>
8:10 pm - Monday May 29, 2023

አለም የዘነጋት ኢትዮጵያ እድሏ ያሳዝናል! ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

አለም የዘነጋት ኢትዮጵያ እድሏ ያሳዝናል!

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

የሰው ልጆች ህይወት ክብር፣ ከጎሳ ወይም ሃይማኖት ማንነት እና መደብ በላይ ነው፡፡ ከጂኦ ፖለቲካ ተፋላሚዎችም በላይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ህይወት ክቡር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህን እውነት በኢትዮጵያ፣በቀሪው የአፍሪካ ክፍል ወይም በመካከለኛው ምስራቅ ስለመኖሩ ምስክርነት መስጠት አይቻለንም፡፡

ባልካናይዜሽን

 ባልካናይዜሽን የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን በነቢብም ፣ በገቢርም ታይቶ የነበረው በአፓርታይዷ የደቡብ አፍሪካ ነበር፡፡ ዛሬ ያሁሉ ሰቆቃ ቀርቶ ( እድሜ ለታላቁ የአፍሪካ ልጅ ማንዴላ ይሁንና ) ዛሬ ያ በአጥር የተገደበ የክልል አይነት ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በአጭሩ ደቡብ አፍሪካ ዲሞክራቲክ ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ዜጎቿ ከአንዱ የሐገሪቱ ክፍል ወደ ሌላው የሀገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው ለመስራት፣ ለማደግ፣ለመማር፣ለመኖር የክልል አጥር አይገድባቸውም፡፡ ሀገራቸውን የነጻነት ምድር በማድረጋቸው ከጎሳ ክልል ተገላግለዋል፡፡ ባልካናይዜሽን የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን የማይስማሙ፣ ምርር ያለ ጠብ ውስጥ የተዶሉ፣ቁጭ ብለው መነጋገር የማይችሉ ወዘተ ክልሎችን ያመለክታል፡፡ ለማናቸውም የእንግሊዝኛ ትርጉሙ ገላጭና አጭር በመሆኑ እንደሚከተለው ጠቅሸዋለሁ፡፡

Balkanize

/ˈbɔːlkənʌɪz,ˈbɒlkənʌɪz/

Learn to pronounce   

verb

 1. divide (a region or body) into smaller mutually hostile states or groups.

“ambitious neighbours would snatch pieces of territory, Balkanizing the country”

ኢትዮጵያን ባልካናይዝ የማድረግ አቅድ ?

የምእራቡ አለም የማርክሲስት ሌኒንስት ( አልባንያ ሶሻሊዝም) አቀንቃኝ ለሆነው፣የጸረ ዲሞክራሲ ሸሪክ፣እንዲሁም አክራሪ ብሔርተኛ፣ ከውልደቱ እስከ ሞቱ ድረስ በጸረ ኢትዮጵያዊነት አቋሙ የሚታወቀው፣ በሙስና እስከጭንቅላቱ ድረስ የተጨማለቀው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትን ደግፈው በመነሳታቸው ምክንያት በብዙ አስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን አስደንግጦ ነበር፡፡ ሀዘንም ላይ ጥሏቸዋል፡፡

በእኔ በኩል  የወያኔ አገዛዝ ከፈጸማቸው አስከፊ ጥፋቶች አራት ምሳሌዎችን እንደሚከተለው    አብራራለሁ፡፡ እነኚህ አራት ምሳሌዎች የወያኔን አረመኔነነት፣ኢሰብዓዊነት ያሳያሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ለእኔ እንደሚመስለኝ የምእረባውያን ዴሞክራሲ፣ የተባበሩት መንግስታት ልዩ ተወካዮች UN specialized agencies ፣ ኤኤፍፒ AFP,፣ሲኤንኤ CNN ፣ወዘተ የአለም መገናኛ ብዙሃን ለጊዜውም ቢሆን ከእውነት ጋር የቆሙ አለመስልህ ብሎኛል፡፡ ለማንኛውም ነጥቦቹን እንደሚከተለው አብራራለሁ፡፡

 1. በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ትግራይ ክልል፣ ለተፈጸሙ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት የሀገር ድንበር ሲጠብቅ በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መክፈቱ በአለም ታሪክ ያልተለመደ ክስተት ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል በትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት ሚሊሻዎችና በኢትዮጵያ የፌዴራል ወታደሮች መሃከል ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዋቢ በማድረግ ለአለም ህብተሰብ ትግራይና የትግራይ ህዝብ እንደተጠቁ በማድረግ አሳውቋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የትግራይን ህዝብ ሰብዓዊ ጋሻ ከማድረግ ውጭ የኢትዮጵያን ህዝብንም ሆነ የትግራይን ህዝብ ሰብዓዊ ክብር ከመጠበቅ አኳያ ጥሩ ሪኮርድ የለውም፡፡ የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ግብረሰይል በመፈጸም የሚታወቅ ድርጅት ነው ፡፡ ስለ ሰብዓዊ መብት ክብር ለመናገር የሞራል ልእልና የለውም፡፡ በብዙ ሺኅ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በትግራይ ባዶ ስድስትና በመላው ሀገሪቱ ሲያሰቃይ የኖረ ድርጅት ነው፡፡ ምእራባውያን ይህን በሰብዓዊ መብት አከባበር አኳያ ጥሩ ስም የሌለውን ድርጅት ችላ ማለታቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ( በተለይም አክሱም ከተማ) ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን አንዳንድ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ተጠያቂ ማድረጉን ልብ ይሏል፡፡
 2. አንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን፣ኤኤፍፒ፣ አንዳድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በማይካድራ፣እና በሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች ስለሚፈጸሙ አሰከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ ያሰሙት ድምጽ ጎልቶ አልተሰማም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ በትግራይ በተለይም አክሱም ከተማ ስለተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ድምጻቸው ከፍተኛ ነበር፡፡ በማይካድራ ሳምሪ በተሰኙ ኢመደበኛ ወጣቶች የተፈጸመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዋነኛ አቀናባሪ የነበረው የትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት ሆኖ ሳለ የምእራባውያን ዝምታ ግን  እጅጉን አነጋጋሪ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁም ነገር ቢኖር፣ አንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና አለም አቀፍ የመብት አስከባሪዎች በኢትዮጵያ የስነ ልቦና ጦርነት የከፈቱ ይመስላል፡፡ 
 3. አስገድዶ የመደፈር መጥፎ ባህልን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር በመደባለቅ የጀመረው የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ነው፡፡ የአንድን አካባቢ ህዝብ አሰፋፈር ለመለወጥ ሲል ታሪክ የማይዘነጋው ወንጀል የፈጸመ ድርጅት ነው፡፡ በወልቃይት አካባቢ የፈጸመውን ግፍ ታሪክ በጥቁር መዝገቡ እንደሚያስፍረው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በወልቃይት አካባቢ የተፈጸመው ግፍ ብቻ የምእራባውያንን፣ በተለይም የተባበረችውን አሜሪካ ሊያሳስባቸው ይገባ ነበር፡፡ ከዚህ የበለጠ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊኖር አይችልም፡፡
 4. እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1970 የአለም አቀፍ የሰብዓዊ ረድኤት ድርጅቶች ለትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት 1ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ ሰጥተውት እንደነበር የሚያወሱ ጥናታዊ ጽፎች እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ በተለይም ኑሮአቸውን በአውስትራሊያ ያደረጉት የድርጅቱ የቀድሞው አባል አቶ ገብረመድህን አርአያ ለአንድ ባህር ማዶ ለነበረ የኢትዮጵያውያን ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንደገለጹት ከሆነ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቀጠር የአሜሪካን ደላር ወደ ህውሃት ካዝና ነበር የገባው፡፡ ለተራበው የትግራይ ህዝብ የተላከውን የምግብ ዘይት፣ዱቄትና ሌሎች የምግብ አይነቶችን ለሱዳን ነጋዴዎች ሸጠውታል፡፡ የወያኔ አገዛዝ ስልጣኑን ያደረገውን ምዝበራ ለመዘርዘር ቦታው ስላልሆነ ትቼዋለሁ፡፡ወያኔ የኢትዮጵያን ሀብት ዘርፎ የግልና የቡድን ሀብት ያከማቸ እኩይ ቡድን ነው፡፡ ለማንኛውም በአለም ባንክ ከሰላሳ አመታት በላይ በአማካሪነት የሰሩት እውቁ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ ስለ ወያኔ ዝርፊያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሰፈሩትን መረጃ እንደሚከተለው እጠቅሰዋለሁ፡፡

In the 1970s international humanitarian agencies poured in an estimated one billion dollars of aid to the TPLF. The purpose was to mitigate the devastating effects of war: famine, starvation, illness etc. What did the TPLF do with the largesse? It diverted hundreds of millions of dollars to its coffers. It sold edible oil and other consumables to merchants in the Sudan and captured the proceeds. A constant attribute of the TPLF is to capture and use political power and accumulate private and group wealth. The end goal always dictated the means, including severed heads of the dead. It is Al-Qaeda like.

ከላይ ከሰፈረው ቁምነገር ለመረዳት እንደምንችለው ምእራበውያን ፣ ከራሳቸው የዲሞክራሲ ባህል ገሸሽ ማለት እንደሌለባቸው ነው፡፡ እነርሱ ምንግዜም ቢሆን ሰልፋቸው ከዲሞክራሲ ጋር መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ አለም አቀፍ የዜና አውታሮች፣ የተባበሩት መንግስታት ልዩ ወኪሎች፣ አለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት አስከባሪዎች የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የሚያወጣቸውን የውሸት መረጃዎች መቀበል ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ወያኔ ከኢትዮጵያ ተጻራሪ የሆነ መረጃ ሲሰጥ መቀበል የለባቸውም፡፡ ይህን ስል የኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጣቸውን መረጃ ይቀበሉ ማለቴ እንዳልሆነ አንባቢውን አስታውሳለሁ፡፡ የእነርሱ ስራ በገለልተኝነት አቋም በኢትዮጵያ ምድር እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ማጣራት በማስረጃ የተደገፈ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ሪፖርት ማቅረብ ይመስለኛል፡፡ ምእራባውያን እና የዜና ወኪሎቻቸውን ይሄን ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔ ከከዳቸው የምእራቡ አለም ዲሞክራሲ የውሸት መረጃን በፈቃደኝነት እንደተቀበለ የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ የምእራቡ አለም በውሸት መረጃ ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያን ማሳጣቱን ከቀጠለበት የተዳከመች፣ የተከፋፈለች፣በጎሳ የተከፋፈሉ የማይዋደዱ፣የሚጣሉ ክልሎች ያሉባት ኢትዮጵያ፣ደሃና በእርዳታ ( በርጥባን ሀገራት) ችሮታ የምትኖር ኢትዮጵያን ማየት ይፈልጋሉ ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ለምንድን ነው አሸባሪ ቡድን የሚደግፉት ለምንድን በትግራይ ለተፈጸመው ግድያ ብቻ ከባድ ሚዛን የሚሰጡት ለምሳሌ በአክሱም የተፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ያወጡተ መግለጫ ይጠቀሳል፡፡ ሆኖም ግን  ¨በማይካድራ የተፈጸመውን አስከፊውን ጎሳ ተኮር ጭፍጨፋ ፣በምእራብ ወለጋ፣ መተክል ቤኒሻንጉል፣ጉራፈርዳ፣ በቅርቡ ደግሞ ሰሜን ሸዋ ኤፍራታ ግድም ወረዳ የተፈጸመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወዘተ ወዘተ የእነርሱ የምእራባውያን ጉዳይ ያለሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው ? (ቢያንስ አሁን ድረስ ጉዳያቸው አልሆነም፡፡ ጊዜው ሲደርስ ግን ጉዳያቸው መሆኑ አይቀርም) ለጊዜው ግን የተረዳናው ሰምተው እንዳልሰሙ፣ አይተው እንዳላዩ ሲሆኑ ለምን ? ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡

እውን የአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ፐሮቶኮል ገለልተኛ ነውን ?

በብዙ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች ጥናት ውጤትና አስተያየት ከሆነ በተለይም አፍሪካውያን ምሁራን አስተሳሰብ ከሆነ መልሱ በፍጹም ገለልተኛ አይደለም የሚል ነው፡፡

በነገራችን ላይ የሰው ልጅ ህይወት ክቡር ነው፡፡ የሰው ልጅ ህይወት ከጎሳ ወይም ከሃይማኖት ወይም ከመደብ ( class affiliation ) በላይ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የሰው ልጅ ህይወት ከጂኦፖለቲካል ሽኩቻም (ተቀናቃኞችም) በላይ ነው፡፡ ይህ እውነት ግን በኢትዮጵያ፣በቀሪዋ አፍሪካ በመሃከለኛው ምስራቅ አይታይም፡፡ ህይወት ክብር የላትም፡፡

በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ስር እንዲሰድ ሁነኛውን ሚና የተጫወተው የወያኔ አገዛዝ ነው፡፡ የወያኔ አገዛዝ የዘራው የዘረኝነት ሰብል ዛሬ እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ወያኔ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ስሜት እንዲጠፋ፣የሰው ልጅ ህይወት ዋጋ እንዳይኖረው፣ሁነኛውን ሚና እንደተጫወተ ያሳየናል፡፡ የውጭ ሀይሎች በተለይም ታሪካዊ ጠላቶቻችን፣ አንዳንድ አለምአቀፍ ድርጅቶችም ሳይቀሩ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ስሜት እንዲደበዝዝ ወይም እንዲጠፋ የማያደርጉት ሴራ የለም፡፡በቀድሞው ዘመን የነበረው መተሳሰብ፣ አንቺ ትብሽ፣ አንተ ትብስ መባባል፣ መረዳዳት፣ ሀዘንና ደስታ ላይ መካፈል፣ ፍቅርና አንድነት ወዘተ ወዘተ ዛሬ አፈር ድሜ እየጋጠ የሚገኘው ከብዙ አመታት ሴራና ሸፍጥ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡

በነገራችን ላይ በአንድ ሀገር የሚከሰትን ትራጀዲ አይቶ አንዳላዩ መሆን፣ ጆሮ ዳባ መልበስ፣ በምክንያት የሚደረግ ነው፡፡ በአንድ ሀገር አንድነት መዳከም፣በአንድን ሀገር መከፋፈል የሚያተርፉ የውጭ ሐይሎች የሚከተሉትን ስልት ይከተላሉ፡፡

 • ግጭቶች እንዲስፋፉ፣ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለሚፈጽሙ እኩይ ቡድኖች በረቀቀ ዘዴ ይረዳሉ፡፡ ( በገንዘብና የጦር መሳሪያ በማቅረብ ሊሆን ይችላል፡፡)
 • የሀሰት ዜናዎችን ማሰራጨት (Disinformation and or misinformation is a tool )
 • በአንድ ሀገር ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ግዛቶች የሰብዓዊ መብት ቢፈጸሙም እነርሱ ማለትም ምእራባውያን ትኩረት የሚሰጡት ከራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም አኳያ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ወለጋ፣ቤኒሻንጉል፣ጉራፈርዳ፣ሰሜን ሸዋ ዞን ወዘተ ወዘተ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸሙ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ፣ አይተው፣ እንዳላዩ ሆነዋል፡፡ በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ በትግራይ አክሱም የተፈጸመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የውግዘት ናዳቸውን አውርደዋል፡፡ ለምን ይሆን በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የረሷቸው በተቃራኒው በትግራይ ክልል ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጩሀታቸውን ያቀለጡት ለምን ይሆን እኔ እንደሚገባኝ የሰብዓዊ መብት አለም አቀፍ ባህሪ ያለው ነው፡፡ በማናቸውም የሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ሰቆቃዎች እኩል ትኩረት ወይም ውገዘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሁሉም ሰዎች በሰውነት ደረጃ እኩል ናቸው፡፡
 • እኔ ያየሁት ክፈተት

ታላላቅ የፖለቲካ ተንታኞች ምሁራን በየግዜው ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከሰጡት ቃለምልልስ ላይ ለመረዳት እንደቻልኩት የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ ግንኙነት ስራዎችና በዲፕሎማሲ ትግል አኳያ ውጤት ማምጣት አልቻለም ወይም ደካማ ነው፡፡የኦነግ ሸኔ ተብሎ የሚጠራው ሀይልም ሆነ የትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት ኢትዮጵያ ላይ ያወረዱትን መአት በተመለከተ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ በተገቢው መንገድ ያሳወቀ አለመስልህ አለኝ፡፡ ከዚህ ባሻግር አለም አቀፍ በገንዘብ የተገዙ ሎቢስትስ የሚያደርጉትን ሴራ ለማክሸፍ፣በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ልተሰጠም፡፡ኢትዮጵያን በተመለከተ የሀሰት ዜና የሚያሰራጩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን፣ ደግሞ የሚያሰራጩት ዜና ሀሰት ስለመሆኑ ለአለሙ ህብረተሰብ የሚያስረዱ ጋዜጠኞች ጥቂቶች ናቸው፡፡

ድክመታችንን እንዴት ማረም እንችላለን ?

 • የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከፊት መስመር ላይ በመሆን ቁልፍና ሰትራቴጂክ ወዳጅ ለሆኑ ሀገራት መሪዎች የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ በግልጽ ማስረዳት፣ መወያየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ( በተለይም ለተባበረችው አሜሪካ፣ለተላቋ ብሪታኒያ፣ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሕዝባዊት ቻይና፣ ለሩሲያ ፌዴሬሽን፣ህንድ፣እስራኤል፣ጃፓን፣ ቱርክ፣ ለስካንዲኒቪያን ሀገራት፣ ቤልጂዬም፣ በአፍሪካ ሀገር ቁልፍ ወይም ወሳኝ ለሆኑ መሪዎች ሊሆን ይችላ፡፡)

የጋራ መተማመን፣ ኢትዮጵያን ለመታደግና እና እውነትን ለማስረዳት ፊተለፊት ተቀራርቦ መነጋገር መተኪያ የለውም ፡፡ ኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘረውን የውሸት ሰበዝ ለመከላከል እጅግ አድካሚና ያልተቋረጠ የህዝብ ግንኙነት ስራ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ባሻግር ዋነኛውና መሰረታዊው ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ግዜ በላይ አንድነታቸውን መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከመከፋፈል በፍጥነት ማዳን አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ካጠነከሩ ከገጠማቸው መጥፎ እድልና ፈተና ይገላገላሉ፡፡ ለአብነት ያክል ግብጽ፣ኢትዮጰያና ሱዳን በታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ዙሪያ የሚያደርጉት ውይይት በአፍሪካ  ህብረት አደራዳሪነት  እንዲሆን፣ ሆኖም ግን፣ ኢትዮጵያውያን የዲፕሎማቲክ ሰዎች በተለይም በምእራቡ አለምና በተባበረችው አሜሪካ መቀመጫቸውን ያደረጉ፣ የኢትዮጵያ ተወካዮች የምእራቡ አለምም ሆነ የተባበረችው አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ሳይገቡ በቴክኒክ እርዳታ ብቻ ጣልቃ እንዲገቡ መወትወት ኢትዮጵያዊ እና ሙያዊ ግዴታቸው ነው፡፡ ይህንን መንፈሳዊ ግዴታቸውን መወጣት ከሆነላቸው አለም በሀሰት መረጃ ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያን መልካም ስእል እንዳያጠለሽ ያግዛል፡፡ በነገራችን ላይ የምእራቡ አለምም ሆነ የተባበረችው አሜሪካ ከትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት ቆመው የነበረው፣በሀሰት መረጃ ላይ ተመስርተው ነበር፡፡ (ይህ ሲባል ግን የኢትዮጵያ መንግስት ስህተት አልነበረውም ማለት ተላላነት ይመስለኛል፡፡ የወያኔ ፕሮፓገንዲስቶች፣ ሎቤስት እንደሚደሰኩሩት ፣በትግራይ ክልል የተፈጸሙትን ሀጢያቶች ሁሉ በመንግስት ላይ ማላከክ ተገቢ አይደለም፡፡ ፣አንዳንድ በመንግስት አኳያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ግን ነበሩ፡፡ ) እውነቱን ለአለም ለማሳወቅ ግን የኢትዮጵያ መንግስት መበርታት አለበት፡፡ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ክልል የተፈጸሙትን  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለማጣራት ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጎንለጎን እሰራለሁ ማለቱ ፣ መንግስትም መፍቀዱ ይበል የሚሰኝ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ ሀገር፣ በበርካታ ግዛቶቿ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባት ሀገር በመሆኗ ለሌሎቹም ትኩረት ቢሰጥ መልካም ነው ባይ ነኝ፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርምራ ስራዎች ላይ አንጋፋ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤም ቢጋበዝ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፡፡

ማተኮር ያለብን ምን ላይ ነው ?

የምእራቡ ሀገራት ተወካዮች ማተኮር ያለባቸው በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ነው፡፡

 • የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፍላጎት ማክበር
 • የራሳቸውን ስትራቴጂክና ብሔራዊ ፍላጎት አለመርሳት ( እነርሱ መንግዜም ቢሆን ብሔራዊ ፍላጎታቸውን አሳልፈው ሰጥተው አያውቁም)
 • በአፍሪካ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን መርዳት ይገባቸዋል፡፡

በነገራችን ላይ አንድነቷ የተጠበቀ፣ ሰላም የሠፈነባትና የተረጋጋች ኢትዮጵያ፣ሁሉንም ህዝቧን አካታች የሆነች ኢትዮጵያ፣ ዲሞክራቲክና በእድገት ጎዳና የምትራመድ ኢትዮጵያ ለአፍሪካው ቀንድና ከሰሃራ በታች ለሚገኙ ሀገራት ሁሉ የምትበጅ( የምትጠቅም) ሀገር ናት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ላለፉት 46 አመታት የነበሩት ማስረጃዎች ፍንትው አድርገው እንደሚያሳዩን ከሆነ፣ የወደቀው ወያኔ ኢትዮጵያን ለማዳከምና እድሏን አሳዛኝ ለማድረግ በብዙ ባጅቷል ወይም እስከ እለተ ሞቱ ድረስ የሴራ ገመዱን ሲጎነጉን ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ የተከፋፈለችና አንድነቷ የተናጋ፣ በጦርነት ቋያ ውስጥ እንድትነድ ያልማሱት ጉድጓድ፣ያልበጠሱት ቅጠል አልነበረም፡፡ ዛሬም ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር፣ ከመቼውም ግዜ በላይ እንቅልፍ አጥተው እያሴሩ ይገኛሉ፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ወያኔ በጉቦ እስከ ጭንቅላቱ ድረስ ተዘፍቆ የነበረ፣ ጨካኝ፣ የዲሞክራቲክ ጸር፣የኢትዮጵያ ጠላትና  ማፊያ የሆነ ስብሰብ ነው፡፡ (Mafia like entity)

ስለሆነም በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ የወያኔ ማፊያ ቡድን ደጋፊዎች ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚያደርጉትን ሴራ እግር በእግር እየተከታተሉ ማውገዝ ፣ እንደ ችሎታቸው ለአለም ህብረተሰብ ማጋለጥ ኢትዮጵያዊ ግዴታቸው ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ይህ ብቻውን በቂ አይደለም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሲቪል ማህበር ውስጥ የተቃፉ ወይም ሲቪል ናቸው፡፡ እነርሱ የመንግስትን ስራ ተክተው መከወን አይቻላቸውም፡፡ የእነርሱ ኡኡታ፣ጩሀት ወይም ማመልከቻ ለሪኮርድ ብቻ የሚጠቅም ይሆናል፡፡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያን ወክለው ኢትዮጵያን በተመለከተ ለጸጥታው ምክር ቤት ማመልከቻ ማቅረብ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት የሚመዘዙ የሀሰት ወሬዎችን፣ ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለጸጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረብ ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት ሀላፊነት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆመው ( የኢትዮጵያ እውነተኛ ወዳጅ ) ማን ይሆን ?

ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚሰራጩ ሀሰተኛ ዜናዎች ወይም የኢትዮጵያን እውነተኛ ታሪክ ለማናጋት የሚቀርቡ የሀሰት ትርክቶች፣ ወይም ሆን ተብለው አለምን ለማደናገር የሚሰቀርቡ መረጃዎች፣ በአለም ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያን አለም አቀፍ ደረጃ ጭራ እንዳደረገው የኢትዮጵያ መንግስት በሚገባ መረዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ በአጼ ሐይለስላሴ ዘመነ መንግስትና ዛሬ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነትና ክብር በተመለከተ ያለውን ልዩነት ለአንባቢው ትቼዋለሁ፡፡ አጼ ሀይለስላሴ በእነ አይዘን አወር፣ዊንሰተን ቸርችል ይደረግላቸው የነበረውን የክብር አቀባበል ስናስታውስ በትዝታ እንባችን ኩልል ብሎ ይፈሳል፡፡ አጼ ሀይለስላሴና ኢትዮጵያ በአፍሪካና በአለም የነበራቸውን ደረጃ ስናስታውስ ኢትዮጵያ ምን ያህል በአለም መድረክ ላይ የተከበረች ሀገር መሆኗን አንረዳለን፡፡ ይህን ታላቅ ክብር ሀሰተኞች በሀሰት ትርክት አለምን ሲያደናግሩ ማየት ያማል፡፡ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ኮሌክቲቭ ሴኩሪቲ ተግባር ከህንድ ፓኪስታንና ህንድ የማያንስ ገድል የሰራች ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ጊዜ የሠጠው ቅል…..እንዲሉ ዛሬ ትንንሾችና ወፍ ዘራሾች ተነስተው የውሸት መረጃ በማቅረብ አለምን ለማደናገር ( ለግዜውም ቢሆን) በመቻላቸው የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን ወደነበረችበት ታላቅ ክብር ለመመለስ የመጀመሪያው ሀላፊነት አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች ይሆናል፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ወይም እኩል ደረጃ የሲቪሉ ማህበረሰብ፣የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተራው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሶስት አስርተ አመታት በላይ የሰፈነውን የጎሳ አጥር በማፈራረስ ወንድማማችነትና ትብብርን መስፈን ይጠበቅበታል፡፡

ለአብነት ያህል በትግራይ ተፈጽሟል ስለሚባለው የሠብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ አለም ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች፣ በታወቁ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ትክክለኛውን ስእል ለአለሙ ህብረተሰብ ማሰማት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በሰዎች ላይ አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ቢሆን ለአብነት ወለጋ፣ቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ወዘተ ወዘተ በንጹሃን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ ብሔር ተኮር ኢሰብዓዊ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ ይህ ክፉ ድርጊት ደግሞ ጠባሳው ዘመን ተሻጋሪ ነው፡፡  ይህም ብቻ በኢትዮጵያውያን መሃከል አንድነት እና መተማመን ለመፍጠር አመታት ሊፈጅ ይችላ፡፡ስለሆንም በትግራይም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም፣ለኢትዮጵያ ወጣቶች ተስፋ ለመስጠት፣ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በማካተት መምራት የኢትዮጵያ መንግስት ሃላፊነት ይመስለኛል፡፡ የውጭ ሀገር ፖሊሲያችንም ቢሆን አካታች መሆኑ ክርክር የሚያስነሳ አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ለመከወን መንፈሳዊ ወኔ ከታጠቀ ከገባንበት ውጥንቅጥ ለመውጣት እንችላለን ብዬ እባለሁ፡፡ 

ምእራባውያን በኢትዮጵያ ስለሚፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የሚሰጡት ምላሽ

በዊኪፒዲያ፣ነጻ ኢንሳይኮሎፒዲያ በአክሱም ከተማ ስለተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የሚያሳይ መረጃ ተጽ ይገኛል፡፡ በመረጃ ቋቱ መሰረት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች እንደተደገሉ ተጽፎ ይገኛል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎቹም የኤርትራ ወታደሮች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

Perpetrators: Eritrean Defense Forces (unsubstantiated

ከላይ የሰፈረው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንድናነሳ ግድ ይለናል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች የኤርትራ ወታደሮች ከሆኑ ለምን ይሆን የአለም አቀፉ ህብረተሰብ ለአብነት ያህል የብይነመንግስታቱ ልዩ ተወካይ ሚካኤል ባሺሌት (Michelle Bachelete )፣ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ( ሲኤንኤን፣ኤኤፍፒ፣ቢቢሲ፣አለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣እንደ ማርቲን ፕላውትን (Martin Plaut) የመሳሰሉ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ወዘተ በፊትለፊት ያላወገዟቸው  ? ይህ በእንዲህ እንዳለ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመፈጸሙ በፊት ብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንጀለኞች ከትግራይ ዘብጥያዎች በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊተአውራሪዎች ትእዛዝ መፈታታቸውን ከመገናኛ ብዙሃን ተሰምቶ ነበር፡፡ ( ወንጀለኞች ፍርዳቸውን ሳይጨርሱ ከእስር አለህጋዊ አግባብ ከተለቀቁ የሚያደርሱትን ጉዳት በተመለከተ ለአንባቢው ህሊና ትቼዋለሁ)፣ ዛዲያ ለምንድን ነው እነኚህ የምእራብ ሀገራት ወኪል የሆኑት አለም አቀፍ ድርጅቶች ወንጀለኞች ተፈተው ሜዳ ላይ በመለቀቃቸው ምክንያት ስለሚያደርሱት ሰብዓዊ ቀውስ በተመለከተ ቢያንስ የህሊና ምስክርነት ለመስጠት የተቆጠቡት ? ለምን ይሆን በማይካድራ ተፈጽሞ ስለነበረው ብሔር ተኮር ፍጅት፣ በምእራብ ወለጋ፣ ቤኒሻጉል፣ አማሮ ወዘተ ወዘተ በየጊዜው ስለሚፈጸመው ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ በተመለከተ ትግራይ ክልል ከተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እኩል ትኩረት ያልሰጡት ? ህሊና የፈጠረባችሁ ጠይቁ፡፡

በነገራችን ላይ የወያኔ አገዛዝ የፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ገና ሙሉበሙሉ ይፋ አልሆነም፡፡ ታሪክ ወደፊት ግን በጥቁር ማህደር ውስጥ ከትቦት ያልፋል፡፡ አለምም ገና ያወቀው አለምስልህ ብሎኛል፡፡ ላለፉት ሃምሳ (50) አመታት ወይም ግማሽ ክፍለዘመን ያህል የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት(ወያኔ) እና ስትራቴጂክ የጥፋት አጋሮቹ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸማቸው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እንዲሁ በአጭር ጽሁፍ የሚቋጭ አይደለም፡፡ የቀድሞው የድርጅቱ አባል የነበሩት አቶ ገብረመድህን አርአያ እና አቶ አብርሃም ያይህ በተለያዩ ግዜያት፣ ለበርካታ ኢትዮጵያዊ መገናኛ ብዙሃንና የመጽሔት ዝግጅት ክፍሎች ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ የወያኔን ግፍ በእውነትና ሞራል መሰረት ላይ ቆመው የህሊና ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ለአብነት ያህል በወልቃይት ጸገዴ፣ጠለምት፣ራያ እና ትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች፣ የጅምላ ፈጅት ስለመደረጉ የሚያሳዩ የጅምላ መቃብር ይገኛሉ ብለው ነበር፡፡ ለምንድን ነው ይህ መራር እና ጎምዛዛ ሀቅ የተዳፈነው ? ( ለግዜውም ቢሆን በአለም አቀፉ ማህበረሰብ አልተጠየቀም) የተዳከመችና የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ማየት ካልፈለጉ በቀር የአለም አቀፉ ህብረተሰብ በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛቶች በወያኔም ሆነ የጥፋት አጋሮቹ፣ወይም ሌሎች ወንጀለኞች የተፈጸሙትን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ሁሉ በማስረጃ በማስደገፍ ካወጡ በኋላ ጥፋተኞች በአለም አቀፍ የፍትህ አደባባይ የሚቆሙበትን መንገድ በተመለከተ የመፍትሔ ሀሳብ መፈለግ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

የወያኔ ግፍ በወፍ በረር ሲቃኝ

ሀ.በአልባኒያ ስታሊንስት ርእዮት ተጠምቆ፣በደደቢት በርሃ ሲጸነስ የትግራይ ማርኪሰስት፣ ሌኒንስት ሊግ፣ ኋላ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት፣የትግሉ ዋና አላማ የነበረው፣የታላቋን ትግሪኝ ትግራይ ሪፐብሊክ ለመመስረት እና ኢትዮጵያን በማይስማሙ ክልሎች ለመከፋፈል (Balkanize Ethiopia) እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ጠበብት የሄዱበት ጉዳይ ነው፡፡

ለ.የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት በማኒፌስቶው ላይ ቁልጭ አድርጎ እንዳስቀመጠው የአማራን ብሔር እንደ ጠላት አድርጎ የቆጠረ እኩይ ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች በሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች ላይ ለተፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ሁሉ በዋነኝነት የወያኔ ቡድን ነው፡፡

ሐ. የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ታሪክ በመክዳት ወደ 100 ( አንድ መቶ አመት) ዝቅ ያደረገ ነው፡፡
መ. የወያኔ ርእዮት አለም አብዮታዊ ዲሞክራሲ የተሰኘ ሲሆን፣ ይሄውም በከፋፍለህ ግዛ እኩይ ሴራ ኢትዮጵያን ሲገዛ ቆይቶ ነበር፡፡

ሠ. እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1991 ጀምሮ ግባተ መሬቱ እስከተፈጸመበት ጊዜ ድረስ ( ኢትዮጵያውያንን እንደ ሰም አቅልጦ፣ እንደ ብረት ቀጥቅጦ ለ27 አመታት ገዝቷል፡፡)  ጎሳና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ ህገመንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በመጫን የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፍሎ ገዝቷል፡፡

ረ. የምእራባውያን ወዳጅ የነበሩት ሟቹ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለሰ ዜናዊ፣ አሻንጉሊት መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ በመፍጠር፣ የውሸት ጊዜውን የጠበቀ፣ነጻና ገለልተኛ ምርጫ በማካሄድ ( የይስሞላ ምርጫ በማካሄድ)፣ ያልታመኑ መገናኛ ብዙሃንን በመፈልፈል፣ የኢትዮጵያን ድንግል መሬቶች ለድንበር ዘለል ኩባንያዎች በአለም ርካሽ በሆነ ዋጋ በመሸጥ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት በውሸት የኢኮኖሚ ቀመር አጋኖ በማስቀመጥ ይታወቁ ነበር፡፡ ( የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ እድገት ታይቶ የማይታወቅ እደገት አስመዝግቧል ተብሎ በብዙ ቢደሰኮርም፣ ህዝቡ አላለፈለትም፡፡)

ሰ.ከወያኔ አገዛዝ በፊት በነበሩት የኢትዮጵያ አገዛዞች ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ ፣ የአቶ መለስ አገዛዝ በ10 ቢሊየን የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር እርዳታ አግኝቶ እንደነበር፣ ሆኖም ግን አብዛኛው የብድር ገንዘብ ፓርቲያቸው እንደተቀራመተው፣የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ እዳ ውስጥ እንደተፈቀ፣ ስመጥር ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚ ጠበብት በጥናት ያተጋገጡት ጉዳይ ነው፡፡

ሸ. የኢትዮጵያ ህዝብ እዳ ውስጥ ሊዘፈቅ የቻለበት መሰረታዊ ምክንያቱ፣ይህ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በእርዳታ ስም ሆነ በብድር ስም ሀገሪቱ ስታገኝ፣ እንደ መልካም አጋጣሚ(ደግነት) በመቆጠሩ ነው፡፡ ይህ ብዙ ሰዎችን ያሳስታል፡፡ አውሮፓውያን ገንዘብ የሚበድሩት ወይም የሚረዱት እንደው ዝም ብለው አይደለም፡፡ ምክንያት አላቸው፡፡ ለሌላው የአፍሪካ ሀገራት እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ ኢትዮጵያን የእነርሱ ዘላለማዊ ጥገኛ ለማድረግ ነው ገንዘብ የሚያበድሩት፡፡

ቀ. የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራዎች በሀብት ማማ ላይ ሲንጠለጠሉ፣ ኢትዮጵያ ከአለም ሐገራት ሁሉ በድህነት ተርታ ላይ ከተሰለፉት ሀገራት ጋር ትገኛለች፡፡

በ.እንደነ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ እና ዶክተር በፍቃዱ በቀለን የመሰሉ እውቅ የምጣኔ ሀብት ጠበብት በጥናት እንደደረሱበት ከሆነ በብዙ ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር ከሀገር እንዲሸሽ ተደርጓል፡፡ ዋነኞቹ ተዋናይ ደግሞ የትግራይ ነጻአውጪ ማፊያ ድርጅት የፖለቲካ ፊተአውራሪ ናቸው፡፡

 • ይህ ከሀገር ተዘርፎ የወጣው መጠነ ሰፊ ሀብት ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት  ይገኛል፡፡ ወይም ኢትዮጵያን ለመቅጣት እየዋለ ነው፡፡

-ያዘጋጁት የምርጫ ውድድር ሁሉ ራሳቸውን ለስልጣን ለማብቃት በሚያስችል መልኩ ነበር፡፡

– ወያኔ ኢትዮጵያን ሲገዛ የነበረው በብረት ሀይል ነበር፡፡በ10ሺህዎች የሚቆተሩ ዜጎችን አስሯል፡፡(ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ መሪዎችና አባላት፣ የሀይማኖት አባቶች ይገኙበት ነበር፡፡) በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ገድሏል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያ ዜጎችን ከመሬታቸው ያናቀለ እኩይ አገዛዝ ነው፡፡ 

– ሁሉም ቁልፍ የፌዴራል መንግስቱ ተቋማት፣ብሔራዊ ጸጥታ ድርጅት፣ብሔራዊ መከላከያ፣የዲፕሎማቲክ ቦታዎች፣የቴሌኮሚንኬሽንና ፖስታ ድርጅቶች፣የኢትዮጵያ አየርመንገድ፣ቁልፍ ኢንዱስትሪዎች፣የገቢና የውጭ ንግድ፣የመሬት ሽያጭ፣የሕንጻ ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ ጉሙሩክና ሌሎች ስትራቴጂክ ተቋማት በዋነኝነት በህውሃት አባላት፣ የተረፉት ደግሞ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን እንደ ፖለቲካ ታማኝነታቸው ደረጃ የተያዘ ነበር፡፡

– አብዛኛውን የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብትና ፖለቲካውን ተቆጣጥረውት ነበር

 

በነገራችን ላይ የወያኔ አገዛዝ በህዝባዊ አመጽ ከምኒሊክ ቤተመንግስት ከስልጣኔ ተሸንጥሮ ከወደቀ በኋላ ምሽጉን ያደረገው በሰሜናዊት ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ነበር፡፡( ነበር ልበል ዛሬ መቀሌን ለቆ በመሄዱ)፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ድርጅቱ ማናቸውንም የሰላም መፍትሔ ( አማራጭ) መቀበል እንደማይፈልግ ከሚያደርጋቸው እኩይ ተግባሩ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ለአብነት ያህል፣ በኢትዮጵያ ላይ የጦር ወንጀል ፈጽሟል( መገለጫው ደግሞ በኢትዮጵያ የጦር ሀይል አባላት ላይ ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ ግድያ ፈጽሟል፡፡(በሰሜን እዝ ስር የነበሩትን ኢትዮጵያዊ ወታደሮች ላይ ማለቴ ነው)፡፡

 ( በማይካድራ ከተማ ንጹህና ሰላማዊ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ጨፍጭፏል፡፡ በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ሀይማኖትና ጎሳን መሰረት ላደረጉ ግጭቶች ውስጥ እጁ እንዳለበት የሚያሳዩ መረጃዎች በየግዜው ከተጎጂዎች አንደበት ሲነገር ተሰምቷል፡፡ በትግራይ የሚገኙ የመገናኛ አውታሮችን አውድሟል፡፡ በኤርትራ አስመራ ከተማ በኢትዮጵያ ባህርዳር ከተማ በሚገኙ የሲቪል አውሮፕላን ጣቢያዎች ላይ የሮኬት ድብደባ አድርጓል፡፡

ሆነም ግን ይሁንና ይህ እኩይ ድርጅት በምእራባውያን ዴሞክራሲና በብይነ መንግስታቱ ልዩ ወኪሎች ወይም በአጭሩ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ,የሚደገፍ መሆኑ ሲታሰብ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች በጥናታቸው እንዳረጋገጡት ከሆነ የወያኔ ቡድን መኖር ስጋቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካው ቀንድ የሚተርፍ ነው፡፡ የወያኔ ርእዮት አለም ፍልስፍና ለኢትዮጵያውያንና ለትግራይ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችን በሰላም መኖርን፣እድገትን፣ጸጥታን እንደማያመጣ ለብዙ ግዜ በገቢርም፣በነቢብም ታይቷል፡፡ ትግራይ እንደ አንድ ክልል፣ የትግራይ ተወላጆች፣ የኢትዮጵያ አንድ አካል ናቸው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊነታቸውን ይዘው እንዲዘልቁ መበረታታት አለባቸው፡፡ ትግራይን እንደ ነጻ ግዛት መቁጠር ከባድ ስሀተት ነው፡፡ ስለሆነም አለም አቀፉ ማህበረሰብ የማይለወጠውን እውነት መቀበል ያለበት ይመስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ አለመታመን፣የሀሰት ወሬ መንዛት፣ውሸት የወያኔ ተፈጥሮአዊ ባህሪዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም፣ በተለይም የትግራይ ተወላጅ ወንዶሞቻን፣ እህቶቻችን የወያኔን ውሸት አደባባይ በመውጣት እርቃኑን ማስቀረት አለባቸው፡፡

በተለይም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ መረዳት ያለበት ቁምነገር ቢኖር የወያኔ ስግብግብነት፣ውሸት በተመለከተ የሚነገረው እንደው ዝም ብሎ ሳይሆን መሰረት ያለው፣ ማስረጃ ማቅረብ የሚቻልበት መሆኑን ነው፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1970ዎቹ ላይ( በትግል ላይ ነበሩ) ከአለም አቀፉ ህብረተሰብ ለሰብዓዊ እርዳታ የተሰጣቸውን 1ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በራሳቸው ካዝና ውስጥ እንደዶሉት አቶ ገበረመድህን አርአያ የተባሉ የቀድሞው የወያኔ አባል አጋልጠዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር አክሎግን የመሰሉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ደግሞ በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ አስፍረውታል፡፡ ይህ እኩይ ድርጊት ደግሞ የተፈጸመው የትግራይ ወንድሞቻችን በድርቅና ጠኔ እንደ ቅጠል በሚረግፉበት በዛ ክፉ ግዜ ነበር፡፡ ከላይ በስም የጠቀስኳቸው ኢትዮጵያዊ ግለሰቦች እንዳረጋገጡት የምግብ ዘይትና ሌሎች የፍጆታ እቃዎች የተሸጡት ለሱዳን ነጋዴዎች ነበር፡፡

በመጨረሻም አለም አቀፍ የሠብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ወኪሎች በብርቱ እንዲያስቡበት የማስታውሰው ጉዳይ ቢኖር ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ሁለት፣ሶስት ግዜ እንዲያስቡበት ነው፡፡

የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት እንደ 1970ዎቹ ሁሉ ተመሳሳይ ድርጊት ይፈጽማል ብሎ መጠበቅ ተላላነት ቢመስልም፣ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ሁነኛ ደጋፊ የሆኑና ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመከፋፈል ሌላ ድብቅ አላማ ያላቸው ቡድኖች በተግራይ የጠከሰተውን ሰብዓዊ ቀውስ እንደመሳሪያ ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ መገመት ፣ ከእውነት መራቅ አይመስለኝም፡፡

 

.

Filed in: Amharic