>
5:18 pm - Friday June 15, 4277

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ !

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ !

አብን ሕዝባችን በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ኹለገብ የማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ በየቦታው ተደራጅቶ እንዲመክርና ወሳኝ አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጥ ለማሳሰብ ይወዳል!
*****
ለተከበራችሁ አገርና ወገን ወዳድ ኢትዮጵያውያን፤
ለተከበርከው የአማራ ሕዝብ፤
በአሁኑ ጊዜ ሕዝባችን የሚቃጡበትን ዘር ተኮር ጅምላ ፍጅቶች በቀጥታ የፈፀሙበትን፣ ያመቻቹትን፣ የተመሳጠሩትን እንዲሁም በስሙ ወንበር ላይ ተቀምጠው ጥቃት ሲከፈትበት፣ አጋዥ ታዛዥና ታዳሚ የሆኑትን አካላት በቅጡ ለይቶና ተገንዝቦ የተሳኩ የማውገዝና የማጋለጥ ሰላማዊ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል።
ሕዝባችን በተለይ ዘር ተኮር ጥቃቶቹ በሁሉም አማራ ደጅ ላይ መድረሳቸውን ተገንዝቦ የኅልውና አደጋውን ለመቀልበስና ፍትኅ ለመጠየቅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህ ረገድ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እና በውጭ አገራት ሰፊ የማጋለጥና የተቃውሞ ሰልፎችን እያካሄደ ይገኛል።
የተካሄዱት ሰልፎች ሰላማዊ ሲሆኑ ለቁስም ይሁን ለሰው ክብር የሰጡና ጥበቃ ያደረጉ መሆናቸውን ተገንዝበናል። በዚህ ኺደት የሚፈፀሙት የዘር ፍጅቶች ቅንጣት ስሜት የማይሰጣቸው አካላት ሕዝቡ ጠፍቶ ስለሚቆናጠጡት ስልጣን መርጋት ብቻ እንደሚጨነቁ በግልፅ ለመገንዘብ ተችሏል።
በመሰረቱ የአማራ ሕዝብ የሚፈፀምበት የዘር ፍጅት፣ የአፈፃፀሙ ዘግናኝነትና የቀብር ሥርዓቱን በማስተዋል ጉዳዩ ለሁሉም የአማራ ተወላጅ(በአማራ ስም የስልጣን ወንበር ለተቆናጠጡ አካላት ጭምር) ቅርብ፣ አሳዛኝ እና አዋራጅ እንደሆነ ሊሳት አይችልም።
በአማራ ሕዝብ ስም ሥልጣን የተቆናጠጠው ሥርዓት የመረጥነው ሳይሆን ቀንደኛ ጠላቶቻችን በስማችን ቀርፀው የጫኑብን በመሆኑ የሚነሱትን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመረዳትም ይሁን ለመፍታት ፍላጎትና አቅም እንደሌለው እናውቃለን። አብንን ጨምሮ የአማራ ልጆች በዚህ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ ትግል ለማድረግ የተገደዱት ያደረና ያልተሰራ ጉልህ አማራዊ የቤት ሥራ በመኖሩ ነው።
ስለሆነም፦
1/ መንግስት ሕዝባችን የዘር ጥቃቶቹን በይፋ መቃወሙን ተከትሎ እንኳ የለመዱትን የይስሙላ መሐላ ማድረግ በመተው የቃላት ስንጠቃና ፍረጃ ውስጥ መግባቱ ተስተውሏል። በርግጥ መንግስት የአማራው መጠቃት የሚገደው፣ ከጽንፈኛው ጎራ የተለየና ሕዝቡን ለመታደግ ፍላጎት ያለው ቢሆን ኖሮ የሕዝቡን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በድጋፍነት ሊወስደው ይገባ ነበር።
2/ የአማራ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች የሰላም፣ የደኅንነትና የኅልውና መሆናቸው እየታወቀ ዘወትር በእዝነኅሌናቸው የያዙትን የጥሬ ሥልጣን አጀንዳ ሲያደርጉ ተመልክተናል። የመንግስት ሥልጣን ስለሚያዝበት የዴሞክራሲ አግባብ በተመለከተ ለአማራ ሕዝብም ይሁን ለአብን የሚሰጥ ተጨማሪ ትምህርት እንደሌለ መዘንጋታቸው ማንነታቸውን በደንብ ያሳያል።
3/ የአማራ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ላቀረባቸው ጥያቄዎች በመንግስት በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ ምላሽ የለም። አሁንም ሕዝቡን ለመተቸት፣ ለማስፈራራት፣ አጀንዳ ለማስቀየርና አለፍ ሲልም ደካማ የሞራል ትምህርት ለመስጠት ጥረት ሲደረግ አስተውለናል።
4/ ንቅናቄያችን አብን ሕዝባችን መንግስት እንደሌለው ተገንዝቦ ራሱን እንዲከላከል በይፋ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል። ተቃውሞዎቹ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወኑ አብን ተከታታይ ምክረ ኃሳቦችንና ማሳሰቢያዎችን ሲሰጥ መቆየቱ አይዘነጋም። የተቃውሞውን ድምጽ በርካታ የፖለቲካ ፖርቲዎችም በግልፅ እንደደገፉት ተረጋግጧል።
ሰልፎች ሰላማዊነትን ብቻ ጠብቀው እንዲሄዱና የሕዝቡን ጩኸት ቅቡልነት የማያሳጡ መልዕክቶች እንዲስተጋቡ አብን ሲያሳስብ ቆይቷል።
ሆኖም ገዥው ፖርቲ:-
ሀ/ መጣራት የሚገባቸውን አንዳንድ ጥቃቅን ችግሮች በመጥቀስ ሕዝቡ ያካሄዳቸው ሰላማዊ ሰልፎች መገለጫ በማድረግ ለማጠልሸት ያደረገው ሙከራ ለሕዝባችን ያለውን የቆየ ጥላቻና ንቀት የሚያሳይና ስህተት የሆነ አቋም መሆኑን፣
ለ/ የሕዝባችንን ጥያቄዎች በአግባቡ አድምጦ መልስ ከመሻት ይልቅ “መንግስታዊ ሰርጎ ገብነትን” በመተግበር ጥቃቅን ችግሮችን ነቅሶ ለማጉላት ሲባዝን መታየቱ፣
ሐ/ በአገራችን ውስጥ በሌላ ቦታዎች የተደረጉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ስንመለከት በንብረት፣ በግለሰቦችንና በሕዝብ ላይ ስጋት፣ ጥቃትና ውድመት አስከትለው መንግስት የሰጠው መልስ “የተበሳጩ ወጣቶች በመሆናቸው መታገስ ይገባል” ማለቱና ከሰማንያ ስድስት በላይ ንፁሃን ወገኖቻችን በአንድ ጀምበር የተጨፈጨፉበትን አጋጣሚ በተመለከተ የነበረው የመንግስት አቋም በጥቅሉ ሲታዩ የመንግስትን ሚዛን አልባነት በግልፅ ያሳያሉ።
እስካሁን ሕዝባችን ያደረጋቸው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች የአማራን ሕዝብ አንድነት፣ ግብረገብነትና ሰላማዊነት በማያወላዳ መልኩ በማረጋገጥ የጠላትን ቅስም የሰበሩ ናቸው። በተጨማሪ የአማራ ሕዝብ የተጋረጠበትን አደጋ ግዝፈትና ምንጮች የተረዳ መሆኑን አሳይቷል።
የተቃውሞ ሰልፎቹ ሰላማዊና ስልጡን ሆነው በመካሄዳቸው አብን አድናቆቱን እየገለፀ ለመላው ሕዝባችን ዛሬም የከበረ ምስጋናውን ያቀርባል።
ሕዝባችን በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ኹለገብ የማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ በየቦታው ተደራጅቶ እንዲመክርና ወሳኝ አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጥ ለማሳሰብ እንወዳለን።
በመጨረሻም ጽንፈኛው ኃይል የአማራን ሕዝብ የሰላም፣ የደኅንነትና የዴሞክራሲ ምኅዳር ለማጥበብ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አድማሱን ማስፋቱ፣ ሥርዓቱም የዚህ አሻጥር አካል መሆኑን መነሻ በማድረግ ሕዝባችንን ያለወኪል በማስቀረት አሁኑን ብቻ ሳይሆን ነገውንም ለማጨለም የሚደረገውን ሴራ በመረዳት፣ የአማራ ሕዝብ ተሳትፎ ማነስ የዘረኝነትና የጭቆና ቀንበር ለመጫን ፍላጎት ላላቸው ኃይሎች ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን በመገንዘብ በምርጫው አጠቃላይ ኺደት ላይ ወጥ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግምገማ ተደርጎ አቋም እስኪወሰድ ድረስ ሕዝባችን በነቂስ ወጥቶ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ ለማሳሰብ እንወዳለን። ችግራችን መዋቅራዊና ሥርዓት ሰራሽ በመሆኑ በተቻለ መጠን ሕዝባችን የማያወላዳ የፖለቲካ ውክልና እንዲኖረው ታሪካዊ ርብርብ ማድረግ ይገባል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካላት አብን ከ2013 ምርጫ ራሱን እንዳገለለ ተደርጎ የሚናፈሱ አሉባልታዎች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን ዛሬም በድጋሜ ይገልፃል።
እጣፈንታችንን በራሳችን እጆች እንጽፋለን!
Filed in: Amharic