>

ለጠቅላይ ሚኒስትሩስ ማን ይንገራቸው?  ለምን ተናግረው ያናግራሉ (አዲስ ምግባሩ)

ለጠቅላይ ሚኒስትሩስ ማን ይንገራቸው?  ለምን ተናግረው ያናግራሉ

አዲስ ምግባሩ

 

ዓብይ አህመድ ፣ ዛሬ የሰጡት መግለጫ ሲጨመቅ ሶስት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አንደኛው ስለ ሽግግር መንግስትና የመንግስታ አቋም፣ ሁለተኛው ስለ ጸጥታ ጉዳይና ሶስተኛው ስለ ምርጫ ነው፡፡ የንግግራቸው ትልልቁ ክፍል ስለ ምርጫውና ስለ ሽግግር መንግስት ሀሳባቸውን የሰጡበት ነው፡፡ ጎልማሳ በሚስቱ፣ ንጉስ በመንግስቱ ይሏልይሄንን ነው፡፡ ንግግር ብቻ ሳይሆን ፣ ጠቅላዩ ዛሬ አለ አመላቸው ሲፎክሩም ውለዋል፡፡ የንግግራቸው ጥቂቱ ክፍል ሰሞኑ ስለተፈጠረው የጸጥታ ጉዳይ የተናገሩት ነው፡፡ ሰሞኑን የደረሰው ግድያና የከተሞች ውድመት የተከሰተው በተገዙ ሽፍቶች ነው ካሉ በኋላም ፣ ምክንያቱ ደግሞ ሕዝቡ መከላከያንና ፖሊሲን ባለመቀላቀሉ ነው አይነት አስገራሚ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 
 
1. ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያስቡት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሾርት ሜሞሪ የለውምና ሁኔታዎችን ያስታውሳል፡፡ ሰሞኑን ሽብር የፈጠሩት የኦነግ አባላት እሳቸው እንደሚሉት መከላከያንና ፖሊስን አልፈው የመጡ አይደሉም፡፡ አሁን ሀገሪቷን በሽብር የሚንጣት ኦነግ ከኤርትራ ከነመሳርያው የገባው ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ ፈቃድ ድንበር አቋርጠው፣ በሬ ታርዶላቸው ነው፡፡ 
 
2. አጣዬም ሆነ ወለጋ ላይ ያ ሁሉ ውድመት የደረሰው ፣ ኃይል ስላልነበረ ወይም ሕዝቡ መከላከያንና ፖሊስን ስላልተቀላቀለ ኃይል አጥሮ አይደለም፡፡ ኦሮሚያ ብቻ ስንት ዙር ልዩ ኃይል አሰልጥኗል፡፡ እውነት ይሄ ሁሉ ኃይል ለወለጋ፣ ከወለጋም ጥቂት ቀበሌዎችን ለመጠበቅ ኃይል አንሶት ነው? ከከሚሴ ጥቂት ርቀት ላይ ያለውችው ደሴ ላይስ ሄደው “ የፈደራል መንግስቱ የሚልከውን በጀት፣ ልዩ ኃይል በማሰልጠን አታባክኑ” አይነት መግለጫ የሰጡት እኮ ክቡር ጠቅላዩ ኖት እኮ ፡፡ ሾርት ሚሞሪ…. ፡፡ ሲያሻዎ ወታደር በማሰልጠን ገንዘብ አታባክኑ፣ ሲመስልዎ ደግሞ ነፍጥ ታጣቂ ሁኑ የሚሉት ነገር ግራ ያጋባል፡፡ ሻሸመኔ የተቃጠለችው ፣ እዛው አጠገቧ ወንዶ ገነት ኮማንዶ ጦር ስላልነበረ ነው? ከሚሴ ላይስ አውዳሚው ጦር ጥፋት ሊያደርስ እየተዘጋጀ እንደነበረ ስላልታወቀና ሾልኮ ስለገባ ነውን? ባደባባይ ሲሰለጥን አልነበረ እንዴ? አጣዬና ካራቆሬ ላይ እኮ ሬሳ ሶስት ቀን አልተነሳም ነበር፣ ውሸት ምን ያደርጋል
 
3. ጠቅላዩ፣ “ የሽግግር መንግስት እናቋቁማለን “ ስላሉት አካላት መልስ ሲሰጡ” ከጀመርንበት ኮርስ አውጥተው ወደ ደም መፋሰስ ይከተናል፣ ያ አስከፊ ደም መፋሰስ እንዳይመጣ” ካሉ በኋላ ይህ ነገር ቢሞከር ያላቸውን ጦር እንደሚመዙና ድምጥማጣቸውን እንደሚያጠፉ በገደምዳሜ ሳይሆን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ያለ ወትሯቸው ጠቅላዩ ፣ ይሄንን ጉዳይ ሲናገሩ በሓይልና በስልጣን ነው፡፡ ደማቸው ሲንተከተክ ይታያል፡፡  እኔን የገረመኝ፣ ጠቅላዩ እንዲህ የሚነዝራቸውና የሚያስቆጣቸው፣ መዓት አውርድ ጦሬን ልኬ ፈጃችኋለሁ የሚያሰኛቸው ስልጣናቸውን የሚገዳደር ሲመጣ ብቻ ነው እንዴ? ምነው ይሄ ቁርጠኝነት ሻሸመኔ ፣ አርሲ ነገሌ እና አካባቢዎቹ ሲወድሙና ሕዝብ ሲያልቅ  አልታየም? ምነው ይሄን ቁጣ እነ አጣዬና ካራቆሬ ሲወድሙ አይተነው ቢሆን?  መከላከያ ሰራዊት ታላቅ ርምጃ እንዲወስድ የሚታዘዘው ስልጣኖ ላይ ለሚመጡ ብቻ ነው? የአብይ ስልጣን መከላከያ ወይስ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ነው? ሕዝብ ሲያልቅ፣ በግፍ ንብረቱ እየተዘረፈና እየወደመ ሲፈናቀል፣ ከተሞች ከነ ሙሉ ንብረታቸው ሲጋዩ ይሄን ርምጃ ወስደው ቢሆን ኖሮ እኮ ፣ እንዲህ ፎክረው ጦሮን አዘው ቢሆን ኖሮ እኮ ፣ ያለ ምርጫ ሕዝቡ ያነግሶ ነበር፡፡ ሻሸመኔ እኮ መንግስት የሌለባት ሶርያን ፣ አጣዬም ባግዳድ የመሰለ ውድመት ሲገጥማት ይሄ አለኝ ያሉት ጦር ምን ነክቶት ነበር? ስራው ሀገርን መከላከል አልነበረ? 
 
4. ጠቅላዩ ፣ሌላው በገደምዳሜ ያነሱት ነገር ፣ ስለ ሽመልስ አብዲሳና ታዬ ደን ደንደአ ነገር ነው፡፡ የክልል መሪዎችና ባለስልጣናት ስለሚናገሯቸው አላስፈላጊ የቃላት ካነሱ በኋላ “ ለሀገር ሲባል ስድብን ብንችልስ”  አይነት አስቂኝ ምክር መክረዋል፡፡ ምላሰ_ባለጌውን መገሰጹ ነው ሚሻለው ወይስ  “ተሳዳቢን ለሀገር ሲባል ቻሉት” ማለት? አፉን ማረም የማይችል ሰው እኮ መሪ የሚሆንበት ድርጅት ብልጽግና  ብቻ እኮ ነው፡፡ እነ ሽመልስ ፣ በየአደባባዩ የሚያስታውኳቸው ቃላት እኮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር አይመጥኑም፡፡ የነታዬ ቅርሻት እኮ እጅግ አስጠያፊ ነው፡፡ የመረጧቸው ባለስልጣናት እኮ ሕዝቡን የባለጌ ቃላት የሚያለማምዱ ግብረገብ የጎደላቸው ትንሾች እኮ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ አንደበታቸውንን መግራት ያቃታቸው ደፋሮችን እና ምላሰ ረጅሞችን መሪ አድርጎ ከመምረጥ፣ አንደበታቸው ለሕዝብ ፈውስ የሚሆኑ አስተዋዮችን መምረጡ አይቀል ይሆን? ይሄስ ድርጅቶንና የርሶን ተቀባይነት ምን ያህል እንደጎዳው ያውቁ ይሆን? አይመስለኝም፡፡
 

የታናሾ ምክር 

 
አብይ አህመድ፣ የርሶ መንግስት ሕዝብንና የሕዝብ ንብረትን መጠበቅ አልቻለም፡፡ በዘመነ መንግስቶ፣ ከተሞች ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ተፈናቅሏል፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው ግን በርሶ ያመራር ክፍተት  ነው፡፡ ህወሀት ላይ የወሰዱትን ቆራጥ ርምጃ ሸኔ ላይ ወስደውት ቢሆን ይሄ ሁሉ ባልመጣ! አብዲ ኢሌ ላይ ይወሰዱትን ፈጣን ምት ሸኔ ላይ አሳርፈውት ቢሆን፣ መንግስቶ ይሄ ኪሳራ ባልገጠመው፡፡ ወላይታ ላይ እኮ ታንክ ነው ያዘመቱት፡፡ ሸኔ ላይ እጆን ምን ያዘው? የሚጠብቀኝ የናቶች ጸሎት ነው ያሉት መሪ፣ ይሄ ሁሉ የኢትዮጵያ እናቶሽ ሲያለቅሱ ምነው እንባቸውን ማየት ተሳነዎ? 
 የሕዝብ ጠላት ላይ እርምጃ ወስደው ሕዝብን በሰላም ማስተዳደር ያቃተዎ ራሶ ኖት፡፡ እንደ ሀገር መሪ Monopoly of violence እጅዎ ላይ ነው፡፡ ሕዝቡ የተቆጣውና የተማረረው በምንድነው? በሞትና በመፈናቀል አይደለምን? ይሄን ማስቆም ሳይችሉ ለምን ሕዝቡን ይራገማሉ፡፡
 
ዓብይ አህመድ፣ ህወሀትን የመሰለ መሰሪ እባብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ አውርደውና ጭንቅላቱን ቀጥቅጠው በመግደል ሁሌም ትውልድ ሲያነሳው የሚኖር ታላቅና አንጸባራቂ ታሪክን ሰርተዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አይነት ስንክሳሯ የበዛ ሀገርም መምራት ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ታሪካዊ ጠላቶቻችንም የውስጥ ባንዳዎችን ታከው ሀገር ለማፍረስ እየጣሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስልጣን ላይ የመጡበት ግዜ እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ ችግር ሕዝብ ይረዳዋል፡፡ ግን ሕዝብ በሰላም የመኖር መብት አጥቶ እንዴት እንዲደግፎት ይፈልጋሉ? ማንን ሊያስተዳድሩ? በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ፣ ፀርፎ፣ ተዋርዶ፣ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ ነው፡፡ ከተሞች እየነደዱ ነው፡፡ ሕዝብ እያለቀ ነው፡፡ የመሪ ዋነኛ ስራ ደግሞ ይሄንን ማስቆም ነበር፡፡you failed on the very task you were supposed to do. 
 
Anger is building up. Empty bravado and laughable press briefings won’t cure the wound. Peace and security first.
Filed in: Amharic