>

ሱዳን በወረራ ከያዘችው ግዛቶች እንድትወጣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች‼ (ህብር ራድዮ)

ሱዳን በወረራ ከያዘችው ግዛቶች እንድትወጣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች‼

ህብር ራድዮ

ጥሪው የቀረበው በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ሲሆን ሱዳን በኃይል ከያዘቻቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ወታደሮቿን እንድታስወጣና ወደ ቀልቧም እንድትመለስ ተጠይቋል።
ሱዳን በትግራይ ግጭት በተነሳበት ወቅት በአካባቢው የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም ግዛቶቹን መቆጣጠሯን አስታውሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገፁ እንዳሰፈረው ሱዳን በአሁኑ ወቅት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ሊቀ መንበር ብትሆንም በአፍሪካ ቀንድ ላለው አለመረጋጋት ዋነኛ ተጠያቂ አድርጓታል።
“በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ውስጥ በመክተት ዋነኛ ተዋናይ ናት። የኢትዮጵያን ግዛቶች ወራለች፣ ሰላማዊ ዜጎችን አፈናቅላለች፣ ዘረፋ የተፈጸመ ሲሆን ሌሎች በርካታ ግዛቶችን ለመያዝ የጦር አታሞ እየጎሰመች ነው” ሲል ጠንከር ባለ ቃል ሚኒስቴሩ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ሁለቱ አገራት የሚወዛገቡባበቸውን የድንበር ግዛቶች በሰላም ለመቋጨት ኢትዮጵያ አሁንም ዝግጁ እንደሆነች አስታውቋል።
አገራቱ በ1972 ውል መሰረት የሕዝቦችን መፈናቀል ከሚያግደው እንዲሁም ዘለቄታዊ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስ የድንበር ጥያቄዎች ወደ ኃይል እንዳያመሩ የሚከለክለው መግባባት መሰረት መመለስ እንደሚገባ ኢትዮጵያ ጥያቄዋን አቅርባለች።
በዚህም መሰረት ሱዳን የያዘችውን ቦታ በመልቀቅ የቀደመ ይዞታዋ እንድትመለስና ግጭታቸውን በሰላም እንዲፈታ ኢትዮጵያ አቋሟን አሳውቃለች።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተጨማሪም ትናንት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ባለስልጣን ሌተናል ጄኔራል ባጫ ጨበሌ ከሱዳን ጋር ጦርነት እንደማያስፈልግና ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እንደሚፈለግ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ሠራዊታቸው ዝግጁ መሆኑንን አስታውቀዋል።
ሱዳን እና ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ለም በሆነው ለእርሻ ተስማሚው አልፋሽቃ የድንበር አካባቢ ይገባኛል በሚል ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ ከገቡ ወራት ተቆጥረዋል።
ሁለቱ አገራት ተፋጥጠው በሚገኙበት በዚህ የድንበር ይገባኛል ምክንያት ወደ ጦርነት መግባት እንደማይፈልጉ ቢገልፁም የሁለቱ አገራት ሠራዊት ግን በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይሰማል።
ሱዳን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1902 የተፈረመው የአንግሎ-ኢትዮጵያ የካርታ ላይ ምልከታ ስምምነት አልፋሽቃ የእኔ መሆኑን በእርግጠኝነት ያሳያል ስትል ትገልጻለች።
አክላም በርካታ ኪሎ ሜትሮች የሚረዝመው የሁለቱ አገራት የድንበር አካባቢ በአግባቡ ባለመካለሉ ከ1980ዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ድንበሩን ዘልቀው ይገባሉ ስትል ትከስሳለች።
ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳያቸውን ለመፍታት ከተደረጉት ሁሉ የተሻለው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተደረገው ውል ወይም ስምምነት እንደሆነ ይነገራል።
በዚህ ስምምነትም መሰረት አገራቱ በይዞታቸው ስር ያላቸውን ግዛቶች ይዘው እንዲቆዩና የአገራቱ መንግሥታት ድንበራቸውን በተመለከተ ጥናት ተደርጎ የድንበር ጉዳይ በሰላም እንዲካለል ለማድረግ ተስማምተዋል።
Filed in: Amharic