>

በአዲስ አበባ የገዥው ፓርቲ ትኩረት መሬቱ ወይስ ሕዝቡ? (ስንታየሁ ቸኮል፤ የህሊና እስረኛ ከቃሊቲ ወህኒ ቤት)

በአዲስ አበባ የገዥው ፓርቲ ትኩረት መሬቱ ወይስ ሕዝቡ?

(ስንታየሁ ቸኮል፤ የህሊና እስረኛ ከቃሊቲ ወህኒ ቤት)

  ምርጫ

ተረኛው ስግብግብ የኦህዴድ/ብልፅግና ፖለቲካ በአዲስ አበባ እየፈጠረ ያለውን ውጥረት የምናስተነፍሰው በምርጫ ካርዶች ነው፡፡
በየትኛውም መልኩ የሰው ልጅ ዘላቂ ሰላም ሲባል በሰዎች መካከል በህይወት መተሳሰርና በሰጥቶ መቀበል መሰረተ ሃሳቦች ላይ የተገነቡ ግንኙነቶችን መፍጠርና ማጎልመስ ማለት ነው፡፡ የማበራዊ ሳይነስ ባለሙያዎች እንደሚሉት የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ በሶስት ደረጃዎች ያልፋል ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህም ልጅነት (Child hood) ጉርምስና/ ወጣትነት (adolescence) እና ጉልምስና /መብሰል/  (maturity) የምንላቸው ናቸው፡፡
  እያንዳንዱ የሰው የእድገት ደረጃ የራሱ የሆነ አመለካከትና ባህሪዎች አሉት፡፡በልጅነት እድሜ ሰው የራሱን ፍላጎቶች ያለ እርዳታ ለማሟላት ስለማይችል፤ ልጅነት ከጥገኝነትና ተመርኳዥነት ባህሪይ ጋር ይያያዛል፡፡
የጉርምስና/ወጣትነት ዘመን ደግሞ ከጥገኝነት ነፃ ለማውጣትና ራስን ለመቻል የሚደረግ ጥረት ላይ ያተኩራል፡፡ በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎች እንደሚረዱት አንዱ ግለሰብ የህይወት ዓላማውን ግብ ላይ ሊያደርስ የሚችለው የራሱ ጥረት ብቻ ሳይሆን የሌሎች ጥረትና ድካም ስለሚደግፈው ነው፡፡ የግለሰብ ፍላጎትና ጥቅም ዘላቂ በሆነ መንገድ የሚሳካው የደጋፊዎቹ ፍላጎትና ጥቅምም ሲሳካ ነው፡፡ ስኬታማ ህይወት እና ሰላም የሰዎችን ጥረትና ማስተባበር መረዳትን በጋራ መስራትን የሚጠይቅ ነው፡፡
የሕንዱ ፈላስፋ የነፃነት ትግል መሪ የሆኑት ማሕተመ ጋንዲ ሰዎችን ሲገልፁ በዚህ ዓለም ውስጥ የማንኛውንም ሰው መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማርካት/ለማሟላት የሚችሉ በቂ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ለሰዎች ስግብግብነትን ምንም ዓይነት ክምችት /መሰብሰብ አያረካውም ሲሉ ተናግረዋል። ስግብግብነት በሸታ ነው፡፡ መቆሚያ የሌለው፤ እራስ ወዳድነት ሁሉን አልጠግብ ባይ አጉዳይ እንደሚባለው ስግብግብነት የመጨረሻ ግቡ የያዙትንም የሚንቅ የሌለውን በመፈለግ የራስ ማጣት የሚያስከትል አደገኛ በሽታ ነው፡፡ በተለይ ስግብግብነት በመዋቀር እና በህግ – የታገዘ መንግስታዊ ስራ ሲሆን አንድ ማህበረሰብ ወዳልተፈለገ ቀውስ ሊያስገባ  እንደሚችል እሙን ነው፡፡
አዲስ አበባ የሀገሪቷ ርዕሰ መዲና፤ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማህበራዊ ትስስሩ የሚንፀባረቅባት ከመሆኗም በላይ በአለም ካሉ ተመራጭ ስፍራዎች ከኒዮርክ ብራስልስ ቀጥሎ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆን ሶስተኛ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ መቀመጫ ነች።
አዲስ አበባ በታሪካችን ውስጥም በርካታ የቀደምት አባቶች ስልጣኔ የራፈባት፤ ትውፊታዊ ቅርሶችን የያዘች በጥንታዊ ስልጣኔ ኃይማኖታዊ ፍልፍል ዋሻዎች የሚገኙባት ነች።   የእረጅም ጊዜ ማህበራዊ ትስስር የጎለበተባት የሀገሪቷ የምጣኔ ሀብት የሚዘወርባት ከተማችን ነች፡፡
ስለ አዲስ አበባ ስናወራ መሬቱና ህንፃው የኛ (ኬኛ) በሚሉ ዘውጌ ብሄርተኞች አይን አውጣ ስብስብነት ተማሮ ውጥረት በተሞላበት የሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በስራ አጥነት ቁጥሩ የበዛ ወጣት ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ከእለት የእለት በኑሮ ውድነት መከራ የሚመለከተው የከተማዋ ነዋሪ በቤት እጦት እና በትራንስፖርት ችግር በውሃና በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ፍዳውን የሚመለከት የአገልግሎት እጦት እንንግልት በእለት ተእለት ህይወቱ ዘርፈ ብዙ ችግር የምናይበት የምስኪን፣ የድሆች ከተማ አዲስ አበባ፤
 ከ46% በመቶ በላይ የከተማዋ ምጣኔ ሃብት በበርካታ የንግድ ዘርፍ ውስጥ እጅግ የበዛ ሀብት የሚዘወርበት በአዲስ አበባ ነው፡፡
በበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንዳለበት ሁሉ  ከ60 በመቶ በላይ ወጣት በስራ አጥነት የተቸገረባት ከተማ ነች።
 ከተማዋን መቆጣጠር የፈረጠመ ፖለቲካዊ ጉልበት የሚሰጥ  በመሆኑ ነው የተለያየ ፍላጎት እየተንፀባረቀ ያለው።
ኦህዴድ/ብልፅግና አዲስ አበባን የሚመለከትበት መነፅር ነዋሪውን ሳይሆን መሬቱን የመፈለግ ነው፡፡ ከምርጫ በኋላ መጤ ያሉትን ህዝብ በመንቀል መሬት ወረራ እንጂ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ጉዳዩ አይደለም፡፡
ይህን አግላይ የፖለቲካ መስመር የምንታገልበት ብቸኛ መንገድ በህዝቡ ውሳኔ ምርጫ እድላችን እና የፖለቲካ ውሳኔያችን የምንወስንበት አይነተኛ ሚና ያለው መሳሪያ ምርጫ ነው፡፡ ምንም እንኳን የምርጫው ሂደቱ ግልፅ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ተአማኒነት ያለው ነው ተብሎ ባይገመትም በተፈጠሩ የምርጫ እድሎች የተዘጋውን በር ከፍቶ መግባት ጭቆና የበረታበት ህዝብ ድርሻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ነዋሪ በተፈለገው እና ባለበት አስጨናቂ ሁኔታ ንቃተ ህሊናው እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም በቁጥሩ ልክ የምርጫ ካርድ እየወሰደ አለመሆኑ ከጥያቄው  ትልቅነት አኳያ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
በከተማዋ 832 በቀጣናዎች በ117 ወረዳዎች ከ1800 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መራጩ ነዋሪ በቸልተኝነት እና በተስፋ መቁረጥ በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች ካርድ ባለመውሰድ እየተዘናጋ ስለመሆኑ በመንግሥት ሚዲያዎች ከምሰማው መረጃ ተረድቻለሁ። ይህ አሳሳቢ ነው። መተለይ ካለንበት ወቅታዊ ከባድ  የፖለቲካ ውጥረት አንፃር ነዋሪው የምርጫ ካርድ ባለመውሰድ መዘናጋቱ የዜግነት ውሳኔ ዕጣ ፈንታውን አሳልፎ እየሰጠ እንደሆነ ሊያጤነው ይገባል፡፡ ይህ ከፍተት ኦህዴድ/ብልጽግና በህገ ወጥ መልኩ ባደላቸው መታወቂያዎች የምርጫ ካርድ በማደል በአቋራጭ ከተማዋን የመቆጣጠር ሁኔታ ምቹ እድል መፍጠር እንደሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በመጪው ምርጫ በአዲስ አበባ ደረጃ የከተማዋን የ’ክልል’ነት ጥያቄ ያነገበው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) የማሸነፍ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ በምርጫው ላይ በነቂስ መሳተፍ በከተማዋ ላይ የባለቤትነት ድርሻውን ሊያረጋግጥ የሚችልበት ፖለቲካዊ ውሳኔ እና እጣ ፈንታውን በእጁ የሚያስገባበት አውድ አለ፡፡ ይህን በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ነው።
አዲስ አበባ የሀገሪቷ ርዕሰ ከተማ እና ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት የሚመነጭባት እንደመሆኗ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማህበራዊ ትስስሩ ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው። በሀገር አቀፍ ድርጃ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የሙቀቱ መለኪያ ናት፡፡
 ሀገራዊ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ካሰፈለገ የአዲስ አበባን ፖለቲካ እና አሰላለፍ መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ከዘውጌ ተረኛ ብሔርተኞች እጅ በማውጣት በነዋሪዎቿ ላይ በጎ ፈቃድ የተመሰረተ አስተዳደር መፍጠር የህልውናዋ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡
 አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የኦህዴድ/ብልፅግና ኃይል ዋነኛ ትኩረቱ በአዲስ አበባ የፖለቲካ የበላይነት መያዝ ነው።  አጠቃላይ ውጤቱ በሀገር አቀፍ ድርጃ የሚወስን ፖለቲካ ጉልበት ስለሚሰጣቸው አዲስ አበባን ከነዋሪዎቿ በመንጠቅ የአዲስ አበባ ታሪካዊ ስራን አፍርሶ በፈጠራ ድርሰት ለመገንባት ነው እቅዳቸው።
  በሀገር ደረጃ አጠቃላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የአዲስ አበባ ህዝብ መሰረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት አለበት። የመሪነት ድርሻ ጎልቶ መውጣት ይኖርበታል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ የራሱን ራስ ገዝ አስተዳድር ወይም  ‘ክልል’ በሕዝበ ውሳኔ በመወሰን ወዶና ፈቅዶ በመረጠውና ውክልና በሰጠው ህዝብ ውሳኔ በማክበር የህዝቡን ብይን መቀበል ሲቻል ነው፡፡ አዲስ አበባ የፖለቲካ እጣ ፈንታ ወሳኝ የመሰረተ ድንጋይ መጣያ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
በአሁኑ ሰዓት በበርካታ ስፍራዎች ህዝባዊ ንቅናቄዎች እየተቀሰቀሱ በመሆኑ በምርጫው ድባብ ላይ ያልታሰበ ክስተት ይዞ እንዳይመጣ ሁሉም ነዋሪ በእኔነት ስሜት ታሪካዊ ሓላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡  የአዲስ አበባ ነዋሪ የምርጫ ካርዱን በመያዝ ለልጅ ልጆቹ የሆነች ሰላሟ የተጠበቀ ከተማውን በውክልናው ማረጋገጥ  ለነገ የማይባል ትውልዳዊ ሓላፊነት ነው፡፡ እኛ የህዝቡን ቃል አክብረን ዋጋ ከፍለናል ህዝቡም ቃሉን በካርዱ በማረጋገጥ ታሪክ ሊደግም ይገባል፡፡

 ‘አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት’ የፈጠራ ትርክት

‘አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት’ የሚባለው የፈጠራ ታሪክ ሲደጋገም እውነት እንዳይመስል በልኩ እና በቁመቱ ልክ መናገር ያስፈልጋል፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ሳይትሆን መላ ሸዋ ከዛጉዌ ስርዎ መንግስት በኋላ የነገሱ የኢትዮጵያ ነገሥታት የግዛት ማዕከል እንደነበረች በታሪካችን በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠ ነው፡፡
 ከግራኝ መሃመድ ወረራ ጋር በተያያዘ ከማዕከላዊ ሱማሌ አካባቢ ከመነሳታቸው እና ወደ ኢትዮጵያ ደጋ አካባቢዎች መንቀሳቀስ ከመጀመራቸው በፊት የነበረው የታሪክ ሃቅ ነው፡፡
 ኦሮሞዎች መሃል ኢትዮጵያ ደርሰው ሸዋ በሰፈሩበትም ጊዜም ሸዋ ውስጥ እስከ መጨረሻው ድረስ የረጋ ስርዓት አልነበራቸውም፡፡ ሸዋን ማዕከል አድርገው ሊገዙ የነበሩት የኢትጵያ ነገስታት እ.ኤ.አ አቆጣጠር ከ1382-1411 ዓ.ም.  ከንጉስ ዳዊት ዘመን ጀምሮ እስከ አፄ ልብነ ድንግል ድረስ ግራኝ መሐመድ ጦርነት ምክንያት እስከተወረረ ድረስ የነገስታቱ ዋነኛ የንግድና የሰርወ መንግስቱ ማረፊያ የስበት ማዕከል ሸዋ አዲስ አበባ ነበረች፡፡
ይህን ደግሞ ዮሐንስ ክራፍ ራሱ አሁን አዲስ አበባ የሚባለውን ቦታ የሚያዋስኑትን ሶስት የተራራ ሰንስለቶች ከእነስያሜቸው በማመላከት መፃፉ ጥሩ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ነገስታት ዋና ከተማቸው ከሽዋ ወደ ጎንደር ለማሽሽ የተገደዱበት ምክንያት በግራኝ መሐመድ ጦርነት ባሌ፣ አፍስንና አብዛኛውን የሸዋ አካባቢ ለመልቀቅ በመገደዳቸው ምክንያት ነው፡፡
ይህ አጋጣሚ የፈጠረው ክፍተት ከግራኝ ወረራ በኋላ ለጀመረው የኦሮሞ ነገድ መስፋፋት እና ሰፋ ያሉ ለም መሬቶችን በመቆጣጠር ነባር ህዝባችን በኃይል በማስለቀቅ በጉዲፍቻ እና ሙገሳ እንዲገቡ ማድረግ ስፋፊ ቦታዎችን ለመያዝ ችለዋል፡፡
በተለይ በሸዋ ውስጥ በወረራ ሰፈሩ እንጂ እስከ መጨረሻው ድረስ በተቆጣጠሩት አካባቢ የኦሮሞ ስርዓተ መንግስት መሰርተው አልነበረም።  ሰርዓት መንግስት መስርተው የጋራ አስተዳደር በሌለው ሁኔታ ይህ ግዛት፤ የተመረጠ ለም መሬት  የእኔ ነው ማለት የታሪክ አመክንዮ የለውም፡፡
 ስለ አገራዊ ዳር ድንበር ወይም የግዛት ባለቤትነት ጥያቄ በድፍረት ማውራት የሚቻለው ቋሚ የመንግስት ስልጣን መመስረት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ህዝብና ዳር ድንበሩ በታወቀ ህዝብ ላይ አገዛዝ አንድ ሁነው ነው መንግስት ሊባሉ የሚችሉ፡፡ ይህ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡
አፄ ምኒልክ የአባቶቹን እና ቅድመ አያቶቹን አፅመ ርስት ከ1865 ዓ.ም.  ጀምሮ እስከ 1886 ሲፈልግ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከተማ በ1886 ዓ.ም ከመመስረቷ በፊት  አፄ ምኒልክ ከ1882 እስከ 1886 ዓ.ም ድረስ በእንጦጦ ተራራ ለአራት ዓመት ገደማ ከትመው ታሪካዊ የአባቶቻቸውን አሻራ በራራን ሲፈልጉ ቆይተዋል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ የነበሩ የታሪክ ስፍራዎች ለአዲስ አበባ ከተማ መመስረት እና የረጋ መዲና መሆን ዋና ምክንያቶች ነበሩ፡፡
  መቁጫቸውን ከእንጦጦ ወደፍል ውሃ በማዛወር አዲስ አበባ የሚለውን ስያሜ ተቀብለው፤ አዲስ አበባ ከተማ ተቆረቆረች፡፡ አፄ ምኒልክም መጀመሪያ ወደ ወጨጫ ከዚያም ወደ እንጦጦ በመጨረሻም ወደ አያት ታሪካዊ አፅመ ርስታቸውን ፈልገው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ በፈጠራ ድረሰት ‘የኦሮሞ ናት’ የሚለው ትርክት ቤት የማይመታ የነጣቂ ጩኸት ነው።  የታሪክ መረጃ የሌለው የህግም መከራከሪያ የሌለው ሃቅ ነው፡፡ የከተማዋ ታሪካዊ ባለቤት አማራ ነው። በአሁኑ ጊዜም አብላጫው ኗሪ አማራው ነው። ሆኖም አማራ ‘ከተማዋ የእኔ ብቻ ነች’ አላለም። ሁሉም ኢትዮጵያውን በባለቤትነት የሚኖሩባት እንደሆነች ያምናል። እውነቱም ይኸው ነው። ይህን እውነታ በልኩ እና በቁመቱ መናገር ያስፈልጋል፡፡

ሀገር መስርቶ ሀገር የጠፋው ህዝብ

የአማራ ህዝብ ለሀገሩ ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ለዴሞክራሲ ልዕልና ታግሏል። ደምቷል፣ ቆስሏል ውድ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ በታሰበው እና በተከፈለው ዋጋ ልክ ለውጥ ሊያመጣ ግን አልቻለም፡፡
ግራ ዘመም የጮርቃ ተማሪዎች ንቅናቄ ኮምኒስታዊ ርዕዮተ ዓለም አመለካከት እርስ በእርስ ተበላልቶ ከመጠፋፋት በላይ በጊዜ ሂደት ሀገሪቷን በዘውጌ ብሄርተኞች ጡዘት ይዟት ወደ ገልፅ የሚሄድ አጥፍቶ ጠፊ ርዕዮታዊ መስመር በህወሓት እና ጄሌዎቹ መሐንዲስነት በኦነግ የመደናቆር ፖለቲካ ዛሬ ላለንበት ውጥንቅጥ ዳርጎናል፡፡ ውድ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡
ወደፊት እንደ ሀገር አብረን እንቀጥላለን ወይ? የሚለው ሰው ከትላንት ይልቅ ዛሬ በዝቷል፡፡ በዋናነት ባለፉት ሰላሳ  ዓመታት ህገ – መንግስታዊ፣ መዋቅራዊ ተቋማዊ በሆነ መስመራዊ ትግል አንገታቸው ተቆርጦ የወደቁ አማሮችን ቤት ይቁጠረው፡፡ ይህን አሳዛኝ ክስተት ዛሬም ድረስ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የየቀኑ ውሎ መሆኑ የነገ እጣ ፈንታችን አስፈሪ አድርጎታል፡፡
የአማራ ህዝብ ደምቶ ባቆማት ሀገሩ በሄደበት ከመሞት ከመሰደድ በችግር ቁም ስለቅሉን መመልከት ሀገር መስርቶ ሀገር የጠፋው ህዝብ ሆኗል፡፡
በሀገር ግንባታ የረጅም ጊዜ ታሪክ ደማቅ የጀግንነት ገድል በደሙ ውስጥ ዘልቆ የገባ ማበረሰብ፤ ኢትዮጵያዊ ፍቅር እንደ ቅቤ ቀልጦ የገባው ውድ ማንነት ዛሬ በሚፈተነው እና አንገቱን በሚደፋው መልኩ ሁሉም አካል በሬሳው ላይ በስላቅ ሲረባረብ ማየት ያማል! ያሳዝናል! የአስራ ስድስተኛው ክ/ዘመን ወረራ እየተደገመ በሚመስል ሁኔታ አንድ ማህበረሰብ በመጨፍጨፍ ኢትዮጵያን ማፍረስን ዓላማው ያደረገ ኃይል ምቹ መንግስታዊ እገዛና መዋቅራዊ ትስስር በመጠቀም የአማሮችን ነፍስ የሰይፍ እና የጥይት ባሩድ ማቀዝቀዣ አድርገውታል፡፡
ይህንን በለቅሶና በሀዘን እንጉርጉሮ እያላዘኑ መኖር ከዚህ በኋላ ቀይ መስመር እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ሁሉም እየተገነዘበው የመጣ ሃቅ ነውና፡፡ ዛሬ የሚያስፈልገን መፋቀር ሳሆን መከባበር ነው። ጊዜውም አሁን ነው፡፡

የአማራ ጥቃት ከመቼ ጀምሮ

በ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ልጓም ባልተበጀለት የጥላቻ ጥግ፤ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት የለወጠው አብዮት በአማራ ህዝብ  ይህ ነው የማይባል እጅግ መራር ዋጋ አስከፍሎታል። እያስከፈለውም ይገኛል፡፡
  ባለፉት 50 (ሃምሳ) ዓመታት ስሜት በጋለበው የፈጠራ ትርክት ከሃቁ በራቀ የሀሰት ክስ እየተሳደደ እንዲገደል በፕሮግራም ተወስኖበታል፡፡ የታማኝነትና የትግል አርማ በማድረግ በዓለም ታሪክ ከሰማነው የሩዋዳ የዘር ጭፍጨፋ ባልተናነሰ ብዙ የግፍ እልቂት ተፈፅሞበታል። ከባድ ዋጋ ከፍሏል፡፡  ለቆመለት  የሀገር ፍቅር እንደ ቅቤ ቀልጦ ማንነቱን በኢትዮጵያዊ ፍቅር ያዋሃደ ህዝብ ለይቶ ማጥቃት ሀገር  የማፍረስ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው፡፡
 በቅርቡ በምስራቅ እና በምዕራብ ወለጋ ሆሮጉድሩ ባገምዴ እንዲሁም በመተከልና በተለያዩ ቦታዎች በንፁሐን የአማራ ወገኖች ላይ የተነጣጠረ ዘራቸው እንደ ሃጢያት ተቆጥሮ እድሜ ያልገደበው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተፈጥሮ አይተናል፡፡  እድሜያቸው ለአካል ጉልምስና ካልደረሱ ህፃናት ጀምሮ በአረጋዊያን እናትና አባቶች ላይ የተፈፀመው ዘግናኝ የዘር ማፅዳት እልቂት ተደጋጋሞ ሲፈፀምባቸው ቆይቷል፡፡ ይህ የሟቾች ቁጥር መብዛት እያስገረመን የተላመድነው መረጃ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ሰው እየሞተ ዘላቂ ሰላም እንዴት እንደሚመጣ አላውቅም፡፡
አንድ ማህበረሰብ ለይቶ በማጥቃት የዘር ጭፍጨፋ መፈፀም በድርጊትም፣ በሃሳብም የተሳተፉ ኃይሎች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ባፈሰሱት ደም መጨፍጨፍ የንፁሐን እንባ ልክ የሚያወራርዱት ሂሳብ እንዳለ ለአፍታም መዘንጋት አይቻልም፡፡ ሙሉ አጣዬ ከተማን ያወደመ ወራሪ ቡድን ሙሉ አማራን እንደ ጋፋትና ማያ የማያፋበት ምክንያት የለም። አዲስ አበባን የማያጠፋበት ምክንያት የለም። አዲስ አበቤ ወራሪውን በካርዱ የሚቀጣበት ጊዜው አሁን ነው።
Filed in: Amharic