የፕሬስ ትዝታዬ ብቁንጽል!!
ዳንኤል ገዛህኝ
ያለ ማንም ተጽእኖ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ የሀሳብ ነጻነትን የሚደነግገው አርቲክል 19 የተወለደው አሁን ሰባዎቹን የእድሜውን ሽምግልና እያጋመሰ ካለው የአለም አቀፉ አጠቃላይ የሰው ልጆች መብት ድንጋጌ universal declaretion of Human Rights 1948 ዶክሜንት ውስጥ ነው። ወያኔ ኢህአዴግ የቀድሞውን መንግስት ከገረሰሰ እና ስልጣን ከተረከበ በሁዋላ አጨራረሱ ባያምርም በተግባር ላይ ያዋለው የፕሬስ ነጻነት አዋጅ 34/85 ለእኔም ታላላቆቼን ተከትዬ ወደ ፕሬስ ስራዎች እንድገባ ትልቅ እመርታ ሆኖልኝ ነበር።
በጊዜው በሀገራችን የቅድመ ህትመት ስራን ለመጨረስ በርካታዎቹ ጋዜጠኛዎች እና አሳታሚዎች የዴስክቶፕ ኮምፒዩተር ግልጋሎት ለማኘት የነበረው ፈተና ቀላል አልነበረም። ከቅድመ ህትመት በሁዋላም በሁዋላቀር የማተሚያ ማሽኖች ተደጋጋሚ ብልሽት የተነሳም ሆነ በህትመት ጣጣ ለቀጣዩ ቀን የጋዜጣ ህትመት እውን መሆን በማተሚያ ቤቶች የጋዜጣ እና ተረፈ ህትመት ምርቶች ላይ በማተሚያ ቤቶች በርካታ ሌሊቶችን ማሳለፍ የተለመደ እና በቀድሞው ነጻው ፕሬስ ውስጥ የነበራችሁ ሁሉ የምትጋሩት ትዝታ ነው።
ዛሬ ጋዜጠኝነት መሳደዱ እና ወከባው በ አለም ዙርያ ባያባራም እንኳን በብዙ ደረጃዎች ግን አድጓል። ማንም ሰው ግን ለህሊናው ታማኝ የሆነ በእጁ ይዞት በሚንቀሳቀሰው የእጅ ስልክ እና ላፕቶፑ የCitzen Journalism መርህን ተከትሎ ጋዜጠኝነትን ይተገብራል። የመናገር ነጻነት ለዘላለም ይኑር።
ከዛሬ 21 አመት ግድም አንድ የጋዜጣ ዘገባ ትልቁ ከርቸሌ ወህኒ ቤት እንድወረወር ሲያደርገኝ በዳኛ ልዑል ገ/ማርያም 5ኛ ችሎት ውሳኔ ለእስር ተዳርጌ ነበር። በውቀቱ በእድሜዬ ገና በሀያዎቹ ደጃፍ ነበርኩኝ። በዝያ በበርካታ አስር ሺህዎች ታሳሪዎች የነበረው የእስር ቤት ውስጥ አስቸጋሪ እና የተለያዩ ስቃይዎች በግዜው መንፈሴን አልሰበረውም። ምክንያቱም ከጉብዝናዬ እና ጥንካሬዬ ጋር ነበርኩኝ እና። ከዚያ እስር በሁዋላ በአዲስ አባባ ፓሊስ፣ ወንጀል ምርመራ፣ ወረዳ 22፣ ወረዳ 14፣ ኢትዮጵያ ሞያሌ፣ ዲላ እስር ቤት፣ አሰላ እና ናዝሬት ምስራቅ ሸዋ እስር ቤቶችን ከተለያዩ ስቃዮች ጋር ታስሬባቸዋለሁ።
በስተመጨረሻም በሀገሬ ተስፋ ስቆርጥ ኢትዮጵያን ለቅቄ በ1997 ምርጫ ማግስት ከአታካች የአንድ ወር የስደት ጉዞ በሁዋላ የመን በጥገኝነት ለአራት አመት ቆይቻለህ። በየመን ቆይታዬም በሀገሪቱ በስደተኛነት ስቆይ የምታዘበውን የመብት ጥሰት ለመታገል በበራሪ ወረቀት freedom journal እንዲሁም በአማርኛ ቋንቋ ጉራማይሌ የተሰኘች ጋዜጣ ከጓደዬ ጋር ማዘጋጀት ጀምረን ነበር ።
ከአራት አመት የየመን አስቸጋሪ የስደት ህይወት በሁዋላ መኖርያዬ ወደሆነችው ዩኤስ አሜርካ ከመምጣቴ በፊት በየመን የሚታተሙት የመን ታይምስ፣ የመን ኦብዘርቨር፣ የመን ፖስት ሀሳቤን ለመግለጽ በራቸውን ወለል አድርገው የከፈቱልኝ ነጻ ሚድያዎች ነበሩ። በዚሁ በሀገሪቱ ይደርሱ ለነበሩ የስደተኝነት የመብት ረገጣ ሞያዊ ድጋፋቸውን ከስነ-ምግባር ጋር ላላጎደሉብን ጋዜጠኛዎች Nadia Al Saqaf ዛሬ በስደት ለሚገኙት Amal Al Ariqi Khalid Al Hilali ምስጋናዬ የላቀ ነው። በአሜሪካን አትላንታ ጆርጂያ ወርሀዊ የአማርኛ ጋዜጣ ህትመት ጀምሬ የነበረ ቢሆንም የህትመቱ ይዘት ለነጋዴዎች አመች ባለመሆኑ በማስታወቂያ መደገፍ ባለመቻልዋ ህትመትዋ ተቋርጧል። የመናገር ነጻነት ትዝ ታዬ አያሌ ነው ይኸውም በመጀመርያው መጽሀፌ ሲዋን እና በእንግሊዝኛው ቅጅ The journey to Death ጥቂት ነገር አንስቻለሁ።
አሁን ደግሞ ህትመት ብርሀን መች እንደሚያይ ባላውቅም አንድ ሰፊ ክፍል የፕሬስ ትውስታዬን የሚያትት መጽሀፌን አል-ቃይዳን ስናቋርጥ መጽሀፌ ውስጥ ብዙ የምለው ይኖረኛል። የዘንድሮውን የአለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ሳስብ በተለያዩ አለም ሀገራት በእስር የሚገኙ የመናገር ነጻነት አርበኞችን በህሊና በማሰብ ነው። ትላንት እንዲያ ነበር ዛሬ ደግሞ ስር በሰደደ የኩላሊት ህመም CKD chronic kidney dis ease የኩላሊት ስራ ማቆም ምክንያት የኩላሊት እጥበት Dialysis አልጋ ላይ ሆኜ ነው ያለሁት። በሀገራችን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የግፉአንን ድምጽ ለማሰማት ብርቱ ጥረት ለምታደርጉ ሁሉ ያለኝን አክብሮት እገልጻለሁ።
መልካም የመናገር ነጻነት ቀን።