>

ኢትዮጵያ ዋጋዋ ስንት ነው? (አሰፋ ታረቀኝ)

ኢትዮጵያ ዋጋዋ ስንት ነው?

አሰፋ ታረቀኝ


መዛግብቶቹ ሁሉ እየሚነግሩን እንደ ሐገር ከተመሰረተች ጀምሮ ለመውረር የመጡባትን እየመከተች ነጻነቷን አስከብራ መኖሯን እንጅ፣ ጎረቤትን ስትተንኩስ ወይም ስትወር አልነበርም፤ እንዳለመታደል ሆነና የቅርቦቹም የሩቆቹም ሰላም ውላ እንድታድር አይፈልጉም፡፡ የየዘመኑ ትውልድ የተጠየቀውን ዋጋ እየከፈለ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ አምጥቷታል፡፡ ከ1983 ግንቦት ጀምሮ ቅጥረኛ አሻሻጮች እጅ በመውደቋ፣ አስከፊ፣ መራርና አሳዛኝ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች፡፡ ታላቁ የብዕር ሰው ሙሉጌታ ሉሌ ባንድ ወቅት፣ “ተከፋፍለን ስላገኙን ይበልጥ አራራቁን” ብሎ ነበር፡፡ እየሆነ ያለው “እንድህ አይነት ሰወች ኢትዮጵያም ውስጥ አሉ እንደ”? የሚያሰኝ ነው፡፡ ነፍሰጡር፣ ህጻናት፤ አረጋዊያን እንድ እንሰሳ እየተሳቡ ሲታረዱ ድምጻቸውን ያላሰሙ የኦሮሞ አባገዳዎች፣ ወሎ ላይ የተወሰኑ ወጣቶች ኦሮሙማ ይውደም ማለታቸውን እንደመነሻ ወስደው “አማራውን” ለማውግዝ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ በቀያቸውና በመልካቸው ላይ የንጹሐን ደም በግፍ ሲጎርፍ ዝምታን የመረጡ አባገዳዎች፣ ተደፈርን ብለው ለተቃውሞ ቸኩለው ስታያቸው፣ ነገሩ የጤና ነው? ብለህ ለመጠየቅ ትገደዳለህ፡፡ እንድህ አይነቱን ዘመን ነው የሐገሬ ሰው፣

‘ እንድህ ያለ ዘመን የተገላቢጦሽ

አህያ ወደቤት ውሻ ወደ ግጦሽ” ብሎ የተቀኘው፡፡

“አማራ” ጠሉ ታሪክ በእንግሊዞቹ የተጠነሰስና ዘመን ያስቆጠረ መርዝ ነው፡፡ ከሁሉ ጋር በሰላም የሚኖር፤ ሁሉን በእኩል የሚያይና የማይስገበገብ በመሆኑ፤ የሁሉንም ብሄረሰቦች አክብሮት ተጎናጽፏል፡፡ ይህ ሁሉን የማክበርና በሁሉ የመከበር ጸጋው ኢትዮጵያን በዘመናት ሁሉ ከመጡባት ወራሪዎች እየተከላከሉ በነጻነት ለመኖር አስችሏቸዋል፡፡እንግሊዞች ኮተት ይዞ መምጣት ሳያስፈልጋቸው፣ አስቀድሞ ቋጠሮውን ማላላት፣ ቀጥሎ መበጣጠስ የሚል ስልት ነድፈው ተነሱ፡፡ ኦነግን በምዕራብ፣ ህዋህትን በሰሜን አሰማርተው፣ የምዕራቡ ቅኝ ተገዛሁ እንድል፣ የሰሜኑ ተጨቆንሁ በማለት ከፍ አድርጎ እንድጮህ  አዘጋጇቸው፡፡ ትጥቁ፣ ስንቁ፣ የሎጂስቲክስ አቅርቦቱና የፕሮፖጋንዳው ሽፋን አየሩን ተቆጣጠርው፡፡በለስ ቀናቸውና ቤተመንግሥት ገቡ፡፡ኢትዮጵያን የመበታተኑና የመሸንሸኑ እቅድ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆናችን ቀረና ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተባልን፡፡Dismembering and disintegrating Ethiopia. ኢትዮጵያን ለመበተን የፈሰሰው ገንዘብና የተቋጨው ሤራ ሌላ አገር ላይ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ፣ ያለማጋነን ሃያ የአፍሪካ ሐችሮችን ድምጥማጣቸውን ማጥፋት ይችል ለበር፡፡ የተሸመነችበት ዘሃ ጠንካራ በመሆኑ፣ እዚህም እዚያም ይምዘዙት እንጅ ሊበጥሱት ከቶ አልሆነላቸውም፡ እነሱ እየተበጣጠሱ ናቸው፡፡

ህዋህትና ኦነግ ከእብደታቸው ብርታት የተነሳ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ሊፈጽመው ቀርቶ ሊያስበው የሚቀፍ ተግባር በ “አማራ”ሕዝብ ላይ እየፈጸሙ ናቸው፤ “አማራ” ጠል ትርክታቸው፣ እስከመቃብር የሚሸኝ እንጅ የሚላቀቁት እንዳልሆነ፣ እነሆ እያየነው ነው፡፡ ጸረ “አማራው” ሤራ አገር በቀል እንዳልሆነ ምስክሩ የሰሞኑ ሁኔታ ነው፡፡ሥጋታቸው፣ ጭንቀታቸውና ዋይታቸው ስለ ትግራይ እንጅ፣ ስለሚታረደው “አማራ” ምዕራቦቹ ምንም አላሉም፡፡ እንዳውም፣ ምርጫውን አቁሙና ተደራደሩ እያሉ ነው፡፡ ባጭሩ ህዋህትና ኦነግ በሌሉበት መንግሥት መመሥረት የለባችሁም ነው፡፡ አስደናቂውና አስገራሚ ነገር፣ ይህንን የንግሊዝንና የአሜሪካንን ሴራ የ “አማራ” ተቆርቋሪ ነን ባዮች ተጋርተው “የሽግግር መንግሥት ይቋቋም” እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ማየቴ ነው፡፡ እንደነ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊወርጊስ አይነቶቹ፣ የ “አማራ”ን ወጣት ትግሉን እስከ አድስ አበባ አድርሰው ሲሉ ሌሎቹ “በጎበዝ አለቃ” ተደራጅ ይሉታል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይንም፣ አንደኛው “ፋሽስት” ሲላቸው ሌላው “አእምሮ የለውም” እስከማለት ርቆ ሄዷል፡፡ የሻለቃ ዳዊትንና የአበበ በለውን “ቃለመጠይቅ” ያስ ታውሷል፡፡ እንደት ነው የ “የአማራ” ተቆርቋሪወች፣ የእንግሊዞችና የአሜሪካኖች ዕቅድ ምርጫውን በተመለከተ አንድ ሊሆን የቻለው? ተወደደም ተጠላም ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን የሚያከበር መሪዋን ያክብራል፡፡ እውቁ ምሁር ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ያስተማሩን ይህንን ነው፡፡ “አቶ መለስ ዜናዊ ቅንጣት ክብር የሚገባቸ ሰው አይደሉም፤ እርሰወ የምለው ለሐገሬ ካለኝ ክብር የተነሳ ነው” ነበር ያሉት፡፡ 

“አማራው” ማንነቱንቱን በሰሞኑ ሰልፍ አስመስክሯል፡፡ያ ሁሉ ሕዝብ በተመመበት ከተማ ብርጭቆ አልተሰበረም፡፡ ከሱዳን፤ ከጉሙዝ ታጣቂወች፤ ከቅማንት፣ የኢትዮጵያ የመከራ ምንጭ ከሆነው ህዋህት ርዝራዥ ጋር መፋለሙ ያነሰው ይመስል፣ ከ “አማራ ተቆርቋሪወች” ትግሉን አድስ አበባ ድረስ ግፋው የሚል ጥሪ እየቀረበለት ነው፡፡ ይቺ ወጥመድ የማናት? “ ሻለቃ ዳዊት እውነታውን አፍረጠረጡት” የሚል ጯሂ ማስታወቂያ አየሁና መከታተል ጀመርኩ፡፡ ስለ አሜሪካ ፖሊሲ በኢትዮጵያና ስለ ግብጽ ተጠይቀው የሰጡት መልስ አስገራሚም አስደማሚም ነበር፡፡ “አሜሪካኖች የኢትዮጵያን አንድነት ይፈልጉታል፤ ግብጾችም ቢሆኑ የደከመች ኢትዮጵያን እንጅ የተበተነች ኢትዮጵያን አይፈልጉም”፡፡ ነበር ያሉት፡፡ እንግሊዞችና አሜሪካኖች ስንት ከፈሉ? መቸም በካፒታሊስቱ አለም ነጻ ግልጋሎት ብሎ ነገር ስለሌለ፣ ኢትዮጵያ ስንት ተተመነች? ከወጣትነት እስከ አዛውንትነት የምናውቃቸውን ጠላቶች አዛኝ አድርገው ያቀረቡልን እንድሁ በነጻ ነው? ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአስፈላጊው ጊዜ ለኢትዮጵያ  ከእግዚአብሔር የተሰጡ ሰው ናቸው፡፡ ለዚያም ነው ምድረ አይሁድ ያለ ጥፋቱ በክርስቶስ ላይ ተስቶ ስቀለው ስቀለው እንዳለው ሁሉ፣ በምድሪቱ ላይ ያለ የጎሳ ጽንፈኛ ሁሉ በእርሳቸው ላይ ተነስቶ የሚጮህ፡፡ አንዳንዱም ጽንፈኛ ዶ/ር አብይን ያዋረደ መስሎት የሚጠቅምበት ጸያፍ ቃል የ”አማራን” አስተዳደግና ሥን ምግባር አይመጥንም፣ ያሳፍራልም፡፡

Filed in: Amharic