>

ለምርጫ አመቺ ሁኔታ አለ? ሀገራዊ የፖለቲካ ኩነቶች ቅኝት (አሰፋ ሀይሉ)

ለምርጫ አመቺ ሁኔታ አለ?

ሀገራዊ የፖለቲካ ኩነቶች ቅኝት

አሰፋ ሀይሉ

የኢዜማ ፓርቲ የቅርንጫፍ አመራሮች የሆኑ ሁለት የምርጫ ተወዳዳሪዎች በተለያየ ጊዜ በደብረዘይትና በጉሙዝ ገና ምርጫው ሳይጀመር በጥይት ተገድለው ከምርጫው በሞት ተሰናብተዋል፡፡ የአብን የመተማ ዞን አመራርም በተተኮሰበት ጥይት መገደሉ በሰሞኑ ከተሰሙ አሳዛኝ ዜናዎች አንዱ ነው፡፡ ‹‹ከተሰሙ›› ያልኩት ከፓርቲው ስለ አባሉ ሞት የተሰጠ መግለጫ ስላላየሁ ነው፡፡
ጦርነቱ በሶስት ሳምንት መጠናቀቁ ከተነገረ በኋላ በየሳምንቱ የመደምሰስ ዜና ወደሚታወጅበት ወደ ትግራይ ስንሻገር ደሞ እስካሁን ጦርነቱ አልበረደም፣ ምርጫ የሚባል ነገር የለም፡፡ የዓለማቀፍ ሰብዓዊ ተቋማትና ሀያላን መንግሥታትና አካባቢያዊ ማህበሮቻቸው በትግራይ ዓለማቀፍ ገለልተኛ አጣሪዎች እንዲገቡና አሉ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና የጦር ወንጀሎችን እንዲያጣሩ ደጋግመው እየጠየቁ ነው፡፡ በአስመራ የአሜሪካ ኤምባሲ ትናንት ባወጣው መግለጫ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዳልወጣ በማሳሰብ፣ በአብይ አህመድ በተነገረው መሠረት ጦሩን እንዲያስወጣ አሳስቧል፡፡
በአብይ አህመድ በኩል አያዎ (አይ እና አዎ) የሆነ ምላሽ እየተቸረው፣ ንትርኩም ጦርነቱም ቀጥሏል፡፡ በትግራዩ ጦርነት የተነሳ አዋሳኝ የአማራ ሕዝብ የሚኖርባቸው አካባቢዎች ሁሉ የስጋት ቀጠናዎች መሆናቸው አልቀረም፡፡ የአማራ የፀጥታ ሀይል በሰሜኑ ጦርነት ተሰማርቶ፣ የአማራ ህዝብና ክልል ለአሸባሪዎች ጥቃት በቀላሉ ተጋላጭ ሆኗል፡፡
በዓለማቀፉና ሀያላኑ ጫና የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ከወጣና፣ ሰፊ የትግራይ ህዝብ ድጋፍ እንዳለው የሚታወቀው የወያኔ ሀይል መልሶ ካንሰራራ በአማራ ሕዝብና በብአዴን (በአማራው ብልጽግና) ላይ የሚደቅና የህልውና ፈተናና አጣብቂኝ ሲታይ – የኤርትራ ጦር መውጣትና አለመውጣት፣ የአማራን ህዝብ ደህንነት ሙሉ በሙሉ በአብይ አህመድ (እና በኦሮሚያ ብልጽግና) መዳፍ ላይ የሚጥል አስጊና አሳሳቢ ክስተት መሆኑን ሁኔታውን ያስተዋለ ሁሉ የሚረዳው ከፊታችን ያፈጠጠ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በመተማ በኩል ከመቶ ኪሎሜትሮች በላይ የሚሆን የኢትዮጰያ ድንበር በሱዳን ሠራዊት የተወረረ መሆኑም እና የአብይ አህመድ ‹‹ለመሬት አንዋጋም›› ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ የመከላከያ ሠራዊት እወጃ ሲታይ፣ የአማራው ሕዝብ በሁሉም አቅጣጫዎች ‹‹ራሱን እንዲያድን›› የተተወና ከባድ የውጭና የውስጥ የህልውና አደጋ እንደተደቀነበት ለማንም ተመልካች ግልጽ ሆኗል፡፡
የሶማሊ ክልል የምርጫ ክልሎች ተወስደውበት ወደ አፋር መካተታቸውን በመቃወም ያቀረበው ቅድመ-ሁኔታ ካልተሟላለት ከምርጫው ራሱን እንደሚያገል ያስታወቀው የእነ ሙስጠፌ ፓርቲ ከምርጫው የመውጣት መብት እንደሌለው በምርጫ-ቦርድና በመንግሥት ከፍተኛ ማስፈራሪያ ደርሶታል፡፡ እስከምናውቀው የምርጫ ህጉ በግድ ተወዳደር የሚል አይመስለኝም፣ ብልጽግና በህገመንግሥትና በአዋጅ ያልተገደበ የዜጎች መብትን በውስጥ ቀላጤ ሊያፍን እንደሆነ ውጤቱን የምናየው ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ብዙዎቹ ቦታዎች እንኳን ሰው የፈለገውን የሚመርጥበትና ተመራጭ የፈለገውን ሃሳብ አስተዋውቆ የሚመረጥበት አመቺ ሁኔታ ሊፈጠር ይቅርና፣ ነዋሪውም ዛሬን አድሮ ለነገ በህይወት ይትረፍ አይትረፍ እርግጠኛ ያልሆነበት የሞት አደጋ ያንዣበበት ክልል ከሆነ ቆይቷል፡፡ ሁሉም የተቃዋሚ ጎራ የሚባሉ ፓርቲዎች በኦሮሚያ ክልል በነፃ ለመወዳደር እክል እንደገጠማቸው ደግመው ደጋግመው ለህዝብ አሳውቀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የኦነግ (ሸኔ) ሠራዊት ቀን ለቀን መከረኛውን ህዝብ እየሰበሰበ በየጫካውና በየቀበሌው ኦሪየንቴሽን ሲሰጥ የሚያሳዩ በርካታ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች በማህበራዊ ሚዲያ እየተሠራጩ ነው፡፡ ክልሉንና ሀገሪቱን ይጠብቃል በሚል ሰበብ ከሰሜኑ ውጊያ እንዲርቅ የተደረገው የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ከኦነግ ሸኔ ሀይሎች ጋር በመተባበር ከወለጋ የአማራ ተወላጆች ላይ ሰብዓዊ ጥቃትና ማፈናቀሎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ብዙ የጥቃቱ ሰለባዎች እማኝነታቸውን እያቀረቡ የሚገኙበት አስደንጋጭ ጊዜ ላይ ነን፡፡
በሐረር የሐረሪ ክልልና የኦሮሚያ ብልጽግና የሚያካሂዱት ቀሪውን የከተማውን ነዋሪ ያገለለ የአደሬ-ኦሮሞ አፓርታይዳዊ ምርጫ ከዕቃ-ዕቃ ጨዋታ የተሻገረ እንዳልሆነ ብዙዎች በሚገልጹበትና፣ የአደሬው ክልል ራሱ ዙሪያውንና ከተማውንም በተቆጣጠረው በኦሮሚያ ብልጽግና የመሰልቀጥ አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ በሚስተዋልበት በዚህ ወቅት የይስሙላው ምርጫ ጉድጉድ እንደቀጠለ ነው፡፡
በየትኛውም ዓለም ተደርጎ በማይታወቅ መልክ – በሚሊየን የሚቆጠሩ መራጮችንና በርካታ ፓርቲዎችን የያዘው የአዲስ አበባ የምርጫ ክልል – ቀሪው የሀገሪቱ ክፍል ምርጫ ካካሄደ ከሣምንት በኋላ ምርጫ እንደሚደረግበት የምርጫ ቦርድና በፊንፊኔ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስታውቀዋል፡፡ ይህ በሀገሪቱም በዓለምም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የምርጫ አሬንጅመንት ብዙዎችን ግራ ያጋባ ከመሆኑም በላይ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሞ ብልጽግናና በአንዳንድ የኦሮሞ አሸባሪ ድርጅቶች አማካይነት የሚደረጉ አስፈሪ ሥጋትን በነዋሪዎች ላይ የሚደቅኑ እንቅስቃሴዎችና ዝግጅቶች መኖራቸውን ፍንጭ የሚሰጡ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
በአጠቃላይ በመላ ሀገሪቱ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሊና ከኦሮሚያ በሚዋሰኑ የአማራ አካባቢዎች ከባባድ የሰው ግድያዎች፣ የታጠቁ ሰራዊቶች የሚያካሂዷቸው ግጭቶች፣ የሰው ስቃዮች፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀሎች፣ የሰው ልጅ ጅምላ ፍጅቶች፣ የከተሞች በኦነግ ሸኔ ጦርሠራዊት በቁጥጥር ሥር መዋል፣ መንደድ፣ የመንገዶች መሰበር፣ የባንኮች በጠራራ ፀሐይ መዘረፍ፣ የንብረት መውደም፣ አጠቃላይ የዜጎች የደህንነት ዋስትና ማጣት የዕለት ተዕለት ክስተት ከሆኑ ሰነባብቷል፡፡ ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ አጠቃላይ ሀገሪቱ ወደ አስፈሪ ሥርዓት አልባነት ደረጃ እንዳትሸጋገር የሚሠጉ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
በጠራራ ፀሐይ 22ሺህ የአዲሳባ ነዋሪዎችን ኮንዶሚኒየም ለኦሮሚያ ገበሬዎች ሰጠሁ በማለት እንዳከፋፈለው፣ የአብይ አህመድ አስተዳደር በየጊዜው የሚወስዳቸው አድሏዊ የተረኝነት እርምጃዎች፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ መብትና ጥቅም፣ የሀገሪቱን አጠቃላይ ደህንነትና የጋራ ብልጽግና ከሚያረጋግጡ ግልጽ የሀገር አስተዳደርና የልማት አቅጣጫዎች ይልቅ፣ የፖለቲካ አሰላለፍን መሠረት ያደረጉ፣ የአንድ ወገን የፖለቲካ ትርፍን ታሳቢ ያደረጉና፣ ተረኝነትን ለዘለቄታው ለማስቀጠል የታለሙ ዓይን ያወጡ መንግሥታዊ ድጋፍ የተቸራቸው እንቅስቃሴዎች – በተለይ በአማራው ህዝብና በአማራ ብልጽግና እንዲሁም በሌሎችም የሀገሪቱ ሕዝቦች ዘንድ በኦሮሙማ በሚዘወረው መንግሥት ላይ ከፍተኛ ቅሬታና ጥርጣሬን እንዲያሳድሩ አድርጓቸዋል፡፡
ከወራት በፊት በአዲስ አበባ የሚገኙ የአማራ ብልጽግና ተወካዮች በኦሮሙማው ስለሚደረገው የሥልጣን ጥቅለላ ሩጫ ያወጡት መግለጫ፣ የኢዜማ ፓርቲ የመግለጫ መስጫና የስብሰባ ክልከላ፣ የአባላት እስርና መዋከብ፣ የባልደራስ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እስርና እንግልት፣ በየጊዜው በፓርቲው ላይ የሚፈጸመው ወከባና መተንፈሻ ሥፍራ መንፈግ፣ በአብን አመራሮች ላይ የተካሄደው እስርና መለቀቅ፣ እንዲሁም በአባላቱ ላይ የሚፈጸመው ወከባ፣ ሥም ማጥፋትና መንግሥታዊ የአደባባይ ውንጀላ፣ በወያኔ ዘመን ከሚደረገው በባሰ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ብዙዎች የሚመሰክሩት መራር እውነት ሆኗል፡፡
በርካታ የኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሀይሎች ከምርጫው ራሳቸውን ማግለል፣ በመንግሥት አባሎቻቸው እንደሚታደኑባቸው፣ እንደሚታሰሩና እንደሚገደሉ በተለያዩ ጊዜያት ለሕዝብ ይፋ ያደረጉባቸው መግለጫዎች፣ መንግሥትን በአደባባይ ያብጠለጠሉ ግለሰቦችን (እንደ ልደቱ አያሌው) ማሳደድና ከሀገር እንዳይወጡ ማገት፣ በፈጠራ ክስ ማሠር፣ በፍርድቤቶች ያለፍርድ በቀጠሮ ማመላለስ፣ እነዚህ ሁሉ በአሁኗ የለውጥ ዘመን መምጣቱን በምትለፍፈዋ ኢትዮጵያ በየዕለቱ እየተከናወኑ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ያሳሰቡና ያሸማቀቁ ክስተቶች ናቸው፡፡
በአጠቃላይ አብይ አህመድ አንዲት ደም ሳትፈስ በመደመር መንገድ ወደ ለውጥ አሻግራችኋለው ምኞቶችና ተስፋዎች ሁሉ ከስመዋል፡፡ አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ ሙጥኝ ብሎ ለመያዝ የተገደደው የአብይ አህመድን ረጋ-ሠራሽ መንግሥት ተቃውሜ ምንነቱን የማላውቀው ምናልባትም የባሰ መከራ ከሚመጣብኝ ያለውን ይዤ ልሰንብት የሚል የባጣ ቆዪኝ ቀቢፀ-ተስፋን ብቻ ነው፡፡ ባልተረጋጋች ሀገር የሚካሄዱ የሀገር ውስጥና የውጪ ቀጥታ ኢንቬስትመንቶች ሁሉ ተሽመድምደዋል፡፡
የአብይ አህመድ መንግሥት ትኩረቱን በተረኝነት ስልቀጣ ስትራቴጂዎችና ሩጫዎች ላይ እስካሰማራና፣ የሀገሪቱን ህዝብ ደህንነትና ፀጥታ በማስከበር ላይ ትኩረቱን አድርጎ ካልሠራ፣ የኦሮሙማውን ከልካይ ያጣ መንግሥት የሀይል ሚዛን ሊገዳደር የሚችል ቼክ ኤንድ ባላንስ የሚያደርግ መንግሥታዊ ሂደት ካልተፈጠረ በቀር – በዚህ ዓይነት ጉዞ ኢኮኖሚውም፣ ፖለቲካውም፣ የሀገርና የህዝብ ደህንነትም እንዘጭ ብሎ የሚወድቅበት ጊዜ እንዳይመጣ የብዙዎች ሥጋት ነው፡፡
ቀድሞ ወዳጅ ከነበሩ ሀያላን ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት ሻክሯል፡፡ ከአረብ ሀገራት እስርቤቶች ውስጥ የታሠሩ ኢትዮጵያውያንን በኢትዮጵያ አየርመንገድ አየጫኑ በማምጣት የተጀመረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የነጻ አውጪነት አይድል ሾው አብቅቶ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በበርካታ የአረብ አገራት (ሌላ ቀርቶ ተስፋ በሌላት በየመን) አስከፊ አያያዝ በሚስተናገደባቸው እስር ቤቶች እየማቀቁ፣ እየተጋዙ፣ እና እየሞቱ ይገኛሉ፡፡ በሀገር ውስጥ በብሔሮች መካከል ያሉ መተማመኖችና የጋራ ዘልማዶች እንዲበጣጠሱና አንዱ ብሔር ከሌላው ብሔር ጋር በጥርጣሬ እንዲተያይ፣ በለውጥ ስም በተቀደደው ቦይ በመግባት ክልልነት ይገባናል የሚሉ የተለያዩ ማህበረሰቦች ሀይሎች እንዲፈስሱና በየቦታው ከዚህ በፊት ያልነበሩ ውጥረቶች እንዲከሰቱ ሆነዋል፡፡
በአጠቃላይ ‹‹ለውጥ›› መጥቶባቸዋል የተባሉት ያለፉት ሶስት ዓመታት ከወያኔ-ኢህአዴግ ዘመኑ የ27 ዓመት የዘረኝነት አስተዳደር ምንም ያልተለዩ፣ እና እንዲያውም እጅግ አስፈሪ የደህንነትና ጸጥታ ስጋቶች፣ ጦርነቶች፣ ሞቶች፣ መፈናቀሎች፣ እና ያፈጠጡና ሕዝብን የናቁ የተረኝነት አካሄዶች የሰፈኑበት – ለኢትዮጵያውያን በሥርዓቱ ላይ ያላቸውን የመጨረሻ እንጥፍጣፊ ተስፋ እየተሟጠጠ የመጣበት ወቅት ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወዳጅነትን ያመጣል የተባለው ምንነቱ የማይታወቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፖሊሲ የጎረቤት ሀገሮችን በሙሉ በጠላትነት በማሰለፍ ተጠናቋል፡፡
ሲጠቃለል – ለውጡ ከሽፏል፡፡ የአብይ አህመድ አመራር ሀገሪቱን ወደተገባላት ተስፋ ሊያሻግራት አልቻለም፡፡ በመነሻው ላይ የተስተዋለውን የሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብና የውጪውን ዓለም ድጋፍ ይዞ ሀገሪቱንና ህዝቧን ወደተሻለ ለውጥ፣ ወደ ተሻለ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ወደ ተሻለ ተስፋ የማሻገር ዕድሉና አቅሙም ከሽፏል፡፡ ከዚያ ይልቅ የአብይ አህመድ አስተዳደር አንድ ጊዜ የሐይማኖት ጎራዎችን እንደ ሥልጣን ማደላደላደያ ስልት ለመቆመር በመሞከር፣ በሌላ ጊዜ እልም ወዳለ የተረኛ ገዢነት ሩጫ በመንቦጫረቅ – ሀገሪቱም ህዝቧም የጣሉበትን የለውጥ ተስፋ አምክኖታል፡፡ ሁሉም ነገር እስክንድር ነጋ እንዳለው ሆኖ ተጠናቋል፡፡ ለውጥ የለም፡፡ ተረኝነት ግን አለ፡፡
ከዚህ በኋላ – እና በዚህ ዓይነት ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ ምርጫ – ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዳለው – እንኳን ምርጫ ለመባል፣ ቅርጫ ለመባል ራሱ አይበቃም፡፡ ሀገሪቱ በዚህ ዓይነት ዘርፈ ብዙ ፀረ-ዲሞክራሲ መስተጋብሮች ውስጥ በተዘፈቀችበት፣ መንግሥት በግዛቱ ሁሉ ላይ ኢፌክቲቭ ኮንትሮል ባላሰፈነበት፣ የህዝቡ ሠላምና ነጻ ሆኖ ሀሳብን የመግለጽና የማደራጀት መብቱ ባልተረጋገጠበትና በማይረጋገጥበት፣ በታጣቂ ጎሰኛ ሀይሎች ተፅዕኖና ቁጥጥር ሥር በዋለ ሀገር ውስጥ፣ እና እንደ ሁልጊዜው አቅሙ የተልፈሰፈሰ የምርጫ ቦርድ ያለአቅሙ ምርጫ አድርጋለሁ ብሎ በሚንጠራወዝበት በዚህ ወቅት – ነጻ፣ ፍትሃዊና፣ እውነተኛና ተዓማኒ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ብቻ ሳይሆን፣ ነገሮችን በተገቢው መልክ የማመዛዘን ተፈጥሯችንንም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት ይህንኑም የይስሙላ (የጨረባ) ምርጫም ቢሆን እንዲታዘብ ጥሪ የቀረበለት የአውሮፓ ህብረት የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ታዛቦ,ቢዎችን ለመላክ አያስችለኝም ብሎ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ታዝቦ ተጭበርብሯል ያለውን የ97 ምርጫ ተከትሎ ሀያላን መንግሥታትና ራሱ የአውሮፓ ህብረት ጭምር የወያኔን መንግሥት ‹‹በሕዝብ የተመረጠ ዲሞክራሲያዊ›› መንግሥት እያሉ ማቆለጳጰሳቸውንና መሞዳሞዳቸውን እንዳላስቀረ የሚታወስ ነው፡፡
ያንን አሳዛኝ ተሞክሮ ያስተዋለ፣ በዚህ ምርጫ ታዘቡም አልታዘቡም፣ የምርጫውን ጨረባነት አጋለጡም አድበሰበሱም – የሀገሪቱን ፖለቲካ ምስቅልቅሉን ባወጣ ተረኛ አምባገነን ሀይል በምትታመስ ሀገር ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ከስም በስተቀር የሚያመጣው የተለየ ፋይዳ እንደሌለ ማንም ህሊና ያለው ሰው ሊክደው የማይችል ሀቅ ነው፡፡
ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳዝነው ነገር ምርጫ ቢካሄድም፣ ምርጫ ባይካሄድም – ራሱን ብልጽግና ብሎ የሰየመው ተረኛ ዘውጌ ገዢ – በሁለቱም ቢላዋ ቁማሩን በልቶ በሥልጣን ላይ ለመቀጠል ምሎ የቆረበ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ – ወተት ነጭ ነው፣ ከሰል ጥቁር ነው ከሚለው በበለጠ – የመሆኑ ጥርሱን ያገጠጠ እውነታ ሲታሰብ ነው፡፡ ምርጫው ቢካሄድም ብልጽግና አሸነፍኩ ብሎ በወረሰው ሥልጣን ሊቀጥል የ40 ዓመት ሸፍጦቹን ሲደልቅ ነው የከረመው፡፡ ምርጫው ባይካሄድም እስኪካሄድ ብሎ በሥልጣኑ ለመሰንበት አይኑን አያሽም፡፡
በሁለት ቢላዋ እየከተፉ – በዚህም በዚያም ሥልጣኑ ላይ ሞቼ እገኛለሁ የሚለው ተረኝነት የወለደው የቃልም የድርጊትም አካሄድ መጨረሻው በምን እንደሚደመደም የሚታወቅ ይመስለኛል፡፡ ሁልጊዜም ሀቅን የያዘውና የዘረኞች የፈረቃ አገዛዝ የመረረው ሕዝብ አሸናፊ መሆኑ አይቀርም፡፡ እስኪያልፍ ግን ያለፋል፡፡ ያ ነው ካለው መከራችን ላይ የሚጠብቀን የወደፊት መከራው፡፡
ቅኝቱን ልደመድም ስል የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አባባል ዳግመኛ ታወሰኝ፡፡ ፈረቃ አለ፡፡ ለውጥ ግን የለም፡፡ ለነገሩ የሰማቸው አልነበረም እንጂ እነሱስ መች ‹‹ለውጥ›› ብለው ተነሱ? ‹‹ሪፎርም›› (‹‹እድሳት››) ብለው ነበር የተነሱት፡፡ እኔ ደግሞ እንዲህ ብዬ እሰናበታለሁ፡፡ እድሳት የለም፡፡ ለውጥም የለም፡፡ መድረቅ ብቻ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይጠብቅ፡፡ ሕዝባችንን ይባርክ፡፡
አበቃሁ፡፡
____________________________________________
ተጨማሪ ሀሳቦችን ለማግኘት፣ የሚከተሉትን የYouTube ሊንኮች ይጫኑ:-
Filed in: Amharic