>
5:18 pm - Saturday June 15, 1247

የብልፅግናው ኦነግ ሸኔ አጭር ታሪክ...!!! (አህመዲን ሱሌይማን)

የብልፅግናው ኦነግ ሸኔ አጭር ታሪክ…!!!

አህመዲን ሱሌይማን

 

በመጀመሪያ “ለውጡ” ን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ አጋሩ የነበረውን ለማ መገርሳን ወደ ኤርትራ በመላክ በዛ የነበረውን የኦነግ ሠራዊት #ከነትጥቁ ወደ ኢትዮጲያ እንዲያስገባ አደረገ። ይህ ኦነግ ወደ ጦላይ ገብቶ በመንግስት በመሰልጠን መከላከያን መቀላቀል ወይም መሳሪያ አስቀምጦ ህብሰተሰቡን መቀላቀል የሚሉ ሁለት ምርጫዎች ተሰጡት። አብዛኛው በጦላይ ስልጠና ሲገባ በድሪባ ኩማ (ጃል መሮ) የሚመራው ቡድን ግን “ከሕወሀት ጋር ገና ያላወራረድነው ሂሳብ አለን፣ እናንተም የህወሀት አስቀጣዮች ስለሆናችሁ አብረናችሁ ልንሰራ አንችልም” በማለት ወደ ጫካ ሸፈተ። ይህ የጃል መሮ ኦነግ ለኦሮሙማው የአብይ አገዛዝ እንደ ጠንቅ በመታየቱ ጥርስ ተነከሰበት።
 
ጦላይ የገባው ኦነግ ከመከላከያ ጋር እንዲሰለጥን ተደረገ። በአብይ የሚታዘዝ የአብይ ስኳድ ተደርጎ ተሰራ። በመከላከያም ቁልፍ ቁልፍ ቦታ እንድይዝ ሆነ። በበላይነት አባ ዱላ የሚያስተዳድረው፣ ለማ መገርሳ የሚያንቀሳቅሰው እና አብይ አህመድ የሚያዘው እንዲሆን ሆኖ ተዋቀረ። በመቀጠልም በበርካታ ኮንቴነሮች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከፈረንሳይ ነፍስ ወከፍና የቡድን መሳሪያዎች በመከላከያ ስም እንዲታዘዙለት ተደረገ። ኮንቴነሮቹ በጅቡቲ ሲደርሱ አገር ከመግባታቸው በፊት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላና አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዛ በመሄድ ርክክብ እንዲያደርጉ በአባ ዱላ ተላኩ። በጅቡቲ ርክክቡ ከተከናወነ በኋላ ጅቡቲ ምንነቱ ምን እንደሆነ ለማይታወቅ ጀብዱ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን የአገሪቱን ኒሻን ሜዳሊያ ሸለምኩኝ አለች። ይህም ዜና ተደርጎ በኢቲቪ እንዲነገር ሆነ። ጅቡቲ ሜዳሊያውን የሸለመችው መሳሪያዎቹን በማስተላለፉ በኮሚሽን ላገኘችው በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠር የገንዘብ ውለታ እንደነበር ይገመታል።
 
እነዚህ በኢትዮጲያ መከላከያ ስም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር የገቡ መሳሪያዎች በቀጥታ ወለጋ ሄደው እንዲራገፉ ተደረጉ። እዛም በአብይና/አባዱላ ሰልጥነው መጤ በሚሏቸው በብዛት አማራዎች ባሉባቸው አካባቢዎች እንዲሰፍር ለተደረገው የአብይ ኦነግ ሸኔ ተከፋፈሉ። ከአልባሳት፣ ከጫማና ከስንቅ አንስቶ በኢትዮጲያ መደበኛ መከላከያ እንኳ በጥቂቱ ብቻ ያሉትን እጅግ ዘመናዊ የነፍስና የቡድን መሳሪያዎችን በብዛት እንዲታጠቅ ተደረገ። ከዛም በአብይና አርሲ በተቀመጠው አባ ዱላ ትዕዛዝ በጃል መሮ ኦነግ ስም ንፁሀንን እንዲጨፈጭፉ ስምሪት ተሰጣቸው። ከዛ ጊዜ አንስቶ ባልተቋረጠ ጭፍጨፋ የአብይ ኦነግ ሸኔ ፍፁም የሆነ አረመኔያዊ የዘር ፍጅቱን አባባሰ። ሀብትና ንብረትን አወደመ። በመቶ ሺዎችን ለስደት ዳረገ።
 
በዚህ ሁሉ ውስጥ የአብይ መንግስት የጃል መሮን ኦነግ በፍጅቱ መክሰሱን ቀጠለ። ጃል መሮ በበኩሉ ባገኘው የሚዲያ አጋጣሚ ሁሉ በቪኦኤ ለበርካታ ጊዜ፣ በአልጀዚራ፣ በቢቢሲና ከትናንት በስቲያ ደግሞ በሮይተርስ እርሱ የሚመራው ጦር ንፁሀንን ፈፅሞ እንደማይገልና እኛ እናቶች፣ ሴት ልጆች፣ አባቶች፣ አርሶአደሮች አሉን፣ ምን ብለን ከኛው ጋር የሚኖርን ምስኪን ደሀ ሕዝብ እንገድላለን? በማለት ሲናገር ቆየ። እኛ እምነታችን አብዛኞቻችን ኦርቶዶክስ ሆኖ እንዴት የእምነታችንን ቦታዎች እናቃጥላለንም ሲል ተደመጠ። በተደጋጋሚም በነ አባ ዱላ የተቋቋመውንና በአብይ አህመድ ቀጥታ ትዕዛዝ የሚመራውን ሸኔን በንፁሀን የዘር ፍጅቶች ከሰሰ። ገለልተኛ አካል ገብቶ ቢያጣራ መልሱን ያገኛል ሲል ሞገተ።
 
የአይን ምስክሮች፣ ከግድያ የተረፉ ተጎጂዎችና በመጠለያ ጣቢያ ያሉ ስደተኞች ሁሉ የጃል መሮ ኦነግን ሳይሆን የመንግስት ወታደሮች ያሏቸውን የአብይ ሸኔን ወታደሮች በፍጅቱ ሲከሱ ተሰሙ። 
 
በቤኒሻንጉልም እንዲሁ በጃል መሮ ኦነግ ስም የአብይ ሸኔ በነ አባዱላ መሪነትና በአብይ የቀጥታ ትዕዛዝ ግድያና ጭፍጨፋዎችን ሲያደርግ ቆየ። 
 
የሰሞኑን የሰሜን ሸዋ የዘር ፍጅትን በተመለከተ ጃል መሮ ለሮይተርስ በሰጠው ቃሉ እርሱ የሚመራው ኦነግ በአካባቢውም ጨርሶ እንደሌለና በዛም ምንም እንደማይሰራ ተናገረ። በሌላም በኩል ከነዋሪዎችና ከተጎጂ አካላት በተገኘ ምስክርነት የአብይ ሸኔ መንግስታዊ መዋቅር ከዞን አመራርና አስተዳዳሪዎች ጀምሮ ግድያውንና ጭፍጨፋውን በመምራትና በማስፈፀም እንደተሳተፈ ደጋግመው ሲናገሩ ተደመጡ።
 
ከሦስት አመት ያላባራ የአማራ ንፁሀን ደም መፍሰስ በኋላ፣ በግርድፉ ኦነግ እየተባለ ይጠራ የነበረው አካል በውል ለየ። የትኛው ኦነግ በከፍተኛ ሁኔታ በኢትዮጲያ ሕዝብ ገንዘብ በመከላከያ ስም የተገዙ መሳሪያዎችን ታጥቆ በየ 15 ቀኑ እስከ 300 ሕዝብ ድረስ እንደሚጨርስ ታወቀ። ጣቶች ሁሉ በመላ አገሪቱ ሲደረጉ በቆዩ ሕዝባዊ ፍጅቶች ምክኒያት ለፈሰሰው የሰው ደም ምንም ግድ ሳይሰጠው በሟች እሬሳዎች ላይ ህንፃ ሲገነባና ሲያስመርቅ፣ አበባ ሲተክልና ሲያጠጣ ወደ ቆየው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ላይ አመላከቱ። 
 
ትናንት እና ዛሬ በነበሩ የሕዝብ ሰልፎችም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስም ተጠቅሶ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ተከሰሰ።
Filed in: Amharic