>

የተያዘው የጸሎት ፕሮግራም እመኑኝ አይሠራም! (ፍርዱ ዘገዬ)

የተያዘው የጸሎት ፕሮግራም እመኑኝ አይሠራም!

ፍርዱ ዘገዬ


ቤተሰቤ አዲሱን የቴሌቪዥን የጸሎት መርሐ ግብር እየተከታተለ አብሮም በጸሎቱና ምህላው እየተሳተፈ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የራሴን የግል የዘወትር ጸሎት አድርሼ አልጋየ ላይ ጋደም በማለት በኢንተርኔት የሀገሬን ወቅታዊ ጉዳይ እየተከታተልኩ እንዳስፈላጊነቱም በምችለው እየተሳተፍኩ ነው – ዛሬ ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 9 ቀን 2013ዓ.ም ሌሊት፡፡

ጸሎቱ ለምን እንደማይሠራ የሚሰማኝን ለመናገር እንዴት ከአልጋየ እንደተስፈነጠርኩ እኔና አንድዬ ነን እምናውቀው፡፡ አሁን ባለቀ ሰዓት ይሉኝታ የለም፡፡ ነገ ልሞት ዛሬ የምደብቀው ነገር አይኖረኝም፡፡ የልቤን እናገራለሁ፡፡

ጓደኛሞች የሆኑ ሙስሊሞች አብረው ሶላት እያደረሱ ነው አሉ፡፡ ሶላትን እያደረሰ ያለ ሙስሊምና በወታደራዊ ሰልፍ ላይ የሚገኝ መለዮ ለባሽን የሚያመሳስላቸው አንዱ ነገር ለዓላማ ቀጥ ብሎ መቆም ነውና ጸሎተኛው ሌላ ሃሳብ ወደ አእምሮው ዝር አይልም፤ ወታደሩም እባብ ቢጠመጠምበት እንኳ ከወታደራዊ ሥነ ሥርዓቱ ዝንፍ አይልም – ይባላል፡፡ እናላችሁ እነዚያ ሙስሊም ጓደኛሞች እየሰገዱ ሳለ አንዱ ቁጭ ብሎ የነበረ ተንኮለኛ ጓደኛቸው በርከት ያሉ ዝርዝር ሣንቲሞችን ከበስተኋላቸው በመበተን ያቅጨለጭልባቸዋል፡፡ ያኔ ሁሉም በደመ ነፍስ ወደኋላቸው ይዞራሉ – የሣንቲም ነገር በተለይ በዚህ ዘመን የደም ዝውውር ያህል ሆኗላ፡፡ ተንኮለኛው ጓደኛ “ይህን ዱኣችሁን እንኳን አላህ እኔም አልቀበለውም፡፡” አላቸውና ጸሎታቸውን አጣጣለባቸው አሉ፤ ትክክል ነው – ከጸለይክ ከልብ መሆን አለበት፡፡

ሃይማኖታዊ ሚዛናዊነትን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ አጼ ምኒሊክ አንድ ወቅት ለአንዱ መነኩሴ “አንቱ መነኩሴ፣ አቡነ ዘበሰማያትን ያላንዳች ሃሳብ ጣልቃገብነት ቀጥ ብለው ከወጡ የጭን በቅሎየን እሸልመዎታለሁ” ይሏቸዋል አሉ፡፡ መነኩሴውም በነገሩ በመስማማት የንጉሠ ነገሥት በቅሎ ሊሸለሙ በደስታ ይዋጡና ጸሎታቸውን በለኆሳስ ይጀምራሉ፡፡ እንደጨረሱም ንጉሡ “በቅሎዋን መስጠቱን እሰጥዎታለሁ፤ ግን በኅያው እግዚአብሔር ይሁንብዎና ምንም ዓይነት ሃሳብ አላናጠበዎትም?” በማለት የከረረ የነፍስ ጥያቄ ይጠይቋቸዋል፡፡ መነኩሴውም ለኅሊናቸው ያደሩ ነበሩና “አይ፣ እውነት ነው፣ መቼም …‹እንዲያው ግን ጸሎቴን ሃሳብ ሳያናጥበኝ ብጨርስ በቅሎዋን ከምር ይሰጡኝ ይሆን› ብዬ አስቤያለሁ” በማለት መለሱላቸውና በአካባቢው የነበሩ መሣፍንት መኳንንትን ፈገግ አደረጉ ይባላል፡፡ ጸሎትን ካላንዳች መናጠብ ለመጨረስ ያድላችሁ ወገኖቼ፡፡ በዚህ ዘመንማ አናጣቢው ብዙ ነው፤ ኦነግ/ሸኔስ የት ሄዶ?

ሃጂ ሙፍቲ ጨርሰውታል፡፡ እግዚአብሔርም እንበል አላህ እንዲህ እንደዋዛ እንደሰው የሚታለል አይደለም፡፡ አዳሜ የልቡን እየሠራ ይቅር በለኝ ቢል ይመስለዋል እንጂ ይቅርታንና ምሕረትን አያገኝም፡፡ ይቅርታና ምሕረት የሚገኘው ከልባዊ ጸጸትና ንስሃ እንጂ በጧት ታጥቦ ከሰዓት ጭቃ ዓይነት የልጆች ዕቃ ዕቃ ጨዋታ አይደለም፤ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ የዓለማችን ቅርጽ ሌላ በሆነ ነበር፡፡ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነው ነገሩ፡፡ ሰውና እግዚአብሔር ሌባና ፖሊስ እየተጫወቱበት ባለ ዘመን ውስጥ የአምላክ ምሕረትና ይቅርታ እንደብርቅ የሚቆጠርና ለጥቂቶች የሚሰጥ እንጂ ማንም ወንጀለኛ እየተነሣ የሚቀልድበትና ለማንም የማይከለከል የቡና ቁርስ አይደለም፡፡

የባል ውሽማ የሚባል ነገር ታውቃላችሁ? የባል ውሽማ ማለት ትዳራቸውን የበተኑ ጥንዶች ያልተቋጨ ፍቅራቸውን ወይም ከሌላ ቦታ ማግኘት የተሳናቸውን በድብቅ እየተገናኙ የሚረክሱበት መንገድ ነው፡፡ አብረው እየኖሩ ያልሆነላቸው በሌላ ሕይወት ገበተው ሳለ በስርቆት ሲማግጡ ነው እንደዚያ የሚባል፡፡ ይህን እዚህ ለምን አመጣሁት?

በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ፣ በየጠቅላይ ግዛቱ፣ በየወረዳና ቀበሌው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያን ከዋዜማው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ሌሊቱንና ማርፈጃውን እንዲሁም እኩለ ቀኑንና ተሲያቱን ጭምር ሲዥጎደጎድ የሚያድርና የሚውል ቃለ እግዚአብሔር ከደመና በላይ ዘልቆ የጽርሐ አርያምን ደጅ መርገጥና የመንበረ ፀባዖትን በር ማንኳኳት አቅቶት ሀገር በአጋንንት ደዌ እየታመሰች ባለችበት ሁኔታ ሊያውም በስንት ጉትጎታ በተደራጀ የይምሰል የግማሽ ሰዓት የቴሌቪዥን ጸሎት የአቢይንና የሽመልስን ኦነግ ሸኔ አሸንፋለሁ ማለት ትልቅ ቀልድ ነው፡፡ ቀልዱ በሰው ላይ ቢሆን ምንም አልነበረም፡፡ ግን እየተቀለደ ያለው ልብንና ኩላሊትን በሚመረምረው ኅያው እግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ ችግራችን የጸሎት ዕጥረት እንዳልሆነ ጠጠር መጣያ እስከሚጠፋ ድረስ ከአፍ እስከገደፋቸው በምዕመናን የሚሞሉ የአምልኮ ሥፍራዎችን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በተለይ በሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትና ሰንበትን ጨምሮ በዕረፍት ቀናት ቤተ ክርስቲያናት ነጫጭ በለበሱ ልባቸው ግን በአብዛኛው በበቀልና በጥላቻ በቀሉ ምዕመናን ጢም ይላሉ፡፡ ብዙው ሰው “የእገሌን መጨረሻ አሳየኝ” ባይ ነው፡፡ ስለሀገርና ስለወገን የሚለምነው ጥቂት ስለመሆኑ ከጸሎታችን ሥምረት መረዳት አያቅትም፡፡ እውነቱን አውቀን መደረግ ስላለበት ማሰብ እንጂ ማለባበስ አይጠቅምም፡፡

አገልጋዮችንና አባቶች ተብዬዎችን ብናይ ስንክሳሩ ብዙ ነው፡፡ በመጀመሪያ ሰላሳውን ሴት እያገባህ የምትፈታ ጳጳስና ኤጲስ ቆጶስ ነኝ ባይ ራስህ ያቆምከውን ቃለ ዐዋዲ አክብርና ላጠፋኸው ንስሃ ገብተህ በንጽሕና ኑር፡፡ ከሌሎች ኃጢኣቶችም ተቆጠብ፡፡ አለባብሰን ብናርስ በአረም መመለሳችን አይቀርምና ዕዳው የኛው ነው፡፡ ሶዶማውያን፣ ሙሰኞች፣ ዘረኞች፣ ሴሰኞችና አመንዝራዎች፣ ዋሾዎች፣ ጠንቋዮች፣ አስማተኞች፣ ሰይጣን ጎታቾች፣ ወዘተ፣ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፡፡ ከአጋንንት ዓለም ውጡ፡፡ ለሁለት ጌታ መገዛት እንደማይቻል ክርስቶስ ያስተማረውን ቃለ ወንጌል አስታውሱ፡፡ ለሰው ይምሰል ልብስህንና ጥምጣምህን አሳምረህ እግዚአብሔርን የምታታልል ካህን ሁሉ ከጠፋህበት ዓለም ተመለስና በትክክል ህዝብንና ፈጣሪን አገልግል፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን ማነብነብ እንደሆነ ሰይጣንም አሳምሮ ይችልበታል፡፡ ስለዚህ ይህ ጸሎት በፈጣሪ ዘንድ ቅቡልነት የለውም፡፡ ቢሰማን እኮ አንዲት ቀንም በቂ ናት፡፡ 

በልጅነቴ የሆነውን ልንገርህ፡፡ በአካባቢያችን ድርቅ ገባ፡፡ ጭንቅ ሆነ፡፡ አባቶችና ካህናት የምህላ ፕሮግራም ያዙ፡፡ ጥጆች ከላሞች፣ ሕጻናት ከጡት ታግደው ዋሉ፡፡ ወጣት ጎልማሣውም እህል ውኃ በአፉ ሳይዞር ዋለ፡፡ ምሽቱን ሕዝቡ ከየቤቱ ወጥቶ በየደጁ እግዞዖታውን አቀለጠው፡፡ እኔም ሕጻን ሆኜ ብዙም ሳይገባኝ ከትልልቆቹ ጋር እወድቅ እነሳ ነበር፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ ወዲያውኑ ሰማይ ጠቋቆረ፤ ታይቶ የማያውቅ ዝናብም እንደጉድ ወረደ፡፡ የዚያን ጊዜው ጸሎት እንዲህ ነበር፡፡ አሁን የት አለ? እግዜርና እኛ እኮ ከተነቃቃን ቆየን – ተቃቅረናል እኮ፡፡ “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል፡፡” የሚሠራውን በደልና ግፍ እንመልከት፤ በከተሞች ውስጥ የሚደረገውን አሥረሽ ምቺው ተመልከት፤ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃና የሎጥ ዘመን የድኝ ዝናብ የተቃረበ እኮ ነው እሚመስል፡፡

የደብር አለቃዎችን እዩ፤ መዘምራንን እዩ፤ ጳጳሣትን እዩ፤ የሰበካ ጉባኤ ኃላፊዎችን እዩ፤ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አባላትን እዩ፤ አብዛኞቹን ዲያቆናትና ቀሳውስትን እዩ … ሁሉንም ተመልከቱ፡፡ ክርስቶስ ነጠላ ጫማ አልነበረውም፡፡ እነዚህ ያነጠነጡና እንደ እምቧይ ሊፈርጡ የደረሱ የሃይማኖት ነጋዴዎች ግን የሚጓዙበት መኪና ራቭ4 እና ቪ8 ነው – አነሰ ከተባለም ቪትስና ያሪስ፡፡ ንስሃ አባት ብለህ ብትይዛቸው የልጆችህን አባት ለማወቅ ከመቸገርህ የተነሣ ዲ ኤን ኤህን ማስመርመር ሊኖርብህ ነው፡፡ በጠፋ ሃይማኖት መጽደቅ አለ እንዴ? አሃ! አታናግሩኛ! በዚህ ምክንያት አይደለም እንዴ ህዝቡ ከቤተ ክርስቲያን እየወጣ ለባሱ እዩ ጩፋዎችና እስራኤል ዳንሣዎች የሚጋለጠው? የዚያኛው ጎራማ ከማሳቅም አልፎ እጅጉን ያሳቅቃል፡፡  እንዲያውም እኮ ፈጣሪ ታጋሽ ነው ያስብላል – በሕይወት መቆየታችን፡፡

ጸሎትና ምህላ በእምነት ቦታዎች እንጂ የሚያምረውና መለኮታዊ ተቀባይነትም የሚኖረው እንደኦፕራ ሾው በቲቪ መስኮት እየቀረበ በወፈፌዎች ሊፌዝበትና በኢአማያን ሊላገጥበት አይገባም፡፡ ስለዚህ አትልፉ፤ አንልፋ፡፡ እውነተኛ ንስሃ ገብተን በየቤታችንም በየአብያተ ክርስቲያንም በግልም ሆነ በቡድን ከልብ እንጸልይ፡፡ በተለይ ደግሞ ሽማግሌዎችና ሕጻናት፣ አእሩግና አንዳንድ የቶበታችሁ ዜጎች በግላችሁ የጠበቀ ጸሎት ያዙ፡፡ በእናንተ ሀገራችን ልትማር ትችላለች፡፡ ዘንድሮ በደቦ መሞት እንጂ በደቦ መዳን በዱሮው የየዋሃን ዘመን ቀረ ጅሌ፡፡ እንጂ በሀገራችን አማራን በየቀኑ የሚጨፈጭፍ ተንከሲስ ቤተ መንግሥቱን ተቆጣጥሮ ባለበት ሁኔታ አንድም መነኩሴ ሃይ የሚል ሲጠፋ ከዚህ በላይ ሃይማኖታዊ ክስረትና ዝቅጠት ከየት አለ? ዮሐንስ በለው ግርማ፣ ገብረ መስቀል በለው ሄኖክ … ታላቅ ይቅርታ ይደረግልኝና ከኔ ከመናኛው ኃጢኣተኛ ዜጋ ባልተናነሰ ሁሉም አጭበርባሪና በፍቅረ ንዋይ የታወረ ሌባ ነው፡፡ የምለው ውሸት በሆነና ኩነኔውን በወሰድኩ፡፡ ደግነቱ ማመዛዘን የማይችልና በነዱት የሚተም ምዕመን ስለሞላ ተከታይ ከብት አያጡም፡፡ በቃኝ እባክህን … ባልተፈጠርኩ የሚያሰኝ ዘመን፡፡  

Filed in: Amharic