ብአዴን ዛሬም እነ ታዬ ደንደአ የጻፉለት የሚመስል መግለጫ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በኩል አውጥቷል…!!!
አቻምየለህ ታምሩ
የአማራ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ እያደረገው ባለው የኅልውና ተጋድሎ እንቅልፍ የተነሳ ብአዴን በባሕር ዳር ሕዝብ ላይ በጫናቸው ምንደኞች በኩል ዛሬም ሌላ መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫው የአማራ ሕዝብ ተጋድሎ ምን መምሰል እንዳለበት ለመወሰን ሞክረዋል። ለመሆኑ እነዚህ ብአዴን የፈለፈላቸው ምንደኞች የአማራ ሕዝብ የሚያደርገውን የኅልውና ተጋድሎ አቅጣጫ እንዲወስኑ ማን ፈቀዳላቸው?
የብአዴን የነፍስ አባት የሆነው ሕወሓትም ግብአተ መሬቱ ከመፈጸሙ በፊት ልክ እንደ ነፍስያ ልጁ ብአዴን አድርጎት በየቀኑ መግለጫ ሲያወጣ ይውል ነበር።ብአዴን እንደ ነፍስ አባቱ ሕወሓት በየቀኑ መግለጫ በማውጣት ላይ የተጠመደው የአማራ ሕዝብ በሚያደርገው የኅልውና ተጋድሎ ስስ ብልቱን ስላገኘው ነው። ፈረንጅም “hit them where it hurts most” ይላል። ጠላትን ማሸነፍ የሚቻለው ስስ ብልቱን ፈልጎ በመምታት ነው።
በመሆኑም ብአዴን እንደ ነፍስያ አባቱ ሕወሓት በየቀኑ መግለጫ እያወጣ ሲለፈልፍ የሚውለው ስስ ብልቱ በመገኘቱ ስለሆነ እንደ ፈጣሪው ሕወሓት ወደ መካነ መቃብሩ ለማውረድ ሲነካ እያስለፈለፈው ባለው ስስ ብልቱ ላይ እያገለባበጡ መግረፍ አስፈላጊ ነው።
ያጋጠመንን ፈተና የምንሻገረው እውነተኛ ህዝባዊነታችን ጠብቀን በመዝለቅ ነው!
ከአማራ ብልጽግና ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!
አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ምትገኝ አገር ናት፡፡ በለውጡ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መመዘግብ የጀመሩበት ኢትዮጵያውን በአጠቃላይ እና በተለይም የአማራ ህዝብ ለውጡን ደግፈው የቆሙበት ሁኔታ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ለለውጡ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑ ህዝባዊ ጥያቄዎች በተለይም የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት፣ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች፣ የኢኮኖሚ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል እርምጃዎችና የተካሄዱ ሪፎርሞች፣ የማህበራዊ ልማት ማሻሻያዎች፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግሮችን የመለየትና የማረም፣ የፀጥታ የፍትህና የደህንነት ተቋማት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የህግ ሪፎርሞች፣ የትላልቅ አገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ችግር ተፈቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለውጥ…..ወዘተ የለውጡ አበይት ትሩፋቶች የታዩባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡
ይሁንም እንጂ እነዚህ ተስፋዎች በተግዳሮች የተሞሉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች ውስጣዊና ውጫዊ ይዘትና ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡ አገራዊ ቀውሱን በማባባስ የተለያዩ የውጭ ኃይሎች እጅ ያለበት ቢሆንም ዋናው ግን የውስጥ ችግራችን ነው፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ መታረም ያለባቸው ውስጣዊ ችግሮች እንደተጠበቁ ሁነው የችግሮቻችን ሁሉ የመጀመያው የትህነግ የክህደት ቡድን ሀገረ-መንግሥቱን የማፈረስ የጥፋት ሚና ሲሆን፤ ቀጥለው የሚመጡት ኦነግ ሸኔ፣ የጉምዝ ታጣቂ ኃይልና በተከበረው የቅማንት ሕዝብ ስም የሚነግደው ቅጥረኛው ታጣቂ የሽፍታ ቡድን የችግሮቻችን ምንጭና የጥፋት ዘር የሚዘሩ ዋና የአገርና የህዝብ ጠላቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ ጸረ-ሕዝብ ኃይሎችና ተባባሪዎቻቸው በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን፣ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞንና ሰ/ሸዋ፣ በማዕከላዊ ጎንደር በጭልጋ የተከሰቱ ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የወገኖቻችን ሞትና የንብረት መውደም ያስከተሉ እጅግ ልብ የሚሰብር፣ ሰው በሆነ ፍጡር ሁሉ ሊደርስ የማይገባው ዘግናኝ አረመኒያዊ ድርጊት ተፈፅሟል፡፡
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ችግሩን ማውገዝ ብቻ ሣይሆን እስከመጨረሻው የሚታገለው በዘር ጥላቻ የመታወር የመርዘኛ አስተሳሰብ ድርጊትና ውጤት ነው ብሎ ያምናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በማንነታቸው በግፍ ለተጨፈጨፉና ለሞቱ ቤተሰቦች፣ የተፈጠረውን ችግር ለማስቆም መስዕዋትነት ለከፈሉ የፌደራልና የክልላችን የፀጥታ ኃይሎች ከልብ የመነጨ መፅናናትን እንመኛለን፡፡ አሁንም የአማራን ክልል ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በየግንባሩ የተሰለፋችሁ የፌዴራልና የክልላችን የፀጥታ ሀይሎች ለምታደርጉት ሀላፊነት የተሞላበት ተጋድሎ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋና ያቀርብላችኋል፡፡
የአማራ ህዝብ ባለበት ወይም በሚኖርባቸው የተለያዩ ክልሎች ሁሉ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በሰላምና በፍቅር እንዲኖር ተመሳሳይ አስተዋፅኦ ለምታደርጉ አካላትም ላቅ ያለ ምስጋናችንን እያቀረብን ይህንን መልካም ተግባር አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉና የወንድማማች ህዝቦችን ሰላምና ደህንነት እንድታስጠብቁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የጥፋት ኃይሎች በአንድ በኩል ዘርን መሠረት አድርገው የሚደርሱ ጥፋቶችን የብሄር መልክ እንዲይዝ ሲያደርጉ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሃይማኖት ገፅታ እንዲኖረው በማድረግ የጥፋት አጀንዳቸውን ማባሪያ እንዳይኖረው በተለዋዋጭ አጀንዳዎች ቀወስ ሲያቀጣጥሉ ይታያሉ፡፡
ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ በቅርቡና ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ፣ በመተከል፣ በአጣዬና አካባቢው የተፈጠሩ ማንነት ተኮር ጥቃቶችና ይህን ተከትሎ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው የሞት፣ ሀብትና ንብረት መውደም መፈናቀል የአማራን ህዝብ በእጅጉ አሳዝኗል፡፡
የአማራው ሞትና መፈናቀል መልኩን እየቀያየረ በመቀጠሉ በህዝቡ ዘንድ ቁጭትና ብስጭትን ፈጥሯል፡፡ ይህን ሁኔታ በመጠቀም ምንጩ የሚታወቅና የማይታወቅ የፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም እርስ በእርሳችን እንድንተላለቅ የጦርነት ድግስ የሚደግሱና እርስ በርሳቸው የሚገፋፉ መልዕክቶችንና ምስሎችን በማህበራዊ ሚዲያ በመለጠፍ ችግሩ እንዲባባስ ለማድረግ ሲሰሩ ይታያል፡፡ ሌሎች ደግሞ የብሄርና የሃይማኖት ፅንፍ በመስበክ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ ለመውሰድ የቀውስ አጀንዳዎችን ሲያቀጣጥሉ ይስተዋላሉ፡፡
ይህን ተከትሎ በአማራ ክልል በአንዳንድ ከተሞች የተፈፀመውን የግፍ ጭፍጨፋ፣ የሰው ሞት፣ የንብረት መውደምና መፈናቀል ለማውገዝ እና መንግስት አስቸኳይ እርምጃ በመውሰድ እንዲያስተካክል ለመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
በሰለጠነና ጨዋነትን በተላበስ መንገድ የደረሱ ጉዳቶችንና ጥፋቶችን ደግመው እንዳይከሰቱ ማውገዝና መንግስትን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅ የዴሞክራሲያዊነትና ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጐች መገለጫ ነው፡፡
ፓርቲያችን ብልፅግና እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢና ተቀባይነት አላቸው ብሎ ያምናል፡፡ ማመን ብቻ ሳይሆን የአማራ ህዝብ ሞትና መፈናቀል በዘላቂነት እንዲቆም ይታገላል፤ በተጨባጭም የፖለቲካና የጸጥታ ስራዎችን ሌትና ቀን እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ መንፈስና ስሜት ለተሣተፉና ሰልፉ ሰላማዊ ሁኖ እንዲጠናቀቅ ለጸጥታ ኃይሉ ተደማሪ ጉልበት የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ክብር አለው፡፡
በሌላ በኩል የተካሄዱት ሁሉም ሰልፎች ለጥፋት ኃይሎችና የመጠፋፋት ነጋሪት ለሚጎስሙ አካላት እንዳቀዱትና ሊፈጥሩት ካሰቡት ጥፋት አኳያ መጠቀሚያ ከመሆን ወጦ በሰላማዊ መንገድ ወደ ቤቱ እንዲመለስ መደረጉ የሚያስመሰግን ነው፡፡ የጸጥታ ኃይላችን ሕዝባዊነትም ከለውጡ ወዲህ መገንባት ስለጀመረው ነጻና ገለልተኛ ተቋም ማሳያ ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡ ለዚህም ሰልፉ ከጅምሩ እስከ መጨራሻው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ላደረጋችሁ የክልላችን የፀጥታ ኃይል አባላት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ምስጋናና አክብሮት ያቀርብላችኋል፡፡
ይሁንም እንጂ የተካሄዱ ሰልፎች ምንም እንኳ በሰላም ተጠናቀቁ ይባል እንጅ በአንዳንድ ከተሞች ከተጠሩበት ሕዝባዊ ዓላማ ውጭ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ምርጫው በሰላማዊና ዴሞከራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ስራ ላይ ባለበት በተቃራኒው ዓላማ ተይዞ የተካሄደ በመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
የሰልፎቹ አላማ ከላይ የተገለፀው ሕዝባዊ አጀንዳ ሆኖ ሳለ በጽንፈኛ ኃይሎች ተጠልፎ የእነሱ ተልዕኮና የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ለማድረግ ሙከራ አድርገዋል፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ በሰልፉ የተሳተፉና ከሰልፉ አላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ የተስተዋሉ አካላት/ቡድኖች የአማራ ክልል ህዝብን የሚወክሉ ባይሆኑም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፣ ፊት የሚያዟዙሩ፣ ጥላቻና መጠራጠርን የሚያሰፉ አሳፋሪ ኩነቶችን ሲያከናውኑ ተስተውለዋል፡፡
የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ የማይለያዩ ትስስር ያላቸው በደምና በአጥንት የተጋመዱ ህዝቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ህዝቦች በመከራም ሆነ በደስታ አብረው ያሳለፉ፣ ረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲመዘዝ ከአንድ ምንጭ የሚቀዱ ህዝቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ህዝቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር ብሔረሰቦች ጋር አገር ያቆሙ፣ የውጭ ወራሪ ኃይልን በጋራ መስዋዕትነታቸው መመከት የቻሉ ህዝቦች ናቸው፡፡ በዚህ ሂደትም በታሪክ ዳገትና ቁልቁለት አብረው ወጥተዋል አብረው ወርደዋል፡፡ የወደፊቱ እጣፈንታቸውም በአብሮነትና በወንድማማችነት መቀጠል አለበት ብለው በፅኑ የሚያምኑ የአገር ዋልታና ማገር የሆኑ ህዝቦች ናቸው፡፡
በሰልፉ የደም ነጋዴዎች እንዳሉት አንዳችን ሌላችን ልናጠፋ ከቶውንም ጤናማ በሆነ አዕምሮ ሊታሰብ የማይችል ተርት ተረት ሲናገሩ አዳምጠናል፡፡ የተራመደው አፀያፊ ሀሳብ ህዝባችንን የማይወክል መሆኑ ብቻ ሳይሆን የአማራ ብልጽግና ፓርቲና መላው ህዝባችን በፅናት ቁመን የምናወግዘውና የምንታገለው እኩይ አስተሳሰብ ነው፡፡ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች በፅናት አብረው ይዘልቃሉ፣ አገርንም ያሻግራሉ፡፡ ትላንት አብረው በመቆም የውጭ ወራሪ ኃይሎችን እንደመከቱት ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ የጋራ ዕጣ ፈንታችውን አብረው ይወስናሉ::
ሌላው በዚህ ሰልፍ የታየው አፍራሽ እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ብልጽግናን በማውገዝ ላይ የተመሰረተ የአማራን ክልል የሁከትና የብጥብጥ ማእከል በማድረግ ቀጥተኛ ተጠቂና ህዝባችን ለአደጋ ተጋላጭ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ድርጊት የአማራ ህዝብ ያለበትን የፀጥታና የፖለቲካ ሁኔታ ያላገናዘበና ይልቁንም ለከፋ ሁኔታ የሚዳርግ የተሳሳተ መንገድ ሆኖ ይታያል፡፡
እርግጥ ነው በሀሳብ የተገነባውን የብልጽግና ፓርቲ በአደባባይ ውግዘት ዝቅ ማድረግ እንደማይቻል እነሱም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ አማራን ያለወንድማማችነት ፖለቲካ ነጥለው መንዳት የሚፈልጉ ፅንፈኛ ሀይሎች በሀሳብ ሞግተው ማሸነፍ እንደማይችሉ በመረዳታቸው ብቸኛ አማራጫቸው ከዚህ ያለፈ ሊሆን አይችልም፡፡
ብልጽግና ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አማራ የሆነውን ጠላት ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ወደ መቃብር እንዲወርድ ያደረገ፣ የተዘረፍነውን ማንነታችንና ነፃነታችን መልሶ ያጎናፀፈንና አንገታችን ቀና እንድንል ያደረገ በፈተናዎች መካከል ትርጉም ያለው ድል የሚያስመዘግብ ተራማጅ የሆነ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሲሆን የአማራ ህዝብም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ ይህ የታየው ውንጀላ በጥቂት ለአማራ ህዝብ የሚታገሉ የሚመስሉ ነገር ግን የአማራን ህዝብ ማህበራዊ ዕሴቶች በማይወክሉ ጠላቶቻችን ታስቦ የተነገረ እርባና ቢስ ድርጊት ነው፡፡ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በአማራ ህዝብ ዘንድ በፅኑ መሠረት ላይ እንዲቆም የምንሰራ ብቻ ሳይሆን ፀረ-ብልጽግና ኃይሎችን ፊት ለፊት በፅናት እንፋለማቸዋልን፡፡
ከሰልፉ አላማ ውጭ የተነሳው ሌላው ጉዳይ ከፌዴራል እስከ ክልል በሚገኘው አመራራችን ላይ የደረሰው የውግዘት፣ የማጥላላትና ስም የማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ መሪውን አክባሪ የተከበረና የዳበረ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ያሉት ወረተ-ብዙ ህዝብ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ መከባበር ሲወርድ ሲዋረድ የኖረና አሁንም ያለ ማህበራዊ እሴቱ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ወርቃማ እሴት ባፈነገጠ መንገድ ጥቂት ግብረ-ገብነት የጎደላቸው በጥላቻ የሰከሩ ግለሰቦች ከፓርቲያችን ፕሬዝዳንት ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን በስም በመጥራት፣ ማውገዝ፣ አልፎ ተርፎም በገዳይ አስገዳይ በመፈረጅ በድፍረት ተናግረዋል፡፡ ይህ የብልጽግናን አመራር ከአማራ ህዝብ ለመነጠል ለማስጠላት የተደረገ ሴራ የወለደው ግልፅ ጥቃት ነው፡፡ ነገር ግን የአማራ ህዝብ ብልህና አስተዋይ ህዝብ ነው፡፡ ከቶውንም ሊቀበላቸው ቀርቶ ሊያዳምጣቸውም አይፈቅድም፡፡ ይልቁንስ ድርጊታቸውን በትዝብት የተመለከተና ቆም ብሎ እየሆነ ስላለው ነገር እንዲያስተውል አድርጐታል፡፡ አብዛኛው ሰውም ድርጊቱን በግልፅ ነቅፎታል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እኛ የብልጽግና አመራሮች ይህ ሁኔታ ለሕዝባችን ተጠቃሚነት ስንል የበለጠ የሚያጠነክረን እንጂ ከቶውንም ከእርምጃችን አንድ ስንዝር ወደኋላ ሊመልሰን አይችልም፡፡ በተለመደው የፅናትና የአሸናፊነት ወኔ ትግላችን አጠናክረን የብልጽግና ጉዟችን እንደምንቀጥል የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ያረጋግጣል፡፡
በሰልፉ ላይ የህዝቡን እውነተኛና ፍትሀዋ ጥያቄ ጠልፈው ለፖለቲካ ዓላማቸው ሊጠቀሙበት ያሰቡ ኃይሎች እነማን እንደሆኑ በድርጊቱ ራሳቸውን አጋልጠዋል፡፡ የሰልፉ ታዳሚ ጥቂት ግለሰቦች ከላይ ከተገለፁት እኩይ ተግባራት በተጨማሪ ከአብን በስተቀር የብልጽግና ፓርቲ እና የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክትና ባነሮች ከተሰቀሉበት ቢልቦርድ ወርደው እንዲቃጠሉና እንዲቀደዱ ተደርጓል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ አሰፈፃሚዎች ተረጋግተው ስራቸውን እንዳይሰሩ ወከባ ሲፈጥሩ የዋሉም አሉ፡፡ይህም የህዝቡን እውነተኛና ፍትሀዊ ጥያቄ ጠልፎ ለራሱ ስግብግበ አላማ በሚያመች መልኩ ስልፉን ሲያስታባርና ሲመራ የዋለው አካል ማን አንደሆነ በግልፅ የታየበት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በሰልፉ የተላለፉ መልዕክቶች የማን ፍላጐትና ዓላማ እንደሆነ ጭምር በይፋ የተመለከትንበት ነው፡፡
ድርጅታችን ብልጽግና ይህ ድርጊት ፍፁም ህገ-ወጥ፤ ፍፁም ወንጀል ነው ብሎ ያምናል፡፡ በመሆኑም የምርጫ ቦርድና ሌሎች የህግ አስከባሪ አካላት ጉዳዩን አጣርተው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰዱ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡ በአጠቃላይ የተፈፀሙ ድርጊቶች የተከበረውን የአማራ ህዝብ አንሶ ማሳነስ የታየበት ያላዋቂዎች ጨዋታ ሆኖ አግኝተዋል፡፡
በመጨረሻም የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ሕዝባችን ያነሳቸውን ፍትሀዊ ጥያቄዎች ይቀበላል፤ ነገር ግን አጀንዳውን ለራሳቸው የፖለቲካ ዓላማ ጠልፈው እየተጠቀሙበት ያሉ ኃይሎች የጥፋት መንገድ በእጅጉ ያሳሰበዋል፡፡ ፓርቲያችን ይህን እኩይ ተግባር ከመላው የአማራ ህዝብና ከሌሎች አገርና ህዝብ ወዳድ ከሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በጋራ በመታገል አገርና ህዝብን ከጥፋት ለመታደግ ዝግጁ መሆናችን ደግመን ደጋግመን ለመላው የክልላችንና የኢትዮጵያ ህዝብ እናረጋግጣለን፡፡
በመጨረሻም በአማራ ህዝብ ሞትና መፈናቀል እጃቸው ያለበትን ማናቸውንም የጥፋት ሀይሎች ለህግ ለማቅረብና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆናችንን ለህዝባችን ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
የወቅቱን ፈተና እንረዳለንና ያጋጠመንን ፈተና የምንሻገረው እውነተኛ ህዝባዊነታችን ጠብቀን በመዝለቅ ነው!!!
“ቅድሚያ ለሀገርና ለህዝብ እንቆማለን!!!”
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት
ሚያዚያ 13/2013 ዓ.ም
ባህር ዳር