>

« የህግ ባለሙያው የፍቅር ደብዳቤ...!!!" (ደሳለኝ የኔአካል - ፍቅርኤል

« የህግ ባለሙያው የፍቅር ደብዳቤ…!!!”

(ደሳለኝ የኔአካል – ፍቅርኤል)

ይድረስ የልቤ ሉአላዊ ስልጣን ባለቤት ለሆንሽው ለምወድሽና ለማፈቅርሽ!
ባንቺ ይሁንታ ብቻ የምኖረው የህግ ባለሙያው አፍቃሪሽ ነኝ፡፡ ደጋግሜ ልገልፅልሽ እንደሞከርኩት ልቤን በsingular title ከወረስሽው ይሄው የፊንፊኔው እሬቻ ሲመጣ አመት ሊሞላኝ ነው፡፡ መጀመሪያ ልተዋወቅሽ ስሞክር ግልምጫ በምትይው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ (preliminary objection) የትውውቅ ሙከራየን ውድቅ ልታደርጊብኝ ከሞከርሽበት ቀን ጀምሮ ፍቅርሽ በልቤ ንውፅውፅታ ፈጥሮብኛል፡፡
እንደ civil procedure code ሸንቀጥ ያለው ቁመናሽ፣ እንደ employment proclamation አንቀፆች በጥንቃቄ የተሞላው ሰበር-ሰካ አረማመድሽ፣ እንደ civil code የነጡ በረዶ ጥርሶችሽ፣ ቀዩን ህገ-መንግሥት የመሠለው ሮማን ከንፈርሽ፣ የዳኞችን ጥቁር ጋዎን የመሠለው ሀር ፀጉርሽ፣ እንደ መዶሻ እጀታ የተመዘዘው መቃ አንገትሽ ተባብረው እንደ አልሸባብ ሰላሜን አሣጡኝ፡፡ የመበርበርያ ትዕዛዝ (search warrant) ሳይኖርሽ የልቤን በር ከፍተሽ ገባሽ (ያውም 12:00 ሰዓት ካለፈ በሗላ)፡፡
ባንቺ ምክንያት እንደ land proclamation ክፍተቴ በዝቶ በቀላሉ ሆድ ይብሰኛል፡፡ በየቀኑ እየከሳሁና እየኮሰመንኩ የcriminal procedure code መስየልሻለሁ፡፡ ለፍቅርሽ ስል የት ልሂድ? የትም ብሄድ ፍቅርሽ extradite አድርጎ እንደሚመልሰኝ አልጠራጠርም፡፡
ውዴ! ባለፈው ቅዳሜ ባደረግነው oral litigation ላንቺ ያለኝን ልባዊ ፍቅር ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ (beyond reasonable doubt) ላስረዳሽ ሞክሬአለሁ፡፡ አንቺ ግን እንደ አስጠቂ ምስክር ያወቅሽውን ሁሉ ካድሽኝ፡፡ በዚህም በጣም ስለተበሳጨሁ በቸልተኝነት የሚፈፀም የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ልፈፅምብሽ ነበር፡፡ ያ ነገር በቸልተኝነት እንደማይፈፀም ትዝ ሲለኝ ተውኩት፡፡
The right to be heard የሚለው ህገ-መንግሥታዊ መርህ ባንቺ ዘንድ ቦታ እንደሌለው አስተውያለሁ፡፡ እንደ 1931ዱ ህገ-መንግስት ራስሽን የመካብ አባዜ ተጠናውቶሻል፡፡ እንደ 1955ቱ ህገመንግሥት ራሴን አሻሻልኩ ብለሽ ትመጻደቂብኛልሽ እንጂ ቅጭም ያለ አቋምሽ አልተለወጠም፡፡ በmutual consent ልብ ለልብ እንድንግባባ ብለምንሽ፡ አንቺ ግን እንደ ኢፌዲሪ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 39ን እየጠቀስሽ ከእኔ ተገንጥለሽ ለመሄድ ያቁነጠንጥሻል፡፡
ፍቅርዬ! የሆድ የሆዴን ሳወራሽ appeal to pity fallacy ነው እያልሽ ታሸማቅቂኛለሽ፡፡ ነገር ግን ሴቶችን ስሜታቸውን በሚቀሰቅሰው appeal to pity እና appeal to people (ad hominum fallacy) ካልሆነ በስተቀር በinductive እና deductive reasoning አንቺን ማሳመን የማይሞከር እንደሆነ አልተሰወረብኝም፡፡
ውዴ! ምነው እንደ ፍትሐ-ብሄር ሕጉ አቋምሽን ማሻሻል ተሳነሽ? ከሕገ-መንግስቱ የማሻሻያ አንቀፆች (አንቀፅ 104 እና 105) የበለጠ ግትር ሆንሽብኝ እኮ ፍቅሬ? አንዳንዴ ሕገ-መንግስቱን መቀበልሽ ራሱ ያጠራጥረኛል፡፡ ህገመንግሥቱን በፍቅሬ ላይ ለመናድ እየተንቀሳቀስሽ ነው ልበል? ምነው እንደ ሰበር ችሎት (cassation bench) ገደብሽን አለፍሽ?? ሴቶች እኔንና ፖለቲካን ለምን እንደምትጠሉን አይገባኝም፡፡ ተስፋ የጣልኩብሽ አንቺ እንኳን ለፍቅር አቤቱታዬ የሰጠሽኝ መልስ ሁከት ይወገድልኝ ብቻ ሆነ፡፡
የኔ ቆንጆ! ጥያቄየ እንደ ስልጤ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ውስብስብ አይመስለኝም፡፡ እንደ ሲዳማ ህዘብ የክክልነት ጥያቄም ደም እንደማያፋስሰን ጠብቄ ነበር፡፡ ታዲያ ምነው እንደ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም አንዴ እምቢ አንዴ እሺ እያልሽ አስቸገርሽኝ? በነገራችን ላይ ውዴ… ሴቶች ግን እንደ tax proclamation ወሬያችሁ ሁሉ ስለገንዘብ የሆነው ለምንድነው? ሁልጊዜ ገቢ መሰብሰብ ብቻ? አንዳንዴም ከእነ insurance እና ጡረታ አዋጆችም ስለመስጠት ትንሽ ተማሩ እንጅ፡፡
ኤጭ! አንዳንዶቻችሁማ እንደ ወንጀል ሕጉ አሸማቃቂ፣ እንደ tax authority ሆዳሞች፣ እንደ civil code ወሬኞችና፣ እንደ ፍርድ ቤት ዳኞች ቀጠሮ አራዛሚዎች፣ እንደ ፀረ-ሽብር ሕጉ ቁጡና ግልፍተኞች ናችሁ፡፡ በዚያ ላይ እንደ ሊዝ አዋጁ የከፈለ ሁሉ የሚከራያቸው ብዙ በእንስት ጾታ የተገለጹ ወገኖች እንዳሉም በሰሚ ሰሚ እማኞች ይደርሰኛል፡፡
ሆድየ! ፀባያቸው እንደ commercial code በሚደብር በስንቱ ሴት ዓመል እንደተለበለብኩ ተረጂኝ፡፡ የፍቅር ስጦታሽን በፍቅርሽ ተቃጥዬ ከሞትኩ በኋላ የሚደርሰኝ mortis causa ሳይሆን፣ በህይወት እያለን የማጣጥመው inter vivos አድርጊልኝ ብዬ በትህትና ሳመለክት በrevocation ተስፋዬን እንደማታጨልሚብኝ በማመን ነው፡፡ በእርግጥ አንቺ በፍቅር ላይ እንደ immovable property ሽያጭ ጥብቅና የተለየ መርህ እንደምትከተይ አውቃለሁ፡፡
የሆነ ሆኖ ህይዎቴን እንደ United Nations Charter አንቀፆች በምትፈልጊው መንገድ እያጣመምሽ እየመራሻት ነው፡፡ ከአፍሪካ Human Rights Charter ጋር ያላችሁን ግንኙነት ባላውቅም አንድ ነገር ግን ያመሣስላቹሃል፡፡ ሁለታችሁም አሳይቶ መንሳት (claw back) ታበዛላችሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ ጥሩ ተስፋ ትሰጡና ቀጥላችሁ ደግሞ ሆኖም ግን፡ ቢሆንም እንኳ፡ ነገር ግን፡ ምናምን እያላችሁ የሰጣችሁትን ተስፋ መልሳችሁ አፈር ታስግጡታላችሁ፡፡
ውዴ… ፍቅሬን renounce ካደረግሽው ሌላ ወራሽ ስለሌለኝ በescheat መርህ መሠረት ፍቅሬ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል፡፡ ማለትም ላንቺ የነበረኝን ፍቅር ወደ ሀገር ፍቅር እቀይረዋለሁ፡፡ ይሄ ከመሆኑ በፊት ግን ፍቅራችን እንደ evidence ህጋችን በ draft እንዳይቀር ወይም እንደ ደርግ ህገ-መንግስት እድሜው እንዳያጥር የበኩልሽን አድርጊ፡፡
እንደ ኢህአዴግ ህገ-መንግሥት የመገንጠል መብት ወይም ሞት እያልሽ በፍቅር ይዞታዬ ላይ ሁከት አታስነሺብኝ፡፡ እኔ እንደሆንኩ እንደ gap-filling provision ሳይሆን እንደ mandatory rule አክብሬ እይዝሻለሁ፡፡ ከሃሳብሽ intentionallyም ይሁን negligently አላፈነግጥም፡፡ ቃሌን እስከ ሞት አላጥፍብሽም፡፡ pacta sunt servanda! ሰው በቃሉ ይታሰራልና!
ውዴ! ልዩነታችን እንደ common law እና civil law legal systems የሰፋ ቢሆንም በ convergence እንደሚጠብ ተስፋ አለኝ፡፡ እስከዚያው የሲቪል ኮዱን ዝና፡ የክሪሚናል ኮዱን ግርማ ሞገስ፡ የህገመንግስቱን የበላይነት፡ የፋሚሊ ኮዱን ቁንጅና እመኝልሻለሁ፡፡ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በቀር በሴት ጾታ የተገለጸው ማንነትሽ ለሹመት ያሳጭሽ፡፡ እንደ መዓዛ አሸናፊ ዘርሽ ይባረክ፡፡ የፈራጆች ቁንጮ ሁኚልኝ የኔ ሆድ!
Giftቲዬ! ሁልጊዜም ራስሽን ከ uninsurable risk ጠብቂ፡፡ ከሽብር አዋጁ ትንኮሳ ራቂ፡፡ የጥላቻ አዋጁ ከአንቺ ይራቅ፡፡ የተሻሻለው የንግድ ህግ ከbankruptcy ይሰውርሽ፡፡ ፍርድቤቶችሽን jurisdiction ይንሳልሽ፡፡ ፅኑ እስራትን ያርቅልሽ፡፡ ያልታሰበ force majeure ቅጣት ቢመጣብሽ እንደነ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ አመክሮና pardon ካንቺ ጋር አብረው ይሁኑ፡፡
ፍቅርዬ፡ ምቀኛሽን ያነሁልልልሽ፡፡ እንደ ብልጽግና ፓርቲ ካመት ዓመት በተስፋ ሰነድ (promissory note) የምትሸጋገሪ ሁኚ፡፡ እንደ ዳንኤል ክብረት ሹመት ጣልቃ-ገብ ተቃዋሚ በፓርላማ ቢነሳብሽ፡ ሆድዬ አትደንግጪ፡፡ የፍቅር ይገባኛል አቤቱታዬን እስከ ሰበር ችሎት ወስጄ እከላከልልሻለሁ፡፡ በተረፈ በአካል እስክንገናኝ ለድርድር የማይቀርበው ከሁሉ የበላይ የሆነ አንድዬ ህገ-መንግሥቱ ጥላ ከለላ ይሁንሽ፡፡
ከአባሪ ሠላምታ ጋር፡
በቃሌ የታሰርኩት፡
ህጋዊ አፍቃሪሽ  
  
(የአፍቃሪው የማይነበብ ፊርማ አለበት) »
Filed in: Amharic