“መርከቧ ከተገለበጠች የሚተርፍ ሰው የለም…!!!
ጸሐፊ እና የፍልስፍና መምሕር ዮናስ ዘውዴ
*…. መርከቧን አንነቅንቃት፣ የሚነቀንቅ በቂ ማዕበል አግኝቷት እያላጋት ነው፤ ተጨማሪ ማዕበል አንሁን…!!!”
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ሚዛን፣ የጥበብ ምንጭ፣ የስልጣኔ መጀመሪያ ይሏታል፡፡ ወደቀች ሲሏት የምትነሳ፣ ሁልጊዜም አሸናፊ የሆነች አሸናፊዎችን የወለደች ሀገር ናት – ኢትዮጵያ፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በረጅም ዘመን ታሪካቸው አያሌ ችግሮች ገጥመዋቸው ሁሉንም በጥበብ አልፈው ሌላ ዘመን ላይ ደርሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች ውስጣዊ ብቻ አይደሉም፤ የውጭም ናቸው እንጂ፤ ኢትዮጵያን ለመዋጥ የሚቋምጡና በኢትዮጵያ ረዘም ባለ ታሪክ የሚበሳጩ ጠላቶቿ በየዘመናቱ በውስጧ ችግር በታዬ ቁጥር በጎን ያሰፈስፋሉ፡፡ ዳሩ የውጭውም የውስጡም ጠላት ያስበዋል እንጂ ሳይሳካለት ተያይዞ ያልፋል፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚችል የለምና፡፡
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ ዮናስ ዘውዴ እንዳሉት ሀገሪቱ በፅኑ ታማለች፤ እየሄደችበት ካለችበት ጎዳና ለማውጣት የሁሉንም ርብርብ ይፈልጋል፡፡
በኢትዮጵያ ንጹሃን ዜጎች እንደ እንስሳ እየተገደሉ እና እየተሳደዱ መሆናቸውን የገለጹት መምሕሩ ይህን ያመጣው ባለፉት ዓመታት የተዘራው መጥፎ ዘር ያፈራው መጥፎ ፍሬ ነው ብለዋል፡፡ “አንደኛው ብሔር ወይም አንደኛው ሕዝብ ሌላኛውን ሕዝብ ጨቁኗል” የሚል ነገር በታሪክ እንደማይገኝም ምሁሩ አንስተዋል፡፡ የጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት ግን ተግባራዊ ሲደረግ ኖሯል ነው ያሉት፡፡ በተለይም የ1960ዎቹ መጨረሻ ያለው አስተሳሰብ በዚህ ዘመን መብቀሉንና የችግሮች መነሻ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ ትህነግ ወደ ጫካ ስትገባ “አማራ ጠላቴ ነው፤ አማራን ማጥፋት አለብኝ” የሚል ዓላማ እንደነበራት ያነሱት የፍልስፍና ምሁሩ የሥልጣን መንበሩን ለመቆናጠጥ አማራና ኦሮሞን ማጋጨት እንደ ስልት ሲጠቀሙበት እንደነበረም አስረድተዋል፡፡ መምህር ዮናስ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በነበረው የሕዝብ ተቃውሞ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል፡፡ የለውጥ ኃይሉ መነሻው የነበረውን አስከፊ ሥርዓት መለወጥ ቢሆንም በሀገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ መፈናቀልና ሞት ማጋጠሙን ጠቅሰዋል፡፡
ለ30 ዓመታት የተዘረጋውን ሥርዓት በአንድ ጊዜ ለመበጣጠስ አስቸጋሪ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ “እኛ ካልመራን ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት፤ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ደግሞ አማራ መፍረስ አለበት” የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች ችግሩን እንደሚፈጥሩትም አንስተዋል፡፡ “ኢትዮጵያ በጽኑ ሕመም ላይ ናት” ያሉት ምሁሩ ሕመሟን የተመለከቱ የውጭ ኃይሎችም አጋጣሚውን ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የውጭ እና የውስጥ ጠላቶችን ሽኩቻ ለተመለከተ ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ዘመን ላይ እንደምትገኝ መረዳት ይቻላል ነው ያሉት፡፡ በንጹሃን ላይ የሚደርሰውን ሞት በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ “ወንድሜ ነው የሞተው” ብሎ መነሳትና መከላከል አለበት ብለዋል፡፡ መርጦ ማልቀስ አሳዛኝ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ከስሜታዊነት በመውጣት “ሀገርና ሕዝብ ከገባበት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በምን መንገድ ነው” ከሚለው መፍትሔ ላይ ማተኮር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የአማራ ክልልን ለማተራመስ ብዙ አካላት ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት የፍልስፍና ምሁሩ “መሪህን ብትሰድብ ትርጉም የለሽ ነው፤ ሰድቦ ለሰዳቢ ከመስጠት ውጭ፤ ብታደክመውም ራስህን ነው የምታዳክመው፤ ሱቅ ብትዘጋ በኢኮኖሚ ነው የምትዳከመው፤ በኢኮኖሚ እንድትዳከም የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ መንቃት ያስፈልጋል” ነው ያሉት፡፡ ጠላት የደገሰውን ድግስ ማወቅና በተቀደደው ቦይ ላለመፍሰስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ ላለመሞትና ላለመፈናቀል የትኛውን መንገድ መምረጥ እና በትኩረት መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡
መርጦ መግደል ሀገርን ይጎዳል፤ በከፊል ወድቆ በከፊል መነሳት የለም፤ የሚያስፈልገው አብሮ መነሳት እንደሆነም መክረዋል፡፡ የተዘራውን መጥፎ ዘር ማጥፋት ይሻላል እንጂ አሁንም ተጨማሪ የጥላቻ ዘር መዝራት አያስፈልግምም ብለዋል፡፡ እንደ ሀገር ፈሪሀ እግዚአብሔር መኖር፣ ለሕግ ተገዥ መሆንና መልካም አስተማሪዎችን መስማት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ መምህሩ ወጣቶች በሚችሉት ሁሉ አስተዋፅዖ በማድረግ የሚፈሰውን የደም ጎርፍ ማስቆም እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ “እንደ ወንድማማች ተከባብረን ካልኖርን እንደሞኞች ተያይዘን እንተላለቃለን” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ግድያ ሰይጣን እንኳን ሊያደርገው የማይችለው ነው ሲሉ ምሁሩ ገልጸዋል፤ ከሰውነት ወደ አውሬነት መውረድ እንደማይገባም መክረዋል፡፡ “ባልና ሚስት በዘር ምክንያት በደም መፈላለግና ከትዳር መለያዬትን ያመጣው ምንድን ነው?” የሚለውን አካሄድ መጠየቅና መረዳት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን እያወደመ “ግብጽ በርቺ፣ ሱዳንም በርቺ” የሚል ኢትዮጵያዊ መፈጠሩ አሳዛኝ መሆኑን ምሁሩ ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጠላቶች የሚችሉትን ሁሉ ተፅዕኖ ለማሳደርና ኢትዮጵያን አደጋ ውስጥ ለመጣል እየሠሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ “በውስጣችን አንድ ከሆን የውጭ ጠላት አይነካንም፤ ድባቅ እንደምንመታው፣ ታሪካችን ያስረዳል፣ እነርሱም ያውቁታል፤ ለጠላት ሸበረክ ብለን አናውቅምም” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከአንዣበበባት ችግር ለመውጣት ነበራዊ ሁኔታውን በትክክል መረዳት፣ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ተፅዕኖ ማወቅ፣ “ማነው ያሰፈሰፈባት?” የሚለው መለዬት፤ ታጋሽ መሆን፣ “ኢትዮጵያን እወዳለሁ” የሚለው ሁሉ የመፍትሔው አካል መሆን ይገባልም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያዊያን እጣ ፈንታ አንድ ላይ የተሳሰረ እንደሆነ በመግለጽ፡፡
“መርከቧ ከተገለበጠች የሚተርፍ ሰው የለም፤ መርከቧን አንነቅንቃት፣ የሚነቀንቅ በቂ ማዕበል አግኝቷት እያላጋት ነው፤ ተጨማሪ ማዕበል አንሁን፤ ያለነው መርከቧ ላይ ነው፡፡ መርከቧ እንድትናወጥ ተጨማሪ ሁከት፣ ጭንቀት አንፍጠር፤ መርከቧ ከተገለበጠች ማናችንም አንተርፍም፤ ወደ መርከቧ ውኃ መግባት ከጀመረ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሁላችንም ያሰጥመናል” ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የከፋ ችግር ገጥሟት አባቶች በትዕግስት ማለፋቸውን እና አሁንም በትዕግስት ማለፍ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ ትዕግስት ሲባል ግን “የንጹሃን ደም ይቀጥል፤ በአንደኛው ዋጋ ሌላኛው ይበልፅግ ማለት” ሳይሆን ሁሉም ሞት እንዳይኖር የሚችለውን ማድረግ እንዳለበት መክረዋል፡፡
“ዓለምን የጎዷት የማያውቁ ሰዎች ሳይሆን እያወቁ ዝም ያሉ ናቸው” ያሉት ምሁሩ እያወቁ ዝም ማለት ተገቢ አለመሆኑን እና መፍትሔው በእጃችን መሆኑን አንስተዋል፡፡ ለዚህም ሁሉም አካል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡