“ቃል!”
(ለ“አሻግሬ”)
…መጀመሪያ – ቃል ነበረ፣
ቃልም ፍጹም – ስጋ ሆነ፤
ጸጋ፣ እውነትን – ተጎናጽፎ፣
በልባችን ውስጥ አደረ…፤
..ቅዱስ ቃሉ የጥቅሳችን፣
እንዲህ ሆኖ እምነታችን፣
ለሃቅ አድረን ለቃል ታምነን፣
ብንከተል “ቃለ-ዐዋዲ”ን…፤
እምነት ከእኛ መች ጎደለ፤
ውርደት ሞቱ ለራሱ ነው…፣
ሕዝብን ንቆ ካታለለ።
ቃል ክቡር! ቃል ኃያል!…
በአገሬ ምድር – በሐበሻ ባህል፤
“ቃሌ ከሚዛነፍ – ያልኩት ከሚጠፋ፣
ከአብራኬ የወጣው – የወለድኩት ይጥፋ፤”
“ቃል ለምድር ለሰማይ…” ይላል በመሃላ፣
ማተቡን ላይበጥስ – እምነቱን ላይበላ፤
“ቃል የእምነት ዕዳ ነው…” ይል ነበር ሎሬቱ፣
ሳትከፍለው ብትቀር – የሚያሰኝህ ከንቱ፤
ቃል ተግባር ካልሆነ ስጋ ካልለበሰ፣
ወናፍ ሆኖ ይቀራል – ባየር የነፈሰ፤
ተጸንሶ.. አድጎ.. – ቃል ካልሆነ ህይወት፣
ጨንግፎስ በቀረ – ሳይወጣ ካንደበት፤
…ሕዝብን አንድ-ሁለቴ- ልታሞኘው ብትችል፣
ሦስተኛው ዳገት ነው – ልትወጣው እማትችል።
የመለኮት ምስጢር – ክቡር የገዘፈ፣
“ቃል የእምነት ዕዳ ነው” – ከ”ቃል”ም ያለፈ።
ጌታቸው አበራ
ሚያዝያ 2013 ዓ/ም
(አፕሪል 2021)