>

አራጅና አሳራጅ ከዓላማ ለማናጠብ በሚያደርጉት የሸፍጥ ‹ውይይት› እንዳንዘናጋ (ከይኄይስ እውነቱ)

አራጅና አሳራጅ ከዓላማ ለማናጠብ በሚያደርጉት የሸፍጥ ‹ውይይት› እንዳንዘናጋ

ከይኄይስ እውነቱ


የእናት ሆድ ዝንጕርጕር ነው ቢባልም እኛ ኢትዮጵያውያን በወገኖቻችን ላይ የሚፈጸሙ ኢሰብአዊ (አረመኔያዊ) ድርጊቶች እንዴት ባንድነት እንዳላቆመን ሳስብ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡ ይሄ በቀላሉ የማይታይ ግለሰባዊና ማኅበረሰባዊ ቀውስና መናጋት ነው፡፡ ይሄ ከሰውነት መራቆት ነው፡፡ ይሄ የዚህ ወይም የዚያ እምነት ተከታይ፣ የዚህ ወይም የዚያ ነገድ/ጐሣ አባል ከመሆን፣ የዚህ ወይ የዚያ ቋንቋ ተናጋሪ ከመሆን ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ወገኖቼ የግድ በእንክብልና በመርፌ መልክ መድኃኒት ካልተሰጠን ካላልን በቀር ባለፉት ሠላሳ ዓመታት አገራችንን ለውድቀት ሕዝቧን ለውርደት የዳረገውንና አሁንም እጅግ ከፍቶ የቀጠለውን ኢሕአዴግ የሚባል አፓርታይዳዊ የጐሣ ሥርዓት ምንነት መረዳት እንዴት ያቅተናል? ምን አዚም ነው የተደረገብን? ዲያቢሎስ ከሚመራው ጉባኤ ምንድን ነው የምንጠብቀው? ከ‹ምክረ አይሁድ› (ከጥፋት መካሪዎች) ኦሕዴድ እና ብአዴን ስቀለው! ስቀለው! እረደው! እረደው! ካልሆነ ምንድን ነው የምንጠብቀው? የወገን ደም እስከ መቃብር ከሚያሳድዳቸው አራጅና አሳራጅ በ‹ውይይት› ሽፋን ለሌላ ዙር ፍጅት በሚያደርጉት ዝግጅት እንዳንዘናጋ፡፡ ኢሕአዴግ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ከተካነበት የማስመሰል ትርኢት መፍትሄን የሚጠበቅ ካለ እሱ ከአእምሮው የተለየ መሆን አለበት፡፡

ባንፃሩም ለነዚህ የጥፋት ኃይሎች (ኦሕዴድና ብአዴን) ጥብቅና የቆሙ፣ ከአጋንንት ትድግና እንደሚገኝ የሚሰብኩ በርካታ ክብራቸው በነውራቸው ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ‹የካህናት አለቆች› እና ‹ጸሐፍት ፈሪሳውያኖች› አሉ፡፡ በዚህ ጎራ ውስጥ አእምሮውን ለጌቶቹ ትቶ በሆዱ ብቻ ከሚንከላወሰው ተራ ካድሬ አንስቶ አእምሮአቸው የመከነ ሊቀ ማእምራን (ፕሮፌሰር) የሚል ማዕርግ እስከ ተሸከሙት አድርባዮች ይገኙበታል፡፡ አድርባይነትን ከጦርነት የባሰ አክፍተውታል ያልከው ወንድሜ ቴዎድሮስ ጸጋዬ እውነት ብለሀል፡፡ እነዚህ አድር ባዮች የአገራችንን እና የሕዝቧን የመከራ ምጥም እያራዘሙ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹም በማር በተለወሰ እሬት ንግግራቸውና ጽሑፋቸው ውይይት መቀመጥ እኮ መልካም ነው፡፡ ታግሠን የሚሰጡንን መፍትሄ እንጠባበቅ እያሉ የምንደኝነት ተግባራቸውን ሲወጡ ጆሮአችንን የምናውስ ነሆለሎች ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ሕፃን ልጁ ቢታረድበት፣ እንጨት ለቅማ ዓይኗን በጭስ አጥፍታ ያሳደገች እናቱ የጥይት ሲሳይ ብትሆን፣ አፈር ገፍቶ ለእግሩ መጫሚያ ሳይኖረው ያሳደገው አረጋዊ ገበሬ አባቱ በደንጊያ ተወግሮ ቢሞትበት፣ እኅት ዓለሙ እና ወንድም ዓለሙ በገጀራ ቢጨፈጨፉበት ከአራጆቹና አሳራጆቹ ጋር ውስኪ ለመራጨትና ከወንጀላቸው ለማምለጥ የሚያደርጉትን የሐሰት ምክክር ለማዳመጥ ጆሮ ይኖረው ነበር?

ለአገራቸው ለወገናቸው የሚገዳቸው በውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ ብሔራዊ መግባባት፣ ብሔራዊ ዕርቅ፣ የሽግግር የፍትሕ ሥርዓት፣ አገራዊ ውይይት ይደረግ እያልን እስኪታክተን የጮኽነው ኢሕአዴግ በሚባል የኢትዮጵያ ጠንቅና ነውረኛ ስብስብ አባላቱ መካከል የሚደረግን የውሸት ውይይት አይደለም፡፡ በጭራሽ! በቅርቡም ምዕራባውያንን ለመሸንገል ነውረኞቹ ዐቢይና አድርባይ ሎሌዎቹ ‹‹ሁሉን አካታች ብሔራዊ ውይይት…›› በማለት ትልቁን አጀንዳ ለራሳቸው ፍላጎት ሲያርመጠምጡት አስተውለናል፡፡ መልካም አስተሳሰቦችን የራሳቸው አስመስለው መስረቅ እና ማርመጥመጥ ከግብር አባታቸው ወያኔ የተማሩት ውርስ ነው፡፡ ማፈሪያዎች! 

ወገን! እንደ ባለአእምሮ እንመላለስ፡፡ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረናል ካልን በተፈጥሮ/በሕገ ልቦና የተሰጠንን ክፉን ከበጎው፣ ሐሰቱን ከእውነቱ የምንለይበትን አእምሮ፣ የምናስተውልበተን ኅሊና እንጠቀም እንጂ!!! አገራችንን እና ሕዝባችንን ለመታደግ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን፣ የቀደመ መልካም ታሪኳን፣ ክብርና ኩራቷን፣ ሉዐላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን፤ የሕዝቧን ሰላምና ደኅንነት የሚያስከብር መንግሥትና መሪ የላትም ከሚል አስተሳሰብ መነሳት ይኖርብናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ርእሰ መጻሕፍቱ እግዚአብሔርን እሺ በጄ በሉት፤ ሰይጣንን እምቢ! ወግድ! በሉት ይለናል፡፡ አገርና ሕዝብ የሚያጠፋውን ኢሕአዴግ፣ በፊታውራሪነት የሚመራውን ኦሕዴድን እንዲሁም ባርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነውን ብአዴን እምቢ ወግድ! ማለት ለምን ይሳነናል? በጉልበት በሰለጠኑበት የኢትዮጵያ ምድር ለሠላሳ ዓመታት ክፋትና ተንኰልን መክረው ዐዘቅት ውስጥ የከተቷትን አገር ዛሬ የወያኔ ወራሽ ጌታ እና የወያኔ ወራሽ ባሪያ በሚያደርጉት ‹ውይይት› እንዲታደጓት መጠበቅ የክፍለ ዘመኑ ቊጥር አንድ ሞኝነት ተብሎ ከሚመዘገብ በቀር ራሳችንን አናታልል፡፡ ከእንግዲህ ዕርፍ ተይዞ ወደ ኋላ አይታረስም፡፡ ለሠላሳ ዓመታት በኢሕአዴጋውያን በጠላትነት ተፈርጆ በእምነቱና ማንነቱ በቋሚነት የዘር ማጥፋት ሰለባ የሆነውን የአምሐራ ሕዝብ በተለይ፣ በዘር መድልዎው የጐሠኛነት ሥርዓት እልቂት የታወጀበትና ቁም ስቅሉን የሚያየው ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ (የትግራይ፣ የጋምቤላ፣ የጉራጌ፣ የኮንሶ፣ የጋሞ፣ የአማሮ፣ የጌድዎ ወዘተ.)  ባጠቃላይ፣ ቀጣይ ህልውናዋ በቋፍ የሚገኘውን የሁላችን ማደሪያ ኢትዮጵያን ለመታደግ በውስጥም በውጭም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ችግሩ የአንድ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን እሳቱ ነገ ተነገወዲያ ሁላችንን የሚያቃጥል መሆኑን ተገንዝበን (ዮዲት የምትባል በመልኳም ባስተሳሰቧም ውብ የሆነች ኢትዮጵያዊት በቅርቡ በ‹ጽዋ ቲዩብ› በተደረገ አገራዊ ውይይት ርስ በርሳቸው በሚገጣጠሙ፣ ሲገጣጠሙ ውብ ኅብርና አንድነት በሚፈጥሩ የእንቆቅልሽ ጨዋታ መስላ፣  አንዱ አካል ከሌላው ተነጥሎ መቆም እንደማይቻለውና አንዱ የሌላውን ጉድለት ሲሞላው እንዴት ሥምረት /harmony/ እንደሚፈጥር እንዳሳየችው ሁሉ) እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናገሪ እንደ አንድ ሕይወት ኗሪ ሆነን ኢትዮጵያን ሁላችን በእኩልነት የምንኖርባት አገር ለማድረግ በብርቱ መሥራት ይኖርብናል፡፡ በዚህ ሂደት በውስጥና በውጭ ያለን ተቀናጅተን ዘረኛው የዐቢይ አገዛዝና ሎሌዎቹ በሚያናፍሱት ማናቸውም አጀንዳ (ኢሕአዴግ የሚባለው የወንጀለኞችና ከሀዲዎች ስብስብ ብሔራዊ አጀንዳዎች ስለሆኑት ስለ ዐባይ፣ የአገር ሉዐላዊነት፣ የግዛት አንድነት ወዘተ. ሊነግሩን የሞራል ብቃት/ልዕልና የለውም) ለቅጽበት ሸብረክ ሳንል፣ ሳንወላውል ውጥናችንን፣ ጅምራችንን ከፍጻሜ ማድረስ ይኖርብናል፡፡ ባንድነት በኅብረት ውስጥ እግዚአብሔር የቸርነቱን ሥራ እንደሚሠራ አንጠራጠር፡፡ ይሄ ጥረት የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርገን መልካም ፍጻሜ እንዲኖረው ከፈለግን  እስላምና ክርስቲያን፤ የዚህ ነገድ የዚያኛው ነገድ አባላት፣ የዚህና የዚያኛው ቋንቋ ተናጋሪ ሳንባባል ዕጣ ፈንታችን ዕድል ተርታችን የአንድ አገር ሕዝብ/ዜጎች ነን ብለን መተባበርን፣ ሕዝብና አገርን አስቀድመን መቆምን ይጠይቃል፡፡ እኛ አንድ ስንሆን፣ ‹ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ› የሚባለውና ተጽእኖ ፈጣሪው የውጩም ኃይል ሳይወድ በግዱ የአብዛኛውን አቋም እንዲይዝ ይገደዳል፡፡ ስለዚህ መፍትሄው ከውስጥ እንጂ ከውጭ አይደለም፡፡ በተግባር ከምናሳየው ሥራችን ጋር ሁላችን እንደየ እምነታችን ላገራችን ህልውናና ለሕዝባችን አንድነት አጥብቀን ከልባችን እንጸልይ፡፡

አራጆችንና አሳራጆችን መለማመጡ አብቅቶ መድረሻቸው ያልታወቀውን ልጃገረጅ ተማሪዎችን፤ በግፍ የታሰሩ እስክንድርና ጓዶቹን÷ ባጠቃላይ የኅሊና እስረኞችን፤ ባገዛዙ ይቅርታ የሌለው ጥፋት ሰለባ የሆኑትን ሰላማዊ የትግራይ ወገኖቻችንን፣ ሆን ተብሎ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመባቸው ያሉ የአምሐራ ወገኖቻችንን፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛቶች በእልቂት፣ በመፈናቀልና በረሃብ እንግልትና መከራ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን ኢትዮጵያን ከሚጠሉ አረመኔዎች እጅ ለመታደግ በኅብረት እንነሣ፡፡ የእርዳታ እጃችንን እንዘርጋላቸው፡፡

የኢትዮጵያ አምላክ የወገኖቻችንን ደም ከንቱ አያድርግብን፡፡ መልካም ጅምራችንን፣ ጥረታችንን ከፍጻሜ ያድርስልን፡፡ የመለያየትና የመከፋፈልን መጥፎ መንፈስ ያርቅልን፡፡ ወደ ዐቅላችን ይመልሰን፡፡

Filed in: Amharic