>
5:13 pm - Friday April 20, 3934

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ከውስጥ ሆኖ ሴራውን በልዩ ሁኔታ እያሴረ ነው!  (ሰውዓለም ጌታቸው)

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ከውስጥ ሆኖ ሴራውን በልዩ ሁኔታ እያሴረ ነው!

 ሰውዓለም ጌታቸው

*….እነዚህ ሰዎች ለዝንጉዎችና ለተስፈኞች ዐቢይ አህመድ ከንፈር ላይ ያለችው ኢትዮጵያና ቤተ ክርስቲያንን በሚዲያ በማራገብ በተግባር ግን ኦሮሙማ ልቦና ውስጥ ያለቸውን ሀገር የማዋለዱ ሥራ ላይ የተጠመዱ ናቸው…!!!
 
ስለዚህ ጉዳይ ባልጽፍ እፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደማየው ጉዳዩን ብዙዎች ልብ እያሉት አይደለም፡፡ በርካታ መምህራንና “ስለቤተ ክርስቲያን እንቆረቆራለን” የሚሉ ሰዎች በዩቱብና በፌስቡክ በየቀኑ ይወያያሉ፡፡ ምድረ ማንቂያ ደወልም ሲፎክር ይውላል፡፡ የባለ ዩቱበሮቹም የማንቂያ ደወሎቹም የውይይታቸው መነሻና ጭብጥ የብልጽግና (ኦሮሙማ) መንግሥት የሚለቃቸውን ማደናገሪያዎች በመያዝ ጊዜአዊ ነገሮችን ማጨህ ብቻ እንጂ ዘላቂ መፍትሔን ሊያመጣ የሚችል ስልትን የተከተሉ አይመስሉም (ሁሉንም ላለማለት በጣም ጥቂት የሚጥሩ እንዳሉ ሆኖ)፡፡ ከማደናገሪያው ደግሞ ላለፉት ሦስት ዓመታት የተማርነው ነገር ቢኖር፣ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ የማይገልጽ መሆኑን ነው፡፡
የኦሮሚያ ቤተ ክህነት የሚባለው በኦሮሙማው አቀንቃኝ ቡድን ተደራጅቶ ቤተ ክርስቲያንን ያዳክም ዘንድ የተቋቋመው አካል ከፍተኛ እንቅፋት ሲገጥመው በመንግሥት በኩል በተደረገ ማደናገሪያ “ከቤተ ክህነቱ ጋር ሆነው ችግራቸውን እንዲፈቱ” ጫና ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ያ ውሳኔ ከምር እንዳልነበርና የተለመደው የዚያ ቡድን ማደናገሪያ መሆኑን መሬት ላይ ያለው እውነታ ያሳያል፡፡ የራሴን  instinct፣ የሰሞኑን የተመስገን ደሳለኝን “አባ ብላ ሁለት፣ እንዲሁም ትናንት አቡነ ሄኖክና አቡና ናትናኤል በኦሮሚያ አህጉረ ስብከት በዚህ አደገኛ ቡድን እየተደረገ ያለውን መጠነ ሰፊ ቤተ ክርስቲያንን የመገንጠል ሥራ የሚያሳይ ደብዳቤ መሠረት በማድረግ የኦሮሙማው ቡድን በቤተ መንግሥትም በቤተ ክህነትም በከፍተኛ ደረጃ ግቡን እያሳካ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ ዶቶቹን መገጣጠምና እየሆነ ያለውን ነገር ማየት ለዚህ ድምዳሜ ያደርሳል፡፡ ከቅንነት ማጣት፣ ከአቅም ማነስ፣ ከፈተና ብዛት እየሆኑ ሳይሆን ሆነ ተብለው በብዙ ማታለያዎች ታጅቦ እየተደረገ ያለ ከፍተኛ የሆነ ወረራ ነው፡፡
ሴኩላር የሆነውን ወረራ ትተን ቤተ ክርስቲያንን effectivelly disable ማድረጉ ላይ እየተሳካላቸው መሆኑን የሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ባለ 11 ነጥብ ለቅዱስ ጳትርያርኩ የቀረበ አቤቱታ ፍንትው አድርጎ ያሳያናል፡፡
የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ቡድን ዝም ያለው ጥያቄውና ፍላጎቱ ስለተሳካ ሳይሆን የጀመሪያ ዙር ታርጌታቸውን (theoretical framework መጣሉን) አሳክተው፣ ወደሁለተኘኛውና በተግባር (application of the model) ወደመግለጽ ስለተሸጋገሩ ነው፡፡ ከውጭ ሆኖ የመታገል ጊዜው ስላለቀ፣ ወደውስጥ ገብቶ ቤተ ክርስቲየያኗን መቀየር የሚል ስልት እየተከተሉ ይመስላል (ይህ ስልት ምናልባትም ተሐድሶ የህንድ ቤተ ክርርቲያንን ለሁለት ለመክፈል የተከተለውን ስልት ይመስላል)፡፡
በኦሮሚያ ባሉ አህጉረ ስብከት በአስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ የራሳቸውን ሰዎች እየሰገሰጉ፣ ቀድሞ የነበረውንና ሲቃወማቸው የነበረውን ደግሞ እያባረሩ ነው፣ እነሱን ሲደግፉ የነበሩ ማኅበራትን ዕውቅና እየሰጡ ሲቃወሟቸው የነበሩትን ዕውቅናቸውን እየነፈጉ ነው፣ ቅጥሮችን፣ ዝውውሮችን ወዘተ በእነሱ በኩል እንዲሆኑ እያደረጉ ነው፣ የእነሱን መምህራንና ደጋፊዎቻችውን ብቻ በየጉባኤያቱ እየላኩ ቀድሞው ሲቃዎሟቸው የነበሩትን እያባረሩ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ (ቀሲስ በላይ) ጀምሮ ያለውን መዋቅር ተቆጣጥረዋል፡፡ ይህንን ድርጊት የሚቃወሙትን ደግሞ በኦሮሚያ ያለው የጸጥታ ችግር ሰለባ ያደርጓቸዋል፣ በዚህም አፍ ያስለጉማሉ፣ ወይም በለውጥ ተቃዋሚና በጁንታነት ይከሷቸዋል ማለት ነው፡፡
ይህ ከፍተኛ የሆነ ማደናገርና የራስን ግብ በባሌም በቦሌም የማስፈጸም ስልት ሀገርን ቤተ ክርስቲያንንም ወደ እልቂት የሚወስድ ከሆነ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ለወደፊት ስለሚሆነው ሳይሆን ዛሬ ስለሚሆነውና ስለምትመሠረተው አዲስ ሀገር ብቻ የሚጨነቅ ነው የሚመስለው፡፡
ሊቃነ ጳጳሳቱ አቤቱታቸውን ለቅዱስ ፓትርያርኩ ነው የጻፉት፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ፓትርያርኩ ደግሞ ከምንግዜውም በላይ በከባድ ጫና ውስጥ እንዳሉ ነው የምረዳው፡፡ ለእኔ ጫናው ቢያንስ ከአራት አቅጣጫ እየመጣባቸው ነው ባይ ነኝ፡-
1ኛ) ቀድመው ዙሪያቸውን ከቦ ቤተ ክርስቲያንን ሲየያተራምስ የነበረው የእነ ሰረቀ ቡድን አሁን ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ በግልጽ ቤተ ክርስቲያንን እዘየለፈና እሰደበ እሳቸውንም የብልጽግና አገልጋይ አድርጎ እያቀረበ በመሆኑ “ወገኔ” ይሉት ከነበረቅ አካል መከዳት ገጥሟቸዋል፡፡
2ኛ) እነ አባ ሰረቀ በፓትርያርኩ ዙሪያ በተሰባሰቡበት ጊዜ ሲያሳድዱት የነበረው ማኅበረ ካህናትና የቤተ ክህነቱ መደበኛ አገልጋይ ደግሞ “ጊዜ ጥሏቸዋል” ብሎ (በቀልም በሚመስል ሁኔታ) ንግግራቸውንም ሆነ ውሳኔአቸውን እንደቀድሞው እየያከበረው፣ ያሉበትንም ጫና እየተረዳቸው ስላልሆነ ከፍተኛ ጫና ይኖርባቸዋል፡፡
3ኛ)  የኦሮሙማው ቡድን በከፍተኛ ፍጥነት የቤተ ክህነቱን መዋቅር እየተቆጣጠረው ስለሆነ እሳቸውን አቅም አልባ የቡራኬ ሰው ብቻ ሆነው እንዲቀሩ እያደረገ ነው፣ ይህም በከፍተኛ ጫናና አፍ ማዘጋት የሚደረግ በመሆኑ ለፓትርያርኩ ጫናው ከፍተኛ ነው፡፡
4ኛ) ዓላማውን በሚገባ እያስፈጸመ ያለው መንግሥት ደግሞ እሳቸውንም ሆነ ቤተ ክህነቱን በቀድሞ ጀንታ አገልጋይነት እየከሰሰና እያሸማቀቀ፣ በተጨባጭ ያሉ ችግሮችን ግን ጆሮ ዳባ ልበስ እያለ ስለሆነ፣ ተጽዕኗቸው ከጊዜ ወደጊዜ እየወረደ የብልጽግናና ጉባኤያት መባረክ ላይ ብቻ እንዲታዩ እየተደረገ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአጭሩ ፓትርያርኩ አቡነ መርቆርዮስ ከመሰደዳቸው በፊት ሀገር ውስጥ ያሳለፉትን የአንድ ዐመት የመከራ ሕይወት ይመስላል፡፡ “አባ ብላ ሁለት” እንደነገረንም መንግሥት ይባስ ብሎ ነጻነታቸውን ገፎ በከፍተኛ ወታደር እያስጠበቃቸውም ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ለዝንጉዎችና ለተስፈኞች ዐቢይ አህመድ ከንፈር ላይ ያለችው ኢትዮጵያና ቤተ ክርስቲያንን በሚዲያ በማራገብ በተግባር ግን ኦሮሙማ ውስጥ ያለቸውን ሀገር ማዋለድ ሥራ ላይ በርትተው እየሠሩ ናቸውማለት ይቻላል፡፡
ምንድን መደረግ ያለበት?
******************
1ኛ) በውጭ ያለውም በውስጥ ያለውም “የብልጽግና ተቋሚ ነኝ” የሚለው የኦሮሙማ ክንፍ ለስተራቴጂ እንጂ ከምር የተከፋፈለ አለመሆኑን መረዳትና ሀገርም ቤተ ክርስቲያንንም የመታደጉ ጉዳይ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ግንዛቤ ከመፍጠርና ሴራዎችን ከማጋለጥ ይጀምራል፡፡ በተጨባጭ እንደምናየው ቅዱስ ፓትርያርኩም ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ጫና ውስጥ ናቸውና በምክርም፣ በተግባርም ከጎናቸው ሆኖ ይህን ቤተ ክርስቲያንን የመገንጠል ሴራ ማክሸፍ ያስፈልጋል፡፡
2ኛ) ምንም እንኳን በሀገረ ስብከታቸው ከእነሱ በላይ ባለሥልጣን የሌለ ቢሆንም የሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ደብዳቤ የሚያሳየው የኦሮሚያው ቤተ ክህነት ቡድን እንቅስቃሴ በመንግሥት አካላት የታጀበና የሊቃነ ጳጳሳቱንም ደኅንንት ጭምር እየተፈታተነ መሆኑን ስለሚያሳይ ከአባቶች ጎን ቆሞ መታገል ያስፈልጋል፡፡ ሀገርንም ሃይማኖትንም ተቀምቶ መኖር የሚፈልግ ካልሆነ በቀር አሁን የሚታየውን ነገር መታገስ ያለበት አይመስለኝም፡፡
3ኛ) በመጨረሻም ምንም እንኳን ብዙም ተስፋ ባይደረግበትም፣ የዚህን ቡድን ሕገ ወጥ ተግባር በሕጋዊ መንገድ መጋፈጥም ከተቻለ ማስረጃዎችን በጥንቃቄ መቀመር ያስፈልጋል፡፡
ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለው ግን እየሆነ ያለውን ነገር በጥንቃቄ ከመመርመር ይጀምራል፡፡ ይህን የምለው ከምሬ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ስትሆን፣ ሀገር ሰላም ስትሆን ነው ስለሌሎቹ ነገሮች መነጋገር የሚቻለው፡፡ አሁን ግን ሁለቱም ከፍተኛ የሆነ እክል እየገጠማቸው ነው፡፡ ሀገር ከውጭም ከውስጥም ከፍተኛ የሆነ ጫና ውስጥ ባለችበት፣ የዜጎች ሞት statistics በሆነበት ሁኔታ የዚህን ያህል በእልህ ሀገር ለማፍረስ የሚጣደፍ ቡድን ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡
Filed in: Amharic