>
5:21 pm - Thursday July 20, 9820

ኢትዮጵያንም የሚወድ ዜጎቿን በእኩል አይን የሚያይ  ሥርዓተ መንግስት መገንባት ይቻላል! (አንድነት ለኢትዮጵያ)

ኢትዮጵያንም የሚወድ ዜጎቿን በእኩል አይን የሚያይ  ሥርዓተ መንግስት መገንባት ይቻላል!

አንድነት ለኢትዮጵያ

የቡድን ወይስ የግለሰብ መብት? ቅድሚያ ለብሔር ወይስ ለአገረ መንግሥት? ዜግነት ወይስ ብሔርተኝነት? የሚሉት ጥያቄዎች ላለፉት አምስት ዐሠርት ዓመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ተዋስዖ ተቆጣጥረውት ቆይተዋል፡፡ አሁንም በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ እንደተወጠርን እንገኛለን፡፡
ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊት አገር ብትሆንም፣ ይህንን ኅብረ ብሔራዊነቷን የሚያስተናገድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አልቻለችም፡፡ በአገራችን የያንዳንዱን ዜጋ መብት ያከበረ ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት እስካልተገነባ ድረስ ዘላቂ ሰላም፣ ዕድገትና ብልጽግና ብሎ ነገር የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ግጭቱና የሕዝብ መፈናቀሉ ሥር እየሰደደ ይቀጥላል፡፡ ሄዶ ሄዶም የዘር ፍጀት የሚከሰትበት አጋጣሚምም ዝግ አይደለም፡፡ ይህ እንዳይሆን፣ ሳይረፍድ ከአሁኑ መላ ልንፈልግ ይገባናል፡፡ ሁላችንም፡፡
የኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት መሠረቱ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ያለ ዴሞክራሲ ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓትን ማሰብ አይቻልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች፤ በተለይም የኢሕአዴግ አመራሮች እና የእነሱን አመለካከት የሚቀበሉ ኀይሎች የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ ወዲህ ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት ወይም በተለመደው አማርኛ “ዴሞክራሲያዊ አንድነት” ተገንብቷል ይላሉ፡፡ ይህ አስተያየት ግን ፈጽሞ ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት ያለ ዴሞክራሲ አይታሰብም፡፡ ኢትዮጵያም ደግሞ ዴሞክራሲያዊት አገር አይደለችም፡፡ ስለሆነም በአገራችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ብሎ ነገር የለም፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያለው ፌደራላዊ ሥርዓት ብዙ ጠቃሚ ጎኖች ቢኖሩትም ያሉበት እንከኖችም በጣም በርካታ መሆናቸውን መካድ አይቻልም፡፡ እንዲያውም ያለንበት ሁኔታ የሥርዓቱን እንከኖች በግልጽ እያሳየን ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንደኛውና መሠረታዊው ችግሩ፣ በብሔረሰቦች መሀከል ያለው መስተጋብር በጎና ሰላማዊ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ፣ እያንዳንዱ ብሔረሰብ የራሴ የሚለውን ክልል ወይም ዞን ወይም ልዩ ወረዳ “የእኔ ብቻ ነው፤ ማንም ሊደርስብኝ አይችልም፤ አይገባምም፤” ብሎ “ሌሎችን” ማኅብረሰቦች ከአካባቢው ሲያባርር፣ የሥራ ዕድል ሲከለክልና ሲገድል ነው የሚታየው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ማንኛውም ዜጋ፣ በራሱ ቋንቋ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተዘዋውሮ የመሥራትና የመኖር መብቱን የሚያስከብርበት፣ ይህ መብቱ ሳያከበር የቀረ እንደሆነ ወደ ፍርድ ቤት አቤት ብሎ መብቱን የሚያስከብርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስላልተመሠረተ ነው፡፡
የዜግነት መብትን አፍኖና ረግጦ ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት መመሥረት አይቻልም፡፡ የቡድንም የግለሰብም (ዜጋ) መብት ሊከበር የሚችለው በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኀይል በአገራችን ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት መመሥረት ግዴታ ነው ይላል፡፡ ግን ምን ያህሉ የፖለቲካ ቡድን ነው ራሱን ለዴሞክራሲ ያዘጋጀው? ምን ያህሉ የፖለቲካ ልኂቅ ነው ከነባሩ የአግላይነት ባህል የተላቀቀው? ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብስ ለዴሞክራሲ ብቁና ዝግጁ ነውን?
ብዙ የምዕራባዊያን ምሁራንና የእነሱን ምክር የሚቀበሉ ለዴሞክራሲያዊ ያልተዘጋጁ የፖለቲካ ኀይሎች ሊያስረዱን እንደሚሞክሩት ዴሞክራሲ የግድ ረዥም ጊዜ መፍጀት የለበትም፡፡ በፈጣን ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር እንደሚቻል እነ እስራኤል፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ደቡብ አፍሪካ ወዘተ… አሳይተውናል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ውስጥ ማለፍ የግድ አይደለም፡፡ ሆኖም የልኂቃኑ ቁርጠኝነት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ቢያንስ ብዙሃኑ (working majority) የፖለቲካ ልኂቅ ከዴሞክራሲያዊ መንገድ ውጪ ምርጫ የለም ብሎ እንዲያምንና ለዚህም ቁርጠኛ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ብሔረሰቤን ቀስቅሼ ወይም አመጽን ተጠቅሜ ሥልጣን መያዝ እችላለሁ፤ ይገባኛል የሚሉ አካላት ከበዙ ዴሞክራሲ የሚታሰብ አይደለም፡፡
በአገራችን ዋናው የዴሞክራሲ እንቅፋት ራሱን የየብሔረሰቡ መሪ አድርጎ የሚሾመው የፖለቲካ ልኂቁ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚገባ የሚቀበል ነው፡፡ የሚጠቅመው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሆነ ያውቃልና፡፡ ጥቂቶች የብዙሃኑን እጣ-ፈንታ የሚወስኑበት ሁኔታ እንዲቆምና በአገራችን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በነጻነትና በሰላም ሠርቶ የሚኖርበትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት መንቀሳቀስ ይገባናል፡፡ ለዚህ ሁሉ የፖለቲካ ልኂቃኑ ቁርጠኝነት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
የቋንቋ አጀንዳ በአገራችን በተለይም በፖለቲካ ልኂቃኑ አካባቢ ትልቅ የፖለቲካ አጀንዳ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ መፍትሔው “የቋንቋ ዴሞክራሲ” የሰፈነበት ሥርዓት ነው፡፡ ይኸውም ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በራሱ ቋንቋ ሊዳኝና ልዩ ልዩ አገልግሎት ሊያገኝ የሚችልበትን ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡
በሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ስዊትዘርላንድ፣ ፊንላንድ፣ ካናዳና በሌሎች በርካታ አገሮች የሚሠራበት አካሄድ ይህ ነው፡፡ ወላይታው ኦሮሚያ ወይም አማራ ክልል ላይ በፈለገው ቋንቋ፣ ቢፈልግ በወላይትኛ፣ ቢፈልግ በኦሮምኛ፣ ቢፈልግ በአማርኛ ሊዳኝና አገልግሎት ሊያገኝ ይገባል፡፡ ኦሮሞው አማራ ወይም ትግራይ ክልል ሄዶ ቢፈልግ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ ወይም በአማርኛ አገልግሎት ማግኘት የሚችልበትን ሥርዓት መገንባት ይገባል፡፡ ሌላውም እንዲሁ፡፡ ይህ ክልል የዚህ ብሔረሰብ ብቻ ክልል ነው፤ ስለሆነም የዚህን ብሔረሰብ ቋንቋ ካልተናገርህ አገልግሎት አታገኝም የሚል አሠራር ፍፁም ኢዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ በሕዝብ መሀከል መልካም ግንኙነት እንዳይኖርና ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓቱ እንዳይጎለብት የሚያደርግ ትልቅ መሰናክል ስለሆነ መወገድ አለበት፡፡
ሁሉንም ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ ማድረግ ከኢኮኖሚ አቅም አኳያ አስቸጋሪ ነው የሚል ክርክር ሊቀርብ ይችላል፤ ይቀርባልም፡፡ ክርክሩ በደቡብ አፍሪካም በሌሎች አገሮችም የነበረ ነው፡፡ የአገር ህልውና እና የሕዝብ ኅብረትና አንድነት ከምንም ነገር በላይ ይቀድማል፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና በትንሹም በትልቁም ችግር የሚናጋ ከሆነና የሕዝቦቿ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የሚሄድ ከሆነ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን የአገር ህልውናና የሕዝብ አንድነት ሊጠናከር ለሚችልበት ተግባር ገንዘብ ማውጣት በጣም ቀላል መስዋዕትነት ነው፡፡ በሌሎች ኅብረ ብሔራዊ አገሮች የተቻለና የሠራ ተሞክሮ ነው፡፡
የትኛውንም ቋንቋ የሚናገር ማንኛውም ዜጋ፣ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ በፈለገው የኢትዮጵያ ቋንቋ አገልግሎት ሊያገኝ የሚችልበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲገነባ ነው ሐቀኛ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ሊፈጠር የሚችለው፡፡ ይህ ደግሞ ይቻላል፡፡ በሌሎች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝሃ ማንነት እና የተካረረ የፖለቲካ አመለካከት ባለባቸው አገሮች ተችሏልና!
ከ ሲራራ-Sirara
Filed in: Amharic