>
5:33 pm - Saturday December 6, 4431

የአማራው ሕዝብ ዋነኛ ፈተና የሚመነጨው ከየት ነው? መፍትሄውስ? (አሰፋ ሀይሉ)

የአማራው ሕዝብ ዋነኛ ፈተና የሚመነጨው ከየት ነው? መፍትሄውስ?

አሰፋ ሀይሉ

 

በዚህ ጽሑፍ የአመራው ሕዝብ ዋነኛ ፈተና የሚመነጨው ከምንም በፊት እወክልሃለሁ ከሚለው ከብአዴን መሆኑን አስረዳለሁ፡፡ እና የአማራው ህዝብ (እና ብአዴንም) ያሉትን ጊዜ የማይሰጡ የመፍትሄ አማራጮች እጠቁማለሁ፡፡ ቴሲሴ አንድ ነው፡፡ ብአዴን የአማራን ሕዝብ የጎዳው በአንድ ዋነኛ ጉዳይ ነው፡- የአማራን ሕዝብ የራሴ የሚለው መቆሚያ መሬት ወይም ነፃ ቀጣና በማሳጣት፡፡ የሚል፡፡ በቀጥታ ወደ ዝርዝሩ እገባለሁ፡፡
 
ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን ያየን እንደሆነ የትግሬው አስገንጣይ ሀይል (ወያኔ) ለምሳሌ ከወታደራዊው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ላደረገው ፍልሚያ ወሳኙንና የመጀመሪያው ትልቁ ምዕራፌ የሚለው የራሴ የሚለውንና እንደልቡ የሚንቀሳቀስበትን ነጻ መሬት ያገኘበትን ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን የራሴ የሚለው ሥፍራ አግኝቶ ራሱን አረጋግቶ ለማደርጀትና ለማንቀሳቀስ በሱዳን፣ በግብጽ፣ በኤርትራ፣ በየመን፣ በሶማሊያና በሌሎችም የትግራይ በረሃዎች ሲንከራተት ኖሯል፡፡ 
 
ለኤርትራ የተለያዩ ተገንጣይ ሀይሎችም ወሳኝ የትግል ምዕራፍ የከፈተላቸው ከሀገር ውጪ በሱዳን እና በሀገር ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የማይደርስባቸውን የሳህል በረሃዎች ተከፋፍለው እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱበት ነጻ መሬት ያገኙበት ምዕራፍ ነው፡፡ 
 
በአሁኑ ወቅት የኦነግ፣ እና ሌሎችም ጽንፈኛና ፀረ ኢትዮጵያ ሀይሎች በኦሮሚያ ውስጥ ያገኙት ትልቅ አደቫንቴጅ ራሳቸውን የሚያደራጁበት፣ እንደ ልብ የሚንቀሳቀሱበት፣ አባሎቻቸውን የሚመለምሉበት፣ ወጣቱን (ማለትም ትግሉን የሚያካሂድላቸውን) ሰልፈኛ የሚሰብኩበት፣ እና ከዚያም አልፎ ከቀበሌና ወረዳ ጀምሮ እስከ ዞኖችና ክልላዊው መሬቶች ላይ ያለ ሥጋት የሚንቀሳቀሱበት፣ የሚሸሸጉበት፣ ለጥቃት የሚንቀሳቀሱበት፣ የሚመክቱበት፣ የሚያገግሙበት፣ እና በአጠቃላይ የእኔ የሚሉት ነጻ ቦታ ማግኘታቸው ነው፡፡ 
 
«ዓሣውን ለማጥፋት ውሃውን ማድረቅ» የሚባል በዓለም ሲሰራበት የኖረ የጦርና ሽምቅ እንቅስቃሴ መርህ አለ፡፡ ጠላትህን ለማጥፋት መጀመሪያ የምታደርገው ነገር መላወሻ ሜዳ ማሳጣት ነው፡፡ የትም ሥፍራ ላይ ተረጋግቶ የሚንቀሳቀስበት ዕድል እንዳያገኝ ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ድርጅቶቹን ሠርገህ ከመግባት ጀምሮ የተለያዩ አካባቢያዊ (ቀበሊኛ) የስለላ ስልቶችን ትጠቀማለህ፡፡ 
 
መንግሥታዊ ሀይሎችን ኮቴያቸውን እየተከታተልክ መላወሻቸውን የመቆጣጠርና የማምከን – ፀረ-አማጺ ወይም ፀረ-ሠርጎ ገብ የስለላ፣ የቅኝትና የአፀፋ እርምጃ እንቅስቃሴዎችን ሳታቋርጥ ማካሄድ፡፡ እና የሰውና የቴክኖሎጂ መረቦችን በመዘርጋት ያልተቋረጡ አሰሳና ቅኝቶችን በተጠረጠሩ፣ በተመረጡ ወይም በአጠቃላይ በግዛትህ ሁሉ ላይ ማካሄድን ይጨምራል፡፡ ድንበር-ዘለል የሆኑ የስለላና ቅኝት ሥራዎችም የዚሁ አካል ናቸው፡፡ 
 
እንግዲህ አንድ ሀይል የሚገዳደሩት ተቀናቃኝ አስጊ ሀይሎች እንዳይፈጠሩበት፣ ወይም ተፈጥረው ከሆነ እንዳይጠናከሩበት ከላይ የተጠቀሱትን የተቀናጁ ተግባሮች በማካሄድ ራሱን ይከላከላል፡፡ ብአዴን የአማራውን ህዝብ ቅስም ከሰበረባቸውና የውስጥ አስጠቂ (የእግር እሾህ) ሆኖ አላራምድ ካለባቸው ነገሮች ሁሉ የከፋው ይህን የጠላት ግዳጅ የአማራ ሕዝብ ጠላት ለሆነው ለወያኔ-ኢህአዴግ ሌት-ተቀን ሲወጣ የመኖሩና፣ አሁንም ከወያኔም በላይ የወያኔን የፖለቲካ ፕሮግራምና ትርክት ወርሶ የአማራውን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ የአማራውን አከርካሪ ሰበርኩ እያለ በአደባባይ ለሚፎክረው የኦሮሙማ ሀይል እየተወጣ የመሆኑ መራር እውነታ ነው፡፡
 
ብአዴን የአማራውን አከርካሪ ለመስበር ለሚንቀሳቀሰው የኦሮሙማው ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አማራ ሀይል ከላይ የጠቀስኳቸውን፣ እና ገዢን ለመቋቋም በሚካሄዱ የትግል እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁሉ ከምንም ጉዳይ በላይ ከባድ ጠንቅ ተደርገው የሚቆጠሩትን የጠላትነት ተግባራት በመፈጸም የአማራው ህዝብ የራሴ የሚለው ነጻ መሬት (ወይም ነፃ ቀጣና) እንዳይኖረው፣ በምሥጢር እንዳይንቀሳቀስ፣ ራሱን እንዳያደራጅ፣ ነፃ የመመላለሻና የግንኙነት መስመር እንዳይዘረጋ፣ የወገብ ቅማል ሆኖ የመዋኛ ውሃውን እየተከታተለ ሲያደርቅ፣ ሲሰልል፣ እና ሲያስጠቃ የመኖሩ ተግባር ነው – ከምንም በላይ የአማራውን ሕዝብ እንደ ህዝብ አቅሙን ያጠመነው ጉዳይ፡፡ 
 
በአብይ አህመድና የኦሮሙማ ቡድኑ የመንቀሳቀሻ ሜዳና፣ የፋይናንስና አቅርቦት፣ እንዲሁም የመገናኛ መስመሮች እንደልባቸው የተከፈተላቸው የኦሮሙማው ህቡዕና መደበኛ ሀይሎች በሁለትና ሶስት ዓመት አጭር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን አግዝፈው ዛሬ ኢትዮጵያን የሚገዳደሩና የኢትዮጵያውያንን አቅም የሚገዳደሩ ሀይሎች ለመሆን ሲበቁ፣ የአማራው ሕዝብ ግን በጉያው በተፈጠረለት እንደ ብአዴን ባለው የጉያው ተላላኪ ሠርጎ-ገብ ጠላት ምክንያት መንቀሳቀሻ ነጻ መሬት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ 
 
በታሪክ በአንድ ሕዝብ ላይ ይህን የሚያደርጉትና የሚያስደርጉት አንድም ቅኝ ገዢዎች ናቸው (ፈረንሣዮች አልጄሪያ ውስጥ፣ እንግሊዞች ኬንያ ውስጥ፣ ጣልያኖች ኤርትራ ውስጥ፣ ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል)፡፡ አሊያም ህዝባቸውንና መንግሥታቸውን ከሚያጠቃ ጠላት ለመከላከል ቆርጠው የተነሱና አቅሙ ያላቸው (ስለሆነም ሕዝቦች ራሳቸውን ለማደራጀትና ለመከላከል የማይገደዱባቸው) አገሮች ናቸው፡፡ 
 
በኢትዮጵያችን ተጨባጭ ሁኔታ የምናየው ግን የዚህን ተቃራኒ ነው፡፡ የአማራውን ሕዝብ ቅስም ለመስበርና ህልውናውን ለመፈታተን ዙሪያውን ያሰፈሰፉ ሀይሎች የራሳቸው ነጻ መሬትና የራሳቸው የእኔ ነው የሚሉት መደበኛ የመንግሥት ድጋፍና ባጀት የሚቸረው ሀይል ኖሯቸው እንደልባቸው እርስ በራስ ተደጋግፈው ራሳቸውን ሲያደረጁና አማራውን የመጉዳት አቅማቸውን ከጊዜ ወደጊዜ ሲያጎለብቱ – አማራው ግን ከራሱ ጉያ የወጣ ቃፊር ተመድቦለት ሌት ተቀን፣ አስራ ሶስት ወር ሙሉ፣ እየተሰለለና እየተጠበቀ ውልፍት የሚልበት ነጻ መሬት እንዳያገኝ የተደረገ ህዝብ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ 
 
የብአዴን ቃፊሮች ከቀበሌና ወረዳ እስከ ዞንና ክልል ድረስ የአማራውን ራሱን የማደራጀትና የመንቀሳቀስ እንቅስቃሴ እየተከታተሉ – ከሕዝብና ከቡድንም ወርደው እስከ ግለሰቦች ድረስ በየቤቱ እየገቡ እያደኑ ለአማራው ጠላቶች የአማራውን ጀግኖች ግዳይ የሚጥሉ፣ በጌቶቻቸው የተሰጣቸውን የአማራውን ሕዝብ የመዋኛ ገንዳ የማድረቅ ስምሪት የሚያከናውኑ፣ የራሳቸውን ሕዝብ ጭዳ-በሬ ለማድረግ ኮስተር ብለው ከጠላት ጋር ሃያ አራት ሰዓት የሚሰሩ የተኩላ መንጋዎች ሆነዋል፡፡ 
 
ስለሆነም አማራው በጠላት የተከበበ፣ የራሴ የሚለው፣ የሚንቀሳቀስበት፣ የሚነጋገርበት፣ በምሥጢር የሚመክርበት፣ የሚደራጅበት፣ የሚሰለጥንበት፣ ራሱን የሚያጎለብትበት፣ አቅርቦቱን የሚያጎለበትና የሚያደረጅበት፣ የራሱ የሚለው ቆራጣ ሜዳ እንኳ የተነፈገው ሕዝብ ሆኗል፡፡ ይህ ሁኔታ ለሁሉም የሚሠራ ቢሆንና፣ መንግሥት የሚባለው ተቋም ማንም ራሱን ማደራጀት ሳያስፈልገው ሕዝቡን ለመጠበቅ ፍላጎቱም፣ ዓላማውምና ብቃቱም ያለው ቢሆን ኖሮ ችግር አልነበረውም፡፡ 
 
ነገር ግን የጨዋታው ህግ ለሁሉም እኩል ሆኖ አያውቅም፡፡ አሁንም አይደለም፡፡ ወደፊትም የሥርዓቱ መሠረታዊ ህግጋትና ትርክቶች እስካልተቀየሩ ድረስ ለሁላችንም እኩል የሆነ ሥርዓት እና የጨዋታ ህግ ሊኖር ከቶም አይችልም፡፡ አፍሪካውያንና የዓለም ቅኝ ተገዢ ህዝቦች ከኮሎኒያሊስቶች ነጻ ለመውጣት ያቀነቀኑትን ዘመን ያለፈበት የኮሎኒያሊዝም ትርክት ከነግሳንግሶቹ በአህያ ጭነው በአማራው ሕዝብ ላይ ያራገፉ፣ እና የእኩልነትና የነጻነት አይዲዎሎጂ ቱምቢያቸውን በፀረ-አማራ ትርክት ላይ የጣሉ የአማራ ጠላቶች ፈርጥመው እስከቀጠሉ፣ እና ለትርክታቸው እውቅናና ሥጋ ያለበሳቸው ህገመንግሥት ከነትርክቶቹ እስካልተስተካከለ (ወይም እስካልተሻሻለ) ድረስም ለሁሉም ዜጋ እኩል የሚያገለግል የጨዋታ ህግ ሊኖርም፣ ሊታሰብም አይችልም፡፡ 
 
በአማራው ሕዝብ እንደ ጭዳ በግ ተላልፎ የተሰጠበት፣ በአማራው ባይተዋርነት የሚገነባው ሥርዓት ጨዋታው በወያኔም ጊዜ አማራውን ጠምጄ አላሳርስ እያልኩ ሌላውን በጠላትነት አደራጅበታለሁ የሚል ጥርሱን ያገጠጠና ሁሉም የሚያውቀው ፋሺስታዊ መንግሥታዊ የበቀል መመሪያ ነበር፡፡ ያ ለአስርተ ዓመታት ሲተገበር ቆይቶ አበቃ ሲባል፣ አሁን ደሞ ይባስ ብሎ ጨዋታው የአማራውን ሕዝብ አንተ በየትም አባክ አትላወሳትም፣ ጠላቶችህን በላይህ ላይ እናደራጅብሃለን፣ ባሰኘን ጊዜ ደምህን እናፈሳለን፣ አንጋለን እንሸናብሃለን፣ በመከራህና በገፈትህ ግን የሚደርስልህ አይኖርም ወደሚል «ራስህን አድን» ወይም ባዶ እጅህን ከአውሬ ጋር ታገል ወደሚል አስቀያሚ (እና «ሩዝለስ») የግላዲያተሮች የፍልሚያ ጨዋታ እንዲገባ ነው የተገደደው፡፡ 
 
ባጭር አነጋገር የአማራ ክልል የጌቶቹ የኦሮሙማዎች የጨበጣ ግላዲያተር ትዕይንት አምፊትያትርነት እንዲቀየር ነው የተፈለገው፡፡ የአማራው ህዝብ በያለበት ሥፍራ ራሱን ለማደራጀትና ለመጠበቅ ፍቃድ የተነሳው፣ ነገር ግን ሌሎች በመንግሥት እውቅናና ድጋፍ እንዲሁም ለከት ባጣ ሌት ተቀን በሚነዛላቸው ጥላቻ እየተደገፉ አማራውን እንዲያጠቁት፣ እንዲገዳደሩትና በህልውናው ላይ ቋሚ ሥጋትና አደጋ እንዲጋርጡበት ሆነ ተብሎ የሚሠራበት ነባራዊ ሁኔታ ነው ያለው አሁን፡፡ 
 
ለዚህም ነው ከምንጊዜውም በላይ በአሁኑ ወቅት አማራው ከማንምና ከምንም በፊት ቁጥር-አንድ ጠላቱ ብአዴን የተባለው ቀድሞ የወያኔ፣ አሁን ደግሞ የኦሮሙማው ተላላኪ አስጠቂና ቃፊር ሆኖ አማራውን አላስቆም አላስቀምጥ ያለ፣ የመዋኛ ገንዳውን አድርቆ ለሌሎች ጥቃት ያጋለጠ የውስጥ ባንዳ ነው የምንለው፡፡ ችግሩን በዚህም በዚያም ብለን ደግመን ደጋግመን ለማሳወቅና ለማሳሰብ ይህን ያህል ካልን፣ መፍትሄውስ ምንድነው ወደሚለው የመጨረሻ አጭር ነጥብ እንሂድ፡፡ 
 
የአማራው ሕዝብ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ (እና አሁን መሬት ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ) ራሱንና ሀገሩን ኢትዮጵያንም ለመከላከል እንዲችል ሆኖ በሁለት እግሮቹ ለመቆም ካስፈለገ፣ ያለው የመጀመሪያ ምርጫ፣ ከብአዴን ተብዬው ተላላኪ ሀይል ጋር ለአማራው ከፊት ለፊት ለመቆም በቆረጡ ሕዝባዊና ፖለቲካዊ መሪዎች (ተወካዮች) አማካይነት ቁጭ ብሎ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ ብሎ ያሉትን ሁኔታዎች በግልጽ መክሮ ከብአዴን ጋር አጋርነትን ለመፍጠር መሞከር ነው፡፡ ይህ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ 
 
የአማራ ሕዝብ ከብአዴን ጋር ቁጭ ብሎ መምከር ያለበት በአንድ በኩል ብአዴንም የተላላከበትን አገልግሎት ሲፈጽም በመጨረሻ እንደ ቀደመው የወያኔ ዘመን ሁሉ ወደ ቀደመው ተራ የግርድና ስምሪቱ መውረዱና መሰልቀጡ እንደማይቀርለት ቁጭ ብሎ መክሮ አስረድቶና አሳምኖ ከተላላኪነትና ከውስጥ ጠላትነት ተግባሩ እንዲቆጠብ ለማድረግና፣ አማራነቱን እንዲያረጋግጥ የመጨረሻ ዕድል ለመስጠት ነው፡፡ 
 
ብአዴን ይህን የማይቀበል ከሆነ ግን፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ፣ ከምንም በላይ ይህን የአማራን ህዝብ የጎን ውጋት ሆኖ በገዛ ሀገሩና መንደሩ ነጻ የመንቀሳቀሻ ሜዳ የነሳውን የጠላት ተላላኪ ብአዴንን ባለ በሌለ ሕዝባዊ ማዕበል፣ አጥብቆ መታገልና ከጫንቃው ላይ ማውረድ ይሆናል – ማለት ነው፡፡ ይህ የመጨረሻ አማራጭ በአሁኑ ወቅት የአማራ ሕዝብ ከተገደደ የሚገባበት የመጨረሻው አማራጩ የሚሆነው፣ ከዚህ ውጭ በአሁኑ ወቅት የአማራው ሕዝብ ራሱን የሚያደራጅበትና የሚከላከልበት ምንም ሌላ መንገድ ስለሌለው ነው፡፡ 
 
የአማራው ሕዝብ የራሱ መላወሻ ሥፍራ ያስፈልገዋል፡፡ የለውም፡፡ ሌላ ቀርቶ እንደሌሎቹ ሲከፋው የሚሰደድበትና የሚጠለልበት ጎረቤት ሀገር የለውም የአማራ ሕዝብ፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ቢያንስ በገዛ ቀዬው ራሱን ነጻ ለማድረግ መታገል ብቻና ብቻ ነው፡፡ ያለው አማራጭ የመዋኛ ገንዳውን የማድረቅ የተላላኪነት ተግባሩን ለሠላሳ ዓመታት ሳይስተጓጉል እየተወጣ ያለውን የራሱን የውስጥ ቃፊር ብአዴንን ከዚህ ፀረ-አማሩ ማስታገስ ብቻ ነው፡፡ ብአዴን ሆይ ስለወገኖችህ መቅሰፍት ባይገድህ፣ ቢያንስ ለራስህ ስትል እንኳ ተመከር፡፡ ለራስህ ስትል አማራ ሁን፡፡ ለራስህ ስትል ጨዉ ሁን፡፡ አለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል፡፡ በማዕበሉም ትወሰዳለህ፡፡ ፈውስም አይኖርህም፡፡ 
 
ፈጣሪ መከራ እየተቀበለ ያለውን የአማራውን ልብ ያበርታ፡፡ ሀዘናችንን ያጽናና፡፡ ኢትዮጵያን እብዝቶ ይባርክ! 
Filed in: Amharic