>

በቃን...!!! (ጎዳና ያዕቆብ) 

በቃን…!!!

 ጎዳና ያዕቆብ 

ከሰሞኑ በሚደረገው ሕዝባዊ ንቅናቄ አብይ አህመድና አገዛዙ በአምስቱ የሐዘን ደረጃዎች ላይ በማለፍ ላይ ይመስላል:: የመጀመሪያውን ደረጃ ያም denial (ክህደት: አለማመንን) የሕዝንብ የሰብአዊ መብትን: በሕይወት የመኖር መብትን ክዶ የሕዝብን ድምፅ የስልጣን ጥያቄ አድርጎ አቅርቦታል:: ወደ ሁለተኛ የሀዘን እርከን በፍጥነት ተሸጋግሮ መግደል ያደግንበት ነውና የረሳነው አታስታውሱን ሲል ደም ለማፍሰስ ያለውን ቁርጠኝነት በግልፅ አሳይቷል::
ቢራቢሮ መስሎን እልል ያልንለት መሪ አባ ጨጓሬነቱን በገሀድ አሳይቷል::
ቁጣው እና ስልጣን ሊቀሙኝ ነው የሚለው ስጋት ረገብ ሲልለት ወደ ድርድር (bargaining) ይሸጋገራል የሚል እምነት ከአንድ ጤነኛ ሰው የሚጠበቅ ቢሆንም እንደአንዛኛው አምባገነኖች ሁሉ አብይ አህመድም ወደ ድርድር አልገባም:: ስልጣን ከኔ በኔ እና ለኔ የሚል እብሪት ውስጥ ከአሁኑ የገባ ይመስላል::
መንበሩ ሞቆታልና ወደ ድብርት (depression) ከዛም የሕዝብን ተፈጥሮአዊ የሆነውን በህይወት የመኖር መብት ለማክበር እና ይህንን እውነተ ወደ መቀበል (acceptance) መቼም በፍቃዱ አይመጣም:: ዝሆን ሚዳቋን ይሰብራል: ይገዛል: የበላል እንጂ ከሚዳቋ ጋር አይደራደርም የሚል አቋም ይዞ እንደሚፀና ግልፅ ይመስላል::
ሀገር ለማዳን: የሰሜን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ህልውና ለማስቀጠል: ለማስጠበቅም በመጀመሪያ በአማራ እና በትግራይ ማህበረሰብ መካከል ግኑኝነት መጠናከር ይኖርበታል::
ለዛም ጥሩ ጅምር የሚሆነው ዛሬ ትግራዋይ ላይ እየደረሰ ያለውን ይህ ነው የማይባል ግፍና ጭፍጨፋን እውቅና መስጠት ያስፈልጋል:: ሀዘንህ የኔም ሀዘን ነው:: የሚደፈሩ ሴቶች እህቶቼ: የሚንገላቱና በረሀብ መሳሪያ የሚደቆሱ እናቶች እናቶቼ ናቸው ማለት ያስፈልጋል:: በጅምላ የሚገደሉ ወጣቶች ደም ደሜ ነው ማለት ያስፈልጋል:: አንዱ የአንዱን ሀዘንና ሰቆቃ መጋራት ግድ ይላል:: ትግራዋዮችም በአማራ ማህበረስብ ላይ የሚደርሰን የዘር ማጥፋት ወንጀል ማውገዝ: መቃወምና አብሮ መቆም ያስፈልጋል::
የጥቃት ኢላማ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም የድርሻዋን ተወጥታ በጎቿን ማቀረረብ: ማወያየት: ማደራጀት ይጠበቅበታል:: በመላው ኢትዮጵያ ያሉትን ምእመናኖቿን ከብሄር አዙሪት ወጥተው ሰው መሆንን: ርህራሄና መቀራረብን ማምጣት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በአማኞቿ ልብ እና ማንነት ውስጥ ማስረፅ መቻል አለባት::
የሙስሊሙም አስተምሮት ከዚህ ጋር የሚጣጣም ነውና የድርሻቸውን መወጣት የሚያስፈልገን ወቅት ላይ ደርሰናል::
አንድ ወዳጄ እንዳለኝ ከጥላቻ ያለፈ ጤነኛ ትምህርት መስጠት አንገብጋቢ  የሀገር እና የዜጎች ደህንነት ጉዳይ ሆኖአል:: የህልውና ጉዳይ ሆኖአልና ሀገር አልባ ከመሆናችን በፊት ቆም ብለን ብናስብና ሕዝብ እንደ ሕዝብ በመደጋገፍ በአንድ ላይ መቆም: መተጋገዝ እና መተባበር ይኖርብናል:: በትግራይ ሴቶች: ወጣቶች እና እናቶች ላይ የደረሰ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በሁላችንም ላይ መድረሱ አይቀሬ ነው:: ነግ በኔ ማለት ጥሩ ነው::
ዛሬ ትግራዋይ ነው ምን አገባኝ ያልክ ሁሉ ሰቆቃው በደጅህ ሲያደባ የሚደርስልህ የሚጮህልህ አይኖርም:: ዛሬ አማራ ሲጨፈጨፍ ከኔ ህይወት ጋር ምን አገናኘው ያልክ ሁሉ ይህ እልቂት በአንተና በቤትህ ላይ መድረሱን ካሁን እርግጠኛ ሆነህ እወቀው:: ይሄ እሳት የማይበላው አንድም አይኖርም:: እንዳልኩት የወረፋ ጉዳይ ብቻ ነውና ለትግራይና ለትግራዋይ ጩህ:: ከአማራው ጋር ወጥተህ በቃን! በል:: እንዲህ አይነቱ ትብብር ከተኩላ መንግስት ዜጎችን ያድናል:: የሀገርን ህልውናም ይታደጋል::
ግፍ በቃን! መጨፍጨፍ በቃን! ረሀብን እንደመሳሪያ መጠቀም በቃን! መፈናቀል በቃን! ብለህ በጋራ ቁም አይ ካልክ ግን በተናጠል ለመበላት ተዘጋጅ::
Filed in: Amharic