>

ኢሕአዴግ ከዘረኛውና አረመኔው ዐቢይ ጋር ፍጻሜውን ያገኛል (ከይኄይስ እውነቱ)

ኢሕአዴግ ከዘረኛውና አረመኔው ዐቢይ ጋር ፍጻሜውን ያገኛል

ከይኄይስ እውነቱ


በዕድሜ ታናሽ በአስተሳሰብ ታላቅ የሆነ ወንድሜ አቻምየለህ ታምሩ ስለ ጀግናችን ጋሼ (ሻለቃ) ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ የጻፈውን አጭር ማስታወሻ አነበብኩና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ውስጤን ነዘረኝ፡፡ እኔም ከአቻሜ ጋር ሱታፌዬን ለመግለጽ ወደድሁ፡፡ ለልቤ የቀረቡኝንና በመንፈስ አባትና ታላቅ ወንድም የሚሆኑኝን ኢትዮጵያውያን ጋሼ የማለት ልምድ ስላለኝ ሻለቃ ዳዊትም ጋሼ ብየ ብጠራህ ቅር እንደማይልህ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አንተ ውስጥ የሚንቀለቀለው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ እምቢኝ!!! በቃኝ!!! ብሎ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን በጀመረው መላው የአምሐራ ሕዝብ ብሎም በቅርቡ የዚሁ ማዕበል አካል በሚሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እጥፍ ድርብ ሆኖ እንዲያድር እመኛለሁ እጸልያለሁ፡፡ 

አባቶቻችን ሊቃውንት ‹ኢይኀድጋ እግዚአብሔር ለሀገር ዘእንበለ አሐዱ ኄር› (እግዚአብሔር አምላክ አገርን ያለ አንድ በጎ/ደግ ሰው አይተዋትም እንደማለት) ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ጋሼ ዳዊት ያሉ ለአገራቸው ለሕዝባቸው የሚያስቡ የሚጨነቁ ሰዎች አሏት፡፡ እባካችሁ ጊዜው አሁን ነውና ወደ መጀመሪያው ረድፍ ብቅ ብላችሁ ከእግዚአብሔር ጋር አገራችሁንና ሕዝባችሁን ታደጉ፡፡ ላለፉት ሦስት ዐሥርታት ባገራችን የሰፈነው የጐሣ አገዛዝ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ በከተተበት ወቅት እንደ ጋሼ ዳዊት ያሉ ኢትዮጵያውያን አገራችንን ከአረመኔዎችና ከዘረኞች ለመታደግ ታላቅ የመንፈስ ብርታትና ተስፋ ነው የሚሰጠን፡፡  

ኢትዮጵያ ዘረኞች ሳይነግሡባት በፊት እንደ ሻለቃ ዳዊት ያሉና ከጋሼ ዳዊትም የላቁ አገር ወዳድ፣ ለወገናቸው ደማቸውን ያፈሰሱ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ባገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን መልካም ስማቸው በዓለም የናኘ ምርጥ ታላላቅ መኮንኖችን አፍርታለች፡፡ ዛሬ ታላቁንና የተከበረውን የኢትዮጵያ ሠራዊት በዘር በጐሣ አዋቅረው ተዋርደው አገርን ያዋረዱ ደናቁርት ምናምንቴዎች ስብስብ ከመሆኑ በፊት በብቃቱና ጥራቱ ስመ ጥር/ስመ ገናና የሆነና በሠለጠነው ዓለም ከሚገኙ ወታደራዊ ተቋማት ጋር በንጽጽር የሚታይ ተቋም ነበረን፡፡ በዚህም ምክንያት አገራችን ሌሎች ችግሮች ቢኖሩባትም በዓለም ዘንድ የታፈረች የተከበረች ነበረች፡፡ ዛሬ (ላለፉት ሠላሳ ዓመታት) ሳይገባቸው በሠራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ የመኮንንነት ማዕርግ የያዙ ግለሰቦች በፖለቲካ ችሮታ የታደሉ ሐሳውያን ‹ጄኔራሎች› ከዕውቀቱም፣ ከልምዱም፣ ከዲስፕሊኑም የሌሉበት፣ ኢትዮጵያንና የህልውናዋ መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ የሚጠሉ ጉዶች ስብስብ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት አገርም ሕዝብም አለኝታ መከታ የሚለው ኃይል የለውም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ኦና ቤት ሆናለች፡፡ ‹ስለተከበረ አገልግሎትህ፣ አለኝታነትህና መከታነትህ እናመሰግንሃለን› ልንለው ቀርቶ ዛሬ ሕዝቡ መለዮ ለባሹን የጠላት ያህል እየሸሸው ይገኛል፡፡ ዛሬ ‹የአገር መከላከያ› የተባለው ኃይል እንኳን የውጭ ጠላትን የሚገዳደር፣ የውስጥ ዓማጽያንን ለመቋቋም ያልቻለ ደካማ ስብስብ እንደሆነ ታዝበናል፡፡

ጋሼ ዳዊት፤ የኢትዮጵያ አምላክ ጤንነት ያለበት ረጅም ዕድሜ እንዲሰጥህ እመኛለሁ እጸልያለሁ፡፡ የጀመርከውን መልካም ተግባር እግዚአብሔር ከፍጻሜ ያድርስልህ፡፡ እኛም በሙሉ አካላችን በሙሉ መንፈሳችን ካንተ ጋር ነን፡፡ 

በዚህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ባጠቃላይ ለአማራ ሕዝብ በተለይ ማሳሰብ የምፈልገው ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ገና መጀመሩ ነው፡፡ የውሸት ምርጫው እንዳያዘናጋን፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ኢሕአዴግ ብቻውን ሮጦ ብቻውን ለማሸነፍ ያቀነባበረው ትርኢት ነው፡፡ ‹ምርጫው› ትእምርተ ባርነት እንጂ ትእምርተ ግዕዛን (ነፃነት) ሊሆን አይችልም፡፡ በየትኛውም መመዘኛ የዴሞክራሲ መገለጫ አይሆንም፤ በዚህም የሚፈታ አገራዊ ችግር የለም፡፡

አረመኔው ዐቢይ ያለው ምርጫ ሁለት ነው፡፡ የፌዝ ምርጫውን አቁሞ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት የሚመጣበት የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የሚሳተፉበት የሽግግር ጉባኤ መጥራት የመጀመሪያው ሲሆን፤ በሠራዊቴ ብዛት በጉልበቴ ተመክቼ ሕዝብ እየጨፈጭፍኹ ኢሕአዴግ የተከለውን የዘረኝነትና የባርነት አገዛዝ ሥርዓት አጽንቼ እቀጥላለሁ የሚለው ሁለተኛው መንገድ ነው፡፡ ይህ የኋለኛውን መንገድ እከተላለሁ ካለ ራስ ወዳድ አውሬ (selfish beast) የሆነው ዐቢይ አገዛዝ ዘመን ኢሕአዴግ (ብል/ጽ/ግና) እስከሚባለው የአጋንንት ተቋም ፍጻሜው/ማብቂያው ይሆናል፡፡ ሆኖም ይህ ሁለተኛው መንገድ የአገር ህልውናን በእጅጉ አደጋ ላይ እንደሚጥል የሚገመት ነው፡፡  

የአምሐራው የዘር ጥፋት እስኪቆም (በግፍ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችን አስከሬን በክብር እስኪያርፍ፣ አካላቸውን ላጡ፣ የሥነ ልቦና ቀውስ ለደረሰባቸው፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት ወደቀዬአቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ፣ በመረጡበት ቦታ በሕይወት የመኖር መብታቸው ዋስትና እስኪያገኝና ለተፈጸመባቸው በደል ሁሉ ተገቢውን ካሣ እስኪያገኙ ድረስ) እና የዘረኝነት አገዛዝ እስከነ ሕጋዊ መሠረቱ (የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ) እና መዋቅሩ ፈርሶ ዜጎች በእኩል ዓይን የሚታዩበት ሥርዓት እስኪሰፍን ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ይዘልቃል፡፡ 

ዘረኛው ዐቢይ ተመዝኖ ቀልሎ ተገኝቷል፡፡ በርእሰ መጻሕፍቱ የተመለከተው ‹‹ማኔ ቴቄል ፋሬስ›› የተባለው አምላካዊ ቃል በኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ‹ግድግዳ› ላይ በጉልህ ታይቷል፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ኢትዮጵያን ለመምራት ብቃት የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ምራቁን የዋጠ ሰው ያስፈልጋታል፡፡ ዕውቀትን ከጥበብ ጋር ያስተባበረ፡፡ እዚህ ላይ ለወገኖቼ ማሳሰብ የምፈልገው በ60ዎቹ የተነሱት የተማሪ ፖለቲከኞች ወይም ‹ያ ትውልድ› የሚባለውና ዛሬ በ‹ሽምግልና› የተሸፈኑ ‹ጎረምሶች› የኢትዮጵያን አገራዊ ዐውድ፣ ታሪክ፣ የእሤቶች ሥርዓት፣ ባህልና እምነቶች ያልዋጀ አስተሳሰብ ይዘው ለኢትዮጵያ የመጠላለፍ፣ የጥላቻና ድንቁርና ፖለቲካ በዚህም ምክንያት እስካሁን ለምናየው አገራዊ ምስቅልቅል ተጠያቂ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢትዮጵያ ከ ‹ያ ትውልድ› ውጭ ወይም ከዛም ዘመን ቀድመውና በዛም ዘመን ኖረው የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው በሳል ኢትዮጵያውያን ባገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም አሏት፡፡ ዛሬ በዓለማችን የሚገኙ ዴሞክራሲ በአንፃራዊነት ሰፍኖባቸዋል የሚባሉ መንግሥታትን የሚመሩ በርካታ አረጋውያን ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ በመሆኑም ወጣትነት ለጥሩ መሪነት ዋስትና እንዳልሆነ ሁሉ፣ በዕድሜ መበልጸግም ለጥሩ አመራር ችግር አድርጎ ማየቱም ትክክለኛ አመለካከት አይደለም፡፡ የግለሰብ መሪ ብቃት ትልቅ ሚና እንዳለው ቢታመንም፣ የአንድ መንግሥትን አመራር የተሟላ የሚያደርገው ጊዜ ተሻጋሪና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሻሻል ሥርዓት መዘርጋት፣ የዴሞክራቲክ ተቋማት መሠረት መያዝ፣ ነፃነታቸው የተረጋገጠ የማኅበረሰብ (ሲቪክ) ተቋማት መስፋፋት፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ የመከላከያ ኃይል መኖር፣ የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆን፣ በዕውቀት፣ በልምድ፣ በጥበብ የበለጸጉ አማካሪ ግለሰቦች ወይም የምርምር፣ የጥናትና የፖሊሲ ተቋማት (think-tanks) መኖር በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የአገሬ ልጆች አበክሬ የማሳስባችሁ የቅድሚያ ተግባራችን ባርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነውን፣ አቻሜ መቃብር ጠባቂ (ሰቃልያነ እግዚእ በክርስቶስ መቃብር ላይ እንዳኖሯቸው ክፉ አይሁዶች) ያለውን የሙታን ስብስብ ብአዴንን ማስወገድ ይሆናል፡፡ እነዚህ ለኢትዮጵያ (ለአምሐራ) ትንሣኤ ጠንቆች ናቸውና፡፡ እነዚህ ከመነሻቸውም ‹አምሐሮች› አይደሉም፡፡ አምሐራ የባርነት መንፈስም ሆነ ሥነ ልቦና የለውምና፡፡

Filed in: Amharic