦርነት ከ10 ሰው በላይ አላመለጠም።
ሠርፀ ድንግል ዝዋይ ላይ ድል ቢያገኝም በዚሁ ወቅት ሸዋና ጎጃም ድንበር ላይ የሠፈሩ ቱለማዎች ተጠናክረው ዐባይን ተሻግረው ጎጃምን ወረሩ። ሠርፀ ድንግልም ወረራውን ለመቋቋም “አደራ” ከሚባል ቦታ ከቱለማዎች ጋር ተዋግቶ አሸነፋቸው።
በዚያው ወቅት ዋግ መወረሩን ሰምቶ ይህንኑ ወረራ ለመከላከል ወደ ዋግ ሲሄድ በምዕራብ በኩል የነበሩት መጫዎች ዳሞትን ወርረው ዘረፉ። በአማራዎችና በጋፋቶችም ላይ ብዙ እልቂት አደረሱ። በስተምሥራቅ ደግሞ ቱለማዎች ሸዋን እንደገና ወርረው ተጠናክረው ሠፈሩበት።
ወረራውን የማቆሙ ጦርነት ለንጉሡ የህልም ሩጫ ሆነበት። ወራሪዎቹ አዲስ የሠፈራ ምድር ለማግኘት የጀመሩት ጦርነት የተሳካ ሆነ።
ቀደም ሲል እንደተገለፀው ጋሎች (ኦሮሞዎች) ከበርበራና ከቤናድር በርሃዎች በሶማሌና በባንቱ ጦረኞች ተባርረው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ መጥተው የሠፈሩበት ዘመን በታሪክ ሂደት ውስጥ በጣም አጭር ጊዜ ነው። ከወላቡ (ቦረና) እና ከኦዳነቤ ተነስተው የኢትዮጵያን አብዛኛውን ግዛት በወረራ ሲይዙ የፈጀባቸው ጊዜ ከ60ዓመት አይበልጥም።
የግራኝ ወረራ ዓላማ የእስልምናን ሃይማኖት ለማስፋፋትና ግዛት ለማግኘት ሲሆን፣ የጋሎች (የኦሮሞዎች) ወረራ ዓላማ ግዛት (የመሥፈሪያ መሬት) ለማግኘት ያለመ ነበር። ከ1517-1567 ዓ.ም በነበረው ዘመን ኢትዮጵያ ከአንድ አስከፊ ወረራ ወደሌላ አስከፊ ወረራ ተሸጋገረች። ግራኝ የቀደደው የወረራ በር ጋሎችን (ኦሮሞዎችን) አስገባ።
ምንም እንኳን ኦሮሞው በአማራው ላይ መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋና ግድያ መፈፀሙ ባይካድም፣ በአጠቃላይ በኦሮሞ ወረራ ሂደት ሠለባ የሆኑ ነገዶች ቁጥር ሥፍር የላቸውም።
ሀዲያዎችና ከምባታዎች ከመኖሪያቸው ከባሌና ከአሩሲ ተፈናቅለው በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በሥደተኝነት አነስተኛ ቦታ ይዘው እንዲኖሩ ተደርገዋል። በዝዋይ ሐይቅ ደሴት አካባቢ ተወስነው የኖሩት በቀሥት የታወቁት የሜያ ነገድም በግራኝም ሆነ በኦሮሞ ወረራ ጦርነት ተመናምነው የት እንደደረሱ አይታወቅም። የጋፋት ነገድም ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል። አርጎባዎች፣ ቀቤናዎች፣ ወርጅዎች፣ አላባዎች፣ ሲዳማዎች የኦሮሞ ወረራ ሰለባ ሆነዋል። የዳውሮና የገሙ ሰዎች ግዛታቸው በኦሮሞዎች ተወስዶባቸዋል።
ከየትኛውም ነገድ፣ ከግድያው የተረፉት በጋላ (በኦሮሞ) የሞጋሣ ሥርዓት ሳይወዱ በግድ ኦሮሞ እንዲሆኑ ወይም እንዲሰደዱ ሆነዋል። ይህ ተግባር በወያኔ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያም በጃራ የተመራው የኦሮሞ እስላማዊ ድርጅት የአማራ ሴቶችን አሥገድዶ ኦሮሞ በማድረግና በማስለም እስከማግባት ዘልቋል።
አባቶቻቸው በጋላ (ኦሮሞ)ወረራ የተገደሉባቸውን የሌሎች ነገዶችን ልጆች፣ ጋሎች (ኦሮሞዎች) በጉዲፍቻ ሥርዓት ውስጥ በማዋል አገልጋይና ከብት ጠባቂዎቻቸው ያደርጓቸው ነበር።
በአጠቃላይ ጋሎች (ኦሮሞዎች) ይህንን መጠነ ሠፊ ወረራ ባካሄዱባቸው አካባቢዎች ውስጥ የነበሩትን ነገዶች፣ ለጀግንነታቸው መለኪያ ይሆን ዘንድ የወንዶችን ብልት በመሥለብ* ሳይገቱ ነገዱንም የራሳቸው ለማድረግ “የሞጋሳና የጉዲፍቻ”ሥልቶችን ተጠቅመዋል።
[*እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ የጋላ ነገዶች በተለይም በባሌ ኦሮሞዎች በግንባራቸው ላይ ተጠልቆ የምናየው የገዳ የወንድ ብልት ቅርጽ የጥንቱ የኦሮሞ ወራሪ የኢትዮጵያን ነባር ሕዝቦች ብልት እየቆረጡ ጀግንነታቸውን ያሳዩበት የነበረ የጋላ (የኦሮሞ) የወረራ ባህል ውርስ ነው፡፡]
ይህ ብቻ አይደለም። በግራኝ ወረራ ክፉኛ የተጎዳው የአማራና የክርስቲያን ዕምነት ተከታይ ሕዝብ ጥንት ይኖርባቸው የነበሩትን ባሊን (ባሌን)፣ ፈጠጋርን (አርሲን፣ ሲዳሞንና ጎምጎፋን)፣ ደዋሮን (ሐረርን)፣ ቢዛምን (ቄለም ምዕራብ ወለጋን)፣ ዳሞትን (ሌቃ ምሥራቅ ወለጋን)፣ እናርያን፣ ወዘተ. በአጠቃላይ ድንግልና ለም መሬቶች በግዳጅ በቀላሉ እንዲለቅ አስገድደውታል። የነባሩን ሕዝብ ሀይማኖት፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነትም አስለውጠዋል።
የጋሎች (የኦሮሞዎች) ወረራ ካበቃ በኋላ የሕዝብ ውህደት ተጀመረ። ለመዋሀድ የወሰደው ጊዜም አጭር ነበር። አብሮ በመኖር የባህልና የቋንቋ መወራረስ ተደረገ። በአቴቴ (ጨሌ) ማምለክ፣ ቦረንቲቻ ማረድ፣ አድባር ሥር ቡና ማፍላት፣ ጭዳ ማረድ፣ ወዘተ. ከገዳ ሥርዐት አምልኮ የተወሰደ የኦሮሞ ነባር ትውፊት ነው።
ጋሎች (ኦሮሞዎች) በወረራ ከመጡ በኋላ ከነባሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብረው በመኖር ረጅም የሰላምና የመረዳዳት ዘመን አሳልፈዋል። ከ17ኛው (ከአሥራ ሰባተኛው) ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ የኦሮሞ ሕዝብ ጭምር የሠራው ታሪክ ነው።
አበቃ፡፡*
* ይህ ጽሑፍ ቀደም ብዬ ካቀረብኩት ‹‹የግራኝ አህመድ ወረራ›› ጥናት ቀጣይ ክፍል ሲሆን፣ የመጨረሻ ሶስተኛውን ‹‹በኦነግ አስተሳሰብና የይገባኛል ጥያቄዎች›› ዙሪያ የተሰነደ ክፍል ወደፊት እናቀርበዋለን፡፡ እነዚህ ጽሑፎች አንብቦ ለማወቅ ለሚፈልግ ዜጋ ተመጥነው የተጻፉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለጥልቅ ምርምር መነሻ የሚሆኑ በርካታ ሀሳቦችንም የያዙ የጥናት ውጤቶች ናቸውና፣ ለታሪክ ተመራማሪ ለአያሌው ፈንቴ እጅግ የከበረ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ጸሐፊው ለጥናቱ የተጠቀመባቸው ዋቢ መጻሕፍትና መረጃ ምንጮች ዝርዝር በዚህ ጦማር አለመካተቱንም በትህትና እገልጻለሁ፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ መልካም ጊዜ፡፡