>

እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችና  መፈናቅሎች ይቁሙ ብሎ  መጠየቅ የዜጎች መብት እንጂ ወንጀል አይደለም...!!!"  መስጠፌ ሙሐመድ - የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት

እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችና  መፈናቅሎች ይቁሙ ብሎ  መጠየቅ የዜጎች መብት እንጂ ወንጀል አይደለም…!!!”
 መስጠፌ ሙሐመድ – የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት

(VOA ሚያዝያ 19/2013 ዓ.ም) በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ዘርና ብሔርን መሰረት ተደርጎ በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች ፣ መፈናቅሎች እና የንብረት ውድመቶችን በሰለጠነ መንገድ ማውገዝ መብት እንጂ ወንጀል አይደለም
በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የአማራ ህዝብ በማንነቱ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርስበት ግድያ እና መፈናቀል ይቁም በሚል በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ወጡ የተባሉ መፈክሮች ከንጹሀን ዜጎች ህይወት እና መፈናቀል በታች ናቸው።
የሰው ህይወት ከተዛባው መፈክር በላይ ነው። ክቡር ለሆነው ለሰው ልጅ ህይወት ደንታ ሳይኖረን በመፈክር ላይ የተዛባ መፈክር ወጥቷል ብሎ ክርክርና እስጣ ገባ ውስጥ መግባት ለሀገርም ሆነ ለህዝብ አይጠቀምም።
ከዚህ ይልቅ ሊያሳስበን የሚገባው ዜጎች በየትኛውም የሀገራቸው አካባቢ በነጻነት መኖር እንዲችሉ ደህንነታቸውን ማረጋገጥ እኛ የመሪዎች ቀዳሚ ተግበር መሆን አለበት።
መሪዎች መሪ እስከሆነ ድረስ ልንብጠለጠልና ልንወቀስ እንችላለን። ግን ደግሞ ከእኛ መወቀስ እና መብጠልጠል በላይ የዜጎች ህይወት ሊያሳስበን እና ሊከነክነን ይገባል።
አንድም ሰው በማንነቱ እና በዘሩ ተለይቶ በገዛ ሀገሩ ያለአግባብ መሞት የለበትም የሚለው ሐሳብ የመላ ኢትዮጵያን እንጂ የተወሰኑ ቡድኖችና ወገኞች ብቻ ወይም የመንግሥት መፈክር ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።
የንጹሐን ሞት እና መፈናቀል ይቁም ብሎ በሰለጠነ መንገድ መንግሥትን መጠየቅም መብት እንጂ ወንጀል አይደለም። ይሔ ደግሞ በእኛ ሐገር የሆነ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ዓለም ሀገራት የሚሆን እና እየሆነ ያለ ነው።
ዜጎች በሰለጠነ መንገድ በመንግሥት ላይ ያላቸውን ጥያቄ ማንሳታቸው ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መንገድ የሚጠርግ ነው።  በመሆኑም በተከታታይ በሚፈጠሩ ግጭቶች  ምክኒያት ንጽሐን በዘርና ማንነታቸው ምክኒያት መሞት የለባቸውም የሚለው መፈክር የሁሉ ዜጎች መፈክር እንጂ የአንድ አካል ብቻ ተደርጎም መወሰድ የለበትም። ለአንዱ የተፈቀደ ለሌላኛው የተከለከለም አይደለም።
Filed in: Amharic