>

ምጽአተ ዐማራ ....!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ምጽአተ ዐማራ ….!!!

አሰፋ ሀይሉ

 

[ማሳሰቢያ፡- ይህን የጥናት ጽሑፍ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንዳያነቡት በትህትና እጠይቃለሁ፡፡]
ቀደም ባለው ክፍል የታሪክ ተመራማሪውን የአያሌው ፈንቴን ሶስተኛ ክፍል ጽሑፍ «ሌንጮ ለታ» በሚል ርዕስ በኦነግ ጭፍጨፋ ላይ የቀረቡ ማስረጃዎችንና የአቶ ሌንጮ ለታን ምላሾች አካትተን አስነብበናል፡፡ አሁን ደግሞ በ2009 በሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት ተዘጋጅቶ በገበያ ላይ ከዋለው “ምጽአተ ዐማራ” ከተሰኘው ባለ 657 ገፅ መፅሐፍ የተወሰዱ የአማራውን ጭፍጨፋ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ከእነ ገፆቹ አጣቅሰን ከብዙ በጥቂቱ አቅርበናል።
(1) የጋራ ሙለታ እልቂት (ገፅ 324)
በጋራ ሙለታ (የሐረርጌ አንዱ አውራጃ) ከጥንት ጀምሮ በርካታ አማሮች ይኖራሉ። ወያኔና ኦነግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓም ሥልጣን ከያዙ በኋላ በክረምቱ ወራት ዐማራዎች ጋራ ሙለታን ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ አሥተላለፉ። በሐምሌ 18 ቀን 1983 ዓም ደግሞ ትጥቅ እንዲፈቱ ተደረገ። ትጥቅ በፈቱ በአራተኛው ቀን (ሐምሌ 22 ቀን 1983 ዓም) በዚሁ አውራጃ የነበሩ የኢሕአዴግ (ወያኔ) እና የኦነግ ሠራዊት አባላት ምክንያቱ ለሕዝብ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ጠብ ፈጥረው እርስ በርሳቸው ጦርነት ጀመሩ።
ነሐሴ 24 ቀን 1983 ዓም የኦነግ ሠራዊት በጋራ ሙለታ የሚኖሩ ዐማራዎችን ቤት በነፍስ ወከፍ በመፈተሽ 32 ዐማራዎችን እንዲታሠሩ አደረገ። ከዚያም የፍጥኝ አሥረው ከጋራ ሙለታ 18 ኪሎሜትር ያህል ርቀት ካለው “ጅሌቻ” ከተሰኘው ገደላማ ቦታ ወስደው ዐይናቸውን ሸፍነው ከፍተኛ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በጥይት ደብድበው ገደሏቸው። ከአንድ ዓመት በኋላ አጥንታቸው ተለቅሞ “ዶጉ መድሃኒዓለም” ከተባለ ቤተክርስቲያን በጅምላ እንዲቀበሩ ሆኗል። ከተገደሉት 32 ዐማራዎች መካከል የ27ቱ ማንነት ታውቋል። ሙሉ ስማቸው፣ ፆታቸው፣ ነገዳቸው እና ዕድሜያቸው በሚገባ ዝርዝሩ አለን።
(2) የወተር እልቂት (ገፅ 326-327)
በሐረርጌ ወተር በመጋቢት 1984 ዓም የተፈፀመውን እልቂት በተመለከተ ጋዜጠኞች አቶ አበበ ምትኬ ለተባሉት ነዋሪ ላቀረቡላቸው ጥያቄ ስለደረሰው ጭፍጨፋ ዕውነቱን ዘርዝረው ተናገሩ። ይህን የሰማው የኦነግ አባልና የአካባቢው አስተዳደሪ የሆነ ሰው የአቶ አበበ ምትኬን ዘጠኝ (9) የቤተሰብ አባላት አሥሮ ከእነ ነፍሳቸው በደኖ እንቁፍቱ ገደል ወርውሮ ጨረሳቸው።
በሐምሌ ወር 1984 ዓም በዚሁ በወተር 48 ዐማራዎች ታርደው ተገድለዋል። 300 አማሮችም ታሰሩ። ለዚህ ዋና ምክንያቱ “ዐማራ” መሆን ቢሆንም፣ ወያኔና ኦነግ እንደገቡ ከጃራ እስላማዊ ኦሮሞ ቡድን (IFLO – Islamic Front for the Liberation of Oromia) ጋር አብረው መሥራት በመጀመራቸው “በደርግ ዘመን ጃራዎችን ያስይዙ የነበሩት አማሮች ናቸው” የሚል ነው።
በጃራ ይመራ የነበረው የእሥላማዊ የኦሮሞ ፅንፈኛ ቡድን በደርግ ጊዜም ሆነ በወያኔና ኦነግ ዘመንም ክርስቲያኖችንና አማሮችን ሲገድል ኑሯል፣ እየገደለም ነው። ያም ሆነ ይህ ወተር ለወራት ከታሰሩ በኋላ ኦነግ ከወያኔ ጋር ሲጣላ፣ የያዛቸውን አማራዎች ወተር የተለያዩ አካባቢዎች ገደለ፣ ገሚሶቹን በደኖ “እንቁፍቱ” ገደል ውስጥ ጨመራቸው።
በወቅቱ ታስረው ከነበሩት የወተር 01 ቀበሌ ነዋሪዎች መሐከል ገደል ተወርውረው የተገደሉት ሰዎች ሥም ዝርዝር በከፊል ይኸውና፡-
«1) መንገሻ ቦጋለ፣ 2) ወርቄ አሸናፊ፣ 3) ሙሉጌታ ትርፌ፣
4) ሲሳይ ተስፋዬ፣ 5) ሽመልስ ኃይሌ፣ 6) መምህር ዘውዱ
ጨፍቅ፣ 7) አለማዬሁ ዓምደብርሀን፣ 8) የሽ ደስታ፣
9) ብርሀኑ አይፎክሩ፣ 10) እንግዳ ዘገዬ፣ 11) ዳኜ ወንድሙ፣
12) አበራ መንገሻ፣ 13) ወይዘሮ ወርቄ፣ 14) ታዬ በየነ፣
15) አባተ ወልደዬስ፣ 16) ይልማ እና 17) ተሾመ መርሻ
የተባሉት የዐማራ ተወላጆች ሲሆኑ፤ ይህንን ግድያ የመሩት
ኦነጎች ደግሞ፡- 1ኛ) ዑጉምሳ፣ 2ኛ) መገርሳ እና 3ኛ) ጫላ
የተባሉ ናቸው።»
በዚህ ወረዳ በዐማራው ሕዝብ ላይ ከተደረጉት በጭካኔነቱ ወደር ከማይገኝለት ዘግናኝ ግድያዎች መካከል አንዱ በእታፈራሁ ደጀኔ ላይ የተፈፀመው ነው። ይህች ወይዘሮ በእህል ንግድ ስለምትተዳደር ለፍታና ደክማ ያፈራችው ንብረትና ሀብት በገዳዮቿ እጅ እንደጣላት መረጃውን የሰጡ ሰዎች ያምናሉ።
እታፈራሁን በመጀመሪያ (ሀ) አሰሯት፣ (ለ) ከዚያ ልብሷን አስወልቀው አካላቷን አንድ በአንድ መቆራረጥ ጀመሩ፣ (ሐ) ጡቷን ቆርጠው እንድትበላው አሥገደዷት፣ (መ) ከመቀመጫዋ ላይ ሥጋዋን ቆርጠው ራሷ በራሷ እንድትበላው አደረጓት፣ (ሠ) ብልቷንም እንዲሁ ቆራረጡት እና (ረ) በሰው ልጅ የመጨረሻ የሚባለውን ስቃይ አሰቃይተው ቆራርጠውና ከታትፈው ገደሏት።
(3) የቀርሳ ድብደባና ተዓምር (ገፅ 329)
ከሐረር ከተማ 17 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ቀርሳ ቀበሌ 10 ዐማሮች በኦነግ ተይዘው መቃብራቸውን እየቆፈሩ እያሉ ዝናብ ሲመጣ ኦነጎቹ ለመጠለል ትንሽ ራቅ ሲሉ 2 ዐማሮች ለማምለጥ ሞከሩ። ብዙም ሳይርቁ ከያዟቸው በኋላ “ይህ የምታዩት ሰማዩም ምድሩም የእኛ ነው፣ የት ነው የምታመልጡት፣ ነፍጠኛ አማራ” በማለት ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ ፈጸሙባቸው።
ይህ ወቅት ወያኔና ኦነግ እየተጣሉበት ያለ ወቅት በመሆኑና ፈጣሪም አማሮችን ትረፉ ሲላቸው፣ ወያኔ ኦነጎችን ገሎ ለአማራው በተዘጋጀው ጉድጓድ ራሳቸውን አዳፍኗቸው ሄደ። ይህ የእግዚአብሔር ተዓምር ነው። ምሥክርነታቸውን ለመስጠት የበቁትም በዚያች ዕለት ከተደገሰላቸው ሞት ከተረፉት መካከል ሁለቱ ናቸው፡፡
(4) የአሰቦት እልቂት (ገፅ 344) 
አሰቦት ገዳም ክረምት ላይ 1983 ዓም 16 መነኮሳትና አርድእት እጃቸውን አስረው፣ ዓይናቸውን ሸፍነው፣ በጀርባቸው ጥይት እየተኮሱ ወደፊት እንዲሮጡ በማድረግ “በኩርባ ጀርቲ ገደል” እየተምዘገዘጉ እንዲወድቁ ተደረጉ፡፡ ከገደል ሲጣሉ መሬት ሳይነካው ተንጠልጥሎ የቀረ አሥከሬን ብዙ እንደነበር የዐይን ምሥክሮች ይናገራሉ።
(5) የአርባ ጉጉ እልቂት (ገፅ 345)
በአርባ ጉጉ አውራጃ በአማራው ላይ ስለተፈፀመው ወንጀል የተሰጠው የምሥክሮች ቃል እንዲህ ይላል፡-
«መስከረም 10 ቀን 1984 ዓም ኦነግ መጣ። በዚያኑ ዕለት  ዘሪሁን የሚባል በበቁሎ እየተመላለሰ የሚሠራ የአገልግሎት  ሠራተኛ መንገድ ላይ በጥይት ተገደለ። መስከረም 17 ቀን
ደግሞ በጀጁ ወረዳ አቡሌ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር የአቶ እልፍነህ ጥግነህ 17 የቀንድ ከብቶች ተወሰዱ። በዚሁ ዕለት  መርቲ ጀጁ ወረዳም ላይ አቶ እሸቱ የሚባል ከእነ ልጁ  ተገደለ። የአማሮችን ሀብትና ንብረት መቀማት ቀጥሎና ችግሩ
ተባብሶ መስከረም 29 ቀን 1984 ዓም የአቶ አበበ አክሊሉ  ሚስትና ልጅ በጥይት ተመተው ልጃቸው ሲሞት  ሚስታቸው ተረፉ። ሳምንት ሳይሞላው ጥቅምት 4 ቀን  1984 ዓም ወንጀሎ ቀርሳ ቀበሌ በአንድ ጊዜ ዘጠኝ (9)  ሰዎች በጥይት ተደብድበው ሁሉም ተገደሉ።»
ኦነግ በአንድ ወቅት በሰጠው መግለጫ ላይ ሙሉ በሙሉ ድርጅቱ ኃላፊነት ባይወስድም የተወሰኑ ግለሰቦች ፈፅመውት ሊሆን እንደሚችል በ Human Rights Watch ተጠቅሶ የምናገኝ ሲሆን፣ አቶ ሌንጮ ለታ ግን ሁሉንም ኦነግ አላደረገም ብሎ ሸምጥጦ በመካድ በድርጊቶቹ የኦነግን ተሳታፊነት ሲያስተባብል ቆይቷል፡፡ ባለፈው ጽሑፍ ኦቦ ሌንጮ ድርጊቶቹ በድርጅት ውሳኔ የተላለፉ ጭፍጨፋዎች አለመሆናቸውንና የዘር ማጽዳትም የኦነግ አቋም እንዳልነበረ እንዲያውም ሌሎችን መሰል ዝንባሌ ያሳደሩ ሀይሎችን እንደሚቃወም የሰጡትን ምላሽ ማቅረባችን አይዘነጋም፡፡ ግን ደግሞ ኦቦ ሌንጮ የኦነግን የቀደመ መግለጫም እንደማይዘነጋው እናምናለን፡፡ እና ሽምጥጥ አድርጎ መካድን ምን አመጣው? — ተጠያቂነትን ፍራቻ?
አንባቢ ሆይ፡- 
ከዚህ በላይ ጽሑፉን መግፋት አልቻልንም፡፡ ዝርዝሩ እጅግ ያሰቅቃል፡፡ ውስጥን ይረብሻል፡፡ የተፈጸሙት ግፎች እያንዳንዳቸው ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ ፍጡር የመሆንን የአስተሳሰብና የድርጊት ልክ ደጋግመን እንድንመረምር የሚያስገድዱ ናቸው፡፡ በንጹሃን ላይ የተደረጉት እነዚያ ግፎች ህሊናን በብርቱ ይፈትናሉ በእውነት፡፡ እና ይህን ያህል ካየን በቃን፡፡ ክፉ ሕዝብ የለም፡፡ ክፉ አድርጊ ሰዎች ግን አሉ፡፡ ፈጣሪ የሕዝባችንን ልቦና ከክፉ አድራጊዎች የጥፋት መንገድ እንዲጠብቅልን፣ በአምላክ አምሳል ወደ ተፈጠረው ወደ መልካሙ ሰብዕናችን ይመልስልን ብለን ከመመኘት ውጭ ማድረግ የምንችለው ጥቂት ነው፡፡
ከእነዚህ ማድረግ ከምንችላቸው ጥቂት ነገሮች አንዱ ስለ ጥፋቶቹ አስቀደሞ አውቆ መገኘት ነው፡፡ እና ሌሎችን ማሳወቅ፡፡ ትውልዳችን ከዚህ ቀደም የተፈጸመውን በግልጽ አውቆትና ተምሮበት ቢሆን ኖሮ፣ አሁን ጥፋቱ ዳግመኛ አገርሽቶ እየተፈጸሙ ያሉት ከቀድሞውም የከፉ ጥፋቶች አይከተሉም ነበር፡፡ እናንብብ፡፡ የተፈጸመብንን እንወቅ፡፡ ሰለባዎቹን እናስብ፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ማንም ይሁኑ ማን በህሊናችን ድርጊቶቹን እንኮንን፡፡ እና እንደየ ዕምነታችን ወደ ፈጣሪያችን አቅንተን እንጸልይ፡፡ ለእኛ ባይሆን ለልጆቻችን፡፡
በቀደመው ትውልዳችን ላይ የደረሰው ጥፋት እነሆ በእኛ ትውልድ በብዙ እጥፍ ተባብሶ እየተደገመ እያየን ነው፡፡ እያንዳንዱን ድርጊት በማስረጃ አስደግፎ መዝግቦ ለትውልድ ማቆየት፣ በእኛ የተደረገው ጥፋት፣ ቢያንስ በልጆቻችንም ዘመን ለሶስተኛ ዙር፣ እና ለሌላም ዙር ደግሞ ደጋግሞ እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ሊያግዛቸው ይችል ይሆናል፡፡ ሁላችንም በቃን! ካልን ይህን ማድረግ ይቻለናል፡፡ አለበለዚያ ‹‹ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ አለመማራችንን ነው›› እንዲል ሾፕንአወር፣ «በጥባጭ እያለ ንጹህ ውሃ መጠጣት አይታሰብም»፡፡ እና ያንኑ የኖርነውን እየደገምነው መኖር አይቀርልንም፡፡ ፈጣሪ ከድግግሞሽ አዙሪት ጨርሶ ያውጣን፡፡
አጠቃላይ የጥናት ጽሑፉ ገና አላለቀም፡፡ ይቀጥላል፡፡ ስለ አማራው እልቂት የጀመርነው ታሪክ ግን እዚህ ላይ አበቃ፡፡ በቀጣይ ተያያዥ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ያሰባሰብነውን ጥናት እናቀርባለን፡፡ የተለያዩ የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሄረተኛ ቡድኖችና ልሂቃኑ መሪዎቻቸው በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያራመዷቸውን ልዩ ልዩም፣ አንድ ዓይነትም ነባር አቋሞች በቀጣይ ፍንትው አድርገን ለማሳየት እንሞክራለን፡፡ እስከዚያው የኢትዮጵያ አምላክ ሁላችንንም በያለንበት ቸር ያቆየን፡፡
እንደተለመደው ለጥናቱ አቅራቢዎች ልባዊ ምስጋናችን ይድረስ እንላለን፡፡
ኢትዮጵያን ለዘለዓለም ትኑር፡፡
Filed in: Amharic