>

ማስተባበሉ አያዋጣም! (ጌታቸው ሽፈራው)

ማስተባበሉ አያዋጣም!

ጌታቸው ሽፈራው

የስነ ጥበብ ባለሙያዎች ሽልማት ላይ የተነሳውን ቅሬታ ጠበቅ ያለ በመሆኑ አዘጋጆቹ የጨነቃቸው ይመስለኛል። እንደኔ የመጀመርያ እንደመሆኑ ስህተት ይፈጠራል ብለው ቢያልፉት ይሻላል። ሲቀጥል ደግሞ ተቻኩለው ያደረጉት ነው። ከመንግስት ጋር ሆነው ያደረጉት እንደመሆኑ በዚህ የጥድፊያ ወቅት የተደረገ ነው ብለው ቢጨምሩበት ሕዝብ ይረዳቸዋል። ከዚህም ባሻገር በመሃል ያልሆነ መመዘኛ የሚያመጣ ሰው አለ። ጫና የሚያሳድር ሰው ይኖራል። አንዳንዶቹ ይህን ጉዳይ ለማስተባበል የሞከሩ ሰዎች በጥሩ ስብዕና የምናውቃቸው ናቸው። ግን በሂደቱ ጫና ሊኖር እንደሚችል እንረዳቸዋለን።
ግን  ዝርዝር መረጃ አምጥቶ መመዘኛ ነው ብሎ መከራከሩ አያዋጣም። ያጋልጣል ይበልጡን። “እንዴ ምንድን ነው ነገሩ?” ያስብላል። ለምሳሌ ሊሸለም ይገባው ነበር የተባለው አንደኛው ታማኝ በየነ ነው።  የቴዎድሮስ ካሳሁንን በእድሜ ብለው ሊያስተባብሉ ሞክረዋል። እድሜ መመዘኛ መሆን አልነበረበትም። እስኪ ለጊዜው እድሜውንም በሚያሟላው ታማኝ መመዘኛዎቹን እንያቸው። ዛሬ የሽልማቱ መመዘኛ ብለው ያስተባበሉባቸው ቅሬታውን የሚያባብሱ ናቸው።  መመዘኛዎቹ የተባሉት ከስር የተጠቀሱት ናቸው።
 
1/ በኢትዮጵያ ሥነ ጥበባዊ ልምምድ ውሰጥ አዲስ ፈለግ ያስተዋወቁ:_ 
 ጥሩ መመዘኛ ነው። ታማኝ በመድረኩም በሌላውም የራሱ የሆኑ ፈለጎችን ያስተዋወቀ ሰው ነው። የሙያ አጋሮቹ ሳይቀሩ የሚያከብሩለት አበርክቶ ያለው ሰው ነው።   ከተሸለሙት አብዛኛዎቹ መካከል በጉልህ የሚታይ ፈለግ አለው። እንዲያውም ወደ ዝርዝር ብንገባ ፈለግ ያላስተዋወቁም እናገኛለን።
2/ ሦስት አራተኛ የሕይወት ዘመን ዕድሜያቸውን በሙያው ውስጥ ያሳለፉ:_
 አሁንም አርቲስትና አክቲቪስት እያላችሁ የምትጠሩት ለዛው መሰለኝ። ነው ነጠላ ዜማ ማውጣት አለበት?
 3/ለሥነ ጥበባዊ እንቅስቃሴ በማይመች ሁኔታ ውስጥ፣ ፈተናውን ተጋፍጠው፣ ጥበባዊ አስተዋጽዖ ያበረከቱ:_
 ይችኛዋ ዝም ብላ የእሱ ናት። በስጦታ ጠቅልላችሁ ስጡት። በዚህ ሽልማትኮ ከመጣው ጋር አጎብድዶ ያለፈው፣ በመንግስት በጀት ሲሰራ የኖረውም ሳይቀር ተሸልሞበታል። ሽርጥ እየለበሰ ደደቢት የሄደ የለም?
 4/ [እንደየ አግባቡ] በባለሙያዎች እና በሕዝብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ:_
 በዚህም ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲያውም በስህተታቸው ሕዝብ አሽርፏቸው የሚሄዱም ተሸልመዋል።  ሕዝብ የሚጠላቸው፣ ጥበቡን ተጫወቱበት የተባሉ፣ ከጥበቡ ይልቅ ከገዥዎቹ ጋር ያላቸው ግንኙነት አሁናዊ ሰብናቸውን የያዘው ሰዎች ተሸልመዋል።
5/ለአዲስ ትውልድ ዕውቀት እና ልምዳቸውን ያካፈሉ። ወይም ውጣ ውረድን ያቀለሉ።:_ 
ይህም ለታማኝ ቀላል መመዘኛ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከተሸላሚዎች መካከልም አርዓያ የማይሆኑ ሞልተዋል።
6/ ለማኅበረሰብ ሕይወት መሻሻል፣ ለማኅበረሰባዊ ዕሴት መዳበር፣ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ተዛማጅ ለኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱ:_
 ሕዝብ ለሕዝብ ፕሮግራም አንደኛው እንዱ አርቲስት ታማኝ በዚህ መመዘኛ የመጀመርያው ነው። ያ ቡድን እንዲቀጥል ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገ ነው። ወይ ቡድኑን እንደ ቡድን መሸለም ነበር። ከዛ ቡድን ደግሞ ታማኝ አይነጠልም። ሀገር የገነቡ አባቶችን ከሂትለር ጋር እያመሳሰለ የዘፈነ ተሸልሞ ስለ ሀገር አንድነትና ሉአላዊነት ሲለፋ የነበረ ታልፏል ነው። የክልል ሉአላዊነትን ካልተከበረ እያለ የኖረ ተሸልሟል። ሌላው ታልፏል። ሕዝብን ከሕዝብ የሚነጥል ዘፈን ዘፍኖ የተሸለመ ባለበት ስለ ሕዝብ አንድነት የሰሩ ተረስተዋል።
ያው ጠቅላይ ሚኒስትሩም አሜሪካ ሄደው “ታማኝ ካልመጣ” ያሉት አስተዋፅኦውን ስለሚያውቁ ነው። ከተመረቁት መካከል አሜሪካ የነበሩት የግድ ካልመጡልኝ አልተባሉም። አዲስ አበባም የግድ ካላገኘኋችሁ አልተባሉም።
7) የተሸላሚዎቹ ዕድሜ፥ ስድሳ እና ከስድሳ በላይ መኾን ይኖርበታል:_
 አይ እድሜ! አይ እድሜ! አይ እድሜ! መጀመርያ ነገር እድሜ መመዘኛ መሆን አልነበረበትም። ከሆነስ የየትኛው አርቲስት እድሜ ነው የሚታወቀው? በእርጠኝነት በእድሜ ቢሆን መመዘኛው አብዛኛው አርባዎቹ አጋማሽ ነኝ ማለቱ አይቀርም ነበር። ሌላው ደግሞ ከተሸላሚዎቹ መካከል ብዙዎቹ በእድሜ ከእነ ታማኝ የሚያንሱ ናቸው። ለምሳሌ ማንያዘዋል እንደሻው፣ ነዋይ ደበበ፣ፀጋዬ እሸቱ፣ኩኩ ሰብስቤ፣ ፀሀዬ ዮሀንስ፣ ሀመልማል አባተ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ነፃነት መለሰ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ ታማኝን ትንሽ በእድሜ ሊበልጡት ይችላሉ። አበበ ብርኔ፣ ሞገስ ተካ፣ መሉአለም እጅጉ በእድሜ ከታማኝ የሚያንሱ ቢሆኑ እንጅ አይበልጡም። ብዙ በእድሜ የሚያንሱ አሉ።
8 ተሸላሚው ጥበበኛ በሕይወት ያሉ ሊኾኑ
           ይገባዋቸል:_
 ደውሉለት! በሽልማቱ ባለመካከቱ ደስተኛ መሆኑን ይነግራችሁ ይሆናል። መቸም ሊከፋው አይችልም።
በዚህ ጉዳይ መፃፌ የሚሰጡት ማስተባበያዎች የማያስተምሩ በመሆናቸው ነው። በሌላው መስክም ግልፀኝነት እንዲኖር፣ ስህተትን በጨዋ ደንብ ማረም እንዲቻል እንጅ ይሄ የሚታለፍ ነበር። ሰውንም በሆነ ባልሆነው ማሳሳት ጥሩ አይደለም። የምርጫ ወቅት ስለሆነ ቀለል ቀለል ባለው ብንማርበት ነው የሚሻለው!
Filed in: Amharic