>
5:21 pm - Monday July 20, 6043

" አልሸባብም አልቃይዳና የአልቃይዳ ወዳጆች እየደገፉት ከዚህ የተሻለ ትጥቅ አላሳየንም!!! " (ጌታቸው ሽፈራው)

” አልሸባብም አልቃይዳና የአልቃይዳ ወዳጆች እየደገፉት ከዚህ የተሻለ ትጥቅ አላሳየንም!!! “
ጌታቸው ሽፈራው

♦ ኢትዮጵያ ተአምር ነው ስታይ የከረመችው..!
 
ይህ አሸባሪ ኃይል ይዟቸው የሚታዩት አብዛኛዎቹ መሳርያዎች በትንሹ ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚሸጡ ናቸው። ደግሞ እንዲሁ የሚገኙ አይደለም። ሌላው ቀርቶ የመከላከያ ሰራዊቱ እንኳን ከበርካታ ክላሽ ያዥ ጋር ነው በመሃል ጣል እያደረገ በአብዛኛው የሚጠቀምባቸው።  የክልል ልዩ ኃይሎች ብዙ የላቸውም።  እስከ 20 የሚደርስ ልዩ ኃይል ክላሽ ያዥ መካከል መሰል መሳርያ የሌለው ይኖራል። የክልል ልዩ ኃይሎች ይህን የመሰለ መሳርያ ቀርቶ ክላሽ አጥተው ከተማ ውስጥ አንድ ልዩ ኃይል ክላሽ ይዞ፣ ሁለት ልዩ ኃይል ዱላ ይዘው የሚዞሩበት ጊዜ ነበር።
አንዳንድ  የክልል መንግስታት  ከፌደራል መንግስት ለመግዛት ያዘዙትን ክላሽ እንኳን ቶሎ  አያገኙም። የክልል መንግስታት መሳርያ አጥተው በኮንትሮባንድ የሚገዙበት ጊዜ ሁሉ እንዳለ ይነገራል። ያውም አያገኙምኮ። ይህኛው በየትም በየትም ተብሎ ይደርሰዋል። ገራሚ ነው መቸም። ተአምር! ይህኛው ኃይል ግን ክላሽ ምን ያደርግልኛል ብሎ መትረየስና ስናይፐር ነው የታጠቀው።
ኦነግ ኤርትራ ውስጥ ነበር፣ የኤርትራ መንግስት እያገዘው ማለት ነው።  የኤርትራ ሰራዊት አባላት ጎማ ጫማ ነው የሚያደርጉት እየተባለ ይፃፋል፣ በፎቶም ይታያል። ከኢኮኖሚ አንፃር ዘመናዊና ውድ የሆነ የሰራዊት ጫማ ማድረግ ባይፈልጉ ይመስላል። እንደ ሀገር የጎማ ጫማ ያደረገ ሰራዊት ባየንበት ታዲያ ኤርትራ እያለ፣ ጎማ ጫማ ሲያደርግ የነበረው “ኦነግ” አሁን አብዛኛው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሌለው ጫማን ተጫምቶት ዘና ፈታ ይላል። የፌደራል ፀጥታ ኃይል አልባሳትን ይቀያይራል። በፎቶው እንደሚታየው ሰራዊቱ ሁሌም የማያገኛቸውን ስንቆች ይዟል። ሲፈልግ በመኪና፣ ሲያሻው በባጃጅ፣ ይንሸራሸራል።
 አብዛኛው የዚህን ኃይል  ትጥቅ ሀገር ተቆጣጥሮ የነበረው አልሸባብም ያለው አይመስለኝም። የውጭ ሀገራት እያገዟቸው፣ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ እየተቆጣጠሩ፣ ሕገ ወጥ ንግድን በዓለም ደረጃ እየሰራበት፣ አልቃይዳና የአልቃይዳ ወዳጆች እየደገፉት ከዚህ የተሻለ ትጥቅ አላሳየንም።
ይህ ኃይል ከ20 በላይ ባንኮችን እንዲዘርፍ ተደረገ። በተለያየ መዋቅር ሕገወጥም የፀጥታ ኃይሉ ትጥቅ፣ ስንቅና አልባሳት እንዲደርሰው ተደርጎ ነው። መከላከያ ሰራዊቱ፣ የአማራና የአፋር ልዩ ኃይሎች ባልተሟላ ስንቅ፣ በከፋ ሁኔታ፣  ከጠላት ጋር እየተፋለሙ ይህ አሸባሪ ኃይል ዘና ፈታ ብሎ ይገድላል። የብዙ ክልል ልዩ ኃይሎች መሳርያ ሳይሟላላቸው፣ ክላሽ የያዙት “በአዲስ ቀይሩልን” ብለው እየጠየቁ፣ ይህ አሸባሪ ኃይል ግን ቀድሞ የቡድን መሳርያ ታጥቋል። በርካታ ክልሎች “ኦነግ ሸኔ” የሚባለው ቡድን የሚያሳየንን የቡድን ትጥቁ የላቸውም።
አንዳንዴ ደግሞ የክልል ልዩ ኃይል ሲመረቅ እንደሚደረገው በአደባባይ፣ በይፋ ዘመናዊ ድንኳኖች ተጥለው፣ በርካታ ዘመናዊ መኪኖች ተደርድረው፣ መነጋገሪያ መድረክ ተዘጋጅቶ ሰራዊቱን ያስመርቃል። ትርኢት ያሳያል። እንዲያውም አንዳንድ ክልሎች “ኦነግ ሸኔ” እንደሚያደርገው ያህል ዝግጅት የላቸውም። በአንድ ሁለት መኪና ይመጣሉ፣ ድንኳንም ምንም ሳይኖር ዛፍ ጥላ ስር አግዳሚ ወንበር ተቀምጦ ሰራዊት ተመርቋል።
Filed in: Amharic