>
5:26 pm - Friday September 17, 7362

የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ምንነትና አስፈላጊነት (አቻምየለህ ታምሩ)

የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ምንነትና አስፈላጊነት

አቻምየለህ ታምሩ

የአማራ ሕዝብ ቀጣይ የትግል እርምጃ በአማራ ላይ የዘር ፍጅትና ጭፍጨፋ የሚያካሂደው የዐቢይ አሕመድ አፓርታይዳዊ አገዛዝ ወኪል የሆነው ብአዴን ከአማራ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ተወግዶ በምትኩ በየአካባቢው የጎበዝ አለቃ አስተዳደር ማቋቋም መሆን አለበት። ይህ ጽሑፍ ስለ ጎበዝ አለቃ አድረጃጀት ምንነትና አስፈላጊነት የሚያስረዳ ነው።
የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት የሚፈጠረው አገር ወይም ሕዝብ አደጋ ላይ በወደቁበት ጊዜ ነው። አገርና ሕዝብ አደጋ ላይ በወደቁበትና አገርና ሕዝብን ከመከራ የሚታደግ መንግሥት በሌለበት ጊዜ የሕዝቡን ደኅንነት፣ ሰላምና ጸጥታ ለመጠበቅ በበጎ ፈቃደኝነትና በራስ አነሳሽነት የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ይፈጠራል። አደረጃጀቱ በአገራችን ለረጅም ጊዜ ሲያገለግል የቆየ ሀገር በቀል ተቋም ነው። ይህ ሀገር በቀል አደረጃጀት በዐቢይ አሕመድ የኦሮሙማ አገዛዝ የጅምላ ፍጅትና የዘር ማጥፋት ለታወጀበት አገርና መንግሥት አልባው የአማራ ሕዝብ  እጅግ የሚፈለግበት ጊዜና ወቅት ነው።
አንዳንዶች የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት መሪ የሌለው የሽፍታ ስብስብ ይመስላቸዋል። በርግጥ ይህ የተንጋደደ እይታ ፕሮግራም ማለት ኮምኒስት ማኒፌስቶ፣ አደረጃጀት ማለት ኅብረተሰባዊነት፤ መሪ ማለት ዋና ጸሐፊ ከሚመስላቸው አፍ ነጠቆች የማይጠበቅ አይደለም። የዚህ የተንጋደደ እይታ ተጠቂዎች የሚያውቁት የመሪ ሞዴል ከኮምኒስት ማኒፌስቶ የሚነሳ በ«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» ወይም በኦሮሙማ ወብል[ጽ]ግና  የተጠመቀ፤  እንደ ሊቀመንበር መለስ ዜናዊና  የብል[ጽ]ግና ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዐቢይ አሕመድ ዓይነት ፈላጭ ቆራጭ ግለሰብ ስለኾነ ከዚያ የተለየ ሀገርኛ የትግል አመራር ዘዴ ቢኖርና ውጤት ቢያመጣ እንኳ መሪ ያለው መስሎ ባይታያቸው አይፈረድባቸውም።  በርግጥ ቤንቶ ሙሶሌኒ ጀምሮት ጀምሮ የተወውን ረጅሙን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ  በጎሳና በመንደር የከፋፈሉት የኦነግና የወያኔ ግብረ በላዎች የኢትዮጵያ አርበኞች በየጎበዝ አለቃው እየተደራጁ ወራሪውን ፋሽስት ሲፋለሙ የእነርሱ አባቶች ባንዳ ኾነው ለወራሪው እንቁላል ይቀቅሉና ጀግኖችን ይፋለሙ ስለነበር ለሀገር በቀል የአርበኛነት ተጋድሎ አደረጃጀቶች ባዕድ ናቸው።
የጎበዝ አለቃ የመሪ ሞዴል እንደ ኦነግና ሕወሓት ፍልስፍና ከአምባገነን የአውሮፓ አገዛዞች ተኮርጆ የመጣ የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት የሚሰፍንበትና ሙታን እድምተኞች ጀሌ ኾነው የሚሰለፉበት ድንግዝግዝ ሳይኾን ከአባቶቻችን የተወረሰ፣ ከውጭ የመጡ ጥጋበኛ ወራሪዎችን በተደጋጋሚ ያሳፈርንበት ሀገር በቀል የኅብረተሰብ አደረጃጀት ዘዴ ነው።
የጎበዝ አለቃ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ፣ ጎበዞች ከመሀከላቸው አንዱን ጎበዝ አለቃ አድርገው ለተጋድሎ የሚሰማሩበት የአርበኞች አደረጃጀት ነው። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት እንደ ብ.አ.ዴ.ን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊና እንደ ብል[ጽ]ግና ዋራ ስራ አስፈጻሚው ዐቢይ አሕመድ
አንድ ጮሌ ሺህ ነፈዞችን በዙሪያው አሰልፎ የሚነግራቸውን ብቻ የሚደግሙ ደናቁርት የተሰበሰቡበት ስምሪት አይደለም። በጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ሁሉም ጎበዞች ስለኾኑ በመካከላቸው የበላይና የበታች የለም። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት እንደ ሕወሓትና ብል[ጽ]ግና ፈጣሪው  ሲጎድል ያለመሪ የሚቀር ስብስብ ሳይኾን ሁሉም በማንኛውም አስፈላጊ በኾነ ጊዜ አለቃ የመኾን ችሎታውም ኾነ ፈቃደኝነቱ ያላቸው ጎበዞች አደረጃጀትና ሥርዓት ነው። ባጭሩ የጎበዝ አለቆች የምንላቸው በራሳቸው ጉብዝና ተከታይ አፈርተው ባለብዙ ተከታይ የኾኑና ከጠላት በፊት ምንም ያልነበሩ ጀግኖችን ነው።
የብ.አ.ዴ.ን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊ ከስታሊን የሞነተው የ«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» እና የእንጀራ አባቱ ዐቢይ አሕመድ ከዚህም ከዚያም የቃረመው የብል[ጽ]ግና  አደረጃጀት፣ በበሉበት የሚጮሁ፣ በሆዳቸው የሚገዙ ካድሬዎች ጥርቅም ነው። ስለኾነም ውላቸው ሆዳቸው እስከሞላ ድረስ ስለኾነ አለመተማመን፣ አለመከባበር፣ ጥላቻ፣ አንዱ ባንዱ ላይ መረማመድ የስብስቡ መገለጫ ነው። ለዚህም ነው በበል[ጽ]ግና ጥላ ስር ተሰባስበናል የሚሉን የኦሮሙማ ግብረ በላዎች  በመንደር አስተሳሰብ ሲታመሱ የሚውሉት። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ግን የመዋቅሩ መሠረት የቆመው በእኩልነት ላይ በመኾኑ መተማመን፣ መከባበር፣ መፋቀር፣ አንዱ ላንዱ አንተ ትብስ መባባል ጎልቶ የሚታይ የስብስቡ መገለጫ የኾነው።
በባሕላችን አንድ ሰው የጎበዝ አለቃ የሚኾነው እንደ ብአዴን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊና የእንጀራ አባት ዐቢይ አሕመድ  ጮሌ ስለኾነ ብቻ ሳይኾን ከስብስቡ ውስጥ በሥነ ልቦና፣ በሥነ ምግባር፣ በሞራል ሥልጣኔ፣ በጥበብ፣ በመንፈስ ጥንካሬና በአመዛዛኝነት የተሻለ ኾኖ ሲገኝ ነው። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት በቤተሰብ ደረጃ በሚታይ መተሳሰብ የቆመ የተጋድሎ መዋቅር ነው። በጎበዝ አለቃ አደረጃጀት የጎበዝ አለቃው አብረውት የተሰለፉ አርበኞችን በቅድሚያ ሸልሞና ማዕረግ ሰጥቶ በትህትና መንፈስ ተልዕኮ በመስጠት ለተጋድሎ ያሰማራቸዋል። ለአርበኞች የሚሰጠው ማዕረግና ሹመትም በብቃት ልክ የተመጠነ ነው። አርበኞቻችን ሁሉ በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ተጋድሎ ዘመን የጎበዝ አለቃ ኾነው ሕዝብ ሲያታግሉ በየጊዜው ሲሾሙና ሲሸልሙ የነበሩት ለራሳቸው ሳይኾን አብረዋቸው ለተሰለፉ ባለንጀሮቻቸው  ነበር።
የብአዴን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊ የገነባው «አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» እና የእንጀራ አባቱ ዐቢይ አሕመድ ያቆመው የኦሮሙማ አስተሳሰብ ግን የበላይና የበታች ያለበት፣ መጠራጠር፣ ፍራቻ፣ ጥላቻ፣ ቅናትና ጊዜን ጠብቆ መጠቃቃትን መርሁ ያደረገ የእፉኝት ልጆች ስብስብ ነው። መለስ ዜናዊ በገነባው «አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» እና ዐቢይ ባስቀጠለው ብል[ጽ]ግና የማዕረግና የሥልጣን ምንጭ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ተቃራኒ ነው። መለስ ዜናዊ በገነባው «አቢዮታዊ ዲሞክራሲ»  እና ዐቢይ አሕመድ በዘረጋው የኦሮሙማ ሞዴል  መለስ ዜናዊና ዐቢይ አሕመድ ለራሳቸውና ለነገድ ወገኖቻቸው በቅድሚያ ሥልጣን ሸልመው በኢትዮጵያ ላይ ቁብ ይሉና የማዕረግ እድገቱንና ሹመቱን የሚቀበሉት ደግሞ ክህሎት በዞረበት ዝር ብለው የማያውቁ ካድሬዎች ናቸው።
መለስ ዜናዊ የፈጠረው የ«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» ማዕከላዊነት አደረጃጀት እና የዐቢይ አሕመድ የብል[ጽ]ግና  የአንድ ግለሰብ አስተሳሰብ ያለ ገደብ የሚፈጸምበት ልቅ ሥርዓት ነው። ስለኾነም የሚያኮርፈው፣ የሚከፋው፣ የሚያዝነውና ቂም የሚቋጥረው ሎሌ፣ አሽከርና ጀሌ ቁጥር የትየለሌ ነው። በጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ግን የሁሉም ሐሳብ በእኩልነት የሚስተናገድበት፣ የተሻለው በውይይት ተቀባይነት የሚያገኝበት፣ ከሐሳቦች ሁሉ ምርጥ የኾነው በሁሉም የጎበዝ አለቆች ይሁንታ አግኝቶ በሙሉ ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረግበት፣ ውጤቱም ሁሉንም የሚያረካ ሥርዓት ያነበረ/ያኖረ የአባቶቻችን አስተዳደራዊ መዋቅር በመኾኑ የሚያኮርፍ፣ የሚከፋ፣ የሚያዝንና ቂም የሚቋጥር አንድም ሰው አይኖርም።
እኩልነት ብሎ ነገር ደብዛው የሌለበት የሊቀመንበር መለስ ዜናዊ የ«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» እና የኦሮሙማው ሥራ አስፈጻሚ የዐቢይ አሕመድ ብል[ጽ]ግ አደረጃጀት ግን፣ ስብስቡ የሚዘወረው በአንድ ሰው ሐሳብ በአንድ ሰው ፍላጎት ስለኾነ የተሻሉ ሐሳቦች ወደፊት የመምጣት እድል የላቸውም። ሊቀ መንበሩና ሥራ አስፈጻሚም ከራሱ የሥልጣን ጥቅም አንጻር ብቻ ስለሚያስብ ውጤቱ አብዛኛውን የስብስቡን አካላት የማያረካ ይኾናል። ይህ የበለጠ ጥርጣሬ፣ የበለጠ በቀለኝነት ያሰፍናል። ሊቀመንበሩና ሥራ አስፈጻሚውም ይህንን ስለሚያውቅ ጥርጣሬና በቀለኝነትን ለመቆጣጠር ሲል ነጻነትን እያፈነ ይሄዳል። «ውስጣዊ ዲሞክራሲ» እና «ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት» የሚሉት የመለስ ዜናዊ «አቢዮታዊ ዲሞክራሲያዊ» አስተሳሰቦች እና ብል[ጽ]ግና የሚለው የዐቢይ አሕመድ ቅራቅንቦ በግለሰብ አምባገነንበት የተደመደሙት ጥርጣሬንና በቀለኝነትን ለመቆጣጠር ሲል ነጻነትን በማፈኑ ነው።
«ልማታዊነቱን» እንዳስመሰከረ በአጋገሶቹ ብ.አ.ዴ.ኖች ሲደሰኮርለት የኖረው መለስ ዜናዊና  አመጣ ስለሚባለው ለውጥ በውታፍ ነቃዮችና በተደጋፊ ተደማሪዎች ሳይቀር ሲመሰከርለት የኖረው ዐቢይ አሕመድ  አስመዘገቡት የተባለው ልማትና ለውጥ  በቃላትና በፊደል የሚሟሟ ይመስል የሕትመት፣ ብሮድካስቲንግና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን ማለትም የግል ጋዜጦችንና መፅሔቶችን፣ የግል ሬዲዮኖችንና የቴሌቪዥን ሥርጭቶችን፣ የሚነበቡና የሚደመጡ ዌብ ሳይቶችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ተቺ ምሑራንንና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን ትንሽ ትልቅ ሳይል በጠላትነት ፈርጆ በማፈን፣ በማዋከብ፣ በማሰርና በማወክ ሥራ ባገዛዝ ዘመናቸው ሙሉ ተጠምደው  የኖሩት የሚቃወሙትን ብቻ ሳይኾን በዙሪያው ያሰለፏቸውን ግብረ አበሮቻቸው  የሰበሰቧቸው ከራሳቸው የሥልጣን ጥቅም አንጻር ብቻ ስለኾነ ጥርጣሬና በቀለኝነትን ለመቆጣጠር ነው።
በእውነቱ የዲሞክራሲ መሠረቱ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ነው፤ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት በጫካ ወይንም በከተማ ሊፈጠር ይችላል። በታሪክ እንደምናውቀው የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት የሚንቀሳቀሰው ጎበዞች የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች በራሳቸው ጥረት ፈልገው በማግኘት ነው። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት መሳሪያ ወይንም ገንዘብ የሚያገኘው በሌላ ድርጅት ሳይኾን በራሱ ጥረት የሚያስፈጉትን ማቴሪያሎች በማሟላት ነው። ሌላው መሳሪያ ወይም ገንዘብ ስለሰጠው ሊያዘው፣ ተከተለኝ ሊል አይችልም። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት የማንም ውለታ የሌለበት፣ እያንዳንዱ አባል ለራሱና በእኩል ለሚያያቸው ጓዶቹ ብቻ ታማኝ የኾነበት አደረጃጃት ነው።  የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት ከጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ይለያል። በመሠረቱ አንድ ግለሰብ ወይንም ማኅበረሰብ መደራጀት ያለበት በመርሕ በሚመራ ዓላማ ሥር እንጂ በፖለቲካ ፓርቲ ወይንም በድርጅት ሥር መኾን የለበትም። የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይንም ድርጅቶች ተቀዳሚ ተግባር ግን ሕዝብ የሚደራጅበትን ዓላማ መቅረጽ ነው።
ስለዚህ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት መሪ አለው፤ መሪዎቹ ደግሞ በአባቶቻችን ትውፊት የተደራጁትና በዘመናዊ መልክ የተቀናጁ መሬት ላይ ያሉ ጎበዞች ናቸው። የጎበዝ አለቆች ተከታቶቻቸውን እየመሩ ያሉት እንደ ብ.አ.ዴ.ን በሆዳቸው እየተገዙ ጀሌ ኾነው ሳይኾን ሕዝባቸው መሀል እየዋሉ፣ እያደሩና የሕዝቡ አካል ኾነው ነው። የጎበዝ አለቆች ከአለቆች አንዱ ሲሰዋ የተሰዋውን አርበኛ በክብር መዝገብ አስፍረው እንደየቤተ እምነቱ በክብር እንዲያርፍ ያደርጋሉ፤ ሲጠቃም ቀድመውት ይወድቃሉ እንጂ እንደ ብ.አ.ዴ.ን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊ «የሟች ወታደሮችን አሃዝ ይፋ የማድረግ ግዴታ የለብኝም» በማለት ያሰማራውን ኃይል ሞራል በመግደልና የጠላትን ሞራል ደግሞ ከፍ አያደርግም፤ እንደ ኦሮሙማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዐቢይ አሕመድ “የአንተ መንደር ሚሊሻ አይደለሁም” አይልም።
ጀግኖች አባቶቻችን በጎበዝ አለቃ ተደራጅተው ሲፋለሙ የኖሩት በአምስት ዓመቱ የፀረ ፋሽስት ተጋድሎ ብቻ ሳይኾን ከዚያ በፊት በተካሄደው የአድዋ ተጋድሎም ጭምር ነው። ጥሊያን አንዱን የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት መሪ ቢገድልም ሁሉም የጎበዝ አለቆች መሪ ሊኾኑ የሚችሉ ጎበዞች ስለኾኑ አንድ መሪ የጎበዝ አለቃ ቢሰዋ ትግሉ ነጻነታችንን መልሰን እስክናገኝ ድረስ ሊቆም ያልቻለው ለዚያ ነበር። በአድዋ ጦርነት ወቅት…
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፤ የተባለው ለዚያ ነበር።
ይህም በመኾኑ በሁለቱ ዙር በተካሄዱ ጸረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎዎች በጎበዝ አለቃ አደረጃጀት የተደረጉ ተጋድሎዎች ነጻነታችንን ለማስመለስ የነበራቸው አስተዋጽኦ የማይተካ ነበር። የፋሽስት ወያኔን አገዛዝ ለማስወገድ የአማራ ሕዝብ በየአካባቢው በመሰባሰብ ሲያካሂደው የነበረው ተጋድሎ በጎበዝ አለቃ  አደረጃጀት የተዋቀረና የቀደምት አያቶቻችንን አሠራር የተከተለ ነበር።
ሕዝባችን  ፋሽስት ወያኔን ለማስወገድ በየአካባቢው ባደረጋቸው ምድር አንቀጥቅጥ ጸረ ፋሽስት ወያኔና እንደራሴዎቹ ተጋድሎና በከፈለው ከባድ መስዕዋትነት ርስ በርሱ ሊተማመንና አብሮ ሊሰራ የሚያስችል የጋራ ትግል እርሾ ፈጥሯል። በሌላ አነጋገር ዛሬ ላይ አማራው በዐቢይ አሕመድ መሪነት እየተካሄደበት ካለው የጅምላ ፍጅትና የዘር ማጥፋት ራሱንና ወገኑን ለመታደግ በሚያደርገው ተጋድሎ  የኦሮሙማ  ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነውን  ነውረኛውን ብአዴንን  ለመንቀል  የሚችልበት መተማመን ላይ ደርሷል። በመሆኑም  ሕዝባችን ሳይፈራ የኅልውና አደጋ ከተጋረጠበት ወንድሙ ጋር የአማራ ባለጉዳይ ባልሆነው በብአዴን ላይ መዶለት ይችላል።
በመሆኑም አማራው በመየንደሩ፣ በየሰፈሩ፣ በየቀበሌውና በየወረዳው በጎበዝ አለቃ መበደራጀት  የአማራ ባለጉዳይ ያልሆነው፣ የጸረ አማራው ሥርዓት በእንደራሴነት ተሰይሞ ፍዳችንን የሚያራዝመውን ብአዴንን ማቆሚያ እንዲያጣ በማድረግ፤ የየራሱን አካባቢ ሕጋዊነት ከሌለው ከእንደራሴው ብአዴን አገዛዝ ነጥቆ በመውሰድ የባዕድ ምንደኞች በመሆን ተጭኖት የኖረውን ነውረኛ ድርጅት ነቅሎ ጥሎ ራሱን ማስተዳደር በመጀመር ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋራ በጋራና በእኩለት የሚኖርባትን አገር፣ ሕግና ሥርዓት ለመመስረት መደራደር መጀመር አለበት። ይህን አንድ ልብ የኾኑ ጀግኖች የኅልውና አደጋ የተጋረጠበትን ሕዝብ ሊያጠፋ በሚሰማራው ጠላት ላይ የሚደረገው  በጎበዝ አለቃ የሚመራ ተጋድሎ ኢንተርኔት ቢያቋርጡ፣ ነፍሰ በላ ጦር ሠራዊት ወይንም ተወርዋሪ ጦር ቢያሰማሩ፣ አፋኝ ቡድንም ኾነ ያላቸውን ምድራዊ ኃይል ሁሉ ቢያሰልፉ ሊያስቆሙት አይችሉም።
Filed in: Amharic