>

በለቅሶው ድንኳን ውስጥ የተደገሰው ሰርግ.. !!!  (ብርሀኑ ተክለያሬድ)

በለቅሶው ድንኳን ውስጥ የተደገሰው ሰርግ.. !!! 

ብርሀኑ ተክለያሬድ

 

*… “የመስቀሉ በግ በእንቁጣጣሹ በግ ይስቃል” 
*…ላለፉት ጥቂት ቀናት በግልፅ የጦርነት አዋጅና ስንቅና ትጥቅ በመከላከያው በሚቀርብላቸው ፈርጣማ ሽፍቶች ትብብር የሸዋ አማራ ቀባሪ እስኪያጣ ተገድሏል፤ የአባቶቹ ከተሞች ወድመዋል፤ በከባድ መሳሪያ ታጣቂዎች  እየተሳደደ ቀዬውን ለቆ እየተንከራተተ ነው።ብበአጠቃላይ ሃገር የሐዘን ድንኳን ጥላ ማዘን ነበረባት። 
 
ገበሬው ጥይት እየዘነበበትና እየረገፈ….. 
ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ጄነራል ብርሀኑ ጁላ፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የተገኙበት ሞቅ ያለ ሰርግና ምላሽ ነበር። የሞቅታው ምክንያት “obn ቴሌቪዥን በጉራግኛ ቋንቋ  ስርጭት መጀመሩን በማስመልከት” ነው። የጉራጌ ህዝብ ነፍጠኛ የሚል ታፔላ በተሰጠበት ቦታ ሁሉ ከአማራ ጋር ነፍጠኛ እየተባለ ሲገደልና የንግድ ቦታው ሲዘረፍ እንዳልነበረ ሁሉ፣ አኩሪ የሽምግልና ባህሉ ተጥሶ “ከ150ዓመት በፊት የምትተዳደርበት የገዳ ስርአት ነው አሁን መመለስ አለበት” እንዳላሉት ሁሉ፣ በተረኞቹ የራሱን ሚዲያ እንዳይከፍትና ያሉትንም ሚዲያዎች እንዳያጠናክር ሴራና መከፋፈል እንዳልተሰራበት ሁሉ ዛሬ በ obn ባንተ ቋንቋ ማሰራጨት ልንጀምር ነው የሚል ሽንገላ አይናቸውን በጨው አጥበው ይዘውለት መጡ።
አማራው በከባድ መሳሪያ እየተለበለበና እየረገፈ....
አቶ ሽመልስ በባህል ልብሳቸው ሽክ ብለው ስለኢትዮጵያዊነት ሰበኩ “ዩቲዩበሮች ጩኸታችሁን ቀጥሉ እኛ በድል ላይ ድልን እንቀዳጃለን” አሉ።እነ ንዋይ ደበበም ሁሉም ቢተባበር.. ብለው አቀነቀኑ። ይህ ሁሉ የሆነው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በየእለቱ ያለኃጢአታቸው እየረገፉባት ባለችው በኛዋ ኢትዮጵያ ነው።
ይህ ሁሉ እየሆነ
ዛሬ በobn በቋንቋችን ስርጭት ተጀመረ ብሎ ጮቤ የሚረግጥም አልጠፋም። ነገሩ “የመስቀሉ በግ በእንቁጣጣሹ በግ ይስቃል” መሆኑ ነው የተራ ጉዳይ እንጂ ሰልቃጭነት ማንንም አይምርም።
ያም ሆኖ……….
ጨልሞ አይቀርም በአስከሬን ላይ ሸጎዬ የጨፈረውም ያጫፈረውም ሙዚቃው ያልቅባቸዋል። እየሞተ የሚያለቅሰውም እምባውን አብሶ ቀና ይላል ጨልሞ አይቀርም!!!
Filed in: Amharic