>

“ከኦስሎ ወደ ሄግ?!¡” (ጌታቸው አበራ)

“ከኦስሎ ወደ ሄግ?!¡”

ጌታቸው አበራ


ነጋ ስንል – የመሸብን፣

ሳቅን ስንል – ያለቀስን፣

ቅፅበት ደስታው – ያልቆየልን፣

ለምን ይሆን? – ምን በደልን?

..የ’ምዬን ስም – በደግ ጠርቶ፣

    እግዚአብሔርን -በአፍ ሞልቶ፣

            ..ማሰለፉ፣ ማስጎንበሱ፣

    ማስጨብጨቡ፣ ማስለቀሱ..፣

    በውብ-ቃላት አፍ ማስያዙ፣

     በደስታ አስማት ማደንዘዙ፤

     ማቀፍ፣ መሳም ፣መሽቆጥቆጡ፣

     ያለምን ጫፍ የመርገጡ..፣

     ህልም-መሰል ራዕያችን

     የት ደረሰ? ያ! ጉዟችን?!

..ነፍሰ-ጡር ሴት ስትታረድ -ህጻናቱ ሲቃጠሉ፣

የእግዜር ፍጡር ንጹህ ዜጎች – ተዘቅዝቀው ሲሰቀሉ፣

ለፍቶ-አዳሪ ምስኪን ድሆች – ከቀዬያቸው ሲታፈኑ፣

በኃይማኖት፣ በዘር ሰበብ – ፊጥኝ ታስረው ሲረሸኑ፣

አስከሬኖች እንደ አሸዋ – በግሬደር ሲታፈሱ፣

ለግበዐተ-መሬት ክብር – ለቀብር ወግ ሥን ሳይደርሱ..፣

ለምድር-ሰማይ የከበደ – የጭካኔ ጫፍ ድርጊቱ፣

ሲከናወን በቀን-ጸሐይ – ባለንባት በምድሪቱ፤

    እየሱስን ተከታዩ – መሐመድን ተከታዩ፣

    ባለ-መሃላው   – አማላዩ፤

      የማጽናኛ  – የነፍስ-ይማር፣

      አንዲትስ ቃል?  – ሌላው ቢቀር?!

   መስሎንኮ የነበረ – የሕዝብ አካል ያገር ተስፉ፣

   ያ! ከፍታ ትህትና.. ወዴት ተኖ ባየር ጠፋ?!

   ከወዴትስ የተገኘ? እንዲህ ያለ ልዩ መንፈስ፣

   ተረት-ዓለም፣ ለበ-ወለድ  …

               ባንድ አካል ውስጥ ሁለት ነፍስ?! 

ሃሴታችን ውሉን ሳይዝ – አጣጥመን ሳንጨርሰው፣

ታጥቦ-ጭቃ፣ ከርሞ ጥጃ፣ – ሆነን ላለም የታየነው፣

ከደግነት – ወደ ክፋት 

ከሽልማት ወደ ቅጣት፣

እሚያጣድፍ ከንቱ ልክፍት.. 

ምንስ ይሆን የኛ ድግምት?!

ከምኔውስ ቀናንና – ታጨን ለእኩይ ከንቱ “ማዕረግ”፣

ከመቼውስ ተጓዝንና -ኦስሎን ለቀን ደረስን ዘ-ሄግ?!

 

 ጌታቸው አበራ

    ሚያዝያ 2013 ዓ/ም

       (አፕሪል 2021)

*ኦስሎ፦ የኖርዌይ ዋና ከተማ ስትሆን፣ የሰላም የኖቤል ሽልማትን በየዓመቱ የምታስተናግድ ከተማ ናት።

 ዘ-ሄግየኔዘርላንድስ (ሆላንድ) ዋና ከተማ፤ የአለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚገኝባት። 

 

Filed in: Amharic