>

ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በሀገሪቱ ወቅታዊ  የጸጥታ ሁኔታ የተሰጠ መግለጫ ሙሉ ቃል !!!

ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በሀገሪቱ ወቅታዊ  የጸጥታ ሁኔታ የተሰጠ መግለጫ ሙሉ ቃል !!!
በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት በንጹሃን ዜጎች ላይ የህይወት እና ንብረት አደጋ ባደረሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ መወሰድ ተጀምሯል ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊታችን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ትግራይ ክልል ውጤታማ ህግ የማስከበር ተልእኮውን በጀግንነት በመፈጸም ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ፣ በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች የጸጥታ ችግሮች እየተስተዋሉ ይገኛሉ ፡፡
እነዚህ  ሆን ተብሎ የሰራዊታችንን ህገ መንግስታዊ ተልእኮ ለማስተጓጎል ታስበው  የተሰሩ የጥፋት ሴራዎች ፣ በሰላም ወዳዱ ህዝባችን እና በመከላከያ ሰራዊታችን የተቀናጀ ስራ ሊከሽፉ ችለዋል ።
አንደኛ በመተማ መስመር ለዘመናት አብረው በኖሩ የቅማንት እና የአማራ ተወላጆች መካከል የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን የፈዴራል እና የክልል የጸጥታ ሃይሎች ከህብረተሰቡ እና ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተቀናጀ ስራ በመስራት የተከሰቱ  የጸጥታ ችግሮን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል ፡፡
ሁለተኛ በወለጋ ቡሬ መስመር ፣ በጊዳ አያና ፣ አንገር ጉቴ አዋሳኝ አከባቢዎች ለረዥም ጊዜ አብሮ በኖሩ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎችን ሆን ብሎ ለማጋጨት ታስቦ የተደረገው ሙከራ በአከባቢው ህብረተሰብ ትብብር  ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ተችሏል ።
ሦስተኛ የሀገራችንን የገቢ እና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴን ለመገደብ በማሰብ ፣ በሱማሌ እና የአፋር ኢሳ ህዝቦችን ለማጋጨት የተሴረው ሴራ በሰላም ወዳዱ ህዝባችን የተቀናጀ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር ለመዋል ችሏል፡፡
አራተኛ ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች በተለይም  በዚህ ሁለት ሶስት ቀን በአጣዬ ከተማ እና በአከባቢው በታጠቁ ሃይሎች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ውድመት ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ፣ በዚህ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች መጽናናትን ይመኛል፡፡
በዚህ የጸጥታ ችግር ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና መሳርያ ይዘው በጸጥታ አካላት ላይ ተኩስ የከፈቱ ፣ የሰራዊቱን እንቅስቃሴ የገደቡ ጸረ ሰላም ሃይሎች ላይ ሰራዊታችን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን እየገለጽን ፣ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የህብረሰተሰቡን ሰላም በማወክ ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል፡፡
በዚህም መሰረት  ፣ በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከክልል እና ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተ  ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል ።
ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን  ጸጥታ በማደፍረስ ስራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራን ይሰራል ።
በዚህም መሰረት የአከባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሲባል የሚከተሉት ክልከላዎች የተደረጉ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ይገልጻል ።
1ኛ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ ፣  ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪሎ ሜትር  ውስጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው ።
2ኛ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የእምነት ተቋማትን እና የመንግስት ተቋማትን ፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤትን እና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጠልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው ።
ከላይ የተዘረዘሩትን እና ቀጣይ በኮማንድ ፖስቱ ለህብረተሰቡ የሚገለጹ ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ የፖለቲካ ድርጅት ፣ የመንግስት መዋቅር እና በድኖች ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑ  መታወቅ አለበት
፡፡
በመጨረሻም መላው ህብረተሰባችን እንደ ወትሮው ሁሉ ከጸጥታ ተቋማት ጎን በመሰለፍ  ለገሀራችን ሰላም እና ደህንነት የበኩሉን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ።
Filed in: Amharic